ሰንሰለታማ ተራሮች፣ የጉም ብርድ ልብስ የተጀቦነ መልክአ ምድር፣ አማላይ ዕይታ፣ ሀገረኛ መዓዛና ጠረን፣ ድንቅ አቀማመጥ በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ፡፡ የተፈጥሮ ውበት ከተራራው በላይ ገዝፎ ይስተዋላል፡፡ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ለማድነቅ ቃል ያጥራል፡፡ ‹‹ስለስሜን ተራራዎች ብዙ ማለት እችል ነበር፤ ነገር ግን ያየሁትን የምናገርበት፣ አካባቢውን የምገልፅበት፣ ከተራሮቹ ጫፍ ቆሜ ቁልቁል ስመለከት ያለውን ፍርሃት እና የማይታመነውን ሰንሰለታማ የተራሮች ኅብር ለመግለፅ ይከብዳል፡፡ ብርቅየዎቹን ዋሊያ እና ቀይ ቀበሮ መመልከቴ ግን ዕድለኛ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርጎኛል›› ብሏል የውጭ ሀገር ጎብኝው፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኘው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከበየዳ እስከ ጠለምት፤ ከጃናሞራ እስከ ደባርቅ፤ ከአዲ አርቃይ እስከ ደባርቅ ከተማ አስተዳደር ባሉት 42 የገጠር ቀበሌዎች ይዋሰናል፡፡ ከደባርቅ ከተማ በሰሜን ምዕራብ በኩል 5 ኪሎ ሜትር እና በሰሜን ምሥራቅ በኩል 22 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚጀምረው ፓርኩ ከባሕር ወለል በላይ ከ1ሺህ 900 እስከ 4 ሺህ 543 ሜትር ከፍታ ይደርሳል፡፡ በዚያ ቅዝቃዜ ብርቁ ባልሆነ ደጋማው ክፍል ከ50 ሺህ ሕዝብ በላይ ፓርኩን አቅፎና ታቅፎ ሕይወቱን ይመራል፤ ሀብትነቱ ግን ከ50 ሺህ ሕዝብ አልፎ የዓለም ከሆነ ወደ 40 ዓመታትን እያስቆጠረ ነው፡፡

ዛሬ ላይ 412 ኪሎ ሜትር ስኩየር የሚያካልለው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከመሳረሪያ እስከ ራስ ደጀን፤ ከሊማሊሞ እስከ ስልቂ አልፎና ተሻግሮ እስከ ቅዱስ ያሬድ ያሉትን የፓርኩን ክፍል ሳያጠቃልል በ1978 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብቸኛው የተፈጥሮ ሀብት ሆኖ በዩኔስኮ ሲመዘገብ የቆዳ ስፋቱ 236 ኪሎ ሜትር ስኩየር ነበር፡፡ 
176 ኪሎ ሜትር ስኩየር የሚሆነውን አዲሱን የፓርኩን ክፍል ለማጠቃለል በሁለት ዙር የተከፈለ እና በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሰፈራ መካሄዱን ከፓርኩ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ በመጀመሪያው ዙር ጃናሞራ ወረዳ አርቋዝዬ የተሰኘች አነስተኛ ከተማ አካባቢ የሚኖሩ 160 አርሶ አደሮችን፤ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ደባርቅ ወረዳ ግጭ አካባቢ 252 አባወራዎች የፓርኩን ክልል ለቅቀው እንዲሰፍሩ ሲደረግ ዩኔስኮ ከመዘገበው እና ካጋጠመው ‹‹የስጋት አደጋ›› በ2017 (እ.አ.አ) እንዲወጣ እረድቶታል፡፡

የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ባለፈው ሚያዝያና ግንቦት 2011 ዓ.ም ባጋጠመው የእሳት አደጋ 1 ሺህ 40 ሄክታር የፓርኩ ክፍል ተጎድቶ ነበር፡፡ ወደ ቀደመ ገፅታው ለመመለስ እስከ 10 ዓመታት ሊፈጅበት እንደሚችልም የዘርፉ ባለሙያዎች ስጋታቸውን ገልጸው ነበር፤ ‹‹ምሥጋና ያልተቆጠበ ጥረት ላደረጉ፣ ድጋፋቸውን እና አሻራቸውን ላሳረፉ ሁሉ ይሁንና ዛሬ ላይ ማገገም እየተስተዋለበት ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ወራትም በተከታታይ ለአራት ዙር ለፓርኩ ተስማሚ መሆናቸው በጥናት የተረጋገጡ 38 ሺህ ሀገር በቀል ችግኞች በእሳት በተጎዳው 21 ሄክታር የፓርኩ ክፍል ላይ ተተክለዋል›› ተብሏል በፓርኩ ጽሕፈት ቤት በኩል፡፡ ‹‹ይህ ማለት ግን የዚህ ብርቅየ ፓርክ ኅልውና በዘላቂነት ተረጋግጧል›› ማለት አይደለም ያሉት የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው የፓርኩን ኅልውና በዘላቂነት ለመጠበቅ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በመሠረተ ልማት ተጠቃሚ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የስሜን ተራዎችች ብሔራዊ ፓርክ በዚህ ዓመት ተደጋጋሚ የሆኑ አደጋዎችን ለሁለት ዙር ቢያስተናግድም ከዚህ ቀደም በክብረ ወሰን ከተመዘገበው 25 ሺህ የውጭ ሀገር ጎብኝ በላቀ ሁኔታ እስከ ባለፈው ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በአንድ ዓመት ውስጥ 32 ሺህ 400 የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን በማስተናገድ ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለአገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ ለመንግሥት እና ለኅብረተሰቡ አስገኝቷል፡፡

ዋልያን፣ ቀይ ቀበሮን፣ ጭላዳ ዝንጀሮን፣ የተለያዩ አዕዋፍትን እና ሀገር በቀል ዕፅዋትን የያዘው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት ደጀን ነው፡፡ ‹‹ይህ ፓርክ ከእኛ ሀገር ቢሆን ታላቁን የቶዮታ ኩባንያ መገንባት ባለስፈለገን ነበር!›› ብለው ጃፓናዊ ጎብኝ መናገራውን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ‹‹ሀብት ላይ ተቀመጠን፣ ሀብት እያመነጨንበት፣ የአካባቢው ኅብረተሰብ የመሠረተ ልማት ጥያቄ የማይመለስበት ዘመን ሊያከትም ግድ ነው›› ብለዋል፡፡ የሕዝቡን እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ቅሬታ እያነሱ፡፡

የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኝባቸው ወረዳዎች በተለይም ጃናሞራ፣ በየዳና ጠለምት ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች የሏቸውም፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 01/2011 ዓ.ም (አብመድ)

Related stories   እንግሊዝ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እቅዷን ይፋ አደረገች፤ ዶክተር ዳንኤል የማይካድራን ጂኖሳይድ ዝም ማለቱ ክህደት ነው

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *