“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎት ለምን ተስተጓጎለ?

BBC Amharic – በመላው ሃገሪቱ ባሉት ቅርንጫፎችና በትልቅነቱ ቀዳሚ እንደሆነ የሚነገርለት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአራት ተከታታይ ቀናት ተስተጓጉሎ የነበረውን አገልግሎት አስተካክሎ መደበኛ አገልግሎቱን መስጠት እንደጀመረ የባንኩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የአብሥራ ከበደ ለቢቢሲ ገለፁ።

ከሰሞኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች የተለመደውን አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ ተገልጋዮች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ22 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችና ከ1450 በላይ ቅርንጫፎች እንዳሉት የገለፁት ኃላፊው፤ ከባለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ ሲስተሙ የመዘግየት ችግር እንዳጋጠመውና ሙሉ በሙሉ ተስተጓጉሎ እንደነበር አረጋግጠዋል።

ይሁን እንጂ ባሳለፍነው እሁድ ወደ መደበኛ አገልግሎት ተመልሶ የኤትኤም ማሽኖች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር ገልጸዋል።

ይኽው አገልግሎት እንደገና ሰኞ ጠዋት ጀምሮ በድጋሚ መስተጓጎል ገጥሞት የነበረ ቢሆንም ማክሰኞ ከሰዓት ጀምሮ መደበኛ አገልግሎታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።

“በአጠቃላይ ለአንድ ቀን ተኩል ያህል ነበር አገልግሎቱ የተቋረጠው” የሚሉት ኃላፊው አገልግሎቱ ከተስተካከለ በኋላ በየቅርንጫፎቹ የደንበኞች ቁጥር ጨምሮ ነበር ይላሉ።

ስለ ሲስተሙ መጨናነቅ የተጠየቁት አቶ የአብሥራ “እንዲህ ነው ተብሎ የሚገለፅ ነገር የለም፤ ግን ቴክኖሎጂ በባህሪው ድንገት የሚፈጠሩ ችግሮችን ያስተናግዳል” ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

የሲስተም መጨናነቅ በባንኩ ውስጥ አሊያም በውጭ በሚፈጠሩ የኢንተርኔትና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት ሊፈጠር እንደሚችል የሚያስረዱት ኃላፊው፤ አሁን ያጋጠመው ችግር ግን በራሱ በባንኩ ሲስተም መጨናነቅ ምክንያት የተፈጠረ ነው ብለዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት ባንኩ ለሚመጡት 10 ዓመታት የሚያገለግል ዘመናዊ የመረጃ ቋት ያለው ቢሆንም ያጋጠመው እክል አንዳንድ ጊዜ በቴክኖሎጂ ላይ በሚፈጠሩ ጊዜያዊ ችግሮች ነው።

በነበረው መስተጓጎል የደረሰውን ኪሳራ አስመልክተን ጥያቄ ያነሳንላቸው አቶ የአብሥራ “ባንኩ የደንበኞች አገልግሎት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ ነበር እንጂ፤ ባጋጠመው መስተጓል ያጋጠመው ኪሳራ ስሌት ውስጥ አልገባም”ብለዋል።

ኃላፊው አክለውም ወደፊት ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥም እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የደንበኞች ቁጥር በጨመረ ቁጥርም እንዲህ ዓይነት መጨናነቆች እንዳይከሰቱ ባንኩ አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሞባይል ባንክ፣ የኢንተርኔት፣ ሲቢኢ ብር፣ በካርድ አገልግሎት ክፍያ መፈፀሚያ ማቅረቡን በመግለፅ ደንበኞች ሳይንገላቱና ሳይደክሙ አገልግሎቱን መጠቀም እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

እንደ አማራጭ የቀረቡት መንገዶች ከኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በኢትዮጵያ ያለው የኢንተርኔት ተደራሽነትና ፍጥነት በርካቶች የሚማረሩበት ነው። እንዲያም ሲል በተለያዩ ምክንያቶች በተለያዩ ጊዜያት መዘጋቱ ጉዳዩን የከፋ ያደርገዋል።

በመሆኑም እነዚህ ንግድ ባንክ ያስቀመጣቸው አማራጭ አገልግሎቶች የበለጠ ጫናው ላይ አይወድቁም ወይ? ስንል ለኃላፊው ጥያቄ አንስተን ነበር።

ኃላፊውም ችግሮች መኖራቸውን አምነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለችግሮቹ እልባት ለመስጠት ሃገሪቱ ውስጥ ያለውን እንዲሁም የራሱንም መሠረተ ልማት አጣምሮ እንደሚጠቀም ገልፀዋል።

በዚህ መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ደንበኞች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

“እስካሁን ከ5 ሚሊዮን በላይ የኤትኤም ካርድ ተጠቃሚዎች እና ከ2 ሚሊዮን በላይ የሞባይል ባንክ ተጠቃሚዎች አሉ” የሚሉት ኃላፊው በኢትዮጵያ ካለው የሕዝብ ብዛት ጋር ሲነፃፀር በጣም አነስተኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ በአገሪቱ የሚፈጠሩ ክፍተቶቹን ባንኩ እየሞላ አገልግሎት መስጠታቸውን እንደሚቀጥሉ ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያጋጠመው መስተጓጎል ተፈታ ካለ በኋላ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ተጠቃሚዎችና የባንኩ ሠራተኞችን በመጠየቅ ለማረጋገጥ ባደረግነው ሙከራ የነበረው ችግር መፈታቱን የገለጹ ሲሆን በተወሰኑ ቦታዎች ላይ የሲስተም ዘገምተኛ መሆን እንዳለ ገልጸዋል።

ስለ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊው እንደነገሩን…

• ከ22 ሚሊየን በላይ ደንበኞች አሉት

• የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ 542 ቢሊየን ብር ደርሷል

• አጠቃላይ ሃብቱ ከ660 ቢሊየን ብር በላይ ነው

• ከ5 ሚሊየን በላይ የኤ ቲ ኤም ካርድ ተጠቃሚዎች አሉት

• ከ2 ሚሊየን በላይ የሞባይል ባንክ ተጠቃሚዎችን ያስተናግዳል

• 38 ሺህ ሠራተኞች አሉት

• ከ1450 በላይ ቅርንጫፎች አሉት

• የደበኞች ቁጥር በየዓመቱ በ2 እና 3ሚሊየን ብልጫ ያሳያል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   አሜሪካ ለጊዜው ሲባል የከረመ ሃሳብ ያካተተ መግለጫ አወጣች፤ ምርጫውን በተዘዋዋሪ ደግፋለች
0Shares
0