ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ብልትን መታጠን ጉዳት እንዳለው ባለሙያዎች አስጠነቀቁ

አንዲት ካናዳዊት ሴት ብልቷን ለመታጠን ባደረገችው ሙከራ ራሷን ካቃጠለች በኋላ የማህፀን ሀኪሞች ብልትን መታጠን ሊያስከትሉ ስለሚችሉ አደጋዎች እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።

የ62 ዓመቷን ካናዳዊትን ተሞክሮ ያካተተው ይህ ጥናት ታትሞ የወጣው በካናዳ በሆድና የማሕፀን ጤና ላይ በሚያተኩር ጆርናል ላይ ነበር።

ይህች በጥናቱ ላይ የተሳተፈችው ሴት የብልት መገልበጥ ሕመም ስትሰቃይ የነበረ ሲሆን ቀዶ ሕክምና ሳታደርግ በሌሎች የሕክምና ዘዴዎች ፈውስ ማግኘት እንደምትችል እምነት ነበራት።

ብልትን መታጠን፣ በሞቀ ውሃ ላይ መቀመጥ፣ በውሃው ላይ ባህላዊ መድሃኒቶችን መጠቀም እየተለመደ የመጣ ተግባር ነው። በውጫዊ የብልት አካባቢ ያሉ አካላትን ለመንከባከብ በሚል ዘመናዊ በሆኑ የውበት መጠበቂያ ቤቶችና ስፓዎች ሳይቀር ለሚፈልጉ ደንበኞች አገልግሎቱን ይሰጣል።

ይህንን ብልትን የመታጠን ልማድ በሚመለከት ኤል ኤ ታይምስ በአውሮፓዊያኑ 2010 ለመጀመሪያ ጊዜ ሪፖርት ያደረገ ሲሆን ከዚያ በኋላ ግውይኔት ፓልትሮው ጉፕ ብራንድ እንዲጠቀሙት ከመከረ በኋላ ግን የበርካቶችን ትኩረት ስቧል። ባለፈው ዓመት አሜሪካዊቷ ሞዴል ክሪሲይ ቴገን ብልቷን ስትታጠን የሚያሳይ ፎቶግራፏን አጋርታለች።

Presentational white space

የውበት መጠበቂያ ቤቶችና ስፓ ማስታወቂያዎችም ብልትን መታጠን እስያና አፍሪካ በዘመናቸው ሁሉ ሲጠቀሙበት የኖሩት መድሃኒት እያሉ ያስተዋውቃሉ፤ እንዲያውም ይህንን ልማድ አንዳንጊዜ ‘ዮኒ ስቲሚንግ ‘ እያሉ ይጠሩታል። ድርጊቱም ብልትን የሚመርዝ ነገርን የማስወገድ ተግባር እንደሆነ ይነገራል።

ባለሙያዎች ግን እነዚህ ድርጊቶች አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ይመክራሉ- በወር አበባ ወቅት የሚከሰትን ህመም ያስታግሳል፣ መካንነትን ይከላከላል የሚሉትን ጨምሮ ስለሌሎች ጠቀሜታውና ፋይዳው እስካሁን የወጡ ማረጋገጫዎች አለመኖራቸውን በመጥቀስ።

በሮያል ኮሌጅ የሆድ አካልና ማሕፀን ሕክምና ክፍል አማካሪና ቃል አቀባይ የሆኑት ዶ/ር ቫንሳ ማኬይ የሴቶች ብልት የተለየ እንክብካቤና ከመጠን ያለፈ ፅዳት ያስፈለግዋል መባሉን ‘ አፈ ታሪክ’ ነው ይሉታል። ይሁን እንጂ ሽታ በሌላቸው ሳሙናዎች ውጫዊ የሆነውን የብልት ክፍል ማፅዳት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።

“የሴቶች ብልት ጠቃሚ የሆኑ ባክቴሪያዎችን ይዟል፤ ባክቴሪያዎቹ እርሱን ለመጠበቅ የተቀመጡ ናቸው ” ሲሉ በመግለጫቸው አክለዋል።

በመሆኑም ብልትን መታጠን በውስጡ ያሉ ባክቴሪያዎች ላይ የጤና መናጋት ያስከትላል፤ የ’ፒ ኤች’ መጠንንም ሊቀንስ ይችላል፤ ከዚህም ባሻገር ማሳከክ፣ መቆጣት፣ ማቃጠል እና ኢንፌክሽን ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን በብልት አካባቢ ያለ ለስላሳ ቆዳ [vulva] ላይ ቃጠሎም ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። በርካታ ሐኪሞችም ብልትን መታጠን የሚያስከትለውን ጉዳት ለማሳየት በካናዳዊቷ ሴት ላይ የሆነውን ሁሉ በተለያየ መልኩ እያጋሩት ይገኛሉ።

የእርሷን አጋጣሚ የጻፉት ዶ/ር ማጋሊ ሮበርት በበኩላቸው ሴትዮዋ በአንድ ቻይናዊ ዶክተር ምክር ብልቷን ለመታጠን ስትሞክር ጉዳቱ እንዳጋጠማት አስረድተዋል።

ይህች ታሪኳ ለሌሎች ትምህርት እንዲሆን ለማጋራት ፈቃደኛ የሆነችው ሴት፤ ብልቷን ለመታጠን ለሁለት ተከታታይ ቀናት ለ20 ደቂቃዎች ያህል የሞቀ ውሃ ላይ ተቀምጣ ነበር ።

ያጋጠማት ጉዳትም ሁለተኛ ደረጃ ቃጠሎ ሲሆን ከጉዳቷ ስታገግም ቀዶ ሕክምና እንደሚደረግላት ተገልጿል። በካልጋሪ ከእንብርት በታች ያሉ ክፍሎች ሕክምና የሚያደርጉትና የቀዶ ሕክምና ባለሙያው ዶ/ር ሮበርት እንዳሉት እንደ መታጠን ያሉ ልማዳዊ ህክምናዎች በኢንተርኔትና በወሬ የሚዛመቱ ናቸው ብለዋል።

” የጤና ባለሙያዎች ለሴቶች አማራጭ ሕክምናዎችን እንዳሉ ማስገንዘብ አለባቸው፤ ይህም ጠቃሚ የህክምና ዘዴዎችን እንዲመርጡ ያስችላቸዋል፤ ሊያጋጥማቸው ከሚችል ጉዳትም ይጠበቃሉ” ሲሉ በፅሁፋቸው ላይ አስያየታቸውን ሰጥተዋል።

Credit – bbc amharic

Related stories   የዓለም ጤና ድርጅት ለቻይናው ክትባት ይሁንታውን ሰጠ