“Our true nationality is mankind.”H.G.

‹‹በክልሉ ያጋጠመው የፀጥታ ችግር መንስኤ የፖለቲካ አመራሩ ብልሽት ነው›› – አቶ ሞገስ ባልቻየደኢህዴን ፅህፈት ቤት ኃላፊ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ ክልል የሚነሱ የክልል እንሁን ጥያቄዎች በአገሪቱ ፖለቲካ ትኩረት የሳቡ ሆነዋል። ከዚህ አኳያ ጥያቄው እንዴትእየተስተናገደ ነው? ክልሉን እያስተዳደረ ያለው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ደኢህዴን/ ክልል እንሁን የሚለውንጥያቄ ለመመለስ እየወሰደ ያለው እርምጃ በጥናት የተደገፈ ቢሆንም በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎቹ ግን ‹‹ጥናቱ ኢሕገመንግስታዊ ነው›› ሲሉ ኮንነዋል። ደኢህዴንስ ምን ምላሽ አለው? የሚሉና ከጉዳዩ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ወቅታዊ ጉዳዮችንሀሳቦችን በማንሳት ከደኢህዴን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ጋር ያደረግነውን ያለ ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አዲስዘመን፡–የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ  ደኢህዴን/ በክልሉ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚልያስጠናው ጥናት መነሻ ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ ሞገስ፡– ጥናቱ ማዕከል የሚያደርገው በክልሉ በአዲስ መልክ ክልል ሆነን እንደራጅ ለሚሉ በርካታ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ታስቦ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በአገራችን ሕገ መንግስቱ ከፀደቀ ወዲህ የመጀመሪያው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሁለተኛ ደግሞ የክልል እንሁን ጥያቄዎች በብዛት የቀረቡ በመሆናቸው መንስኤያቸውን እና መፍትሄያቸውን ለመለየት በአግባቡ መረጃ ላይ መመስረት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው። በመሆኑም እነዚሀን አይነት ጥያቄዎች በተረጋጋ መልኩ ለማየት እና ለትክክለኛ የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በመፈለግ ነው።

ክልላችን በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ያሉበት እንደመሆኑ በሕገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎች በብሔረሰቦች ምክር ቤት ውሳኔ ካሳረፉበትና ጥያቄ ካቀረቡ እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ሊስተናገዱ ይችላሉ በሚለው መሰረት ክልሉ ካለው ብዝሀነት አንፃር እና የዞን ምክር ቤቶችም በመኖራቸው የሚነሱ ጥያቄዎችንም በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የማይቻል ነው።

በመሆኑም ጥያቄዎቹን ለመመለስ የሚደረገው ክልላዊም ሆነ አገራዊ አንድምታው እና የክልል ተልዕኮን በአግባቡ ለመወጣት አዳጋች እንዳያደርገው ሁኔታውን ሰከን ብሎ ማየት አስፈላጊ ይሆናል። በዚህ ረገድ ህዝቡን ማወያየት አስፈላጊ ይሆናል ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ የሌሎች አገራትን ልምድ በማካተት ህዝቡን ወደዚህ ጥያቄ የገፉትን ምክንያቶች ለመለየት በተሟላ እና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማየት አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ነው ጥናት ውስጥ ሊገባ የተቻለው።

አዲስ ዘመን፡– ‹‹ክልል የመሆን ጥያቄው መመለስ ያለበት በሕገ መንግስቱ ብቻ ነው፤ የክልልነት ጥያቄው በጥናት ይመለስ የሚል ሕገመንግስቱ ላይ በሌለበት ሁኔታ ደኢህዴን ያስጠናው ጥናት ኢ–ሕገመንግስታዊ ነው›› በማለት በክልላችሁ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችይናገራሉ፤ ለዚህ ምን ምላሽ አለው?

አቶ ሞገስ፡– ጥናቱ ከሕገ መንግስቱ ጋር ምንም ጠብ የለውም። ጥናቱ የህዝቡን ሕገ መንግስታዊ መብት በፍፁም አያጓድልም፤ እንዲቀርም አያደርግም። የተነሳውን ጥያቄ ለመመለስ ፤ወደ ሕገ መንግስታዊ ሂደቱ ከመገባቱ በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ የተሟላ ነገር ይዞ ህዝቡን ለማወያየት መስራት እንጂ ሕገ መንግስታዊ ሂደቱ ተሽሯል ማለት አይደለም። ሕገ መንግስቱ ላይ ተደንግጓል፤ ተፅፏል። እነዚህ ጉዳዮች በፌዴራሉም ሆነ በክልሉ ሕገ መንግስት ላይም ተጽፈው ተቀምጠዋል።

በእኛ ክልል ውስጥ የዞን ምክር ቤቶች አሉ። ልዩ ወረዳዎች አሉ፤ ብሔረሰቦች ምክር ቤቶች አሏቸው። በክልላችን 56 ብሔር ብሔረሰቦች አሉ። የብሄረሰብ ምክር ቤቶችም እንዲሁ። 11 ምክር ቤቶች ክልል እንሁን ብለው ጥያቄ አቅርበዋል። ጥያቄዎቹ የቀረቡባቸው መንገዶች ሕገ መንግስታዊ አይደሉም አላልንም። ጥያቄው ሕገ መንግስታዊ ነው፤ ለዚህ ምንም የተለየ መልስ የለንም። ነገር ግን ጥያቄው በተለየ እና እንግዳ በሆነ መልኩ ስለመጣ ከወትሮው በተለየ መንገድ የመጣበት ምክንያት ምንድን ነው የሚለውን መመለስ አስፈላጊ ሆኗል።

የቀረበውን ጥያቄ በፈለገው መንገድ ይስተናገድ ብሎ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ መተው ተገቢ አይደለም። ይህን የመሰለ አቋም በመያዝም ለህዝብ ውግንና አለን ብሎ መውሰድ አያስደፍርም። ስለዚህ ይህን ምክንያት ተጠንቶ መነሻ ምክንያቱና መፍትሄው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለህዝቡ ለውይይት ይቀርባል። ህዝቡ ‹‹እኔ ጥናቱን አልቀበልም፤ ሕገ መንግስቱን ተከትዬ ነው መሄድ የምፈልገው›› ካለ መብቱ ነው የሚከለክለው ነገር የለም።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ፖለቲካው ዋልታ ረገጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህን ጉዳይ የሚያጦዙ ሀይሎች ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ ሕዝቡ ተረጋግቶ ሁኔታውን እንዲመለከት ይረዳል በሚል የሚወሰደው እርምጃ ደግሞ ጥናት ላይ ተመስርቶ የተገኘውን መረጃን ይዞ ለውይይት መቀመጥ ነው። ይህ ደግሞ ፋይዳው በጣም ትልቅ ነው። ስለዚህ ከሕገ መንግስቱ ውጭ የሚኬድ መንገድ የለም። በሕገ መንግስቱ ላይም ቢሆን ሪፍረንደም ተደርጎ የሚወስነው ህዝቡ ነው። አብሬ ብሆን ይጠቅመኛል ወይም በራሴ ክልል ሆኜ እቀጥላለሁ ብሎ ነው የሚወስነው።

ስለዚህ ለእንደዚህ አይነት ውይይቶች ላይ ጥናት ትልቅ ግብዓት ይሆናል፤ ትርጉምም አለው ማለት ነው። በዚህ መንገድ ማየት እጅግ ኃላፊነት የተሞላበት ነው። ከዚህ ባለፈም መረጃ ላይ የተመሰረተ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባትና ውይይት ለማድረግ እድል የሚሰጥና ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ስለሆነ ‹‹በሕገ መንግስቱ መሰረት ብቻ ነው ማለቅ ያለበት›› የሚሉ አካላት የሚያነሱት ሃሳብ ከቅንነት የተነሳ ነው ብዬ አልወስድም። እውነት ለህዝቡ ተቆርቁሩው ነው ብዬም አላምንም።

አዲስ ዘመን፡– ጥያቄው ሕገ መንግስታዊ ነው ካሉ ጥናት ሳይደረግ ሕገ መንግስታዊ እልባት መስጠት አይቻልም ነበር? ይህ መንገድለደኢህዴን ለምን ችግር ሆነ?

አቶ ሞገስ፡– አዎ! በትክክል ችግር ነው። የክልሉ መንግስት ህዝቡ በሰጠው ይሁንታ መሰረት ክልሉን የሚመራ ፓርቲ ነው። ህዝብ የሰጠው ይሁንታ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የጋራ እና ዘላቂ ጥቅሞች የሚሰጡት አግባቦች ላይ ማጤን ይገባል፤ አንዱ ይሄ ነው። ሁለተኛ ደኢህዴን አደራጅቶ የሚያታግላቸው ህዝቦች በርካታ ማንነት ያላቸው ህዝቦች ናቸው። ሁሉም በየአካባቢው በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ብቻ ተንተርሶ በሕገ መንግስቱ ብቻ አድርጌ ልሂድ የሚል ከሆነ ህዝቡን ራሱ የማይጠቅሙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ።

ሌላው በአፈፃፀም ላይ ችግር ይፈጥራል፤ ያስቸግራል። ጥናቱ ራሱ አንድ ይዞት የመጣው ጉዳይ ሕገ መንግስቱ ቢሆን ዝርዝር ነገሮች ሊኖሩት ይገባል የሚል ምላሽ ነው። ለምሳሌ በእኛ ክልል ተጨባጭ ሁኔታ በወረዳ የብሔረሰብ ምክር ቤት አለ። አሁን ባለው ሁኔታ ይህ የብሔረሰብ ምክር ቤት ክልል ሁኜ ልውጣ ብሎ በብሔረሰብ ምክር ቤት ካፀደቀ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሕገ መንግስቱ ያስተናግዳል።

እንደዚህ አይነት ነገሮች ሕገ መንግስቱ ላይ ጭምር መታየት እንዳለበት ጥናቱ አመላክቷል። በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ላይ ያሉ አፈጻጸሞች ሕገ መንግስቱ ላይ ተፅፎ ስላለ በሚል ኃላፊነት በጎደለው መንገድ መሄድ በራሱ ጥሩ አይሆንም፤ ማንንምም አይጠቅምም። ይህን ኃላፊነት መውሰድ እጅግ አስፈላጊ ነው።

አዲስ ዘመን፡– በአገሪቱ ያሉ ክልሎች ሲዋቀሩ በጥናት አይደለም፤ ነገር ግን አሁን ደኢህዴን እየሄደ ያለው መንገድ አዲስ እና የተለየ ለምንሆነ? የሚሉ ሀሳቦችን እንዴት ያዩዋቸዋል?

አቶ ሞገስ፡– ክልል ሲደራጅ በጥናት አይደለም የሚለውን ለመመለስ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው። የእኛ ክልል የተደራጀበት ሁኔታ ጠቃሚ የሚሆነው እንደዚህ አይነት ጥናቶች ቢኖሩ ይህን መሰረት አድርገሀ ትገልፃለህ፤ አለበለዚያ ግን በመላምት ትናገራለህ ማለት ነው። አልተጠናም፤ ተጠና ሊልህ ይችላል።

በዚህ በአሁኑ ጥናት የተገኘው ክልሉ ሲደራጅ በምክንያት መሆኑን ነው፤ የህዝብ ፍላጎት እና ውይይት ጭምር የነበረበት ነው፤ አምስት ክልል የነበሩ ናቸው አንድ ክልል ሆነው የተደራጁት። እዚህ ላይ ከአምስት ወደ አንድ ሲመጡ ዝም ብሎ ተጨፍልቆ፤ በትእዛዝ አንድ ሆኖ የተደራጀ ክልል አይደለም። ህዝቡ በነበረው መደባዊና ብሔራዊ ጭቆና ተነስቶ በበለጠ ደግሞ በውስጡ ያሉ አቅሞችን የበለጠ አቀናጅቶና አደራጅቶ መንቀሳቀስ ቢችል ጥቅሙ ከፍ ያለ ነው።

በወቅቱም በህዝቡ ውይይት የተደረገበት ልሂቃንም አስተያየት የሠጡበት፤ አመራሩም ውይይት አድርጎበት አንድ ላይ መደራጀቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትርጉሙ ከፍ ያለ መሆኑ ታይቶ ነው አሁን ላይ ያለው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የተደራጀው።

ስለዚህ ክልሉ የተደራጀበት መንገድ ምክንያታዊ ነው። ዝርዝር ጥናት ነበረው ወይ የሚለውን ለማየት በወቅቱ የነበረውን እሳቤ ማስታወስ ይፈልጋል። በተለይ የነበረውን የፖለቲካ ሁኔታ ማየት ይጠይቃል። ስለዚህ ከእኛ አኳያ ጥናቱም ይዞት የመጣው ጭብጥ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል።

ስለዚህ ክልሉ የተደራጀው በምክንያት ነው። አሁን በተለየ ሁኔታ ክልል ሁኜ ልውጣ የሚለው ጥያቄ የመጣበትን ሁኔታ ማጥናት ጠቃሚ ነው የሚል አስተሳሰብ ተይዞ ነው የተጠናው። ተጠንቶ በመጣው ግኝት ላይ ተመስርቶ ህዝቡ እንዲወያይ ይደረጋል። ህዝቡ መልሶ ይጠቅመኛል፤ ያግዘኛል ክልሉን ለማስቀጠል ፋይዳ አለው ካለ ደግሞ የክልሉን ፍቃድ እና ፍላጎት መሰረት ያደረገ እንዲሆን ይሰራል።

አዲስ ዘመን፡– በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥናቱን ሳይቀበሉ ጥያቄያቸውን በሕገ መንግስት ብቻ የማስፈፀም መብትአላቸው?

አቶ ሞገስ፡– ይህን ኃላፊነት መስጠት የሚገባው ለፓርዎቹ ሳይሆን ለህዝቡ ለራሱ ነው። ህዝቡ ሕገ መንግስታዊ መብቱ እየተነፈገ አይደለም። ሕገ መንግስታዊ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይዘን የመጣናቸውን ጉዳዮች እናወያያለን። ጥናቱ ለውይይት ሲቀርብ የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮች ይቀርባሉ። እነዚህ መፍትሄዎች የራሳቸው ጠንካራ እና ደካማ ጎኖቹም አብረው ይቀርባሉ። ህዝቡ እነዚህን አመዛዝኖ ውሳኔ ላይ ይደርሳል።

የክልሉ ምክር ቤት የሁሉም ዞኖች ተወካዮች ያሉበት በመሆኑ አንድ ዞን ክልል ሆኖ ለመውጣት የሌላውን ዞን በጎ ፍቃድ ይፈልጋል። ምክር ቤቱ የሁሉም ዞኖች ተወካዮች ያሉበት ነው። አንድ ዞን ብቻ ሁሉን ነገር አድራጊ ፈጣሪ አይደለም።

አንድ ዞን ክልል ሁኜ ልውጣ ሲል ይህን ጉዳይ የሚያስፈፅም የክልል ምክር ቤት አለ፤ ይህ ምክር ቤት ደግሞ የክልሉ የሁሉም ዞኖች ተወካዮች ያሉበት ነው። ስለዚህ አንዱ በሌላው ላይ አሉታዊም አዎንታዊ ጫና ሊያሳድር ይችላል ማለት ነው።

ስለዚህ ብቻዬን ክልል ሁኜ ልውጣ ብቻ ሳይሆን ለመውጣት ባለው ሂደት የሌላውም ዞን ትብብር እና ተሳትፎ ትልቅ ነው ማለት ነው። ይህን ነው የምናወያየው፤ እናም 11 ዞኖች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ይጓዙ ቢባል አንዱ በሌላው ላይ አዎንታዊ ፍላጎት ማሳየት አለበት ማለት ነው። ለዚህም ነው ውይይቱን በዝርዝር እናድርግ፤ አማራጮችንም እናቅርብ የምንለው።

ህዝቡ ጥናቱ ላይ ተመስርቶ የሰከነ ውሳኔ እንዲያስቀምጥ ነው የምንፈልገው። አለበለዚያ ወቅታዊ በሚመጡ ግፊቶችና የተለያዩ ሀይሎች ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የሚሄድ ከሆነ ፍፃሜው ጥሩ አይሆንም ነው። ስለዚህ እናወያያለን ስንል ህዝቡ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ተነጋግሮ የመወሰን እድል እንፈጥርለታለን ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡– አንዱ ዞን የሌላውን ዞን ይሁንታ የሚጠይቅ፤ አሊያም የሚጠብቅ ከሆነ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብቱ የት ላይ ነውታዲያ?

አቶ ሞገስ፡– አንድ ዞን የሌላውን ዞን ይሁንታ የሚጠብቀው በሕገ መንግስቱ አካሄድ ነው። ራስን በራስ በማስተዳደሩ የራሱን አስተዳደር አካባቢ ከመምራት የሚከለክለው ነገር የለም። የደቡብ ክልል አደረጃጀት ከሌሎች ክልሎች አደረጃጀት ይለያል። እያንዳንዱ ዞን የራሱ ምክር ቤት አለው። በውስጡም አባላት አሉት። የሌሎች ክልሎች ዞኖች ላይ ይሄ የለም። ምክር ቤቱ ማንነቱን ለማሳደግና ልማቱን ለማፋጠን በርካታ እድሎች አሉት።

ከዚህ ወጥቶ ክልል የመሆን ጉዳይ ላይ በሚሄድበት ወቅት ግን እነዚህ ክልል ሆኖ የመሄድን ጉዳይ የሚያስተዳድረው በሕገ መንግስቱ የክልል ምክር ቤት ነው። የክልሉ ምክር ቤት ማለት ደግሞ በክልሉ በሁሉም ዞኖች ያሉ ተወካዮች ማለት ነው። የክልሉ ምክር ቤት ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ መግባባት፣ መስማማት እንዲሁም ጥቅሙንና ጉዳቱን ማመዛዘን መቻል አለበት።

አለበለዚያ ይህን ጉዳይ አግባብተህና አወያይተህ ሳትጨርስ 11 ዞን ክልል ሁኜ ልውጣ ብሎ ቢመጣ አንደኛ እልህ ይሆናል፤ ሁለተኛ ምክንያቱን በውል ያልተረዳ ከመሆኑ የተነሳ አንዱ በሌላኛው ላይ ያለውን ጉዳይ እንዲረዳና እንዲያግዘው ያደርጋል። ስለዚህ የዞን ምክር ቤት ብቻውን ሳይሆን የክልል ምክር ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ ይሁንታ ያለው መሆኑን መረዳት ይገባል። ሕገ መንግስቱም ይህን ያስቀምጣል። ይህ ወደ አዲስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄ ውስጥ እየገባን መሆኑን አመላክቷል።

ይህን ጉዳይ በተደራጀ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ እንድንፈፅም ያደርጋል። ነገር ግን የሕገ መንግስታዊ ጥያቄ ብቻ አድርጎ መውሰድ፤ አሊያም ዝም ብሎ በሕገ መንግስቱ ብቻ ይለቅ ብሎ መተው ጠቃሚ አይሆንም። ምክንያቱ ታውቆ ህዝቡም መረጃ ለይ ተመስርቶ ውይይት ማድረግ ቀጣይ ሂደቱም ጤናማና ዴሞክራሲያዊ አካሄድ እንዲኖረው አድል ይፈጥራል።

አዲስ ዘመን፡– ‹‹አምስት የነበረው ወደ አንድ ክልል መጣ›› ያሉት ሀሳብ ህዝቡ ‹‹የማነሳው የክልል እንሁን ጥያቄ የቆየ ነው›› የሚለውን ያጠናክራል። ታዲያ አሁን የሚነሳው የክልል እንሁን ጥያቄ ለምን ፈተና ሆነ?

አቶ ሞገስ፡– ያኔ አምስት የነበረውን ክልል አንድ ማድረግ ተችሏል። አሁን ያለው ሁኔታ እና የቀድሞው ሁኔታ ይለያያል። የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ እድገቱ አጠቃላይ አገራዊ ፍላጎት እና ነባራዊ ሁኔታው ይለያል። በዚያን ጊዜ አምስት የነበሩት አንድ እንሁን ብለው የተደራጁ ከሆነ ክልል ልሁን ብሎ ጥያቄ ያቀረበ 11 ዞን ክልል ምክር ቤት አቅርቧል። ስለዚህ በሕገ መንግስቱ መሰረት ያላቀረቡትም ቆም ብሎ ማየት ጠቃሚ ሆኖ ስላገኙት ነው እንጂ ሕገ መንግስታዊ መብት የለንም፤ ወይም አይመለከተንም ብለው አይደለም።

ስለዚህ 11 ዞን ክልል ይሁኑ ብለን መተው ያለብን አይመስለኝም። ይህ በእኛ በደቡብ ክልል ተጨባጭ ሁኔታ በርካታ የብሄረሰብ ምክር ቤቶች ያሉበት ከመሆኑ፣ አሁን ጫፍ የረገጠ ፖለቲካ ውስጥ ከመኮነኑና የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ እንደዚህ አይነት ሁኔታዎችን ማሟሟቅ ተገቢ አይደለም፤ ፋይዳ የለውም ስሜት ነው የሚሆነው። ስለዚህ ረጋ ብሎ ማየት ይጠቅማል። ረጋ ብለህ ለማየት ደግሞ የተጣራ መረጃ ይዘህ ስትቀርብ ከሌላም ጋር ለመከራከር ጥናቱን ይዘህ ይሻላል።

በመሆኑም ጉዳዩ ቀላል ነው ብሎ መውሰድ ከጉዳዩ ሩቅ ላለ ነው፤ ለቅርቦቹና ውስጡን ለሚያውቀው ሰው ደግሞ ምን ያህል ከባድ እና ውስብስብ እንደሆነ ያውቀዋል። ለዚህም ነው ካለብን ኃላፊነት አንፃር ጉዳዩን ቆም ብሎ ማየት እጅግ ይጠቅማል የምንለው። በውይይቶቹ እያየን ያለነው ጉዳዮች እነዚህ ናቸው። አንዳንዱ በወቅቱ የነበረው የምክር ቤቱ አካሄዶች የእኛ ጉዳይ ምን ይሆን የሚልም ስለነበር በዚሁ ተገፋፍተው የሄዱበት ሁኔታ አለ። አንዳንዱ ደግሞ በእርግጥ ለረጅም ጊዜ የነበሩ ጥያቄዎች ጋር ተያይዞ የነበረና የቆየ ጥያቄ ነው የምናነሳው ብለው ይቀርባሉ።

የተነሳውን ጥያቄ በሚመለከት ጥናቱ ይዞት የመጣው ጉዳይ አለ። ክልል ሆኖ ለመቀጠል ለምን ጥያቄ አቀረባችሁ ተብሎ ሲነሳ በዋናነት የተለዩት መንስኤዎች 10 ናቸው። እነዚህ መንስኤዎች ለውይይት እድል ይሰጣሉ። ነገር ግን ‹‹ይሄ ሕገመንግስታዊ መብቴ ነው፤ አትንኩኝ›› የሚል ካለ ምንም የማያግባባ ክርክርና ጭቅጭቅ ይሆናል ማለት ነው። በዚህ መንገድ ማየቱ ጠቃሚ ነው የሚል ሀሳብ አለኝ።

አዲስ ዘመን፡ ጥናቱን በሚመለከት ከአደረጃጀት ጀምሮ ችግር አለ ይባላል፤ አጥኚዎቹ የድርጅቱ ቅርበትና ውግንና ያላቸው ናቸው የሚልትችትም ይቀርባልና በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

አቶ ሞገስ፡– ይህ የተሳሳተ አስተያየት ነው። የፓርቲ ውግንና ያላቸው ናቸው ብሎ ማጠቃለል ተገቢ አይደለም። ጥናቱ እንዲደረግ ኃላፊነት ወስዶ አቅጣጫ እያስቀመጠ ያለው ደኢህዴን ነው። እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጉዳይ ጥናቱ ሳይንሳዊ ነው ወይስ አይደለም የሚለውና በጥናቱ ሂደት የተሳተፉ ባለሙያዎች ምን ያህል ጥናቱን በነፃነት እንዲጠና አደረጉ የሚለው ነው። ከዚህ ባለፈ ደግሞ እንደዚህ አይነት ጥናት ላይ እንዲሳተፉ የተለዩ አካላት ተቀባይነት እንዲኖራቸው ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ እንዲሆኑ ተደርጓል።

በመሆኑም ከፍተኛ ልምድ ያላቸው፤ የምርምር ነፃነት ያላቸው አካላት በዚህ ጉዳይም በዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ተመራማሪዎች ናቸው በጥናቱ የተሳተፉት። ቀድሞውንም በክልሉ መመስረት ላይ ልምዱና አስተዋፅኦ የነበራቸው ናቸው። የክልሉ ብዝሀነት በርከት ያለ በመሆኑ ለአሉባልታ እና ለጥርጣሬ በር እንዳይከፍት በእያንዳንዱ ውስጥ ያሉ አካላት በጉዳዩ ላይ እንዲሳተፉ ተደርጓል። የተመራማሪ አቅም የብዝሀነት ተዋፅኦን እና የረጅም ጊዜ ልምድ ያካተተ ሆኖ ነው የጥናት ቡድኑ የተዋቀረው።

በእኛ በኩል ማረጋገጥ የምፈልገው ቡድኑ ግልፅ አሰራር አውጥቶ ጥናቱን በነፃነት አከናውኗል። የትኛውም ፓርቲ የጥናት ሂደቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይመራ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል። የጥናት ቡድኑን ነፃነት በሚመለከት እነሱን መጠየቅ ይቻላል። የጥናት ቡድኑ ያዘጋጀውን መጠይቅ የሞሉት አካላት ምን ያህል ነፃ እንደነበሩ ለማየት ቀረብ ብሎ ማየት ያስፈልጋል። ስለዚህ በሩቅ ሆኖ የጥናት ቡድኑ የድርጅቱ ወዳጅ ናቸው ብሎ ማጥላላት መረጃ ላይ የተመሰረተ አይደለም።

አዲስ ዘመን፡– ለሰባት ቀናት ባደረጋችሁት ስብሰባ ‹‹በጥናቱ ላይ በመስማማት አጠናቀናል›› ብላችኋል። በምን ነጥቦች ላይ ነውየተስማማችሁት?

አቶ ሞገስ፡- በስብሰባው ጥናቱ የያዘው ነጥብ በዝርዝር ቀርቦ፤ መፍትሄዎቹ ከእነ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖቹ ተለይተው ተቀመጡ። የትኛው ለህዝብ ይቀርባል በሚለው ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። የትኛው መንገድ ለህዝብ ይጠቅማል፤ የህዝቡን ሁኔታ ማየትና ዘላቂ ጥቅም መለየት እና መወያየት ትኩረት አድርጎ ተወያይቷል።

ሁሉም አማራጮች ቀርበዋል። በ56ቱም ብሄር ልክ ክልል መሆን የሚለው ሀሳብ ሳይቀር ተነስቷል። አንድ ክልል ሆኖ መቀጠልም በጥናቱ ቀርቧል። ሁለትም ሶስትም ሆኖ ክልል ማደራጀትም በመፍትሄነት ተነስተዋል። እያንዳንዱ አማራጭ ጠንካራ እና ደካማ ጎን አሉት፤ እነሱም ለውይይት ቀርበዋል።

እዚህ ላይ የአመራሩ ሚና የሚሆነው ጠንካራ እና ደካማ ጎን ላይ ትኩረት በማድረግ መርምሮና መዝኖ መውሰድ ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ጉዳይ ከተነሳ በኋላ አመራሩ ተወያይቶ ክልሉ አሁን ካለበት ሁኔታ በመነሳት አብሮነቱ የበለጠ ጥሩ ይሆናል። በዚህም ላይ ሰፊ ክርክር አድርጓል። ይህን ሁኔታ ደግሞ ወደ ህዝቡ ይዘን ወርደን ወሳኙ ራሱ ህዝቡ ይሆናል። በቀጣይ ህዝቡን በስፋት ለማሳተፍ እቅድ ተይዟል። በዚህ ሁኔታ አሉ የሚባሉ ምሁራንም በውይይቱ ይሳተፋሉ። የሚመለከተው ሁሉ የሚሳተፍበት መድረክ ይሆናል ብለን እናምናለን።

አዲስ ዘመን፡– ከሶስቱ አማራጮች የተስማማችሁት ክልሉ አንድ ሆኖ በመቀጠሉ ላይ ይቀጥል የሚል ግልፅ አቋም ይዛችሁ መሆኑንእየገለፁልኝ ነው?

አቶ ሞገስ፡– አማራጮቹ አንድ ብቻ አይደሉም፤ አማራጮቹ ሶስት ናቸው። ከሶስቱ አማራጮች የተሻለ ነው ብለን፤ በእኛ ደረጃ መግባባት ላይ እየመጣን ያለነው ህዝቡን የበለጠ ሊያስተሳስሩ የሚችሉ የአደረጃጀት ሁኔታዎች ጠቃሚ ነው ብሎ የወሰደበት ርቀት አለ። አንዳንድ በሕገ መንግስቱ አስቀድሞ የሄደው የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ምርጫ ቦርድ የደረሰና በሕገ መንግስቱ መሰረት እየሄደ ቢሆንም የሲዳማ ህዝብንም ቢሆን እናወያያለን። ምርጫ ቦርድ የደረሰውን መብቱን በሚገባ እናስፈፅምለታለን። የሲዳማ ጉዳይ ብዙ ርቀት የተጓዘ በመሆኑ ይህን በሚገባ ማስፈፀም አለብን።

አዲስ ዘመን፡– የቀሪዎቹ ዞኖች ጥያቄስ መጨረሻው ምንድን ነው? ሌሎቹ በያዛችሁት አማራጭ አንድ ሆነው የሚቀጥሉ ናቸው?

አቶ ሞገስ፡– ጥናቱ ያመጣውን አማራጭ ይዘን ወደ ህዝቡ እንወርዳለን። ህዝቡ የሚለውን እንሰማለን፤ ተወያይቶ የሚወስነው ይሆናል ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡– ለሰባት ቀን ያደረጋችሁት ስብሰባ በስምምነት የጨረሳችሁት ጥናቱን የሚቃወሙ አባላት ከታገዱ በኋላ ነው። ውሳኔውስዴሞክራሲያዊና ሁሉንም ያካተተ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ሞገስ፡– ሰዎች የታገዱት በአካባቢው በተፈጠረው ጉዳት ሳቢያ ነው፤ ይህ ደግሞ የአመራር ውድቀት ነው። አመራር በመስጠት ሂደት ውስጥ የነበረ ውድቀት በመሆኑ የፖለቲካ ተጠያቂነት ተረጋገጠ ማለት ነው። የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ዛሬ የተነሳ አይደለም። ባለፈው መስከረም ላይ በተደረገው የድርጅት ጉባኤ ላይ የተቀመጠ አቅጣጫ ነው። ዛሬ ተነስቶ በዚህ መንገድ ይሁን የሚል አካል የለም። እዚህም ላይ ተመስርቶ የክልል ምክር ቤት በሕገ መንግስቱ መሰረት ሪፍረንደም ተዘጋጅቶ ወደ ስራ እንዲገባ ወስኗል። ይህም በዚህ አግባብ እየሄደ ነው።

እኛ ያገድነው ሰው አምስት ነው። ከታገዱት ውጭ የሲዳማ ዞንና ወረዳ አመራሮችን ጨምሮ ስብሰባውን የተሳተፈው 539 አመራር ነው። አንድ ሰው እና ሁለት ሰው በመቅረቱ ስብሰባው ወይም ውሳኔው ዴሞክራሲያዊ አይደለም፤ እንዲሁም ይህን ጥናት የተቃወሙ አካላት በሌሉበት የተካሄደ ነው ብሎ ሁሉን ያላካተተ ነው ማለት ፍፁም የተሳሳተ ነው። ከእገዳው ጋርም አይገናኝም።

አዲስ ዘመን፡– ደኢህዴን አሁን ካለበት ችግር ወጥቶ እንዴት ወደ ፊት መቀጠል ይችላል?

አቶ ሞገስ፡– ደኢህዴን ለይስሙላ የተደራጀ ፓርቲ አይደለም። ድርጅቱ የአርሶ አደርና የአርብቶ አደር ነው። ከተማ ያለ ጭቁን ህብረተሰብ ወኪል የሆነ ድርጅት ነው። በተለያዩ ጊዚያት የሚፈጠሩ ብልሽቶች ከአገራዊ ስርዓት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ በአመራር በኩል ያለው የሚስተካከል ነው። ለደኢህዴን የተለየ ነገር የለውም። አመራር ውስጥ ያለው ችግር በደኢህዴን ብቻ የመጣ አይደለም፤ በሁሉም ድርጅቶች ውስጥ ያለና አጋጥሞ የነበረ ነው።

እነዚህ ችግሮች ደግሞ የሚፈቱ ናቸው። በአመራር መድረኩ ያየነው በአመራሩ በኩል ያለው ተነሳሽነት ድርጅቱን ለማጠናከር የአገሪቱንም አንድነት ለመፍጠር የተነሳሳበት መድረክ ነው። ስለዚህ ዛሬም ቢሆን ደኢህዴን ጠንካራ ነው። የሚታዩ ችግሮች አገራዊም ክልላዊም አንድምታ ያላቸው ችግሮች አሉ። ስለዚህ እነዚህን ችግሮች ፈትቶና ጠንካራ ድርጅት ሆኖ ህዝቡንም አታግሎ የሚጓዝ ነው። ደኢህዴን ይዳከማል የሚሉ አካላት አሁንም በጠንካራ አቅሙ ላይ እንዳለ መገንዘብ ይገባቸዋል። በውስጣችን ያሉ ጉዳዮችን አስተካክለንና አርመን ለመሄድ የሚያስችል ቆፍጠን ያሉ አቋሞች የተወሰዱበት መድረክ ነው።

አዲስ ዘመን፡– በደኢህዴን የወሰናችሁትን ውሳኔ ከተበተናችሁ በኋላ የዞን አመራሮች በተናጠል ሲቃወሙና ተቃራኒ መግለጫ ሲሰጡይታያል። ይህ ሁኔታ ደኢህዴን ተሰንጥቋል ለማለት አያስችልምን?

አቶ ሞገስ፡– ይህ የአመራር የዲሲፒሊን ጥሰት፣ የዲሞክራሲ ማዕከላዊነት መጓደል፤ የድርጅት መርህ ጥሰት የአመራር ብልሽትና ግድፈት ነው። እነዚህ የአመራር ግድፈቶች ላይ በአመራሩ ሰፊ ግምገማ ተደርጎበታል። ይህ ደግሞ ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ እስከ ታችኛው ድረስ ያለ መሆኑን ካድሬው አንስቷል። ይህን ችግር አመራሩ በሚገባ ወስዷል። ትክክል አይደለም አርማለሁም ብሏል።

 ይህን ለማረም ደግሞ በቀጣይ እያስተካከልን እንቀጥላለን። ስለዚህ ችግሩ ሊስተካከል የሚችል ነው። በተወሰነ ደረጃ የተለያዩ የሀሳብ ልዩነቶች መገለፃቸው እንግዳ ሊሆን ይችላል፤ በሌላ በኩል ሀሳቦች በተለያየ መንገድ መገለጻቸው ነውር ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ነገር ግን ከድርጅት ዲሲፒሊን አንፃር ስህተት ነው መጠበቅ ነበረበት። ሊታረም የሚችል ነው። የአመራር ሁኔታችን ሲስተካከል ወዲያው የሚፈታ ነው። ይህ ከድርጅት መሰንጠቅ ጋር አይያያዝም።

አዲስ ዘመን፡– የክልሉ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ ምን መልክ ይዟል?

አቶ ሞገስ፡– በክልሉ ያጋጠመው የፀጥታ ችግር ዋናው የፖለቲካ ብልሽት ነው፤ የፖለቲካ አመራሩ ብልሽት ነው። የፖለቲካ መዋቅሩ ብልሽት ነው ለፀጥታ ችግር የዳረገን። ፖለቲካዊ ሁኔታችንን በሚገባ ማስተካከል ከቻልን የፀጥታው ሁኔታ በቀጥታ ይስተካከላል። ሆኖም ግን የህዝቡን ደህንነትና ሰላም ከማረጋገጥ አንፃር በተለይ በአንዳንድ ቦታ ላይ ተደራጅቶ የሚንቀሳቀሰው በወጣት ስም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በአንዳንድ ቦታ ላይ በሲቪክ ማህበረሰብ ተደራጅተው መብትና ግዴታቸውን አውቀው የሚሄዱበት ሁኔታ አለ።

በአንዳንዱ ቦታ ደግሞ መልክ ስላልያዘ የደቦ ፍርድ እና ሁከቶች፤ መንገድ የመዝጋት ተግባራት ህዝቡ ስጋት ውስጥ እንዲገባ አድርጓል። የስርዓት አልበኝነት ሁኔታዎች በስፋት ታይተዋል። ህዝቡ ደህንነት እንዲሰማው በክልሉ ኮማንድ ፖስት እንዲኖር ተደርጓል። ኮማንድ ፖስቱ ከፌደራል ሀይሉ ጋር ተቀናጅቶ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ እንቅስቃሴዎችን እንዲመራ ተደርጓል። ይህ በመሆኑ ባለፉት ቀናት ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል። ስርዓት የመያዝ ገደብ የመያዝ፤ ህዝቡም መረጃ በመስጠት ተባብሮ ከመሄድ ጋር ተያይዞ ለህዝቡ የበለጠ አስተማማኝ ሰላም የሚያረጋግጥበት እድል ይፈጥራል።

በድርጅቱ ውስጥ አሁን በተፈጠረው መነሳሳት እና የአመራር ሁኔታን የማስተካከል ጉዳይ ሲታይ በፍጥነት ተሰርቶ ክልሉ ወደሚታወቅበት አስተማማኝ የሰላም፣ አረንጓዴ ልማት መገለጫነቱ ይመለሳል። ኮማንድ ፖስቱ የሰጠው መግለጫም በአጭር ጊዜ ውስጥ ህዝቡን ወደ ሰላም የመመለስ እድል መኖሩን ያሳያል። ስለዚህ ሁለቱንም ጎን ለጎን አቀናጅተን ማስኬድ ከቻልን በቅርቡ ወደ አስተማማኝ ሰላም እንመለሳለን።

አዲስ ዘም ነሃሴ 2/2011

 ሀብታሙ ስጦታው

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››
0Shares
0