“Our true nationality is mankind.”H.G.

የሻደይ ጨዋታ ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲተዋወቅ እየተሠራ ነው፡፡

የሻደይ ጨዋታን የማስተዋወቅ ሥራው ከባህላዊ እሴቱ ባፈነገጠ መልኩ እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

በሰቆጣ ከተማ አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ሻደይ የልጃገረዶች ጨዋታ በጊዜ ሂደት መልኩን እንዳይቀይር እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በየቤቱ ለመጫወት ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ባህሉ በሚያዝዘው ልክ ከቤተ ክርስቲያን መልስ ከሁሉም አከባቢዎች የሚደረገው ጨዋታ ባህላዊ ስርዓቱን ጠብቆ እንዲከወን ለማድረግና ለማበረታታት ውድድሮችም ይኖራሉ ተብሏል፡፡

“የሻደይ ወቅት ድባብ እና ውበት በህይወት ዘመኔ ሁሉ ቶሎ ቶሎ እንዲመጣ የምጓጓለት ባህሌ ነው” ያሉት የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ እና የበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል አቶ ታደሠ እሸቱ “ከ10 ዓመታት ወዲህ እየታየ የመጣው መቀዛቀዝ ግን ቱባውን ባህል ስጋት ውስጥ የከተተ ይመስለኛል” ሲሉ ትዝብታቸውን ነግረውናል፡፡ የመቀዛቀዙ ምክንያት ደግሞ ሻደይ በየቤቱ መከበሩ እየተዘነጋ በአንድ መድረክ ለማክበር ትኩረት መሰጠቱ ነው የሚል አስተያየት ነው የሰጡን፡፡

በአንድ ቦታ መከበሩ ሌሎች ሕዝቦች እንዲያውቁት ከፍተኛ ሚና ቢጫወትም በየቤቱ የነበረውን ድባብ ግን እንዳደበዘዘው ነው የተናገሩት፡፡ ዘንድሮ እስከ አዲስ አበባ ከሚከበረው በዓል ባሻገር ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በየቤቱ እንዲከበር ኮሚቴ አዋቅረው እየሠሩ መሆናቸውንም ነው አቶ ታደሰ የተናገሩት፡፡ የሻደይ በዓል ከባህላዊ ጨዋታነቱ ባለፈ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች መስህብ እንዲሆን ይዘቱን ሳይለቅ፣ እውነተኛውን ክዋኔ መጫወት አዋጭ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ይህን በማሳካት ረገድ የአካባቢው ሕዝብ እና መንግሥት በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

አሸንዳ 1.jpg

አካባቢያዊ ድባቡ መቀዛቀዙን ያመኑት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ኃላፊ አቶ ምስጋናው መስፍን ባህሉ በወጉ ተጠብቆ እንዲከበር እና ለተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተሰንዶ እንዲቀርብ በማድረግ በኩል የተሠሩ በርካታ የጥናት እና ምርምር ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡ በየቤቱ የነበረውን ጨዋታ በመቀነስ፣ ከአውዱ ውጪ በመድረኮች ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ተግባራት በዘንድሮ በዓል ቱባውን ባህል እንዳያቀዘቅዙት በየቀበሌው እየሠሩ እንደሆነም አቶ ምስጋናው ተናግረዋል፡፡

የሠቆጣ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ባለሙያ አቶ ታደሠ ሞላ ልጃገረዶቹ ሻደይን ከመጫወት ባለፈ ቱባ ባህሉን መጠበቅ ላይም ማተኮር እንዳለባቸው አስታውሰዋል፡፡ ልጃገረዶቹ በነጻነት እንዲጫወቱት ከማድረግ ባለፈ በመንግስት በኩልም ለቱባ ባህሉ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡ ባሕሉ እንዳይበረዝ ለማድረግ በዘንድሮው የሻደይ ጨዋታ ለጨዋታ የደረሱ በሁሉም የዕድሜ ደረጃ ያሉ ሴቶች እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡

በዓሉን በትክክል ማስተዋወቅና መከወን ላይ ያተኮረ ውድድርም ይካሄዳል፡፡ ባህላዊ ይዘቱንና ክዋኔውን በትክክል መግለፅ ለሚችሉ ተወዳዳሪዎች ደግሞ ማበረታቻ እንደሚበረከትላቸው ታውቋል፡፡

የሻደይ በዓል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከነሃሴ 16 እስከ 21/2011 ልጃገረዶች እና ወንዶች በየቤቱ እየዞሩ የሚጫወቱት የክፍለ ዘመናት ታሪክ ያለው በዓል ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 12/2011 ዓ.ም (አብመድ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   አሜሪካ ለጊዜው ሲባል የከረመ ሃሳብ ያካተተ መግለጫ አወጣች፤ ምርጫውን በተዘዋዋሪ ደግፋለች
0Shares
0