“Our true nationality is mankind.”H.G.

ʻክልል እንሁንʼ ጥያቄዎችን ከህገ-መንግስታዊ መብትነታቸው ባሻገር ፣ … ደኢህዴን

– በዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነትና በውጤቱ መነጽር ማጤን !

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ – መንግስት በአንድ ክልል ውስጥ የተካተቱ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች ፣ ህዝቦች የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው ሲል ይደነግጋል፡፡

ይህ ህገ-መንግስታዊ መብት እንደ መብት ህገ – መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው መብት ነው፡፡ ይህ መብት የህጎች ሁሉ የበላይ በሆነው በህገ-መንግስቱ ውስጥ የሠፈረ መብት በመሆኑ መብቱን ማክበርና ማስከበር ተገቢ መሆኑን በአንድ ጫፍ መያዝ፣ በሌላኛው ጫፍ ደግሞ ለአብነት በደቡብ ውስጥ 56 ብሔሮችና ብሔረሰቦች ፣ አስራ ስምንት ዞኖች፣ ከአራት በላይ ልዩ ወረዳዎች በአጠቃላይ ከሃያ ሶስት በላይ የዞንና የልዩ ወረዳ የብሄረሰብ አስተዳደር ምክር ቤቶች መኖራቸውን እዲሁም ብሄሮች ፣ ብሄረሰቦቹም ሆኑ የብሄረሰብ ምክር ቤቶቹ ክልል ሆነው የመውጣት መብታቸው በመርህ ደረጃ ህገ – መንግስታዊ መብት መሆኑን ተረድቶ ሀላፊነት በተላበሰ መንገድ ሁኔታውን ማገናዘብ ጠቃሚ ነው፡፡

አዲስ ክልል የመሆን መብት በህገ መንግስቱ የተሰጠው በነባሩ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች መሆኑን ፣ በደቡብ ክልል ውስጥ ደግሞ 56 ብሄሮችና ብሄረሰቦች መኖራቸውን ፤ ሁሉም ደግሞ በመርህ ደረጃ እኩል መብት ያላቸው መሆኑን መረዳት የዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት ማሳያ ነው፡፡ አዲስ ክልል ሆኖ የመውጣት መብት እንደ መብት በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠ ቢሆንም በኢትዮጵያ ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዘ በተግባር የተደገፈ ልምድ ባለመኖሩ ምክንያት በተግባር ሂደት ምን ሊያጋጥም እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡

በተለይም አስራ አንድ ዞኖች ክልል እንሁን ጥያቄ ማቅረባቸው ብቻ ሳይሆን ያልጠየቁትም ቢሆን በመርህ ደረጃ ከጠየቁት እኩል መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን ባጤነ የዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት አግባብ ጉዳዮን መመርመር የኃላፊነት ስሜት መገለጫ ነው፡፡

በህገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን ʻክልል የመሆን መብትʼ በደቡብ ተጨባጭ ሁኔታ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ 56 ብሄሮችና ብሄረሰቦች በአንድ ክልል ውስጥ ከሃያ አራት ዓመታት በላይ አብረው መዝለቃቸውን ማስታወስ፣ የጋራ ጉዟቸውን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ በሂደት የገነቡትን የጋራ የማንነት እሴትና ፋይዳ መረዳት ነገሩ ‘የነቶሎ ቶሎ ቤት ግረግዳው ሰምበሌጥ’ ዓይነት እንዳይሆን ይረዳል፡፡ ከሃያ አራት ዓመታት በላይ እድሜ ያለውን ህብረ- ብሄራዊ የጋራ ጉዞ ለተጓዙ 56 ብሄሮችና ብሄረሰቦች ʻክልል መሆን መብትʼ ነው ከሚለው ድንጋጌ በላይ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነትን ማዕከል ያደረገ መፍትሄ ማፈላለግ እንደሚጠይቅ ማስታዋል ይጠቅማል፡፡

ጉዳዩን ከ56ቱም ብሄሮችና ብሄረሰቦች ጥቅምና ጉዳት እንዲሁም ከአገራዊ አንድነትና ከለውጡም መንፈስ አንጻር መመርመር ይገባል፡፡ ግጭቶችንና አለመግባበቶችን አስቀድሞ በመከላከል መነጽርም ማየት ያሻል፡፡

የጥያቄውን አንድና ሁለት ጫፍ ይዞ የቀሪ ሃምሳና ከዚያ በላይ የሆኑትን ብሄርና ብሄረሰቦችን ህልውና መብት ዘንግቶ ጥሎ በማለፍ ሂሳብና በከረረ ብሄረተኝነት ተሸብቦ መንቀሳቀስ ሊያስከትለው የሚችለውን ቀውስ ከወዲሁ አሻግሮ ማየት በተለይም ለሊህቃኖች ትልቅ የቤት ስራ ሊሆን ይገባል፡፡ አንዳንድ ሊህቃን ያዛቡት ጉዳይ ህብረተሰብንም ሊያዛባና አገርንም ሊያቆረቁዝ ይችላል፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን መብት መሬት ላይ መተግበር ጥበብና ኃላፊነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ጥያቄውን በህገ መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መንገድ ብቻ እንደወረደ እንወጣው ቢባል አንኳን የሚያስከትለው ቀውስ ምን ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ መገመት ብልህነት ነው፡፡ የሀሳብ መፈክር በተግባር ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ተገቢ ነው፡፡

በህገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጠው ʻክልል የመሆን መብትʼ በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ለሁሉም የብሄረሰብ አስተዳደር ምክር ቤቶች ወይም ለ56ቱም ብሄሮችና ብህረሰቦች የተፈቀደ መብት ነው፡፡ ይህ መብት የጋራ መብት ነው ብለን ወስደን ሁሉም የብሄረሰብ አስተዳደር ምክር ቤቶች ወይም 56ቱም ብሄሮችና ብሄረሰቦች ክልል ለማቋቋም ቢንቀሳቀሱ ምን ያህል የማያባራ ውጥንቅጥ ሊፈጠር እንደሚችል በሀላፊነት ስሜት ማጤን ተገቢ ነው፡፡ 
ህገ-መንግስታዊ መብቱ የʻስለት ልጅምʼ ይሁን የʻእንጀራ ልጅʼ እንደሌለው እና ለሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች እኩል መብት የሰጠ መሆኑን በልቦና መያዝ ያሻል፡፡ ይህንን የጋራ መብት በአግባቡ ለመጠቀም ደግሞ ምክንያታዊና ዴሞክራሲያዊ ብሄረተኛ ከመሆን ባሻገር የሞራል ልእልናንም ማረጋገጥ ያስፈልጋል ፡፡ ህገ-መንግስታዊ መብቱ እንደ መብት ለሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች የተከፈተ የመብት በር መሆኑን ማስተዋል ከችግሩ መውጫውን መንገድ ለማማተርና ለማቅለል ያግዛል፡፡

ህገ-መንግስታዊ መብት ለሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች የተዘረጋ እድል እንጂ የህዝብ ቁጥራቸው አነስተኛ፣ የመሬታቸው የቆዳ ስፋትም መለስተኛ የሆኑትን ያገለለ በሚያስመስል መንገድ እና ሰፋ ያለ የህዝብ ብዛትና የመሬት ቆዳ ስፋት ላላቸው ደግሞ ልዩ ዕድል የሚሰጥ ተደርጎ የሚወሰድበት አንዳንድ አተያይም ከሚዛናዊነት አንጻር ሊስተካከል የሚገባው ነው ፡፡ መብቱ ለ5 ሚሊየኖችም ፣ ለ500 ሺህዎችም፣ ለ5 ሺህዎችም ከዚያ በታች ለሆኑትም የተፈቀደ መብት መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ደግሞም አንዳችን ያለአንዳችን ውበታችንም ይሁን ጉልበታችን ጎዶሎ መሆኑን ልብ ይሏል ፡፡

የህዝቦች ዕጣ ፈንታ በጋራ ራዕይና ጥረት ላይ በተመሰረተበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ፣ የህዝቦች ትስስር ዘመን ተሻገሪና ከአደረጃጀት ወሰንም የላቀ ሀያል የስበት ሀይል በሆነበት እውነታ ውስጥ ሆነን አንዳችን ስለሁላችንም ፣ ሁሉም ደግሞ ስለእያንዳንዱ የማይጨነቅ ከሆነ እንደማህበረሰብም ይሁን እንደ ሀገር እንዴት በጠንካራ መሰረት ላይ መቆም ይቻለናል ?

ስለሆነም በደቡብ ተጨባጭ ሁኔታ ʻ ክልል እንሁንʼ የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ስንሞክር ህገ-መንግስታዊ መብቶችን ከማክበርና ከማስከበር የተሻገረ አርቆ አሳቢነትና መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ እና አሻጋሪ መፍትሔ ማፈላለግ ወሳኝ ነው ፡፡

ʻክልል እንሁንʼ የሚሉ ጥያቄዎችን በህገ መንግስቱ ላይ እንደተቀመጠው ʻ ብሔሮችና ብሔረሰቦችʼ የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት ተጠቅመው ይወጡት በሚለው መንገድ መሔድን ብቻ ከመረጥን ዙሪያው ገደል እንዳይሆንብን ያሰጋል፡፡ በደቡብ ውስጥ ʻ ክልል እንሁን የሚል ጥያቄ ያቀረቡ አሥራ አንድ ዞኖች “ የእገሌ ክልላዊ መንግስት” የሚል ታፔላ እየለጠፉ ደቡብ ውስጥ በትንሹ አሥራ አንድ አዳዲስ ክልሎች ተፈጠሩ ማለት ነው፡፡

የዚህን ሁኔታ ጉዳትና ጥቅም ለመለየት ደግሞ የግድ በቀውስና በውድቀት ቅርቃር ውስጥ መዘፈቅ አይጠበቅብንም፡፡ የማንኛውም ህግ ዓላማና ግብ ህዝቦችን መጥቀም ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ በቀናናት የተቀመጡት መብቶች መሬት ላይ በተግባር ሲፈተሹ፣ በህዝቦች ጥቅም ሲመነዘሩ ችግር የሚያጋጥም ከሆነ ህግ መንግስቱን እሰከማሻሻል የሚሄድ መፍትሄ ማፈላለግ እንደሚገባስ የታወቀ ጉዳይ አይደለምን ? ህግ በሰዎች ፣ ለዜጎች ጥቅም ሲባል የሚደነገግ ድንጋጌ አይደለምን ?

ከህዝባችን 80 በመቶ አርሶ አደርና አርብቶ አደር በሆነበት ሁኔታ መጨነቅ የሚገባን ገጠርንና ግብርናን በማዘመንና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ ወይንስ ውስኑን በጀት በሚቀራመት አዳዲስ መዋቅር ዝርጋታ ላይ? …

በጉዳዩ ላይ በአግባቡ እንምከርበት ፡፡ ተጨማሪ የወጪ ሜኖ ከመደርደር ይልቅ ለምርታማነትና ለገቢ እድገት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ በሚችሉ አማራጮች ብንዳክር ዕጣፈንታችን ያመረ ሊሆን ይችላል፡፡

ስለዚህም ʻ ክልል እንሁንʼ የሚሉ ጥያቄዎችን ከህገ-መንግስታዊ ቅቡልነታቸው ባሻገር ቀውስን በሚቀንሱ በሌሎች አማራጮች እንሞከረው ማለት ሀላፊነት ከሚሰማው ወገን የሚመነጭ አማራጭ እንጂ ህገ-መንግስታዊ መብቶችን የመደፍጠጥ ተልዕኮ እንዳለው ተደርጎ ባይታይ የተሻለ ነው ፡፡ ግልጽና ተጨባጭ ቀውስ የሚያስከትልን ጉዳይ በተነፃፃሪነት በተሻለና ቀውሱን በሚቀንስ መንገድ እናስተናግደው ማለት ሀገርንና ህዝብን የመታደጊያ መንገድን መምረጥ እንጂ ህግን መፃረር ተደርጎ ባይታይ መልካም ነው፡፡ ህጎች ደግሞ የህዝቦችን ጥቅም ማስከበሪያ መሳሪያዎች ናቸውና በቃላቱ ብቻ ሳይሆን ከቆሙለት ዓላማም አንጻር እንፈትሻቸው፡፡

ʻክልል እንሁንʼ የሚሉትን ጥያቄዎች ከህገ-መንግስታዊ ቅቡልነታቸው ባሻገር በሳይንሳዊ ጥናት በተደገፈ አግባብ ለማስተናገድ መሞከር ለምን ተመራጭ አማራጭ ይሆናል በሚለው ላይ በቅድሚያ ግልጽነት ካልተፈጠረ የጥናቱን ሂደት ፣ ግኝትና ምክረ ሀሳቦችን መቀበል ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡

ʻክልል እንሁንʼ ለሚሉ ጥያቄዎች መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መንገድ ፖለቲካዊ መፍትሄ ማፈላለግም ከሀላፊት ስሜት የሚመነጭ ነው፡፡ ደኢህዴን የ56 ብሄሮችና ብሄረሰቦች ወኪል በመሆኑ የ56ቱም ጉዳይ ያገባዋልና ክልል እንሁን የሚለው ጥያቄ ከህገ መንግስታዊ መብትነቱ ባሻገር ተጨማሪ አማራጮችን የሚፈልግ መሆኑን ደኢህዴን ስላመነበት ጥያቄው ጥናትን መሰረት አድርጎ እንዲስተናገድ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ፡፡

ጥያቄውን በህገ መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መንገድ ብቻ እናስተናግደው ብንል ይህ አማራጭ መሬት ላይ ካሉት እውነታዎች ምን ያህል ይጣጣማል ? አማራጩስ የ56ቱንም ብሄሮችና ብሄረሰቦች ህልውናና መብት ያከበረና ሀላፊነት የተሞላበት ይሆናልን ? ተከትለው ሊመጡ የሚችሉ አካባቢያዊና ሀገራዊ ቀውሶችንስ ምን ያህል ያገናዘበ ነው? የሚሉትንና መሰል ጉዳዮችን በቅን ልቦናና በዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት መንፈስ ማገናዘብ መልካም ነው ፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያራመዱት ያለው አቋም የዴሞክራሲ መርህን የጣሰ ነው
0Shares
0