የተወለዱት በቀድሞው ካፋ ጠቅላይ ግዛት ኮንታ ወረዳ ውስጥ ሲሆን፣ የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት ካሉበት አካባቢ 110 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በጅማ ከተማ ነው:: በወቅቱ ለአካባቢው አንድ ለእናቱ በሆነው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስና ፖለቲካል ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአሜሪካ አገር በኢንተርናሽናል ፋይናንስ ሰርተዋል፤አምባሳደር ጥሩነህ ዜና፡፡

እኚህ 72 ዓመት አዛውንት በውጭ ጉዳይ ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ያገለገሉ ሲሆን፣ በኒዮርክ በኢትዮጵያ አምባሳደርነት ለአራት ዓመትአገልግለዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆንም ሰርተዋል፡፡ አዲስ ዘመን ከአምባሳደሩጋር ባደረገው ቆይታ በሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይና በዲፕሎማትነታቸው ወቅት ስለሰሯቸው እንዲሁም ስለሌሎችም ጉዳዮች በማንሳትያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡

አዲስ ዘመን፡– ወደ ኮሚሽነርነት ከመምጣትዎ በፊት ስለሰሯቸው ቢገልጹልን?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– በኮሚሽነርነት የሰራሁት ለአምስት ዓመት ያህል ብቻ ነው፡፡ ህይወቴን በሙሉ ያሳለፍኩት በዲፕሎማሲው ላይ ነው፡፡ በመጀመሪያ ውጭ ጉዳይ እንደገባሁ የሰራሁት በዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ነው፡፡ ይህም ኢኮኖሚ መምሪያና ዓለም አቀፍ የሚባል መምሪያ ነበር፡፡

በዚህ ጥቂት ጊዜ ከሰራሁ በኋላ በቀድሞው ምስራቅ ጀርመን የኢኮኖሚ አማካሪ ሆኜ ሄድኩ፡፡ በፊትም በዚሁ ሀገር ከስድስት ዓመታት በላይ አገልግያለሁ፡ ፡ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አውሮፓ መምሪያ ውስጥ ዋና የክፍል ኃላፊ በመሆን ሰርቻለሁ፡፡ በፕሮቶኮል እንዲሁም በዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥም አገልግያለሁ፡፡

ኢህአዴግ እንደገባም በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያን ኤምባሲ ለመክፈት ሄድኩ፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ ለምን እንደሆነ ባላውቅም ከደቡብ ኮሪያ ጋር ቶሎ ግንኙነት ማድረግ ፈለገች፡፡ በወቅቱ እኔን አምባሳደር አድርገው ሊሾሙ አይችሉም፡፡ምክንያቱም እኔ የደርግ ሰው ነበርኩ፡፡ እንዲዚያም ቢሆን የላኩኝ አምነውኝ ነው:: ሌሎቹን ሲያስሩና ሌላም ሌላም ነገር ሲያደርጉ እኔን በእምነት ነበር ሲያሰሩኝ የነበረው፡፡ ኤምባሲውን ለመክፈት ሲሄድ ገንዘቡ በእኔ አካውንት ነበርና በወቅቱ ይዞ ለመጥፋት በራሱ የሚያጓጓ አይነት ነበር፤ ነገር ግን እኔ ሁሉን ሳከናውን የነበረው በእምነት ነው፡፡ ኤምባሲውን ከፍቼ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ፡፡

ወደ አዲስ አበባ ከተመለስኩ በኋላ ደግሞ ወደ ኒዮርክ ለስብሰባ ተላኩኝ፡፡ከዚያም በወቅቱ ጋና የነበሩት የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋን ወደሌላ ሀገር ለመላክ በመፈለጋቸው እኔን ወደ ጋና ላኩኝ፡፡ በአምባሳደርነት ሳይሆን ኤምባሲው ውስጥ እንድሰራ ነበር የተላክሁት፡፡ እኛ ኬርየር ዲፕሎማቶች ነው የምንባለው፡፡ በእርግጥ ደግሞ አምባሳደርነት እንዲሁ በቀላሉ የሚሰጥ አይደለም፡፡ የፓርቲ አባል መሆን አሊያ በሚኒስትርነት ማገልገልንም ይጠይቃል፡፡

በጋና ለሰባት ወር እንደ ሰራሁ ወደ ኒዮርክ ሂድ ተባልኩ፡፡ ኒዮርክ በአማካሪነት ተመድቤ በሄድኩበት ጊዜም በርካታ ስራዎችን ሰርቻለሁ፡፡ እውነቱን ለመናገር ኒዮርክና ብራስልስ በርካታ ስራዎችን ነው የሰራሁት፤ የሚመደቡት አምባሳሮችን ጨምሮ ሌሎችም ወደ ኤምባሲው የሚላኩት በአብዛኛው አዲስ በመሆናቸው ብዙ ቦታ ገብቼ እንድሰራ ያስገድደኝ ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡– በወቅቱ በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸም ነበር ተብሎ ይነገራልና እርስዎ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር እንዲሆኑሲመረጡ ምን ተሰማዎት?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– መናጆ ሊያደርጉኝ የፈለጉኝ ነው የመሰለኝ፡፡ ነገሮችን አድበስብሰው ለማለፍ እኔን እንደ አንድ መጠቀሚያ የፈለጉኝ ያህል ነበር የተሰማኝ:: ፓርላማው ያለ አንዳች ድምፀ ተዓቅቦ የመረጠኝ ሰውም ነበርኩ፡፡በወቅቱ በእርግጥ ለረጅም ጊዜ በውጭ ጉዳይ እንዲሁም በማማከር አገልግሎትም በዩኤንዲፒም እሰራ ነበርና ልምድ ነበረኝ፤ደግሞም የተሻለ ገንዘብም ተከፋይ ነበርኩ፡፡ በቀን ወደ 300 ዶላር አካባቢ አገኝም ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡– በተቋሙ በኮሚሽነርነት ከማገልገልዎ በፊትና ተመርጠው ስራውን ከጀመሩ በኋላ ያስተዋሉት ነገር ምንድን ነው?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– ከመጣሁ በኋላ ብዙ የሚሰሩ ነገሮች መኖራቸውን በማየቴ ስራው ያጓጓኝ ነበር:: በርካታ ነገሮችንም መስራት እንደምችል ተረዳሁ፡፡ ደግሞም ብዙዎቹን ነገሮች ማሻሻል እንደምችልም ገምቼ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ የተሰጠን የህግ ድጋፍ እንደልብ መስራት የሚያስችል ነው፤እንዲያውም ከየትኛውም ዓለም ይልቅ የተሻለ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡– እንዲያው አምባሳደር ላቋርጦትና ህጉ በሚያስቀምጠው ልክ መሮጥ ይቻል ነበር ይላሉ?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– አይቻልምእኔ እንደ መጣሁ ብዙም ሳልቆይ ተጣለሁ፡፡ ‹‹ይህን ትሰራለህ፤ያንን አትሰራም›› በሚል ማለት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡– ከእነማ ጋር ነው የተጣሉትከልካዮቹስ እነማን ናቸው?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– አይ! ከወደቁ በኋላ ስም መጥቀስ እንዳይሆን እንጂ ከእነ አቶ በረከት ጋር ነው የተጣላሁት:: እኔ የዚያን ያህል አቅም ያላቸው አለመሰለኝም፡፡ በህግ የተሰጠኝን ነገር ማስፈፀምና መፈፀም የማልችል ከሆነ ጥዬ እንደምወጣ ነገርኳቸው::

እኔ ኢህአዴግ ከመግባቱ በፊት አብዛኛውን ስራ በውጭ አገር ሆኜ ነው የሰራሁት፡፡ ስለዚህም በጉዳዩ ዙሪያ በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ እምብዛም አላውቅም:: ከእነ አቶ በረከት ጋር በተጣላሁ ማግስት ከፍተኛ የመንግስት ባስልጣናትም ሆኑ ሌሎች ተሰሚነት ያላቸው አካላት መልቀቂያ እንዳስገባ ጎተጎቱኝ፡፡ ምክንያቱም እኔ መልቀቂያ ካላስገባሁ ሊያባርሩኝ አይችሉም፡፡ መልቀቂያ አስገባ የሚል ጫና ከምቀርባቸውም ሆነ ከማከብራቸው አካላት ሲበረታ የ‹ልልቀቅ› ደብዳቤ አዘጋጀሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡– የጥላችሁ መንስዔ ምን ይሆንምን ያህልስ ጊዜ ከሰሩ በኋላ ነው ቅራኔው የተፈጠረው?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– አንድ ዓመት ከምናምን ያህል እንደሰራሁ ነው፤የቅራኔው መንስዔ ደግሞ ምርጫ 2002ን መከታተልና ሪፖርት ማቅረቤ ላይ ነው፡፡ የምከታተልበት ምክንያት ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ግዴታ በመሆኑ ነው በማለቴ ነው፡፡ እነሱ ደግሞ ‹አይደለም› በማለታቸው ነው:: በመሆኑም ይህን ማድረግ የማልችል ከሆነ በሚልና ሰዎችም ለቀህ ውጣ ባሉኝ መሰረት ልወጣ ከወሰንኩ በኋላ በዚህ መሃል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደውለው አንድ ነገር እንድስራ ጠየቁኝ:: ከዚህም አቶ መለስ ዘንድ የደረሰ አንዳች ነገር አለመኖሩንና እንደምለቅ የሚያውቁ አለመሆኑን ስረዳ ለምን ብዬ ነው ታዲያ የምለቀው በማለት በወቅቱ ‹ልቀቅ› ባዮችን ዞር በሉ አልኳቸውና ስራዬን ቀጠልኩ፡፡

አዲስ ዘመን፡– ከዛስ በኋላ በስራ ላይ ቆይታዎ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ነበርካለስ እስከምን ድረስ ነበር?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– እንዴ በጣም ነበር! ግን ህጉ አይፈቅድላቸውም፡፡ ስለዚህም ህጉ እንደማይፈቅድላቸው በመናገር መስራት ይቻላል:: ነገር ግን አሁን ደርሶ አንበሳ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ምንም አይናገሩም ነበር፤ እኔ ግን በአደባባይ እናገር ነበር:: አሁን ይህ ሁሉ አንበሳነት ከወደየት መጣ ብዬ እገረማለሁ፡፡ ስለዚህ በወቅቱ ህጉ የሚፈቀድልኝን ያህል እየተጫቃጨቅኩ ሰርቻለሁ፡፡ ህጉ የሚያሰራ ከመሆኑም በተጨማሪ የመንግስትን ጣልቃ ገብነት የማይፈቅድ ነው፡፡ ደግሞም የአንድ አገር የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ከሚሰራው የተሻለ ሰርቻለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡– የተሻለ ስራ ሰራሁ ከሚሏቸው መካከል ለአብነት የሚጠቅሷቸው ይኖሩ ይሆን?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– አዎ! በጣም ደስተኛ የምሆንበትን ስራ ሰርቻለሁ፡፡ ምን መሰለሽ እኔ የራሴ የሆነ አቋም አለኝ፡፡ ይኸውም በመጀመሪያ ደሃውንና አቅም የሌለውን ነው መርዳት ያለብን የሚል ነው:: መቆም ያለብን ከድሃው ጎን ነው፡፡ከተማ ውስጥ አንድ ሰው ሊታሰር ይችላል፡፡ በዚህ ወቅት የተለያዩ አገራት፣ተቋማትና ግለሰቦችም ይጮሃሉ፡፡

በሌላ በኩል ጋምቤላ አሊያም ጎጃም ወደ 200 ያህል ሰው ሊሞት ይችላል፡፡ ማንም ግን ግድ ሲሰጠው አይስተዋልም፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ኦሞ ውስጥ የአንድ ህፃን ጥርስ የላይኛው ክፍል ስለበቀለ ‹‹የእግዚአብሄር እርግማን ነው›› በማለት የሚወረውሩ አሉ፤ይህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው:: አንድም ሰው ስለዚህ ጉዳይ አያነሳም፡፡ ለእኔ ግን ትልቁ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እሱ ነው፡፡ ሰብዓዊ መብትን ቤተሰብ፣መንግስት እንዲሁም የትዳር አጋር ሲጥስም ጭምር እንጂ ሰው ሲታሰር ብቻ አይደለም ሰብዓዊ መብት ተጣሰ ማለት ያለብን፡፡

ህጉ ሰው ሲታሰር ብቻ ነው ሰብዓዊ መብት ተጣሰ የሚባለው አይልም፡፡ እኔ ህጉ ሲወጣም የነበርኩ ሰው ነኝ፡፡ ህጉ በኒዮርክ በኩል ነው የሚልያፈው፡፡ እኔ ደግሞ ለስምንት ዓመት ነው በኒዮርክ የሰራሁት፡፡ ስለዚህ ለኔ እዚህ እንደሚወራው አይነት ነገር አይደለም:: ምክንያቱም እዚህ ምን እንደሚሰራ አውቃለሁና ህሊናዬ አይቀበለውም፡፡ እኔ በአፌ ያስቀመጡትን ሳላኝክ ዝም ብዬ የምውጥ ሰው አይደለሁም፡፡ ከእነርሱ የተሻለ ልምድ አለኝ:: ህጉ ላይም ድርድር ሲደረግ ከእነርሱ በተሻለ ተሳትፌያለሁ፡፡ በመሆኑም እስራ የነበረው በትክክለኛውና እውነተኛው መንገድ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡– ስራዎን በትክክል እሰራለሁ በሚሉበት ወቅት እንቅፋት አላጋጠመዎትምእውነተኛ ነገር ከማይፈልጉ አካላትስአላላተመዎትምካለ ቢያብራሩልን?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– እንዴ! በየአጋጣሚው ሁሉ እላተማለሁ እንጂ፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩልሽ ልቀቅ ባሉኝ ጊዜ እምቢኝ ብያቸዋለሁ፡፡ አይሆንም ባልኳቸው ጊዜ አብረውኝ የሚሰሩ ሁለት መልካም ምክትል ኮሚሽነሮች ነበሩ፡፡ ከሁለቱ ሰዎች ጋር በጣም በመግባባት እሰራ ነበር፡፡ ስራዬን ለማኮላሽት ሲሉ ሁሉቱንም አነሷቸውና ሌሎችን አምጥተው አስቀመጧቸው፡፡ የመጡት ሰዎች በአጭሩ ስራ እንዳይሰራ የሚያስቆሙ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በስራ ሂደት ውስጥ ደግሞ መስማማት የሚባል ነገር አለ፡፡ ሶስት ሆነን ሁለቱ ከወገኑ አንድ ሁሌም ብቸኛ ነውና በሁለቱ ይዋጣል፡፡

አዲስ ዘመን፡– ሰብዓዊ መብት ተጣሰ የሚባለው ከተማ አካባቢ በሚፈፀመው እስር ብቻ የሚለካ አለመሆኑን በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍልምየሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ብለው በማሳያነት የተናገሩት ነገር አለና እርስዎ በዚህ ዙሪያ የሰሩት ስራ ይኖር ይሆን?

እምባሳደር ጥሩነህ፡– ትልቅ ነገር ሰራሁ የምለው የቱን መሰለሽ? እኔ የተወለድኩት ባላገር ውስጥ ነው:: ባላገሩ ደግሞ በጣም የሚጎዳው በፍትህ እጦት ነው:: ስለዚህም አንድ ነገር አሰብኩ፤እሱም ክፍተቱን መሙላት የሚል ነበር፡፡ለፍትህ የሚቆም አካል በየቦታው ካቆምኩ ትልቅ ስራ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ ስለዚህም የህግ እርዳታ (ሌጋል ኤይድ) የሚባል ነገር ለማቋቋም ይረዳኝ ዘንድ ወደየአንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ በመሄድ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡

ዩኒቨርሲቲዎችን የህግ ሰው እንዳላቸው ነገርኳቸውና እኔ ደግሞ ገንዘብ እንደምሰጥ ከገለፅኩላቸው በኋላ አንድ ላይ በመቆም የፍትህ ያለ የሚለውን ወገን መድረስና ጥብቅና መቆም ይቻላል ስልም አስረዳኋቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ይሁንታቸውን ስለሰጡኝ ከፈረንጆች ገንዘብ ለምኜ አመጣሁ፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ቢያንስ ሰባትና ስምንት ሌጋል ኤይድ በየቦታው መሰረተ::

ይህ ሌጋል ኤይድ ደራሽ ለሌለው አካል ማኛውንም አይነት ጥብቅና ይቆምለት ጀመር፡፡ ለዚህ ለተቋቋመው አካል ህጋዊ ፈቃድ በማስወጣት በአግባቡ ስራውን መስራት ጀመረ፡፡ ይህን የሚያደርጉት ለፍቺም ሆነ እንዲሁም ቤተሰባዊ ጉዳይና ሌላውም ቢሆን እስከመጨረሻው ድረስ እንዲሟገቱላቸው ነው የተደረገው:: ተከሳሹ መንግስት እንኳ ቢሆን ለእነዚህ አጋር ለሌላቸው አካላት ነው የሚቆሙላቸው፡፡ በዚህ አይነት ሂደት በዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ እስከ 30 ሺ ለሆኑ አካላት ጥብቅና ተቁሞ ችግራቸው እንዲፈታ ተደርጓል:: ይህ ስራ ለህሊናዬ ትልቁን ደስታ የሚሰጠኝ ተግባር ነው፡፡

ነገር ግን በዚህ ስራ ወደፊት መግፋት ብፈልግም የስራ ዘመኔ አምስት ዓመት ላይ ያበቃ በመሆኑ ስራዬን አልጨረስኩም ያስብለኛል፡፡ የእኔ ሐሳብ የነበረው በአገር አቀፍ ደረጃ በእያንዳንዱ ወረዳ አንዳንድ በጥቅሉ ወደ 500 ሌጋል ኤይድ ለመመስረት ነበር:: ይሁንና በቆይታዬ መመስረት የቻልኩት 130 ብቻ ነው፡፡የተመሰረቱትም እስካሁን በመስራት ላይ ናቸው::

አዲስ ዘመን፡– ስራዎን በሚሰሩበት ወቅት ከታዘቧቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ እነዚህን እነዚህን በሪፖርትዎ እንደዳያካትቱተብለው ያውቃሉአሊያም ይህን ብናገር ተፅዕኖ ሊደርስብኝ ይችላል በማለት በሪፖርትዎ ሳያካትቱት የቀረ ነገር ይኖር ይሆን?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– በፍፁም! እኔ የዚያ ትውልድ ሰው አይደለሁም፡፡ 72 ዓመቴ ነው፡፡ ለመዋሽትም ህሊናዬም አይፈቅድም፡፡

አዲስ ዘመን፡– ግን እኮ ወቅቱ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምበታል ይባል ነበርና እርስዎ ግን ምንም ችግር የለም ነው የሚሉን?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– እንግዲህ የያሁት ነገር እውነት ነው ወይ አላውቅም፡፡ለምሳሌ ማረሚያ ቤት እሄዳለሁ:: ማዕከላዊ እሄዳለሁ፡፡ እዛ ሄጄ ሰዎችን በምጠይቅበት ጊዜ (የሰው ስም አልጠራም እንጂ) እስረኛው ወጥቶ ሲነግረኝ የሚሰጠኝ መረጃ መልካም የሆነውን ብቻ ነው፡፡ እንዲያውም ምንም ችግር እንደሌለና የማዕከላዊ ሰዎችም መላዕክ መሆናቸውን ነው ሲያስረዱኝ የነበረው፡፡በእርግጥ መልካሙ ብቻ የመነገሩ ምስጢር ፍርሃት ሊሆን ይችላል፡፡

አዲስ ዘመን፡– ላቋርጥዎትና በወቅቱ እኮ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመኖሩ ጉዳዩ በሚመለከታቸው በተለያዩ ዓለምአቀፍተቋማትም ጭምር ይነገር ነበርና ይህን ችግር ለማውጣት አምባሳደር ጥሩነህ እስከምን ድረስ ሄደዋል ማለት ይቻላል?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– ጥሩ፤የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምንድን ነው? ለምሳሌ እኔ ሁሉም ማረሚያ ቤት ተንቀሳቅሼ ያየሁት ወዲያው ነበር፡፡ ሁሉንም ጎብኝቻለሁ፡፡ እውነቱን መቶ በመቶ ‹አይተሃል አላየህም› ብትይኝ አላውቅም፡፡ያሳዩኝን ነው ያየሁት:: በተቋሜ ውስጥ አንድ ሰው ብቻ ውር ውር ሊል ይችላል፡፡ ደካማ ሊሆንም ይችላል፤መንግስት ደግሞ ይሸፋፍን ይሆናል፡፡

በእርግጥ ያ ሁሉ ሰው ሲገረፍ የት ነበርክ የሚባል ከሆነ ማነው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲያደርስ እኔን እያሳየ የሚያከናውነው፤ አይደለም፤ ሲገረፍም እንዲሁ ነው፡፡ ተገርፏል ተብሎ የሚታሰበውም በሚጠየቅበት ጊዜ አለመገረፉን ነው የሚናገረው:: wበእርግጥ ደግሞ እውነት ተገርፏል ወይ፤እኔ እንደምታይኝ ሽማግሌ ነኝ:: ሰው ሁሉ የሚያወራውን ተቀብዬ ልጮህ አልችልም፡፡

ግን ደግሞ በወቅቱ ያደረኩትን ልንገርሽ፤ ማረሚያ ቤቶችን ዛሬ በጎበኘሁበት ወቅት ታራሚዎች የሚተኙት መሬት ላይ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ስራ ያደረኩት ፍራሽ ላይ መተኛት እንዲችሉ ነው፡፡ ታራሚዎች አልጋ ከነፍራሹ እንዲኖራው ማድረግ ችያለሁ፡፡ እንዲሁም ምግባቸው በጣም የወረደ የሚባል አይነት ነበር፤ ለምግብ ይስጣቸው የነበረው ገንዘብ እጥፍ እንዲሆን አድርጌያለሁ፡፡ ይህ ይህ ነገር ግን አይወራም፡፡

አንዳንድ ሰዎች ‹‹እስኪ አሳየን እባክህን፤ እነዚህ ድብቅ ማረሚያ ቤቶች የሚባሉትን ጠቁመን፡፡›› ይሉኝ ነበር፡፡ እኔም ይባላል እንጂ አላውቅም ነበር መልሴ፡፡

አዲስ አበባ፡እርስዎ ታዲያ የሚያውቁት ነገር ነበር እንዴ?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– እንዴ! እኔ አላውቅም፡፡ በዚህ እድሜዬም መዋሸት አልችልም፡፡

አዲስ ዘመን፡– በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ከሰብዓዊ መብት አያያዝ አኳያ እንዴት ይመለከቱታል?

አምባሳር ጥሩነህ፡– ከሰብዓዊ መብት አኳያ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር የተመጣጠነና በልኩ መሆን አለበት፡፡ በአሁኑ ወቅት ዝም ብለሽ ሰው ለቀሽ የሰው ህይወት እንዲያጠፋ ከፈቅድሽ ግን መንግስት አይደለሽም፡፡የመንግስት ዋናው ስራ የእኔን ህይወት መጠበቅ ነው፡፡ ትልልቅና ጠንካራ አቅም ካላቸው አካላት ደካማውን መጠበቅ ነው፡፡ ብሎም የእኔን ንብረት ከዘራፊዎች መጠበቅ ነው፡፡ ግብር የምንከፍለው ለዚህም ጭምር ነው፡፡

ይህንን ካልሰራ መንግስት የለም፤ሰብዓዊ መብትም የለም፡፡ ሁለተኛው የተመረጠ ብቻ ነው በህዝብ ስም ሊናገር የሚችለው፡፡ መንግስትም መብት ሊያገኝ የሚችለው ከህዝብ ነው፡፡ በገንዘብ አቅም ተቀባይነትን ማግኘት አይቻልም፡፡

አዲስ ዘመን፡– የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዴት መሆን አለበት ይላሉ?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– አሁን እያታየ ያለው መልካም በመሆኑ መቀጠል አለበት ባይ ነኝ፡፡ ነገር ግን ህግና ህግ ብቻ መከበር አለበት፡፡ መንግስትና መንግስት ብቻ መወሰን አለበት፡፡ እያንዳንዱ በየመንደሩ ከወሰነ ያስቸግራል፡፡

ይህ ህዝብ እኮ እኔ ትናንት እያየሁ እንደ እምቦሳ እየዘለለ በመሄድ አገር አትፈርስም በሚል ቅንነት ዚይድባሬን የተጋፈጠ ነው፤ የፈረሰውን አገር እንኳ እንደገና ሲያቋቁም አይቻለሁ፡፡ ስለዚህ እሱ የገነባው አገር መፍረስም የለበትም:: በመሆኑም መያዝ ያለብን በጥንቃቄ ነው፡፡ የዚህች አገር ባለቤት በገጠሪቷ የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖረው አርሶ አደሩም ጭምር እንጂ አፈኛው ብቻ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የነበራት ስኬት እንዴት ይገለፃል?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– ከፍተኛ ነው፡፡ እንዲህ ስልሽ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ረገድ ከንጉሱ አፄ ኃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ መልካም የሚባል አይነት ነው፡፡በእርግጥ በንጉሱ ዘመን ስለነበረን የዲፕሎማሲ ሁኔታ ፅፌያለሁ፤በወቅቱ ደካማ ነበርን፡፡ የኢኮኖሚ አቅም የለንም፡፡ ይሁንና የበለጠ ለማጠናከርና ተሰሚነትንም ለማግኘት ሲሉ አቅም ያለውንና የሌለውን ሰው ሁሉ የከተቱት ውጭ ጉዳይ ውስጥ ነው፡፡ የአፍሪካ አንድነት (ኤ.ዩ) ወደዚህ እንዲመጣ የተደረገበት ጊዜ ነበር:: ይህን ካደረጉ ሰዎች መካከል እነ አቶ ከተማ ይፍሩ፣ አቶ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ አቶ ምናሴ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አላደገም የሚሉ ካሉ እነርሱ ውሸታሞች ናቸው:: በእርግጥም ምንም እንኳ ችግር ቢኖርም በእኛ ደረጃ ካሉ አገሮች 90 በመቶ ያህል እንሻላለን፡፡ ለምሳሌ ናይጄሬያ በጣም ሀብታም አገር ናት፤ እኛ በዓመት የምናገኘውን እነርሱ ከቤኒዚን ሽያጭ ብቻ በወር ያገኛሉ፡፡ ግን የእኛ ህዝብ 30 በመቶው ብቻ ድሃ ሲሆን፣ የናይጄሪያ ህዝብ ግን 60 በመቶው ደሃ ነው፡፡ ይህ የአሁን መረጃ ነው፡፡የናይጄሬያ አምስት ሰዎች ያላቸው ሀብት የአገሬው ህዝብ በሙሉ ካለው ይበልጣል፡፡

በአሁኑ ወቅት በዲፕሎማሲው ረገድ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ይታያል፡፡ እኔ በገባሁበት ወቅት ግን ደካማ ነበር፡፡ በወቅቱም ብዙ ጠላቶች ነበሩን፡፡ አቅምም አልነበረንም፤ ይሁንና በፍፁም አልተንገዳገድንም፡፡

አዲስ ዘመን፡– ዲፕሎማሲው በቀጣይስ እንዴት መመራት አለበት ይላሉ?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– አሁን ትንሽ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን አያለሁ፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሪፎርም ተደርጓል፡፡ እኔ ከ30 ዓመት በላይ በውጭ ጉዳይ ሰርቻለሁ፡፡ ይሁንና በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ማማከርና ካለኝ ልምድ ማካፈል ስችል አንዳቸውም እንኳ ምንም አይነት ጥያቄ አላቀረቡልኝም፡፡

ትናንት ከትምህርት ቤት የወጡ ልጆች በኢንተርኔት ብቻ ታግዘው ሲያወሩ ነው የሰማሁት:: በዘርፉ ልምድ ካላቸውም አካላት ከተሞክሮ የሚገኝ በርካታ ነገር አለና ብንጠየቅ ያለንን ለማካፈል አንዳች የምንጠይቀው ወረታ የለም፡፡ ቢያንስ የሰሩትን ስራ አሳይተውኝ ‹ከዚህ የተሻለ ነገር አለ ወይ ምን ትላለህ› ቢሉኝ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ የበኩሌን ላደርግ እችላለሁ፤ በዘርፉ ከ35 ዓመት በላይ ልምዱ አለኝ፡፡

አንዴ ትዝ ይለኛል፤አሜሪካኖች ‹‹ኢ.ሲ.ኤ አሁን አያስፈልግምና ይጥፋ አሉ፡፡ አገራቱ የኢኮኖሚውን ሁኔታ በራሳቸው ማካሄድ ይችላሉና ምክር አያስፈልጋቸውም›› በማለት በቡድን ሰባት አባል አገራት አቀረቡ፡፡ ወቅቱ ደግሞ ገና ኢህአዴግ እንደገባ አካባቢ ነበር፡፡

ስለዚህ በሌሎች አካባቢ በኢስያና በላቲን አሜሪካ የኢ.ሲ.ኤ አይነት በመኖሩ የእነዛ አገር ዲፕሎማቶችን በየአህጉራቱ ያለውን ሊያጠፉ ነውና አንድ ላይ ካልጮህን አልቀናል አልኳቸው:: የእኛ ሰዎች ግን ካለመረዳት የተነሳ ዝም ብለው ነበር:: በወቅቱ አቶ መለስ ኒዮርክ ሲሄዱ፣ አቶ ስዩም ላቲን አሜሪካ ሄደው ነበር:: በአገር ቤት ያለው ሰው ሊመልስ የሚችል አልነበረም:: ያነጋገርኳቸው አህጉራት በሚኒስትር ደረጃ ኒዮርክ ላኩ፡፡ ለቡድን ሰባት አባል አገራት ጉዳዩን አቀረብን:: አቋምም ያዝን፡፡ ጉዳዩን ለማስፈፀም በወቅቱ እውነት ለመናገር ሰባት ቀን ወንበር ላይ አድሬያለሁ:: እኔ ገንዘብን አስቤ ሰርቼ አላውቅም፡፡ ሁሌም ቢሆን አገርን ማስቀደም ተቀዳሚ ግቤ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡– እርስዎ እንደሚታወቀው በዲፕሎማትነትም ሆነ በሰብዓዊ መብቱ ዙሪያ የሰሯቸው ስራዎች እንደመኖራቸውለኢትዮጵያውያን የሚያስተላፉት መልዕክት ካልዎት?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– ኢትዮጵያ ዛሬ አንድ ሆና እንድትቀጥል የመቻሏ ምስጢር ከአደዋ ጀምሮ እስካሁን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ በከፈሉት መስዋዕትነት መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ የዚያን ህዝብ ጉስቁልናና መስዋዕትነት ሁሌም ቢሆን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ የዜጋው የመሞት መንስዔ በሱ ሞት አገር ትቀጥል ዘንድ ነው፡፡

እኛ በገንዘብና በጥቅም አገርን መሸጥ የለብንም:: ህዝባችን ትልቅ ህዝብ እንደመሆኑ በራሳችን መቆም ይኖርብናል፡፡ ይህን ትልቅ ህዝብ ይዘን ምንም መሆን እንችላለን፡፡ ጥቅም፣ ገንዘብና ፖለቲካ እንዲሁም ሌላው ያወደሰኝ ያኛው ደግሞ ያሞግሰኝ አይነት ነገር አላፊና ትንሽ ነገር ነው፡፡ ለአገር አንድነት መስራት አለብን፡፡ እኛም ሆንን ትውልዱም ታሪክ እንዲቀጥል ማድረግ አለብን፡፡ ነፃ ህዝብና ነፃ አገር መመስረት ይጠበቅብናል፡፡

አዲስ ዘመን፡ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ::

አምባሳደር ጥሩነህ፡– እኔም በጣም አመሰግናሁ፡፡

አዲስ ዘመን ነሀሴ 7/2011

አስቴር ኤልያስ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በሳሊቫኪርና በሪክ ማቻር መካከል እያገረሸ ያለውን ቅራኔ እየተባባሰ በመምጣቱ በደቡብ ሱዳን አዲስ ግጭት እንዳያገረሽ ተሰግቷል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *