“Our true nationality is mankind.”H.G.

የምንኖርበትን ዘመን በ60ዎቹ በፃፋቸው መፃሕፍት የተነበየው ደራሲ

BBC AMHARIC – 1968 ላይ የተፃፈው ‘ስታንድ ኦን ዛንዚባር’ የተሰኘው ልብወለድ፤ ከብዙ በጥቂቱ ስለ ቫያግራ [ወሲብ አበረታች ክኒን]፣ ስለ ቪድዮ ስልክ ጥሪ፣ ስለተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ያወራል።

ይህ ልብ ወለድ መፅሐፍ የጆን በርነር ነበር፤ የሳይንሳዊ ልብ-ወለድ ደራሲው በርነር። እርሱ ይኖርበት በነበረበት ዘመን ገመድ አልባ የነበረው ነገር ያኔ አጀብ የተባለለት ራድዮ ነበር።

ጆን በርነር

በግሪጎሪጎሪሳውያን አቆጣጠር 1934 ዓ.ም. ኦክስፎርድ በተሰኘችው የእንግሊዝ ከተማ ጆን ሂውስተን በርነር የተባለ ጨቅላ ከነቃጭሉ ዱብ ይላል። ቤተሰቦቹ ‘ነብይ ልጅ ተወለደልን’ ብለው የሚደሰቱበት ወቅት አልነበረም። ዓለም በጦርነት የታመሰችበት ዘመን ነበርና።

የበርነር አያት አንዲት መፅሐፍ ነበረቻቸው። መፅሐፏን ጎናቸው ሻጥ አድርገው ካልዞሩ ሰላም አይሰማቸውም። ‘ዋር ኦፍ ዘ ዎርልድስ’ ትሰኛለች። ታድያ ይህች መፅሐፍ በርነር ገና የ6 ዓመት እንቦቃቅላ ሳለ ከእጁ ትገባለች።

በርነር፤ ከአያቱ መፅሐፍ ጋር ከተዋወቀ ወዲህ ነበር በሳይንሳዊ ልብ-ወለድ መፃሐፍት ፍቅር ቅልጥ ያለው። ዕድሜው 9 ሲረግጥ ከማንበብ አልፎ መሞነጫጨር ይጀምራል።

በ13 ዓመቱ አጠር ያለች አንድ ሳይንሳዊ ልብ-ወለድ ይዘት ያላት ፅሑፍ ለአንድ ጋዜጣ ይልካል። ‘አንት ታዳጊ ገና አልበሰልክምና አርፈህ ቁጭ በል’ የሚል ምላሽ ይደርሰዋል። ምላሹ ለበርነር የሚዋጥ አልነበረም።

በ17 ዓመቱ አሜሪካ ውስጥ ላለ አንድ ጋዜጣ ‘ዘ ዋቸርስ’ ሲል ርዕስ የሰጣትን ፅሑፍ ይልካል፤ ፅሑፏም ትታመለታለች። በርነር ይሄኔ የግል ትምህርት ቤት ተማሪ ነበር፤ ጉዞው ደግሞ ወደ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ። ‘ትምህርት ለምኔ’ ያለው በርነር አስኳላውን ትቶ ቁጭ ብሎ መሞነጫጨር ይይዛል።

ቢሆንም አንዳች ውስጣዊ ፍራቻ ሰቅዞ ይይዘዋል። ምናልባት ባይካልኝስ? ኦክስፎርድ ዪኒቨርሲቲ መማር እችል የነበርኩ ሰው እንዲሁ በዋዛ ስባትት ልኖር? የሚሉ ሃሳቦች ይመላለሱበታል።

ይሄን ብድግ ይልና በኤሌክትሪክ የምትሠራ ‘ታይፕራይተሩን’ ከፊቱ አመቻችቶ ይቀመጣል። ዘውጋቸው ሳይንሳዊ ልብ-ወለድ የሆኑ ፅሑፎችን ማምረትም ይጀምራል። ፅሑፎቹ ለተለያዩ ጋዜጣዎች የሚከፋፈሉ ናቸው።

በርነር በወጉ 25 ዓመት ሳይሞላው 80 ያክል ልብ-ወለድ ፅሑፎችን በስሙ አሳትሞ ነበር። በ14 ዓመት የምትበልጠው የፍቅር ጓደኛው ማርጆሪን ያገኛትም ጋዜጣ ላይ ‘ትዳር ፈላጊ’ የተሰኘው ዓምድ ላይ አይቷት ነው። በተገናኙ አራት ወራት ውስጥ የተጋቡት ጥንዶቹ በፍቅር ክንፍ ይላሉ።

ማርጆሪ እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ የበርነር አማካሪ፣ ወኪል እና የልብ ወዳጅ ሆና እንደቆየች ይነገርላታል።

‘ነብዩ በርነር’

ሰው ሰራሽ ልህቀት [አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ]፣ ዘረኝነት፣ ዕፅ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የሕዋ ጉዞ እና ቴክኖሎጂ የበርነር ሥራዎች ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ያላቸው ሃሳቦች ናቸው።

ሥራዎቹ ገደብ የለሽ ምስጠት የሚስተዋልባቸው ሲሆኑ አንዳንድ ልብ-ወለድ ትልሞቹ እንደው የማይሆን ነገር ተብለው ቢታለፉም በርካታ ታሪኮቹ አሁን የምንኖርበትን ዓለም ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።

1972 ላይ የፃፈው ‘ዘ ሺፕ ሉክ አፕ’ የተሰኘው ልብ-ወለድ የሰው ልጆች ቁጥር በዝቶ ምድር በሕዝብ ብዛት ስትጨናነቅ እና አካባቢ ብክለት ዓለምን ወደ መጥፊያዋ ሲያቀርባት ያሳያል።

በርነር በጭስ የታፈነች ዓለም ብሎ የፃፈው 1975 ላይ ነበር፤ ይህ ፎቶ ሕንድ ውስጥ የተነሰው ደግሞ 2017 ላይ ነውImage copyrightGETTY IMAGESአጭር የምስል መግለጫበርነር በጭስ የታፈነች ዓለም ብሎ የፃፈው 1975 ላይ ነበር፤ ይህ ፎቶ ሕንድ ውስጥ የተነሰው ደግሞ 2017 ላይ ነው

1975 ላይ የሳለው አንድ ገፀ-ባሕርይ ደግሞ ዓለም ያጨበጨበለት የኮምፒውተር ሞጭላፊ [ሃከር] ነው። በበርነር ዘመን ‘ሃከር’ ምናልባት የኪስ ቦርሳ ሞጭልፎ የሚሮጥ እንጅ ከኮምፒውተር ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር አልበረም። ኮምፒውተሩንስ ማን በውል አውቆት።

ነገር ግን በርነር ከአታሚዎቹ ጋር ሰላማዊ ግንኙት አልነበረውም። ለፅሑፉ አርትዖት ከሚሰጡ ሰዎች ጋር ይጋጭ የነበረው ደራሲው የኋላ ኋላ አታሚ እያጣ ይመጣል። የሚስቱ በሞት መለየት ደግሞ ነገሮችን ‘በእንቅልፍ ላይ ጆሮ ደግፍ’ ያደርጉበታል።

ይሄኔ ነው ሎንዶን ውስጥ የነበረውን መኖሩያ ቤት ሸጦ ወደ አንዲት የገጠር መንደር መሰደድን የመረጠው።

‘ስታንድ ኦን ዛንዚባር’

በርነር ከሚታወቅባቸው ሥራዎች ጉምቱ ያሰኘው ‘ስታንድ ኦን ዛንዚባር’ የተሰኘው ልብ-ወለድ ነው። እዚህ መፅሐፍ ላይ በ2010 የዓለም ሕዝብ 7 ቢሊዮን እንደሚደርስ በርነር ፅፏል፤ ተንብይዋል ማለቱ ሳይቀል አይቀርም። የዓለም ሕዝብ 7 ቢሊዮን መድረሱ ይፋ የሆነው 2011 ላይ ነበር።

ልብ-ወለዱ ሁለት ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ አፓርታማ ተጋርተው የሚኖሩ ሰዎችን ምናባዊ ታሪክ የሚከተል ነው። አንደኛው ነጭ ሰላይ፣ ሌላኛው ደግሞ አፍሪቃ አሜሪካዊ የንግድ ሰው። አክሎም መፃሐፉ የዓለም ኃያላን መንግሥታት ከሰው ልጆች የላቀ ዘረ-መል ለመፍጠር ሲያሴሩ ያስነብባል።

እንደ አውሮፓ ሕብረት ያለ አንድ ድርጅት እና ቻይና የአሜሪካ ተቀናቃኝ ሃገር ሆና መገኘት በበርነር ሥራዎች ውስጥ በ1960ዎቹ የተዳሰሱ ናቸው።

በርነር ሳይንሳዊ ልብ-ወለድ ሥራዎቹ የምንኖርበትን ዓለም ዓይነት ቅርፅ ይኖራቸው ዘንድ እንዲያግዘው በማሰብ የተለያዩ ክፍለ ዓለማትን ዞሮ ጎብኝቶ ነበር።

እስካዛሬ ያላየናቸው ነገር ግን በርነር የተነበያቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ወደፊትም አይፈጠሩም ብሎ መገመት ግን ከባድ ነው።

* ከላይ የተጠቀሱት ጊዜዎች ሁሉም በግሪጎሪሳውያን አቆጣጠር የተፃፉ ናቸው።

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0