“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት ውስጥ በፅኑ የሚያከራክሩ ጉዳዮች

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ውስጥ አከራካሪ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ለብሄሮች የተሰጠው መብት ነው። በአንድ ወገን ህገ መንግስቱ ለሀገራዊ አንድነት ብዙም ትኩረት ሳይሰጥ ለብሄር ብሄረሰቦች ገደብ የለሽ መብት በመስጠት ሀገራዊ አንድነት አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጓል ሲሉ፤ በሌላ ወገን ደግሞ ህገ መንግስቱ ለብሄር ብሄረሰቦች መብት መስጠቱ ለሀገራዊ አንድነት ስጋት ሊሆን አይችልም። እንዲያውም ሀገራዊ አንድነትን ያጠናክራል የሚል መከራከሪያ ይቀርባል።

ህገ መንግስቱ ለሀገራዊ አንድነት ትኩረት አልሰጠም የሚሉ አካላት ህገ መንግስቱ ለብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የመገንጠል መብት ያለገደብ መስጠቱ፤ የክልሎች ወሰኖች ከአስተዳደር መለያነት ባሻገር የሉዓላዊነት መገለጫ እንዲሆኑ መደረጉ፤ የክልሎች አወቃቀር በማንነት ላይ የተመሰረተ ማድረጉ በመከራከሪያነት ተነስቷል።

ሀገሪቱ የአንድ ህዝብ ሀገር ሳትሆን የብሄር ብሄረሰቦች ሀገር ተደርጋ መቀመጧ ለሀገራዊ አንድነት ስጋት መሆኑን ሲገልጹ በሌላ ወገን የመገንጠል መብት ያለገደብ መስፈሩ፤ የአስተዳደር ወሰኖች የሉዓላዊነት መገለጫ መደረጋቸው፤ የክልሎች አወቃቀር ማንነትን መሰረት ያደረገ መሆኑ እንዲሁም ሀገሪቱ የብሄሮች ሀገር ተደርጋ መቀመጧ ለሀገራዊ አንድነት አደጋ አይሆኑም ሲሉ ይከራከራሉ። እንዲያውም በብሄር ብሄረሰቦች መካከል መተማመን እንዲፈጠር በማድረግ ሀገራዊ አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ እንዲታነጽ የሚያደርግ ነው ሲሉ በሌላ በኩል ይከራከራሉ።

የክልሎች አወቃቀር

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 46 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ክልሎች የሚዋቀሩት በህዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፈቃድ ላይ በመመስረት እንደሆነ ደንግጓል። ለሀገራዊ አንድነት ወሳኝ የሆኑ ሌሎች ነገሮችን ወደ ጎን በማድረግ የክልሎች አወቃቀር ማንነት ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑ የህገ መንግስቱ ክፍተት ነው ብለው ከሚከራከሩ ምሁራን መካከል በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲ የህግና ፌዴራሊዝም ረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ ጥጋቡ ናቸው። የክልሎች አወቃቀሩ ማንነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ብሄር፣ ብሄረሰቦችን ለማለያየት የተሰራ ሴራ ነው ይላሉ። የማለያየት ስራ በመሰራቱ ብዙ ችግሮችም ተፈጥረዋል። በሌላ በኩል በፌዴራሊዝም ውስጥ ትልቅ ትኩረት ከሚሰጥባቸው ዋነኛው የሆነው አስተዳደራዊ አመቺነት ጉዳይ ሆን ተብሎ ወደ ጎን ተገፍቷል ሲሉ ይሞግታሉ።

ከአስተዳደራዊ አመቺነት በተጨማሪ፤ በህዝቦች መካከል ለረጂም ዘመን የነበረው ማህበራዊ መስተጋብር፤ የባህልና የሀይማኖቶች መወራረስ፤ የተገነባው የጋራ ታሪክ በክልሎች አወቃቀር ከግምት አለመግባቱ ሀገሪቱ ከፌዴራሊዝም ስርዓት ማግኘት የነበረባትን ብዙ ትሩፋቶችን እንድታጣታ አድርጓታል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ አወቃቀሩ ሀገራዊ አንድነትንም ቅርቃር ውስጥ ከቶታል ይላሉ።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ ማብራሪያ፤ አወቃቀሩ ማንነትን ብቻ መሰረት ያደረገ በመሆኑ ተመሳሳይ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች ያሉባቸውን አካባቢዎችን በአንድ ላይ ማካለል ስለሚያስፈልግ አንዳንድ ትላልቅ ክልሎች ሲፈጠሩ ሌሎቹ አነስተኛ ክልሎች ሆነዋል። ይህም በክልሎች መካከል የፖለቲካ ሚዛን አለመጠበቅና የክልሎች የአቅም አለመመጣጠን እንዲኖር የሚያደርግ ነው። ትላልቅ ክልሎች የፌዴራል መንግስትን የመቆጣጠርና ጫና ለማሳደር አቅም የሚሰጥ ነው። ክልሎች ፉክክር ውስጥ እንዲገቡም የሚያደርግ በመሆኑ ብሄራዊ አንድነትን የመርሳት፤ በመጨረሻም ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል።

በሌላ ወገን በሀገሪቱ ውስጥ ለዘመናት ከቆየው የብሄሮች ጥያቄ አንጻር የክልሎች አወቃቀር በማንነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ችግር ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም ይላሉ። አወቃቀሩ ችግር ሳይሆን እድል እንደሆነ ሊታይ ይገባል ከሚሉት መካከል በአርሲ ዩንቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ዶክተር ዳግማዊ ተስፋዬ አንዱ ናቸው። ዶክተር ዳግማዊ የረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ ሀሳብን ይቃወማሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ሀገሪቷ ለዘመናት ስትከተል በነበረው አሃዳዊ ስርዓት ብሄሮችን ሲያጋጥማቸው የነበረውን ችግር ለመቅረፍ የተሻለ ይረዳል ተብሎ ስለታሰበ በማንነት ላይ የተመሰረተ አወቃቀር ተግባራዊ ተደርጓል። ከነበሩት ችግሮች አንጻር ህገ መንግስቱ ማንነትን መሰረት ያደረገ አከላለልን መከተሉ ተገቢ ነበር። ምክንያቱም በየአቅጣጫው የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎች ነበሩ። ቋንቋቸውን የማሳደግ፣ የመንከባከብ፣ ባህላቸውን የመጠበቅ ጥያቄዎችን መመለስ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ማንነትን መሰረት ያደረገ አወቃቀር ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ብዙ ውጤቶች ተመዝግበዋል የሚሉት ዶክተር ዳግማዊ፤ ብሄር ብሄረሰቦች ቋንቋቸውን ለመማሪያነት፣ ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን ማሳደጋቸው ይኸው አወቃቀር ካስገኘላቸው ጥቅሞች ተጠቃሽ ናቸው ይላሉ። የብሄር ብሄረሰቦች ቋንቋዎች የትምህርት ቋንቋ እስከ መሆን ደርሰዋል። እነዚህ በቀላሉ ሊታዩ የሚገቡ አይደለም ይላሉ።

እንደ ዶክተር ዳግማዊ ማብራሪያ ዛሬ በአንዳንድ ልህቃን እየተነሱ ያሉ የክልሎች አወቃቀር የአስተዳደር አመቺነትንና ሌሎች መስፈርቶችን የተከተለ ሊሆን ይገባል የሚሉ ጥያቄዎች በወቅቱ ብዙም አይነሱም ነበር። በተለይም በልሂቃን ዘንድ ከማንነት ባሻገር ሌሎች ነገሮችም ከግምት መግባት አለበት የሚሉ ሀሳቦች መታየት ጀምረዋል።

ወደ ቅድመ ዘመናዊ (እርሊይ ሞደርን) ማህበረሰብ እየተፈጠረ መሆኑን አመላካች ነው። ሆኖም በመልክዓ ምድርና በኢኮኖሚ አመቺነት ላይ በተመሰረተ መልኩ ሊዋቀር ይገባል የሚሉ ጥያቄዎች እውነትም ከማህበረሰቡ የሚነሱ ናቸው ወይስ ከላይ ከልሂቃን በህዝቡ ላይ እንዲሰርጽ እየተደረገ ያለ አስተሳሰብ የሚለውን መለየት ያስፈልጋል።

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት…

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ማንኛውም ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ መሆኑን ይደነግጋል። የህግና ፌዴራሊዝም ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ ጥጋቡ ይህ አንቀጽ ለሀገራዊ አንድነት ስጋት ነው ከሚሉት መካከል አንዱ ናቸው።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ በአንቀጽ 39 መሰረት በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ 80 በላይ ብሄሮች ያለ ምንም ገደብ ሀገር እንዲመሰርቱ የሚፈቅድ ነው። ከሰማንያ በላይ ብሄር ብሄረሰቦች አንዳች በደል እንኳ ሳይደርስባቸው በህገ መንግስቱ ውስጥ የተቀመጠውን ሂደት ተከትለው ሀገር የመሆን ጥያቄ ቢያቀርቡ ያለ ማንም ከልካይ ሀገር እንዲሆኑ የሚፈቅድ ነው።

በአጠቃላይ የፌዴራልዝም ዋና ዓላማ አንድ ሀገር መገንባት ነው። ኢትዮጵያም ይህንን ስርዓት መከተል የፈለገችው አንድ ጠንካራ ሀገራ ለመገንባት ነው። አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት ዓላማ እንዳለው ህገ መንግስት ተቀምጧል። የሀገሪቱ የማህበረሰብ ክፍሎች በፈለጉበት ወቅት በራሳቸው ፈቃድ ብቻ ሊለያዩ ይችላሉ የሚል አንቀጽ የህጎች ሁሉ የበላይ በሆነ ህግ ውስጥ ማስፈሩ ብሄሮች በውስጣቸው ስጋትና ጥርጣሬ ይዘው እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ ነው። ብሄር ብሄረሶች በማንኛውም ጊዜ ሊጠይቁት የሚችሉትንና ማንም የማያስቆመው የራስን ሀገር የመመስረት መብትን ህገ መንግስት ውስጥ አስቀምጦ አብረን እንኖራለን የሚል መተማመን ሊመጣ አይችልም።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ፤ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ውስጥ የተቀመጠው የብሄር ብሄረሰቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ያሉበት ነው። አንደኛው የመገንጠል መብት በህግ መታወጁ ህገ መንግስቱ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተርና ከሌሎች ሰነዶች ጋር የሚጣረስ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ከሚገነጠለው ብሄር ወይም ህዝብ ዉጪ ያሉ ህዝቦች በተገንጣይ ህዝቦች መገንጠል ዙሪያ ምንም አይነት ድምጽ እንዳይኖረው መደረጉ ከባድ ችግሮች ናቸው ይላሉ።

ይህ ማለት መብቱን በሚጠይቀው ህዝብና በሌላው የኢትዮጵያ ህዝቦች መብቱን በሚጠይቀውና በመብቱ ዙሪያ ምንም አይነት ድምጽ የለውም እንደማለት ነው። ይህ መሰረታዊ ችግር ነው። ሀገራዊ አንድነትን አስቦ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ የነበረው ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ድምጽ እንዳይሰጥ መደረጉ ተገቢ አይደለም፡፡ የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ አንድ ማህበረሰብ የአገሬ ግዛት ነው በሚለው የሀገሪቱ አካባቢ ለረጅም ዘመናት ሲሰራ ሀገራዊ እሴቶችን እያዳበረ ኖሮ በመጨረሻ አይመለከትህም የሚባል ከሆነ ሳይንሳዊ አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ፤ የመገንጠል መብት በቅድሚያ በህግ ተፈቅዶ የሚቀመጥ ሳይሆን ነባራዊ ሁኔታ ሲያስገድዱ በዓለም አቀፍ ህጎች መሰረት ሊተገበር የሚችል ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ፤ በአንድ ብሄር ወይም ማህበረሰብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸምበት፤ የማግለል ሁኔታዎች ሲከሰት የብሄሮች የመገንጠል መብት በህገ መንግስቱ ባይፈቀድ እንኳ ቅቡል ሊሆኑ እንደሚችሉ የዓለም አቀፍ ሰነዶች ላይ መስፈሩን ያነሳሉ። የብሄሮችን መብትም በዚያ መልኩ ማስከበር ይቻላል። ነገር ግን ገና ለገና ችግሮች ይፈጠራሉ በሚል የመገንጠል መብት ማወጅ ከዓለም አቀፍ ህጎችና ልማዳዊ አሰራሮች ጋር የሚጋጭ ነው።

የታሪክ መምህር ዶክተር ዳግማዊ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ለብሄር ብሄረሰቦች የተሰጠውን የመገንጠል መብት አጥብቆ መፍራት ከአመለካከት የሚመነጭ ነው ይላሉ። ህገ መንግስቱ ሲቀረጽ የኢትዮጵያ ብሄሮች ችግር ምንድን ነው የሚለው ታይቶ ነው። በሀገሪቱ ውስጥ የብሄሮች መብት አለመከበር አንዱ ችግር መሆኑ በወቅቱ ህገ መንግስቱን ባረቀቁት አካላት ዘንድ ከስምምነት የተደረሰበት ነው። የብሄሮች መብት አለመከበር ለብዙ ችግሮች መንስኤ ነው ከሚል መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ ህገ መንግስቱ ውስጥ ለብሄሮች መብት ያለ ገደብ እንዲቀመጥ መደረጉን ያወሳሉ።

ህገ መንግስቱ ውስጥ የብሄሮች የመገንጠል መብት እንዲቀመጥ የተደረገው በመተማመን ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ አንድነት ለማጠናከር ዋስትና እንዲሆን ነው የሚሉት ዶክተር ዳግማዊ፤ የብሄር ብሄረሰቦች መብት የተከበረባት አዲስቷን ኢትዮጵያን መገንባትን ግቡ ያደረገ ህገ መንግስት ነው። ይህ እንደ ትልቅ ውጤት መታየት አለበት። ሀገሪቱ ውስጥ ከዚያ ቀደም ከነበረው ችግር አንጻር ችግሮች ዳግም ቢፈጠሩ እንኳ ለብሄሮች የመገንጠል መብትን በማጎናጸፉ ችግሮች እንዳይከሰቱ እንደ መከላከያ የሚሆን ነው።

እንደ ዶክተር ዳግማዊ ማብራሪያ፤ ሀገራዊ አንድነት ማስጠበቅ የሚቻለው ህገ መንግስቱንና የብሄሮችንና የግለሰቦችን ህገ መንግስታዊ መብቶችን በመጠበቅ፤ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ፤ ችግሮች ሲፈጠሩ በመነጋገር በመፍታት እንዲሁም የብሄር ብሄረሰቦች መብቶች እንደ አንድ አንኳር ጉዳይ በማየት ነው። የብሄሮች የመገንጠል መብት መቀመጡ ስጋት ሊሆን አይችልም።

ስለዚህ በህገ መንግስቱ ላይ አንቀጽ 39 እንደ አንድ መሰረታዊ ነገር ቢቀመጥም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በተለያዩ መንገዶች የተሳሰሩ ናቸው። በመሆኑም እስካሁን የመገንጠል ጥያቄ ያነሳ የለም። በፊት የመገንጠል ጥያቄ ያነሱ የነበሩ ቡድኖች ጭምር ሀሳባቸውን ቀይረው የብሄራቸው መብት ከተከበረ የሚገነጠሉበት ምንም ምክንያት እንደሌለ እየገለጹ ናቸው።

ይህ የሚያሳየው አንቀጹ በብሄሮች መካከል መተማመን እንዲፈጠር ማድረጉን ነው። ወደ ፊትም የሚገነጠል ሊኖር አይችልም። በመሆኑም አንቀጹ ለሀገራዊ አንድነት ስጋት ሊሆን አይችልም የሚሉት ዶክተር ዳግማዊ፤ ብሄሮች እንዲገነጠሉና ሀገሪቷ እንድትበታተን ሊያደርግ የሚችለው የብሄሮችን መብትን አለማክበር፣ ነጻነትን መግፈፍ፣ እኔ ብቻ አዋቂ ነኝ ማለት፤ ኢትዮጵያን በበላይነት እኔ ነኝ የማስተዳድራት የሚሉ አመለካከቶች ለሀገራዊ አንድነትም ስጋት ይሆናል ብለዋል።

የብሄሮች ሉዓላዊነት

አንቀጽ 8 ላይ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች እንደሆኑ አስቀምጧል። ህገ መንግስቱም የሉዓላዊነታቸው መገለጫ እንደሆነ አስፍሯል። እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ ማብራሪያ በዓለም ሁለት አይነት ፌዴራል ስርዓቶች አሉ። አንደኛው አንድ ብሄር ያላቸው ሀገራት ለአስተዳደር አመቺነት የሚተገብሩት ፌዴራሊዝም ሲሆን ባለብዙ ባህል ሀገራት ብዝሃነትን ለማስተናገድ የሚከተሉት ፌዴራሊዝም ነው።

ብዝሃነትን የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት ብዝሃነትን ለማስተናገድ የፌዴራል ስርዓትን ተግባራዊ ካደረጉት ሀገራት ሁሉ የተለየ ነው። ከህገ መንግስቱ መግቢያ ጀምሮ እኛ የህገ መንግስቱ ዳራሲዎች እኛ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች እያለ ይሄዳል። የኢትዮጵያ ህዝብ አይልም። በኢትዮጵያ ስራ ላይ የዋለው ፌዴራሊዝም ከሌሎች ሀገራት በተለየ መልኩ ብሄሮችንና ብሄረሰቦችን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት አድርጎ አስቀምጧል ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ።

ብዝሃነትን ለማስተናገድ ብሄሮችን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት አድርጎ ማስቀመጥ የግድ አስፈላጊ አይደለም ይላሉ። የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ተደርጎ መቀመጥ ያለበት የአንድ ሀገር ህዝብ ነው። በህገ መንግስቱ መሰረት ግን 80 የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች አሉ። ይህ በየትኛውም ዓለም ያልተለመደ ነው። አንድ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት እንዳለ መቀመጥ ተገቢ ነበር።

ህገ መንግስቱ በረቀቀበት ወቅትም ሆነ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ሳይሆን የአንድ ህዝብ ወይም የአንድ መንግስት ሀገር (ሀገረ ብሄር) አድርጎ ማስቀመጥ አይቻልም የሚሉት የታሪክ መምህሩ ዶክተር ዳግማዊ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች እንዳሉ የሚታይ ሀቅ ነው። ይህን በመካድ ሀገሪቷን ሀገረ ብሄር አድርጎ ለማስቀመጥ መሞከር አደጋው የከፋ ነው።

በተለይም ብሄር ብሄረሰቦች ንቃተ ሂሊና፣ መግባባት፣ ማንነታቸው መከበሩ ያስገኘላቸው ጥቅም ከተረዱበት በኋላ የሀገሪቱ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት አንድ አካል እንዲሆን በማድረግ ወደ አሃዳዊ ስርዓት ለመመለስ መሞከር አይቻልም ይላሉ። የአንድ ህዝብ ወይም ብሄር ሀገር አድርጎ ለመሳል ጥረት ማድረግ ከባድ ነው።

የክልሎች ወሰን…

በህገ መንግስቱ ላይ ቅሬታ የሚያቀርቡ አካላት ህገ መንግስቱን ከሚተቹባቸው ጉዳዮች አንዱ የክልሎች ወሰን የአስተዳደር ግዛት መለያ ሳይሆን የሉዓላዊነት መስፈርት መደረጉ ነው ይላሉ። የህግና ፌዴራሊዝም ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ፤ የፌዴራሊዝም ዋነኛው ዓላማ ክልሎችና ማዕከላዊ መንግስት ሚዛናቸውን ጠብቀው እንድሄዱ ማስቻል ነው። ሁለቱ ተመጣጥነው ካልሄዱ ወይም አንዱ አሸንፎ ከሄደ ፌዴራሊዝም አለ ለማለት ይከብዳል።

የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ውስጥ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ተደርገው የተቀመጡት ብሄር ብሄረሰቦች ቢሆኑም ክልሎችም ራሳቸውን ሉዓላዊ አድርገው መመልከት ጀምረዋል። የክልሎች ወሰኖችም የአስተዳደር መለያ ሳይሆን የሉዓላዊነት መገለጫ ተደርገው እየታዩ ናቸው።

በፌዴራል ስርዓቱ ውስጥ የፌዴራል መንግስቱ የማስተባበር ስልጣን ብቻ ነው ያለው። የፌዴራል መንግስቱ የማስተባበር አቅሙን ካጣ አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ፤ ሉዓላዊ ስልጣን ተከፋፍሎ መቀመጡ ሀገሪቱን አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ተብሎ እንዳይጠራ ያደረገ፤ ለአንድ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ለአንድ ማህበራዊና እንዲሁም ወደ ፊት ለአንድነት ስራ እንዳይሰራ ትልቅ ገደብ የጣለ መሰረታዊ ችግር ነው። ክልሎች ራሳቸውን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት አድርገው መመልከት በመጀመራቸው ድንበርና ማንነት ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆኑ መጥተዋል።

የክልሎች የአስተዳደር ወሰን የሉዓላዊነት መስፈርት መሆናቸው አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር ወይም ሀገራዊ አንድነት ለማምጣት አዳጋች ያደርገዋል የሚለው ስጋት ከአመለካከት የሚመነጭ ነው በማለት የረዳት ፕሮፌሰሩን ሀሳብ የሚሞግቱት የታሪክ ምሁሩ ዶክተር ዳግማዊ፤ የሀገራዊ አንድነት መሰረቱ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ናቸው፤ ብሄር ብሄረሰቦቹ የሚኖሩባቸው ክልሎች ናቸው ይላሉ። ብሄር ብሄረሰቦች የሚኖሩባቸው ክልሎች ሉዓላዊነታቸውን ሀገራዊ አንድነትን ማረጋገጥ የሚቻለውም እነዚህ ብሄር ብሄረሰቦች ሉዓላዊነታቸውን አረጋግጠው ለሀገራዊ አንድነት በጋራ ሲሰሩ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

ክልሎች የራሳቸውን ሉዓላዊነት አስከብረው የጋራ ፌዴራል ስርዓትን እንዲገነቡ የፌዴራል ስርዓትን መከተል ማስፈለጉን የሚያነሱት ዶክተር ዳግማዊ፤ የክልሎች ሉዓላዊነትን እውቅና አለመስጠት ከስጋት የሚመነጭ ነው። ነገር ግን መሆን የለበትም። የክልሎችንና የብሄር ብሄረሰቦችን መብትና ሉዓላዊነት እውቅና ያለ መስጠትና በተንሸዋረረ እይታ የማየት ሁኔታ የሀገር አንድነትን ሰበብ በማድረግ የሚካሄደው ሂደት በብሄር ብሄረሰቦች አለማመን ነው። ብሄር ብሄረሰቦች የሚጠቅማቸውን ያውቃሉ፤ ሉዓላዊነታቸውም እስከ የት እንደሆነ እንዲሁ ያውቃሉ። የክልሎችን ሉዓላዊነት አለመቀበል የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ካለመገንዘብ የሚመነጭ ነው ሲሉ ያብራራሉ

እንደ ዶክተር ዳግማዊ ማብራሪያ፤ የሀገራዊ አንድነት መሰረቱ ብሄሮች መሆናቸውን በመዘንጋት ሀገራዊ አንድነት በተወሰኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የሚቀነቀን አስተሳሰብ ተደርጎ የሚታይ ከሆነ አስቸጋሪ ነው። የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ ለመኖር የጋራ ሰነድ ጽፈዋል፤ የኢትዮጵያ ብሄሮች የጋራ አንድነት አላቸው። አሁን በየቦታው እየተነሱ ያሉ የማንነት፣ የድንበርና የጥቅም ጥያቄዎች የልማት ጥያቄዎች ናቸው። ለአንድነት ስጋት የሚሆኑ አይደሉም።

ብሄሮች የሚያነሱት የሉዓላዊነት ጥያቄ ኢትዮጵያን ይበታትናታል የሚለው ስጋት የተጋነነ ነው የሚሉት ዶክተር ዳግማዊ፤የብሄሮች ወይም የክልሎች ሉዓላዊነትና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚደጋገፉ እንጂ የሚገፋፉ አይደለም። የክልሎች ሉዓላዊነት እንዲያውም ኢትዮጵያዊነትን ይበልጥ ያደምቀዋል፤ ያፈከዋል ሲሉ ዶክተር ዳግማዊ ይሞግታሉ።

አሁን ካሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የተነሳ ብሄሮች የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን እያነሱ ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች ግን የመበታተን ጥያቄዎች አይደሉም። የመበታተን ጥያቄዎች ናቸው የሚል ስያሜ በራሱ ጥሩ አይደለም። እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች የጋራ አንድነትን የበለጠ የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ያብራሩት ዶክተር ዳግማዊ ብሄሮቹ እያነሱ ያሉትን ጥያቄዎችን በመመለስ የተሻለ ሀገራዊ አንድነትን ማምጣት እንደሚቻል ያብራራሉ።

መፍትሄ

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ ማብራሪያ፤ በክልሎች አወቃቀር ላይ ከማንነት ባሻገር ያሉ ነገሮች እንዲካተቱ መደረግ አለበት፤ በክልሎች መካከል የሚስተዋለውን ሚዛኑን ያልጠበቀ የሀይል አሰላለፍ የሚጠብቅ የፌዴራል ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፤ ልዩነቶችን ማንነትን መሰረት ባደረገ ክልል አወቃቀር ሳይሆን የተመጣጠነ የምርጫ ስርዓቶችን በመከተል ልዩነቶችን በምርጫ ማስተናገድ ያስፈልጋል።

እንደ ዶክተር ዳግማዊ ማብራሪያ፤ በአንዳንድ ልሂቃን የሚነሱ ሀሳቦችን መሰረት በማድረግ ህገ መንግስቱንና ክልሎችን ሙሉ በሙሉ በማፍረስ በአዲስ መልክ ለማዋቀር መሞከር እጅግ አደገኛ ነው። በርካታ መዘዞችንም ይዞ ሊመጣ ይችላል። መፍትሄ ሊሆን የሚችለው በህገ መንግስቱ ዙሪያ የሚነሱ አንዳንድ ክፍተቶችን እየሞሉ፤ ችግሮችን እየፈቱ፤ መካተት ያለባቸውን በማካተት ህገ መንግስቱና ፌዴራል ስርዓቱ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል።

አዲስ ዘመን ነሀሴ 9/2011

መላኩ ኤሮሴ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ
0Shares
0