ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ተግባር !! የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት ያስገነባቸው አራት ትምህርት ቤቶች በመስከረም ስራ ይጀምራሉ

አዲስ አበባ፡- የአይነስውራን ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት ከሚገነቡት 21 ትምህርት ቤቶች ውስጥ አራቱ በነሀሴ ወር መጨረሻ ላይ ግንባታቸው ተጠናቆ ለመጪው ዓመት ተማሪዎችን የሚቀበሉ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ፈንታ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተገነቡትና ሊበን ጭቋላ፣ ጉጂ፣ ጃኮና ሎዛ ማርያምየተባሉት አራት ትምህርት ቤቶች ግንባታ ከ80 እስከ 87 ከመቶ የደረሰ ሲሆን በዚህ ክረምትም ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባሉ፡፡

አራቱ ትምህርት ቤቶች በመጪው የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተማር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሉቀን ለተማሪዎቻቸውም የደንብ ልብስና ቦርሳ የሚበረክትላቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ጅግጅጋ ቁጥር አንድና ሁለት፣ አፋር፣ አሶሳ፣ መተከል፣ አዌ ጉዴና፣ ጋምቤላ፣ ዋግህምራና ሽሬ ትምህርት ቤቶችን በመጪው ዓመት ለማጠናቀቅ ግንባታቸው እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በመጪው ዓመት ግንባታቸው ከሚጀመሩት ትምህርት ቤቶችም የደባርቅ፣ ሸካ፣ደቡብ ኦሞና ጌዲዮ ትምህርት ቤቶች የግንባታ ጨረታ የተጠናቀቀ መሆኑንና የደባርቅ ትምህርት ቤትም በመጪው ዓመት ተጠናቆ ወደ ስራ የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹ የሚገነቡት በሁሉም ክልሎች ሲሆን፤ በተለይም የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ሁለተኛ ደረጃ እንዳይሄዱ የቦታ ርቀት እንቅፋት በሆነባቸው አካባቢዎች እንደሆነ አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል።

ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው በመላው አገሪቱ በ304 ሚሊዮን 832 ሺህ 244 ብር ወጪ 20 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እና በ400 ሚሊየን ብር ደግሞ አንድ የአይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ለማስገንባት ከወራት በፊት የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸው የሚታወስ ነው።

አዲስ ዘመን ነሃሴ 13/2011

ጌትነት ምህረቴ

Related stories   የዓለም ጤና ድርጅት ለቻይናው ክትባት ይሁንታውን ሰጠ