ኢትዮጵያና አሜሪካ የሕግ ማስከበር እና የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱ ዝርዝር መረጃ ባይቀርብበትም አሜሪካ አገር ከፍተኛ ሃብት ይዘው የገቡና ያከማቹ፣ እንዲሁም ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ አካላትን ወደ ህግ ለማቅረብ በይፋ ለተጀመረው እንቅስቃሴ ህጋዊ መስመር ለማስያዝ የተደረገ ውል እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ገልጸዋል።

ስምምነቱንም የፈረሙት የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሀት ካሚል እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይኖር ናቸው። ቀደም ሲል ዶክተር አብይ በፓርላማ የተናገሩትን ቃል በቃል በመድገም አምባሳደሩ አገራቸው ህግን ከማስከበር አንጻር ከኢትዮጵያ ጋር አብራ አንደምትሰራ መናገራቸው አይዘነጋም።

የአሁኑ ስምምነት ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ለፌደራል ፖሊስ እንዲሁም ለፍትህና ሕግ ማስከበር አካላት ድጋፍ በመስጠት የሕግ ማስፈጸም እና የፍትሕ ዘርፉን ለማሻሻል ያለመ መሆኑንም የሰላም ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል። ይሁን እንጂ ” የሕግ ማስፈጸም” ሲል ምን ምን ጉዳዮችን እንደሚያካትት አላብራራም።

ስምምነቱን ተከትሎ ተቃውሞ ያቀረቡ ወገኖች በማህበራዊ ገጾቻቸው ” ምን አገባት” ሲሉ አሜሪካንን ሲወቅሱ፣ ጉዳይ በቀላል የሚታይ እንዳልሆነና በእርጋታ ውጤቱን ማየት እንደሚሻል በመጥቀስ ድጋፋቸውን የሰጡ አሉ። ” ምንክንያቱን እግዚአብሄር ይወቀው” ሲሉም በለሆሳስ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አካሄድ ያስገረማቸውም አልታጡም። የሰላም ሚኒስትሯ ” ጥፍርና ጥርስ አውጥተዋል። ዝምታ የለም” ሲሉ በቅርቡ ስርዓት በለቀቁ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቃቸውም አይዘነጋም።

ፎቶ ፋና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *