“Our true nationality is mankind.”H.G.

አይ የኛ ፖለቲካ? የኢህአፓና መኢሶን ሽኩቻ ማንን ጠቀመ?

የኢህአፓና መኢሶን ሽኩቻ ማንን ጠቀመ? (በድጋሚ የተለጠፈ፣ ከተወሰኑ ማስተካከያወች ጋር) 

ይሄን ጽሁፍ ቀደም ሲል ለጥፌዉ ነበር። ምን ያክሉ ሰዉ አንቦ ግንዛቤ ወስዶበት እንደነበር ግን አላዉቅም። ብቻ ጽሁፉ የአማራ ፖለቲካ ሊገባበት የሚችለዉን ቅርቃር ቀድሞ የተነበየ ነበር። ነገር ግን ሰሚ በመጥፋቱ ፣ እነሆ ዛሬ ቅርቃር ዉስጥ ገብተናል።

ለሁሉም ይሄ ጽሁፍ፣ ገና በአየር ላይ ቢቆይ ሂወት እንደሚኖረዉ ስላመንኩ፣ ጓደኞቸ እንደገና በጥሞና ታነቡት ዘንድ፣ የተወሰኑ ነጥቦችን ጨማምሬ እንደገና ለመለጠፍ ወደድኩ። አንቡት።

በአገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች ታሪክ ዉስጥ፣ የደርግ፣ ኢህአፖና መኢሶን ነገር መቸም አይረሳም። ሶስቱም የርስበርስ መጠፋፋት ጥሩ ተምሳሌቶች ናቸዉ። በወቅቱ አብዮቱን ለማስቀጠል ከደርግ ይልቅ፣ ኢህአፓና መኢሶን የተሻለ እድል እንደነበራቸዉ ይነገራል። ነገር ግን በተለይም መኢሶንና ኢህአፓ፣ ተባብሮ ከመስራት ይልቅ፣ መደማመጥ እንኳን የማይችሉ ድርጅቶች ሆነዉ አረፉት። ይህ አለመደማመጥም ከከፋ ጫፍ አድርሶ፣ሁለቱ ድርጅቶች እርስ በርስ ለመጠፋፋት ከመሞከራቸዉም በላይ፣ አንዱ ወገን ከደርግ ወግኖ ( በዚህ በኩል መኢሶን ነዉ የሚታማዉ ) ሌላዉን ለማጥፋትና ማስጠፋት ተንቀሳቀሱ።

ደረግ የሁለቱን ድርጅቶች አለመግባባት በሚገባ ተጠቀመባት። መጀመሪያ ላይ ሁለቱንም ድርጅቶች እንደ ስጋት ይመለከታቸዉ የነበረ ቢሆንም፣ ሁለቱ ሲጋጩለት ደግሞ፣ አንዱን እንደመሳሪያ በመጠቀም ሌላኛዉን(ኢህአፓን ) ለማጥፋት/ ለማዳከም እድሉን ተጠቀመበት። አያ ደረግ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ኢህአፓን እንዳይሆኑ አደረገዉ። መጨረሻ ለይ ደግሞ መኢሶንንም እንዳይሆኑ አድርጎ በላዉ። ከዚህ በሁዋላ፣ እድሜ ለመኢሶንና ኢህአፓ እንጅ ፣ ደርግ ለጊዜዉ በአገሪቱ ብቸኛዉና ሁነኛ ተቀናቃኝ አልባዉ ሀይል ሁኖ መዉጣት ቻለ። ደርግ ኢህአፖና መኢሶን በሰሩት ስህተት ተጠቅሞ ፣ ስልጣኑን ያደላደለ፣ ለ17 አመታት አገራችንን ክፉኛ አበሳቆላት። ደርግን ለዚህ እንዲበቃ/ ያበቁት ኢህአፓና መኢሶን፣ ዛሬም ድረስ ለሰሩት ስህተት በታሪክ ይወቀሳሉ፣ ገናም ሲወቀሱ ይኖራሉ። 

አሁን ላይ የአማራ ፓለቲካና ፖለቲከኞች፣ የመኢሶንንና የኢህአፓን ታሪክ እንዳይደግሙት እጅጉን እፈራለሁ። ዛሬ ሁሉም በአማራ ስም የተደራጁ ሀይሎች ከተቻለ ወደ አንድነት የሚመጡበት፣ ካልተቻለ ደግሞ ተቀራርበዉ ለጋራ ጉዳይ በጋራ የሚቆሙበት ወቅት እንጅ በትልቁም በቲንሹም ነገር መካሰስ የሚገቡበት ወቅት መሆን አልነበረበትም። ጊዜ ሲገኝ የሚፈታዉን ነገር ለጊዜ ሰጥቶ፣ አሁን ወሳኝ በሆኑ የአማራ ህዝብ ጥያቄወች ላይ ብቻ ማትኮር ይገባ ነበር።

አሁን ዛሬ እየታየ ያለዉ ሁኔታ፣ ትልቁ ቁምነገር ወሳኝ አማራዊ ጥያቄወች ላይ መሆኑ እየቀረ በደራሽና ወቅታዊ ፈተናወች/ ችግሮች መጠመድ ላይ ሁኗል። ይህ መሆኑም ባልከፋ ነበር። ችግሩን እያከፋዉ ያለዉ ነገር፣ የልዩነት እንቅስቃሴወቻችን ፣ ዉስጣዊ አንድነታችንን የሚጎዱ እየሆኑ መታየታቸዉ ነዉ። አሁን ትግሉ በመንግስትንና ህዉሀት ላይ ጫና ፈጥሮ የአማራን ወሳኝ ጥያቄወች (በተለይም የህገ መንግስት፣ ወሰንና ማንነት ጥያቄወች )እንዲመለሱ መስራት ላይ ሳይሆን፣ የራሳችንን የዉስጥ አቅም በሚያዳክም መልኩ መጓዝ ሁኗል። እጅግ ያሳዝናል። ብዙ ዋጋ የተከፈለበት አማራዊ ትግልና አንድነት ፣ በብቁና አቃፊ፣ አስተዋይና አርቆ ተላሚ መሪ መጥፋት ምክንያት፣ለጊዜዉም ቢሆን እንዲህ ተሽመድምዶ ማየት እጅግ ያናዳል። 

አሁን ወቅቱ ነገርን መሸፋፈን አይፈቅድልንም። ከገባንበት ቅርቃር ለመዉጣት ቸኛዉ መፍትሄ ሀቅን መዳፈር መጀመር ነዉ። ለዚህም የመጀመሪያዉ ጉዳይ፣ በአሁን ጊዜ ፣ ከዋናዉ አጀንዳችን በሚያስወጣን ጉዳይ እየተጠመድን መሆኑን ማመን ነዉ ። ሁለመናችን፣ ማን መጣ፣ ማን ሄደ፣ ለምን ይመጣል፣ ማን ታሰረ፣ ማን ተፈታ… ወዘተ የሚል ነገር ዉስጥ እየገባን ነዉ።

እኛ መተማመን ያለብን፣ በምንገነባዉ ብሄርተኝነት እና በጥያቄወቻችን ትክክለኛነት ላይ እንጅ ማንም ሰለመጣና ሰለሄደ፣ ግለሰቦች በስህተትም ቢሆን ስለተፈቱና ስለታሰሩ መሆን አልነበረበትም። እዉነትን በጃችን ሰናስገባ፣ሁሉም ይገለጥ ነበር።

ሌላዉ ችግር፣ ለኛ ድክመት ሌሎችን ማሳበብያ ከማድረግ ዛሬም አልተላቀቅንም። የብሄርተኝነት ግንባታችን ዋነኛ የችግር ምንጮች ሌሎችን አድርጎ መዉሰድ ዛሬም አልቆመም። ይህ ትክክል አይደለም።፤ ዛሬም እደግመዋለሁ፣ የኛ ችግሮች ዋነኛ ምንጮች እኛዉ ነን!! ይሄን ሀቅ ከተቀበልንና ለመፍትሄ ከተዘገጀን ብቻ እናገግማለን። የኛ የብሄርተኝነት ግንባታ ጎምርቶ መዉጣት ያለበት በሌሎች ተፈትኖና አሸንፎ እንጅ አንዲሁ ያለ ፈተና መሆን የለበትም ብየ አምናለሁ። ተፈትኖ ያላሸነፈ ትግል ለጊዜዉ በለስ ቢቀናዉ እንኳን፣ ብዙ ሊጓዝ እንደማይችል ግልጽ መሆን አለበት።

ስለሆነም፣ የአማራ ብሄርተኝነት ሊፈትኑት በሚፈልጉ አካላት ሁሉ ተፈትኖ እና አሸንፎ መዉጣት ያለበት ስለመሆኑ ስምምነት ሊያዝበት ይገባል። በዚህ መልኩ ያልተገነባ ብሄርተኝነት ደግሞ የእምቦይ ካብ ከመሆን አይድንም። ወይ ባልጀመርነዉ እንጅ፣ ከጀመርነዉ ደግሞ፣ ብሄርተኝነታችን እንዲህ እንዲሆን አንፈልግም። ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ ከፈለግን ደግሞ፣ መጠላላፍ ሳይሆን መደማመጥና አብሮ መስራት ያስፈልጋል። fb ተመቸኝ ተብሎ ፣ የሆነ ያልሆነ ነገር እየመዘዙ ሲቀባጥሩ ከመዋል መቆጠብን ይጠይቃል።

ስለሆነም፣ እዉነትም የአማራ ህዝብ አጀንዳወች፣ አጀንዳወቻችን ከሆኑ፣ አሁን እየገባንበት ካለዉ የርስበርስ መካሰስ ወጥተን ፣ በወሳኝ ጥያቄወች ላይ እናትኩር፣ የማያስማሙን ነገሮች ካሉ ቀን ሲገኝ እንፈታቸዋለን፣ አሁን ጊዜ የለም፣ እኛ ሳበዉ ጉተተዉ ስንባባል፣ እነ እንቶኔ አሻግረዉ እያዩንና እየሳቁብን፤ የራሳቸዉን ሽምጥ እየጋለቡ ነዉ።

የነገን ለነገ ትተን ለዛሬዉ በጋራ እንቁም፣ ዉስጣዊ አቅማችንን አናምክነዉ። ነገሮች እጅግ ፈጣን በሆነ ሁኔታ እየተቀያየሩ ነዉ። አማራዊ አንድነት ከመቸዉም ጊዜ በላይ አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። እንዲህም ሁነን መገኘት አለብን፣ ያለ በለዝያ ዉሀ ሲወስድ እያሳሳቀ ነዉ!! ይባላል። እርስ በርስ ስንካሰስ እና ስንሰዳደብ የምንዉልበትን ጊዜ፣ አቅም፣ገንዘብና ችሎታ፣ መግባባትና መተባበር ስለምንችልበት ሁኔታ እንጠቀምበት።

ማሳሰብያ:- ለአዴፓና አብን!!!!!!!!

ከይቅርታ ጋር አንድ ነገር በድፍረት ልወርፋችሁ ነዉ። ከተቀየማችሁ የራሳችሁ ጉዳይ፣ ነገ ነገሩ ሲገባችሁ ታመሰግኑኛላችሁ። ነገሩ እንዲህ ነዉ!
አሁን ያለዉን የሁለታችሁን ወቅታዊ ሁኔታ ሰገመግመዉ፣ የመኢሶንንና ኢህአፓን ታሪክ፣ ቢያንስ በአማራ ክልል የምትደግሙት ይመስለኛል። ማን በመኢሶን? ማን በኢህአፓ ሊመሰል ይችላል? ፈልጉት። የኔ ወቅታዊዉ እዉነተኛ ስሜት ግን ይሄዉ ነዉ። ብቻ ሟርት ሆኖ ይቅር በሉኝ።

ለምን እንዲህ ምርር ብየ እናገራለሁ? ምክንያት አለኝ። ይሄዉም በሁለታችሁ መካከል ያለዉ ወቅታዊ ሁኔታ አልጣመኝም። በተለይም የሰኔ 15 ጉዳይ ሁለታችሁ እንደ አንድ አማራዊ ሀይል በአንድ ለመቆም ያስቻላችሁ ስለመሆኑ ሲበዛ እጠራጠራለሁ። በዚህ ወቅት ታሳሪና አሳሪ ሆኖ መገኘት፣ ነገ ነገሮች ወደየት ሊያመሩ እንደሚችሉ ፣ ለአንድ ፖለቲከኛ ነገሮችን ለመተንበይ ምርምር አያስፈልገዉም። ስለሆነም በጋራ ቁሙ፣ መተማመን ፍጠሩ፣ ችግር ካለ ሁለታችሁም ስትምሉበት ለትምሉበት ህዝብ ይፋ አድርጉት። ህዝባችን ችግሩን ይፈታዋል።

እንዲሁም”የአማራ አክቲቪስት”ነን ለምትሉ። ሚኪ አማራ እንኳን የለሁበትም ብሏል። ሌሎቻችሁስ? ናችሁን? “አይነጋም መስሏት…. አለች” ይባላል። እረፉ። ነገ ሁሉም ሲገለጥ ለምታፍሩበት ነገር ባትሳሳቱ ጥሩ ነዉ። የማያልፍ ጊዜና መከራ የለም። ያልፋል። ከቻላችሁ ስለ አማራዊ አንድነት ሰበኩ፣ ካልቻላችሁ ከfb ዉጡና የግል ስራችሁን ሰሩ። አንዳንዱ እኮ fb ላይ ካልጻፈ ሌላ የኑሮ መሰረት ያለዉ አይመስልም።

ለወጣቶቻችን:- ራሳችሁንና የአማራን ህዝብ ብቻ ሁኑ። የማንም እርባና የለሽ አጀንዳ ማራገፍያ ላለመሆን የቻላችሁትን ሁሉ ጣሩ። የልጅ ታላቅ ሁኑ። ዛሬ ላይ ሁናችሁ ነገን ተመልከቱ።

አበቃሁ!!!!!

ቸር ሰንብቱ!

Chuchu Alebachew
0Shares
0