“Our true nationality is mankind.”H.G.

ለትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ተግባራዊነት የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል

 በተለያየ ዘመን የኖሩ ፈላስፋዎች፣ የስነ ጽሁፍ ሰዎችና የትምህርት ባለሙያዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ወዘተ ትምህርት ምንድ ነው? ለሚለው የተለያየ ብያኔ ሰጥተዋል፡፡ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንትና የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ‹‹ትምህርት ማለት እጅግ ሃይለኛው አለምን የመቀየሪያ መሣሪያችን ነው›› ብለውታል፡፡ እአአ ከ1844 እስከ 1922 የኖረው ፈረንሳዊ ጸሃፊና ገጣሚ አናቶሌ ፍራንስ ደግሞ ‹‹ትምህርት ማለት ምን ያህል ሸምድደን በእምሮአችን ይዘነዋል፣አለያም ምን ያህል የመጻህፍትን ክፍሎች አንብበናል ሳይሆን የምናወቀውንና የማናውቀን ምን ያህል መለየት ችለናል የሚለውን መመለስ የሚያስችል ነው›› ሲል ገልጾታል፡፡

በትምህርት ቤቶች የሚሰጥ ትምህርት ዋነኛ ግብ ያለፉት ትውልዶች ያደረጉትንና የተማሩትን ብቻ መድገም ሳይሆን ተማሪዎች አዳዲስ ነገሮች መስራትና ማበልጸግ እንዲችሉ ብቁ ማድረግ መቻል መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም ሃገራትና መንግስታት እንደየሃገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ ማሳካት የሚፈልጉትን ግብ ታሳቢ በማድረግ የትምህርት ስርዓት ቀርጸው ይሠራሉ፡፡ በዚህ ስርዓት የሚማሩ ተማሪዎችም አለምን ለመቀየር፣ ክፉና ደጉን ለመለየት፣ ሃገርንና ህዝብን ወደ ብልጽግና ለመምራት፣ ስነምግባሩ የተጠበቀ ማህበረሰብ እንዲኖር ለማደረግ፣ ወዘተ በእውቀትና ክህሎት ይታነጻሉ፡፡

በሃገራችንም ዘመናዊ ትምህርት ከተጀመረ አንስቶ በርካታ ምሁራን ማፍራት ተችሏል፡፡ እነዚህ ምሁራን በየዘመናቸው የየራሳቸውን ስራ ሰርተዋል፤ እየሰሩም ነው፡፡ እነዚህ ምሁራን ለማፍራትም ወቅቱና ሁኔታው የሚፈቅደው ስርዓተ ትምህርት ተተግብሯል፡፡ አሁን በስራ ላይ ያለው ስርዓተ ትምህርትም ሃያ አራት አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህ ስርአተ ትምህርት ስኬትም ውስንነቶችም ነበሩት፡፡ ስኬቶቹን ለማስቀጠል ውስንነቶቹን ደግሞ ለመቀነስ እኤአ 2030 ድረስ የሚተገበር የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ተጠናቆ ለትግበራ ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡

በስራ ላይ የቆየው የትምህርት ስርዓት 4ሺ የነበሩትን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወደ 39 ሺ፣278 የነበሩትን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወደ 3ሺ300፣ 16 የነበሩትን የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ወደ 1ሺ546፣ ሁለት የነበሩትን ዩኒቨርሲቲዎች ወደ 50 እንዲሁም 2 ሚሊዮን የነበሩትን ተማሪዎች ወደ 28 ሚሊዮን ማሳደግ አስችሏል፡፡ ይህ በመንግስት ብቻ በተሰራ ስራ ነው፡፡ በእነዚህ አመታት በትምህርት የተገኘው ውጤት ሃገሪቱ ለተከታታይ አመታት ላስመዘገበችው ባለሁለት አሃዝ ኢኮኖሚያዊ እድገት፣በጤናው ዘርፍ ለተገኘው ስኬት፣ወዘተ. የራሱ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ይህ ስኬት እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ውስንነቶችም ነበሩበት፡፡

በትምህርት ተደራሽነት ላይ አበረታች ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም፣ በትምህርት ጥራቱና አግባብነቱ ላይ ገና በርካታ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች መኖራቸዉን መንግሥት፣ የትምህርት ባለሙያዎችና የማህበረሰብ አባላት በተለያዩ መድረኮች ሲያነሱና ሲጽፉ ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል። ከውስንነቶቹ መካከል የተማሪዎች መሰረታዊ ክህሎትና እውቀት አለመያዝ፣ ተመርቀው ሲወጡም የብቃትና ክህሎት ውስንነት መኖር፣ የተግባቦትና የምክንያታዊነት ክህሎት  ውስንነት፣ ሀገር አቀፍና አለምአቀፋዊ ጉዳዮችን ያለማወቅና ያለመረዳት፣ የስራ ፈጠራ ዝግጁነትና ተነሳሽነት ጉድለት እንዲሁም የስነ ምግባርና ግበረገብነት ህጸጾች መታየታቸው ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደ ጥናት ተለይቷል፡፡

ስለሆነም በዚሁ መሠረት ቀጣይ የትምህርት ሥርዓቱ እንዲሻሻል በመታመኑ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ጥናት ተካሂዶ በሰነዱም ላይ በሀገር ደረጃ (በሁሉም ክልሎች፣ ከተማ መስተዳድሮችና በፌዴራል ባሉ ሴክተሮች) ከምሁራን፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ከሕዝብ ጋር ግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ በሁለንተናዊ እድገታቸው የበቁና የላቁ ዜጎችን ማፍራት እንዲቻልም የትምህርት ስርኣቱ ከአደረጃጀቱ ጀምሮ ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ መፈተሽና መሻሻል እንዳለበት ዝርዝር ምከረሃሳቦች ቀርበዋል፡፡

በምክረ ሃሳቡ መሰረትም ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህ ፍኖተ ካርታ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ በክህሎትና እውቀት፣ በስነ ምግባርና ግብረ ገብ እንዲሁም በስራ ፈጠራ ዝግጁነትና ተነሳሽነት፣ በተግባቦትና ምክንያታዊነት ክህሎት ብቁ ዜጋ ለማፍራት የሚያስችል ነው፤ እስከ 2022 ዓ.ም/እኤአ 2030/ የሚተገበር ነው፡፡ ስለሆነም ውጤቱ በሂደት የሚታይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የሁሉም ድጋፍና ርብርብም ይፈልጋል፡፡

የትምህርት ፋይዳው ዜጎችን በማህበራዊ፣ ስነ-ባህሪያዊ፣ አካላዊ፣ መንፈሳዊ፣ ሙያዊና አእምሯዊ አቅም እንዲጎለብቱ፣ እንዲለሙ እና የላቁ እንዲሆኑ አካባቢያቸውን ሀገራቸውን ብሎም አለምን በበጎ እንዲለውጡ ማስቻል ነው። የኢትዮጵያ መንግስትም ሀገራችንና ህዝቦቿን ከድህነት ለማውጣት፤ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ለማድረስ፡ ብቸኛው አማራጭ የሰው ሀይላችንን በማስተማርና በማሰልጠን መሆኑን በማመን ለትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ በጀት እየመደበ የዜጎችን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡

በዚህም መሰረት ፍኖተ ካርታው በተለይ በከፍተኛ ትምህርት በአእምሮ የጎለመሱ፣ በሙያቸው የበቁ፣ በመንፈሳቸው የተረጋጉ፣ በስነባህሪያቸው የበሰሉ፣ ምክንያታዊና ሚዛናዊ የሆኑ ስነምግባር ያላቸው የአገራቸውንና የማህበረሰባቸውን ታሪክና እሴቶች አውቀው በማክበርና በመጠበቅ ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ለሀገራቸው እድገትና ለሕዝባቸው ልእልና የሚተጉና ለአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ከመዘጋጀት አልፈው የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች፣ አልሚዎች፣ ተግባሪዎች የሚሆኑ ዜጎችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብሎ በትምህርት ሙያና በሌሎች ዘርፎች ምሁራን በጥናት የተለዩና በየደረጃው ሰፊ ዉይይቶች የተካሄደባቸውና ስምምነት የተገኘባቸውን የኮርሶች ስብስቦች ከነ ይዘታቸው ዝግጁ ሆነዋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ማህበረሰብ አባላት ጋር በተለይ ኮርሱን የሚሰጡ ባለቤት የትምህርት ክፍሎች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ እነዚህም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በአንደኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡ ስለሆነም ለትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው ትግበራ ስኬት ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበረሰብና መንግስት ተቀናጅተው ሊረባረቡ ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 ቀን 2011 ዓ.ም

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ
0Shares
0