ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

አሳዛኝ ዜና – ያለ ገበያ ጥናት የተገዙ 6ሺ ትራክተርና 4ሺ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች መፍትሄ የሚሰጥ በመጥፋቱ አፈር እየበላቸው ነው

የአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ያለገበያ ጥናት የተገዙ 4 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 10ሺ ትራክተሮችና የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ወደ አፈርነት ከመቀየራቸው በፊት መንግስት ውሳኔ እንዲሰጥ ተጠየቀ።

የኢንዱስትሪው ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ድሪባ ሁንዴ፤ ያለገበያ ጥናት ተገዝተው ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በኢንዱስትሪው ግቢ ተከማችተው ጸሐይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው ለብልሽት የተጋለጡ ትራክተሮችና የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ሙሉ ለሙሉ ወደ አፈርነት ከመቀየራቸው በፊት ጥቅም ላይ እንዲውሉ መንግስት አፋጣኝ ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ያለገበያ ጥናት በአንድ ጊዜ 15ሺ ትራክተሮችን ገዝቶ በኢንዱስትሪው አከማችቶ እንደነበር ያስታወሱት ሻለቃ ድሪባ፤ በየዓመቱ በአማካይ ስምንት መቶ ትራክተሮችን ሲሸጥ ነበር። ሆኖም ከብዛታቸው አንፃር ሁሉንም ሸጦ ማጠናቀቅ ስላልቻለ ቀሪዎቹ ለብልሽት እየተዳረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

Related stories   በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 110 ሺህ ዶላር ተያዘ

እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ 6ሺ ትራክተርና 4ሺ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች በዝገት ወደ አፈርነት ተቀይረው ከጥቅም ውጭ ከመሆናቸው በፊት መንግስት ዋጋ ቀንሶም ቢሆን መሸጥ አለበት። መሳሪያዎቹ ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት አገልግሎት ላይ መዋል ካልቻሉ ከጥቅም ውጭ ስለሚሆኑ ለአርሶ አደሩ በነፃ የመስጠት ውሳኔ እስከማሳለፍ መወሰን ይኖርበታል።

‹‹በኢንዱስትሪው የተከማቹትን ትራክተሮችና የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን የግብርና ሚኒስቴር፣ የክልል ግብርና ቢሮዎች፣ የዞንና የወረዳ ሀላፊዎች እንዲጎበኙ ተደርጓል። መሳሪያዎቹ ላይ መወሰድ ስላለበት እርምጃም ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ቀርቧል። ኮርፖሬሽኑም ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቋል። ነገር ግን አፈር እየበላው ያለውን የህዝብ ሀብት ወስኖ ወደ ስራ የሚያስገባ አካል እስካሁን አልተገኘም›› ሲሉ ዋና ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል ።

Related stories   “አቡነ ማቲያስ የሰጡት መግለጫ የግላቸው እንጂ የቅዱስ ሲኖዶስ ወይም የቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ አይደለም”

ዋና ስራ አስኪያጁ ‹‹መንግስት ቆላማ ቦታዎችን ለማልማት የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የውጭ ምንዛሬ አውጥቶ ትራክተሮችና የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ከመግዛት እነዚህን መጠቀም አለበት። ትራክተሮቹ ከስምንት እስከ 180 የፈረስ ጉልበት ያላቸው ሲሆኑ፤ በዓለም ገበያ ተፈላጊ ከመሆናቸውም በላይ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ተሞክረው ውጤታማነታቸውም ተረጋግጧል። በመሆኑም ውሳኔ ሊያሳርፍባቸው ይገባል›› ብለዋል።

ኢንዱስትሪው ሰባት ቢሊዮን ብር እዳ እንዳለበት የገለጹት ስራ አስኪያጁ፤ ትራክተሮቹ የገቡት በብድር በመሆኑ የብድሩ የእፎይታ ጊዜም በመጠናቀቁ ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወለድ እየታሰበ ነው። ኢንዱስትሪው በየዓመቱ ከ50 እስከ 200 ሚሊዮን ብር ኪሳራም እየተመዘገበት በመሆኑ ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።

መሳሪያዎቹ ረጅም ዓመታት በማስቆጠራቸው ስለዛጉ ወደ ስራ ለማስገባት ዘይት፣ ባትሪና ሌሎች እቃዎቻቸው ቅያሬ ስለሚያስፈልጋቸው ለአንድ ትራክተር ከ40 እስከ 50ሺ ብር ወጪ ያስወጣሉ። በዚህ ሁኔታ ተሸጠው ማትረፍ ስለማይቻል ትርፉ ቀርቶ ዕዳቸውን ችለው ለአርሶ አደሩ ጥቅም እንዲውሉ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

Related stories   "በፕሮፓጋንዳ እስካሁን የተወናበድኩት ይበቃኛል ብሎ ቆም ብሎ ማሰብም ይገባል ... ወጣቱን ያለ እድሜው ህይወቱን ይቀጩታል"ሌ.ጀ ዮሐንስ

ኢንዱስትሪው ካለበት ችግር ወጥቶ ውጤታማ እንዲሆን የተከማቹት መሳሪያዎች ላይ ውሳኔ በማሳለፍ መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ በቀጣይም ገበያን መሰረት ያደረገና ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ ሁለትና ሶስት አይነት ምርቶችን በማቅረብ የአርሶ አደሩን ግብርና ለማዘመን እንደሚሰራ ገልጸዋል።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰኔ 21 ቀን 2009 ዓ.ም “አምስት ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ትራክተሮችና ተቀጽላዎች ለብልሽት መዳረጋቸው ተገለጸ” በሚል ርዕስ ዘገባ መስራቱና ማስተካከያ እንዲደረግ መጠቆሙ የሚታወስ ነው።

አዲስ ዘመን ነሀሴ 15/2011

 አጎናፍር ገዛኸኝ