ለዓመታት ባለሙያዎች ሲቃወሙት የነበረው የቀድሞው ስርዓተ ትምህርት እንዲመክንመደረጉ ተገለጸ። አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በአዲሱ ዓመት ተግባራዊ እንደሚሆን የትምህርት ሚኒስትር ይፋ አደረገ። የቀድሞው ስርዓተ ትምህርት የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ያንኮታኮተ፣ አዲሱን ትውልድ በጎሳና በብሄር አስተሳሰብ የሚያንጽና አገራዊ ማንነትን የሚክድ ነበር።

ዛሬ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የትምህርት ሚኒስትሩን ጠቅሰው ይፋ እንዳደረጉት አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በመልካም እሴት፣ ስነ ምግባርና በብቃት የታነጸ ዜጋን ለማፍራት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ነው።

(ኤፍ ቢ ሲ) በትምህርትና ስልጠናው ፍኖተ ካርታ ከተቀመጡት 37 የመፍትሄ አቅጣጫዎች መካከል ከቀጣዩ የትምህርት ዘመን ጀምሮ በተመረጡት 13 የርብርብ መስኮች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከቀጣዩ የትምህርት ዘመን ጀምሮ መንግስት በመልካም እሴት፣ ስነ ምግባርና በብቃት የታነጸ ዜጋን ለማፍራት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም የትምህርት ስርዓቱ የሃገሪቱን አንድነት የሚያስቀጥል፣ ከማህበረሰቡና ከተማሪው ጋር የተጣጣመ እንዲሁም ሃገር በቀል እውቀቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ ይሰጣልም ነው ያሉት።

ሚኒስትሩ በመግለጫው ወቅት አዲሱ የትምህርት መዋቅር በሶስት ክፍሎች ተመድቦ እንደሚሰራ ጠቅሰው፥ 6 ዓመት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት፣ 2 ዓመት የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሁም 4 ዓመት ደግሞ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሆን ተወስኗል ብለዋል።

ተማሪዎች 6ኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ ክልላዊ ፈተናን የሚፈተኑ ሲሆን፥ ከዚህ በፊት ክልላዊ ፈተና የነበረው 8ኛ ክፍል ደግሞ ሃገራዊ ፈተና ይሆናልም ተብሏል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት በግል ዘርፍ ተይዞ የቆየው የቅድመ መደበኛ ትምህርት (የህጻናት ማቆያን ጨምሮ እስከ ኬ ጂ) በግልና በመንግስት እንዲያዝ ይደረጋልም ብለዋል በመግለጫቸው።

በመግለጫው ከዚህ ቀደም ሲሰጥ የቆየው የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና አይኖርም የተባለ ሲሆን፥ የ12ኛ ክፍል ፈተና ለከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ሊሆንም ላይሆንም እንደሚችል ተጠቁሟል።

በተጨማሪም የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠናዎች ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ይጀመራል ተብሏል።

በዚህም ተማሪዎች በቴክኒክና ሙያ ትምህርት መርሃ ግብር ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 8 (እስከ ሶስተኛ ዲግሪ) ደረጃ ድረስ መማር እንደሚችሉም በመግለጫው ወቅት ተነስቷል።

Related stories   በሺህ የሚቆጠሩ አጭበርብረዋል የተባሉ የስራ አፈላላጊ ኤጀንሲዎች ታገዱ፤ የሚከሰሱ አሉ

የመምህራን ድልድልን በተመለከተም መምህራኑ ያላቸውን የትምህርት ደረጃ መሰረት ባደረገ መልኩ ይተገበራልም ነው የተባለው።

ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው መምህራን፣ ለሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪ (ማስተርስ) እንዲሁም ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሁለተኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ ያላቸው መምህራን የሚመደቡ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *