“Our true nationality is mankind.”H.G.

ሜቴክ በ12 ማምረቻ ፋብሪካዎች ላይ ውሳኔ አሳለፈ!50 አመታትን ያገለገለ ማሽን ለደብረ ብርሀን

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ቦርድ በቂ ጥናት ሳይደረግባቸው ግንባታቸው በተጀመሩ 12 ማምረቻ ፋብሪካዎች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ።

ኮርፖሬሽኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች ቢሊየን ብሮችን በመመደብ የ12 ፋብሪካዎች ግንባታ ጀምሮ ነበር።

ይሁን እንጅ አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶቹ የመሰረት ግንባታ ያከናወኑ እና የማሽን ግዢ ብቻ የፈፀሙ መሆናቸውን የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀኔራል አህመድ ሃምዛ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልፀዋል፡፡

በዚህ መሰረት የኮርፖሬሽኑ ቦርድ አዋጭ ያልሆኑትን እንዲቋረጡ ፣ ጊዜ የሚፈልጉትን ማቆየት እና ማጠናቀቅ የሚቻሉትን ደግሞ በበጀት አመቱ በማጠናቀቅ ወደ ምርት እንዲገቡ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የተጀመሩት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ አለመጠናቀቀቻው ተቋሙን ላልተፈለገ ወጪ እንደዳረጉትም ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹን በተመለከተ በተካሄደ ጥናትም የፋብሪካዎቹን ግንባታ ለማስቀጠል ቀድሞ ከወጣባቸው በተጨማሪ ከ6 ቢሊየን ብር በላይ ወጪን ይጠይቃሉ፤ ዋን ዳይሬክተሩም ተቋሙ ተጨማሪ ወጪ ማድረግ አይችልም ብለዋል፡፡

አሁን ባለው አቅምም ማጠናቀቅ የሚቻለው አንዱን ፋብሪካ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም ቀድሞ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውና ከ25 ሚሊየን ብር በላይ የሚጠይቀው የመቐለ ራዲያተር፣ ኮፐርና አሉሙኒየም ፋብሪካ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።

አዋጭ ሆነው በርካታ ስራዎች የሚቀራቸው የደብረ ማርቆስ የክሬንና ሊፍት ማምረቻ እንዲሁም የነቀምት የብረታ ብረት ማምረቻዎች ይጠቀሳሉ።

የነቀምቱ ፋብሪካ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን በተካሄደው ጥናት ተጨማሪ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ያስፈልገዋል፤ ለፋብሪካው እቃ ከተገዛም አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል ተብሏል፡፡

ከ237 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የሆነበት የደብረ ማርቆሱ ፋብሪካ ደግሞ ምንም አይነት የግንባታ እንቅስቃሴ ያልተከናወነለት ሲሆን ግንባታውን ለማጠናቀቅም ተጨማሪ 237 ሚሊየን ብር ይጠይቃል ነው የተባለው።

በመሆኑም እነዚህ ተቋማት ሲጠናቀቁ ከሚሰጡት ጥቅም አንፃር ሜቴክ በራሱ አቅም ማጠናቀቅ ባይችልም ከሁለቱ ክልሎች ጋር በጋራ ለመስራት እንዲቻል ተወስኗል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ከክልሎቹ በጎ ምላሽ እያገኙ ሲሆን ወደ ስራ ሲገባ ራሳቸውን የቻሉ ኩባንያዎች ይሆናሉ ብለዋል፡፡

በዳሰሳ ጥናቱ ግንባታው ቢጠናቀቅ እንኳን ኪሳራው እንደሚያመዝን የተረጋገጠውና 44 ሚሊየን ብር የወጣበት የደብረ ብርሀን ብረት ማቅለጫ ፋብሪካ ነው።

50 አመታትን ያገለገለ ማሽን የተገዛለት ይህ ፋብሪካ ከመለዋወጫ ጀምሮ ወደ ስራ በማስገባት ሂደት ውስጥ ያሉ ግብአቶች የማይገኙለት እና ከምርት በኋላም አዋጭ እንዳልሆነ ተለይቷል።

በመሆኑም ይህ ፋብሪካ መገንባት ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ይቋረጣል ተብሏል፡፡

ሌላው ደብረ ብርሀን ከተማ ይገነባል የተባለው የባለጎማና የባለ ሰንሰለት ማሽነሪ ማምረቻ ፋብሪካ ሲሆን፥ ይህ ስፍራ አነስተኛ መካከለኛ እና የጭነት ተሽከርካሪ መገጣጠሚ ይደረጋል ብለዋል። ይህም በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ላይ ያለውን ጫና ለማቃለል እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኘውና ከ100 ሚሊየን ብር ወጪ የሆነበት የተርባይን ጄኔሬተር ፋብሪካ ተጨማሪ 64 ሚሊየን ዶላር የሚጠይቅ በመሆኑ እንዲቆይ ተወስኗልም ነው ያሉት፡፡

በደብረ ብርሀን የሚገኘው የመበየጃ ፋብሪካም 44 ሚሊየን ብር ተጨማሪ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ቢቻል ከፋፍሎ ስራውን ማጠናቀቅ ካልተቻለ ደግሞ ወደ ቀጣይ በጀት አመት እንዲዞር የተወሰነበት ነው።

በመቐለ የሚገኘውና ተጨማሪ ጥናትን የሚጠይቀው የራዲያተር ማምረቻ ፋብሪካም ለጊዜው እንዲቆይ መወሰኑን ጠቅሰው፥ ቦርዱም የተጠቀሱትን ጉዳዮች መሰረት አድርጎ ውሳኔ ማሳለፉን እና አሁን ላይ ወደ ተግባር እየተገባ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም ሜቴክ ከመንግስት ለመገንባት የወሰዳቸውን ፕሮጀክቶች በተለይ ህዳሴ ግድብና ስኳር ፋብሪካዎችን ባሉበት ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ማስረከቡንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

FBC

0Shares
0