ሕዝቦቿን በባርነት ለመግዛትና የተፈጥሮ ሀብቷን ለመዝረፍ አፍሪካን በቅኝ ግዛት የተቀራመቱት አውሮፓውያን አህጉሪቷን በወንጌል ቃል ለማቅናትና ለመጎብኝት በሚል ሰበብ ወደ ቀየው ዘልቀው የገቡ ሲሆን፤ በሂደት ግን የአፍሪካውያንን የሰው ኃይልና ተፈጥሮ ሀብትን በመዝረፍ ታላቅ ስብራት ጥሎ ያለፈና ይሄ ነው ተብሎ ሊገመት የማይችል ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ታሪካዊ ቀውስና ክስረት ያጎናጸፈ መራር የጨለማ ዘመን ታሪክ ሆኖ አልፏል።

አፍሪካውያን ወይም በአጠቃላይ ጥቁር ህዝብ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ስብዕና የላቸውም ብለው የሚያምኑት አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት በተቀራመቱበት ዘመቻ፤ ጥቁር ህዝቦችን ከሰውነት ተራ በማውረድ በገዛ መሬታቸው ባይተዋር አድርገዋል። አፍሪካዊያንም የተፈጥሮ ሀብታቸው ተዘርፎ፤ ባህላቸው ተንቆ፤ ለዘመናት ያፈሩት ስልጣኔያቸው፤ ታሪካቸውና ቅርሳቸው የእነርሱ እንዳልሆነና “ጥቁር ህዝብ እንዲህ ዓይነት የረቀቀና የመጠቀ ስልጣኔ ባለቤት አይሆንም” በሚል እኩይ አስተሳሰብ ቅርሶቻቸውንና ታሪካቸውን ወደ አውሮፓ ቤተ-መዘክሮችና ዐውድ ርዕዮች ተግዘው ለእነርሱ ከፍተኛ የገቢ ማስገኛ ምንጮች ሲሆኑ፤ እነርሱ በገዛ ታሪካቸውና ቅርሳቸው ባይተዋር ሆነው ታሪክና ቅርስ አልባ የሆኑበትን ዘግናኛ የመከራና የሰቆቃ ዘመን በአፍሪካ ትልቅ የታሪክ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።

በዚህ ግፍና መከራ ኅሊናቸው የቆሰሉ አፍሪካውያን ይሄን ግፈኛ ስርዓት ከጫንቃቸው አሽቀንጥሮ ለመጣል ሲሉ ነበር በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ የጸረ- ኮሎኒያሊስት እንቅስቃሴ ያቀጣጠሉት፤ በተለይም ደግሞ በደቡብ አፍሪካ በነበረው የአፓርታይድ ዘረኛና ከፋፋይ ሥርዓት ክፉኛ የተቆጡና የህዝባቸው ውርደትና ሰቆቃ በእጅጉ እንቅልፍ የነሳቸው አፍሪካውያን፤ ይህን ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታሪክ ሊያደርጉት ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ African National Congress Party (ANC) ን አቋቋሙ።

ከዚህ ፓርቲ መቋቋም በኋላ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ተላቅቀው ነጻነታቸውን አውጀዋል። ከነዚህ አገራት መካከል ካሜሮን በፈረንሳይና በእንግሊዝ ለሁለት ተከፍላ በቅኝ ግዛት ስር ወድቃ የነበረች ሲሆን፤ አገሪቱ ከነዚህ አገራት የቅኝ ግዛት የመከራና የግፍ ይዞታ ወጥታ እኤአ በ1961 ሁለቱ ግዛቶች ተጣምረው አንድ አገር መስርተዋል።

ምንም እንኳን ዛሬ ላይ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት ቢላቀቁም ቅሉ፤ አውሮፓዊያኑ ዛሬም በእጅ አዙር በኢኮኖሚና በፖለቲካው እያደቀቁ አፍሪካን በመዳፋቸው ስር አድርገው ይገኛሉ። እንዲሁም ትናንት አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት ተቆጣጥረውበት በነበረው ወቅት፤ ለአገዛዝ እንዲያመቻቸው ባሰመሩት ድንበር፤ እንዲሁም ባሰረጹት ቋንቋ እና ኃይማኖት ዛሬም አያሌ አፍሪካውያን ወንድማማቾች ጦር እየተማዘዙ ህይወታቸው ያልፋል። በመሆኑም፤ አውሮፓውያኑ በአህጉሪቷ በረጩት የመለያየት መርዝ የአህጉሪቷ ህዝቦች መግባባትና መተባበር ተስኗቸው በስልጣኔና በቴክኖሎጂ ኋላቀር ሆነው በድህነትና በኋላ ቀርነት እንዲማቅቁ ሆነዋል።

በአህጉሪቷ ይህ የአውሮፓውያኑ የመለያየት መርዝ ጥላው ያጠላባት ካሜሮን፤ ህዝቦቿ ከፈረንሳይና ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የተላቀቁበትን 56ኛ ዓመት እኤአ ጥቅምት 2017 ባከበሩበት ወቅት፤ በተለይ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩት የአገሪቱ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ህዝቦች ብዙ የህዝብ ቁጥር ባለው የአገሪቱ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብ “መድልዎና መገለል ይደርስብናል” በማለት የእንግሊዘኛ ቋንቋ በሚነገርባቸው ግዛቶች በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች የተቃውሞ ድምጽ አሰምተው ነበር።

በወቅቱም ተቃውሞው ተቀጣጥሎ በሁሉም የእንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆኑ የካሜሮን ግዛቶች የተቃውሞ ሰልፍ የተካሄደ ሲሆን፤ ሰልፈኞቹም ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት መስሪያ ቤቶች መገለል ደርሶብናል፤ እንዲሁም ፈረንሳይኛ ቋንቋን እንድንናገር የአገሪቱ ህግ ግዴታ ጥሎብናል። በአንድ አገር አንድ መንግስት ሁሉንም ዜጎች በእኩል አይን ባለማየቱ በአገሪቱ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል የለም በሚል ለዓለም ህዝብ ድምጻቸውን አስተጋቡ።

በኋላ ላይ የተቃውሞ ሰልፉ መልኩን ቀይሮ ነጻነትን እንፈልጋለን የሚሉ ተምሳሌታዊ የሆነ የነፃነት አዋጆችንም በዚሁ አጋጣሚ ተቃዋሚዎች ያሰሙ ጀመር። ተቃዋሚ ሰልፈኞቹም በዚህ ሳያበቁ የእንግሊዘኛ ተናጋሪ በሆኑ ግዛቶች በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ይወክለናል ያሉትን ሰንደቅ ዓላማ አውለበለቡ።

በተቃራኒው የአገሪቱን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብ ተቃውሞችንና የነጻነት ጥያቄዎችን በመንቀፍ መንግስትን በመደገፍ “አንድ ካሜሮን” በሚል መፈክር በዱዋላ ከተማ የአገሪቱ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ዜጎች ለተቃውሞ የወጡ ሲሆን፤ በወቅቱ በሁለቱ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል በተደረገ ግጭትና መንግስት የተገንጣይ አመለካከት አለባቸው ብሎ ባመነባቸው ዜጎች ላይ በወሰደው እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ህይወታቸውን ሲያጡ፤ ከ500 ሺህ በላይ ህዝብ ከሚኖሩበት ቀየ ተፈናቅሏል።

እንዲሁም፤ ከተቃውሞ ሰልፉ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የካሜሮን መንግስት ህዝባዊ የሆኑ ስብሰባዎችን እንዲሁም ጉዞዎችን የእንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆኑ የካሜሮን ግዛቶች አግዶ የነበረ ቢሆንም፤ ህዝባዊ አመጽና ሁከት በእንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆኑ የአገሪቱ ግዛት በማየሉ የአገሪቱ መንግስት ብዙ ቁጥር ያላቸውን ተቃዋሚዎችን ዘብጥያ አውርዷል። የካሜሮን ወታደሮችም ብዙዎቹን ገድለዋል። በዚህም የሰብአዊ መብት አቀንቃኞች መንግስት ሰፊ ቁጥር ላላቸው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ዜጎች ያደላል በሚል የኮነኑ ሲሆን፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾቹም የታሰሩ ሰዎች እንዲለቀቁ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እየተቃወሙ ይገኛሉ።

ይህ ለመብት የተጀመረው እንቅስቃሴ አሁን ላይ እስከ መገንጠል ጥያቄ ተቀይሯል። በዚህም፤ በማዕከላዊቷ አፍሪካ አገር ካሜሮን በሁለት እንግሊዝኛ ተናጋሪ ግዛቶች ውስጥ እኤአ ጥቅምት 2017 ጀምሮ የመገንጠል ጥያቄ መቀንቀን የጀመረ ሲሆን፤ የመገንጠል ጥያቄውንም በወቅቱ ያቀጣጠሉት አዩክ ታቤ የተባለ ሰው ነበር። እርሱም ራሱን የ“አምባዞኒያ”(በአገሪቱ በሰሜንና በደቡብ ምዕራብ የሚገኙ የሁለቱ የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ግዛቶች) ፕሬዚዳንት እኔ ነኝ በማለት ሲጠራ ቆይቷል። ይህ ሰው ግዛቷ በዓለም ህዝብ እውቅና ባይቸራትም ራሷን የቻለች አገር ናት በማለት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

ነገር ግን፤ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ እለት ኢስት አፍሪካ በድረገጹ እንዳስነበበው፤ ይህ ራሱን የአንግሎፎን መሪ ነኝ ብሎ የሚጠራው ሰው በአገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት “በሽብርተኝነት እና በመገንጠል” ክስ የቀረበበት ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ እርሱንና ዘጠኝ ግብር አበሮቹን ጨምሮ የእድሜ ልክ እስራት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል ብሏል።

በአገሪቱ የህግ ባለሙያ የሆኑት ማርቲን ሉተር አቼት ለኤ ኤፍ ፒ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ “በአገሪቱ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ፍራንኰፎን ሲባሉ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች አንግሎፎን ተብለው ይጠራሉ። አንግሎፎኖች በአገሪቱ ዝቅተኛውን ቁጥር የሚይዙ ሲሆን፤ 24 ሚሊዮን ከሚሆነው የካሜሮን ህዝብ አምስት በመቶውን ይይዛሉ። እነዚህ ህዝቦችም በአገሪቱ በሰሜንና በደቡብ ምዕራብ ግዛቶች የሚገኙ ሲሆን፤ ከፈረንሣይ ተናጋሪ ግዛት ጋር የተካተቱት ከስድስት አስርት ዓመታት በፊት ካሜሮን ነጻነቷን ባወጀችበት ወቅት ነው።

“ነገር ግን አንግሎፎኖች ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍልና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፤ እንዲሁም በትምህርት እድል እና በኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችን በፍራንኮፎን የፖለቲካ የበላይነት በመያዙ ፍትሃዊ ፍርድና የሀብት ክፍፍል አላገኝንም በሚል ለዘመናት እየተቃወሙ ይገኛሉ። በመሆኑም እራሱን የአንግሎፎኖች ነጻ አውጪ ነኝ ብሎ የሚጠራው አዩክ ታቤ፤ የአንግሎፎኖች መሪና የአምባዞኒያ አስተዳዳሪ እኔ ነኝ ብሎ አውጆ አገሪቱን ለመገንጠል ሲንቀሳቀስ ነበር፤” ብለዋል።

ይህ ሰው እራሱን “የአንግሎፎኖች መሪና የአምባዞኒያ አስተዳዳሪ እኔ ነኝ” ብሎ ቢያውጅም፤ የካሜሮን መንግሥት የመገንጠል ጥያቄዎችን ውድቅ በማድረጉ በዓለም ዙሪያ ለዚህ ሰው የተሰጠው እውቅና አልነበረም። በመሆኑም፤ የአገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት እራሱን የአምባዞኒያ አስተዳዳሪ ነኝ ብሎ የሚጠራውን ይህን ሰው በአቀረባበት የሽብርተኝነትና የመገንጠል ክስ ዘጠኝ ተከታዮቹን ጨምሮ ጥፋተኛ ሲል በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ቀጥቷል ብለዋል።

ነገር ግን፤ ባለፈው ወር የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ግድያዎችን እና ከመጠን በላይ ኃይልን መጠቀምን ጨምሮ በዜጎች ላይ “አስነዋሪ ወንጀሎች” ፈጽመዋል፤ ሲሉ የከሰሱ ሲሆን፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾቹም ይሄንን የወታደራዊ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ “የነጻነትን ጥያቄ ለማፈን የተደረገ ፍርድ” ሲሉ አጣጥለው አውግዘውታል።

ካሜሮን በእንግሊዝና በፈረንሳይ ለሁለት ተከፍላ በቅኝ ግዛት የተገዛች ሲሆን፤ እኤአ በ1961 ሁለቱ ግዛቶች ተጣምረው አንድ አገር መስርተዋል። ሆኖም የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ብዙ የህዝብ ቁጥር ባለው የፈረንሳይኛ ተናጋሪ መድልዎ ይደርስብናል በሚል እራሳቸውን ችለው አገር ለመመስረት እየታገሉ ይገኛሉ።

 አዲስ ዘመን ነሀሴ 17/2011

ሶሎሞን በየነ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *