በድሬዳዋ ከተማ ብቻ 7258 ሰዎች በ ቺኩንጉኛ ቫይረስ ወረርሽኝ ተጠቅተዋል:: ሌሎችም እየተጠቁ ስለሆነ ቁጥሩ በቀናት ልዩነት ከፍ ሊል ይችላል::ስለበሽታው ምንነት አንዳንድ መረጃዎችን ከዚህ በታች የሚከተለው ላቀርብ እሞክራለሁ::

ቺኩንጉኛ (ቺክ) በእንግልዘኛው Chikungunya (CHIK) የሚመጠው በቺኩንጉኛ ቫይረስ Chikungunya virus (CHIKV) ሲሆን ከህመምተኛው ሰው ወደ ጤነኛው ሰው የሚተላለፈው አዴስ አልቦቺክታስ (Aedes albopictus) እና አዴስ አጂፒቲ (Aedes aegypti) ተብለው በሚጠሩና በቫይረሱ በተጠቁ የትንኝ አይነቶች ንክሻ አማካኝነት ነው::

አዴስ አልቦቺክታስ የሚባለው የትንኝ አይነት በብዛት የሚገኘው በደቡብ ምዕራባዊው ኤስያ ሲሆን ከድንበር ተሻጋሪ እንቅስቃሴዎች የተነሰ ባርካታ የአለማችን ክፍሎች መታየት ጀምሯል:: ይህ የትንኝ አይነት በሆዱና በእግሩ ላይ ከሚታየው ዝንጉርጉርነት የተነሰ የኤስያው ነብር የሚል ቅጥል ስም አለው (ፎቶ: 5 ይመልከቱ ):: አዴስ አልቦቺክታስ ከቺኩንጉኛ በተጨማሪ Yellow fever Virus (በተለምዶ ቢጫ ወባ ተብሎ የሚታወቅ): Dengue virus (ደንጉ ቫይረስ) ና ዲሮፍላሪያ ኢሚቲስ (Dirofilaria immitis) የሚባሉ በሽታ አምጭ ተዋህሳን ተሸካሚ መሆኑ ይታወቃል:: ከዚህ በተጨማሪ ዚካ ቫይረስንም (Zika virus) ተሸካሚና አስተላላፊ መሆኑ ይታመናል::

ሌላኛው የትንኝ አይነት አዴስ አጂፒቲ የተገኘውና በብዛትም የሚገኘው አፍሪካ አህጉሪ ውስጥ ሲሆን ከቺኩንጉኛ በተጨማሪ የቢጫ ትኩሳት ቫይረስ: ዚካ ቫይረስ: ማያሮ (Mayaro) እና ደንጉ ቫይረስን ያስተላልፋል:: በብዛት በአፍሪካ ይገኝ እንጂ በብዙ ሞቃታማው የአለማችንም ክፍል እንደሚገኝ ጥናቶች ያሳያሉ:: ይህን ያህል ስለ ትንኙ ካወረሁ በአድስ መልኩ በአገራችን ወረርሽኝ እያስከተለ ስላለው ስለ ቺኩንጉኛ በሽታ አንዳንድ መሰረታዊ እውነታዎችን ልጠቁም::
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በሽታው የሚመጠው በቫይረስ ሲሆን ዋና ዋና ምልክቶቹ ከፍተኛ ትኩሳት(40 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ): ራስ ምታት: የመገጣጠሚያና የጡንቻ ህመም: የመገጣጠሚያ እብጠትና ሽፍታ ናቸው (ፎቶ: 1: 3 ና 4 ይመልከቱ) :: የበሽታውም ስም ከሲዋህለኛ ወደ አማርኛ ሲተረጎም “ማጠፍ” ( በእንግሊዘኛው that bends up) ማለት ነው:: ይህም ከመገጣጠሚያ ህመም የተነሰ ቀጥ ብሎ መቆምም ሆነ መሄድ አለመቻልን ለማመልከት ነው::

የበሽታው ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት በበሽታ አምጪ ቫይረስ የተመረዘች ትንኝ በነደፈች ከሁለት እስከ አስረ ሁለት ቀናት በሉት ጊዜያት ነው:: ብዙውን ጊዜ ምልክቶቹም የሚቆዩት እስከ ሳምንት ባለው ጊዜ ቢሆንም የመገጣጠሚያ ህመም ግን ከወራት እስከ አመታት ሊቆይ ይችላል::

የበሽታው የመግዳል አቅም (risk of death) አንድ ሰው ከአንድ ሺ ሰው ነው:: ይህም ማለት በሽታ ከተጠቁ አንድ ሺ ሰዎች መካከል አንዱ ሊሞት ይችላል ማለት ነው:: ይህ ቁጥር ትንሽ የሚባል አይደለም:: በተለይ ህፃነት: አዛውንትና በተለያዬ በሽታ ቀድመው የተጠቁ ሰዎች ላይ አደገኘነቱ ይበረታል::

በላብራቶሪ የቫይረሱን ዘረ-መል (RNA) ወይም ቫይረሱ መጠቃት ምክንያት ሰውነታችን ለመከላከል ያመነጫቸውን ፀረ ቫይረስ ንጥረነገር (antibody) በማየት ሲሆን ይህ አይነቱ ምርመራ እንደ ELISA ና RT-PCR (የላቦራቶሪ ቴክኒኮች ናቸው) ያሉ መመርመሪያዎችን ይፈልጋል:: በእኛ አገር ሁኔታ ለሁሉም ተደራሽ ባይሆንም መሳሪያዎቹ በአገር ደረጃ እንዳሉ አውቃለሁ ነገር ግን ለዚህ ምርመራ የሚያስፈልጉ ተጨማሪ ግብኣቶችን መግዛት ያስፈልጋልና በዚህ ላይ እውቀቱ የለኝም::

ህክምናውን በተመለከተ በሽታው ከላይ እንደጠቀስኩስ በቫይረስ የሚመጣ ሲሆን ለዚህ ቫይረስ ህክምና የሚሆን ፀረ-ቺኩንጉኛ እስካሁን ባለኝ መረጃ የለም:: ስለሆነም ህክምናው የሚያተኩረው በበሽታው ምክንያት የሚከሰቱ ምልክቶችን ማለትም ትኩሳት: ድካም: በትኩሳት ትነት የሚወጣውን ፈሳሽ መተካት ይሆናል ማለት ነው:: በተጨማሪም ለበሽታው መከላከያ የሚሆን ምንም አይነት ክትባት እስካሁን ገበያ ላይ አልዋለም::

የበሽታው መከላከያ የበሽታ አምጪውን ትንኝ መቆጣጠር ሲሆን ከወባ በሽታ መከላከያ ጋር ተመሳሳይ ነው(ፎቶ: 2 ይመልከቱ):: በተላይም እያንዳንዱ ሰው በዙሪያው የሚገኙት ለትንኝ መራቢያ አመቺ የሆኑ ነገሮችን ማስወገድና የአከባቢውን ንፅህና መጠበቅ ፍቱን መፍትሄ ነው:: 
ከወባ በተለየ ሁኔታ ትንኞቹ በቀን (ቀትር) ላይ ዝውውር ስለሚያደርጉ ቀን ላይ ለሚታኙ ህፃናትና የታመሙ ሰዎች ቴንትና በቆዳ ላይ የሚቀባ ትንኙን የሚያርቅ ቅባት መጠቀም ተገቢ ነው:: ይህ ቅባት ለቺኩንጉኛ ተብሎ የተሰረ ወይም በውስጡ ትንኞቹን ማራቅ የሚችል ጠረን ያለውን ንጥረነገር ወይም ኬሚካል የያዘ መሆን አለበት (ከጤና ተቋም ብቻ መግዛት ተገቢ ይሆናል)::

መከላከል እየቻልን አንድም ሰው እንዳይሞት ትኩረት እናድርግ!

ከድሬዳዋ ወደ ሌላው አከባቢ እንደይሰራጭና በቅርቡም ከአገራችን የቺክንጉኛንና የመሰል ወረርሽኝ አምጪ ተዋህሳንን መጥፋት እንደምንሰማ ተስፋ አደርጋለሁ::

ተስፈኛው ተክሌ

Tekle Airgecho  ከኦስሎ ዩኒቨርስቲ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *