መደበኛ መገናኛ ብዙሃን የጥላቻ ንግግሮችን የመቀልበስና ለህዝብ ትክክለኛውን መረጃ የማድረስ ሚና ቢኖራቸውም ይህን ማድረግ እንዳልቻሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህራን ተናገሩ።

መምህራኑ ከአገሪቱ የፖለቲካ ለውጥ ማግስት ጀምሮ እየመጣ ያለውን የመፃፍና የመናገር ነፃነት ተከትሎ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ክብርን የሚነኩ የጥላቻ ንግግርች እየገነኑ መምጣታቸውን ይናገራሉ።

በተቋማትና በግለሰቦች ላይ የሚደረጉ የጥላቻ ንግግሮች በተለያዩ አካባቢዎች የግጭትና የግንኙነት መሻከር መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸውንም ጠቁመዋል።

የጋዜጠኝነት መምህሩ አማኑኤል አብዲሳ እንደሚሉት በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎች የተአማኒነት ችግር ያለባቸውና በሂስና በጥላቻ ንግግር መካከል ያሉ በመሆናቸው ጉዳታቸው ያመዝናል።

Related stories   የአውሮፓ ህብረት የይስሙላ ምርጫዎች ሲታዘብ ቆይቶ አሁን አልታዘብም ያለበትን ምክንያት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሳውቅ ተጠየቀ

ይህም የሆነው ማህበራዊ ሚዲያው የሚመራበት አሰራር ባለመኖሩና መደበኛ የመገናኛ ብዙሃኑ የስራ ውስንነት ስላለባቸው ነው ብለዋል።

ሌላው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ዶክተር ሙላቱ አለማየሁ እንደሚሉት በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች በአብዛኛው ከፖለቲካ ለውጥ፣ ከኢኮኖሚ ልዩነት መስፋትና ተያያዥ ሁኔታዎች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ናቸው።

መረጃው እውነትም ይሁን ሐሰት በህዝቡ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት መረጃውን እንደሚፅፈው ሰው ተቀባይነትና እንደ መረጃ ተጠቃሚው ግንዛቤ ደረጃ ይለያያል። ይሁንና በዚሁ ከቀጠለ ለአገሪቱ የፀጥታ ስጋት ነው።

Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

የጥላቻ ንግግሮች በተለይ መረጃዎችን በትክክል አመዛዝኖ አገናዝቦ የሚጠቀም ማህበረሰብ ባልተፈጠረበት አገር የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል።

ይሁን እንጂ ለጥላቻ ንግግር መግነን ምቹ ሁኔታን የፈጠረው የመደበኛ መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ የሆነ መረጃን ማቅረብ አለመቻል መሆኑንም ይናገራሉ።

አሁን ያለው ሚዲያ “ፍርሃት የሸበበው፣ መርጦ የሚዘግብ፣ ፈጣን ያልሆነ እና ዝም ያለ ነው” ያሉት ዶክተር ሙላቱ የጥላቻ ንግግርን መቀልበስ ይቅርና ትክክለኛ መረጃን ለማድረስም ውስንነት እንዳለበት ገልፀዋል።

Related stories   ሀገሪቷን ከጥፋት ለመከላከል ፣ ህግን ለማስከበር ፌዴራል ፖሊስ ተግባሩን ያጠናክራል

በመሆኑም በማህበራዊ ሚዲያው የሚለቀቁ ያልተረጋገጡ የጥላቻ ንግግሮች ህዝብን ወዳልተገባ ተግባር እንዳያስገቡ ከተፈለገ መደበኛ መገናኛ ብዙሃን ስራቸውን በአግባቡ ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

መደበኛ መገናኛ ብዙሃኑ በለውጡ ማግስት ጀምረውት የነበረውን የአገራዊ መግባባት ውይይት በአሁኑ ወቅት መቀነሳቸው በራሱ ቀጣይነት የሌለው የዘመቻ ስራ መስራታቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የማህበረሰቡን ችግር ነቅሶ የመዘገብና ፈጣንና ትክክለኛ መረጃን የማቅረብ ስራቸውን ቀጣይ ቢያደርጉ ችግሮቹን መቀነስ ይቻላል ሲሉ ነው ምክረ ሃሳባቸውን የለገሱት።

ኢዜአ ነሀሴ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *