ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ዲጂታል “ወያኔ”፤ የ “እረኛውን ግደል፣ መንጋው ይበተናል” መርህ ያስፈጽማል፤ መሪዎቹ የፌደራል መንግስቱን እንታደግና ህግ ይከበር ጥሪ ያሰማሉ

የተለየ ሃሳብ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች፣ መሪዎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው  ” ባንዳ ” በሚል ከማህበራዊ ትሥሥር እንዲገለሉ የሚደረግባት የትግራይ ክልል መሪ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጠሪ አቀረቡ። ዜጎች በሰላም እንዲኖሩ የሕግ የበላይነት ሊከበር እንደሚገባም አሳሰቡ። ይህንን ሲሉ በህግ የሚፈለጉና እሳቸው ከለላ ስለሰጡዋቸው ተጠርጣሪዎች ግን ያሉት ነገር የለም።

ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ሰላም የሰፈነባት፣ ህዝቦቿ በመከባበር የሚኖሩባትን ሀገር ለመገንባት ሁሉም የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት ማሳሰቢያ የሰጡት፣ “ህገመንግስትና ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓትን ማዳን ለዴሞክራሲያዊ ሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በመቀሌ ከተማ የተጀመረውን ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

በአገሪቱ ከተከሰተው ቀውስና አለመረጋጋት ጀርባ ስሙ የሚነሳው ህወሃት በመሪው አማካይነት “ባለፉት ጥቂት ዓመታት በታየው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የዜጎች መብቶች በአደባባይ ሲጣሱ የታየበት፣ ህዝቦች በነፃነት ተንቀሳቅሰው መስራት የማይችሉበት፣ ሃብት ለማፍራት የተቸገሩበት፣ ለጥቃት የተጋለጡበትና የህግ የበላይነት አደጋ ላይ የወደቀበት ነበር” በሚል ተገምግሟል። ቀደም ሲል ህወሃት አገሪቱን እየመራ በነበረበት ወቅት የተሻለ አመራርና የጽድቅ ጊዜ እንደነበር ተደርጎ ለመሳልም ተሞክሯል።

ሲፈለግ በዲጂታል ዝርጊዳቸው አማካይነት፣ ሲፈልጉም ራሳቸው ትግራይ ወደ መገንጠል እያመራች እንደሆነ የሚናገሩት የትግራይ ገዥ ዶክተር ሰብረጽዮን “ህገመንግስትና ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓትን ማዳን ለዴሞክራሲያዊ ሀገራዊ አንድነት”  በምል ርዕስ በተጠራው ስብሰባ ላይ በሚመሩት ” የፌደራል ስርዓቱን እንጠብቅ ” ሲሉ ተደምጠዋል።

“አሁን ላይ በሀገሪቱ በስፋት እየተከሰቱ ያሉትን ችግሮች ህገ መንግስቱን ካለማክበርና የህግ የበላይነትን ካለማረጋገጥ የሚመነጩ ናቸው” ሲሉ አገር የሚመሩትን ወገኖች ሲወቅሱ፣ እሳቸው ያሉበት የኢህአዴግ ስራ አስፈሳሚ ሚና የት ጋር እንደሚመደብ ያሉት ነገር የለም። ሀገ መንግስት የጣሱት አካላትና ክልሎች እነማን እንደሆኑም አላብራሩም። በህግ ጥሰት በይፋ ስለሚከሰሰው የሳቸው አስተዳደርም የተነፈሱት ጉዳይ የለም።

“ብዝሃነትን መሰረት ያደረገው ፌዴራላዊ ስርዓት አሉታዊና አዎንታዊ ገፅታዎች እንዳሉት የማይካድ ሀቅ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። ይሁን እንጂ አሉታዊ ሲሉ ያነሱትን ጉዳይ አላብራሩም። ንግግራቸው አብዛኞች የስርዓቱ አወቃቀር ለብሄር ግጭት በር መክፈቱን፣ አገሪቱ የምትከተለው የነበረው ትክክለኛውን ፌደራልዝም ሳይሆን አለም የተፋው ” የጎሳ ፌደራሊዝም ” በመሆኑ ይህ ጣጣ ህወሃት ያመጣው እንደሆነ የሚደመጠውን ሃቅ በግርድፉ የመቀበል ተደርጎ ተውስዷል።

Related stories   በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 110 ሺህ ዶላር ተያዘ

ዶክተር መንበረ ጸሃይ ባቀረቡት ጽሁፍ ህገ መንግስቱ በተለይ በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ውስጥ የነበሩ መሰረታዊ የማንነት፣የሰላም እጦትና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄዎችን የመለሰ መሆኑንም ደፍረው መናገራቸው ታውቋል። ይሁን እንጂ በስፍራው የተገኙ ” የመሬት ባለቤት ማን ነው” ሲሉ ጥያቄ ስለማቅረባቸው ዜናውን በዘገበው የፋና ሪፖርት ውስጥ የተካተተ ነገር የለም። እኚሁ ” በሚዛናዊ ፍርዳቸው የሚታወቁት የቀድሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት “ህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ስርዓት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሑፋቸው፣ ” ህገ መንግስቱ ከመጽደቁና ተግባራዊ ከመደረጉ በፊትም በ22 ሺህ ቀበሌዎች ውስጥ በህዝብ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ነበር” ሲሉ ሕዝባዊነት የተላበሰ አሰራር ተከትሎ የተዘጋጀ መሆኑንን መስክረዋል።

የትግራይ ክልል መሪ ሲነጋ ” እንደምን አደራቹህ፣ ሲመሽ ሰማ እደሩ” በማለት የሚንከባከቡት ዲጂታል ወያኔን አስመልክቶ ጎልጉል የሚከተለውን ዘግቧል። ህግ ይከበር የሚባለው ይህ እየተደረገ ነው።

ዲጂታል “ወያኔ”፤ “እረኛውን ግደል፣ መንጋው ይበተናል”

አገራችን ከህወሓት አፋኝ የግፍ አገዛዝ ወጥታ በለውጥ ሒደት ውስጥ ትገኛለች። ሆኖም በአፋኙ ዘመነ ወያኔ እንኳን ሆኖ በማያውቅ መልኩ በአሁኑ ጊዜ አገራችንን እያፈረሰ የሚገኘው በማኅበራዊ ሚዲያ እየተሰራጨ ያለው የሃሰትና የፈጠራ ዜና ነው። ለዚህ ደግሞ በርካታ መዋዕለ ንዋይ እየፈሰሰ ቀንተሌት ተግተው የሚሠሩ “የሳይበር ወታደሮች” ተመድበዋል። እነዚህ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በትጋት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ዓላማቸው መረጃ ማዛባት፤ የሃሰት መረጃ መበተን፤ የሚወጡ መረጃዎችን ማወዛገብ (ሕዝብ እውነቱንና ሐሰቱን እንዳይለይ ማድረግ)፤ ወዘተ ናቸው።

ይህ በዕዝና ቁጥጥር የሚመራ ኃይል ዋና ትኩረት የሚያደርገው በለውጡ ዙሪያ ያሉትን አመራሮች ማጠልሸት፤ የሕዝብ ድጋፋቸውን ማምከን፤ ከተቻለም ሕዝብ እንዲነሳባቸው ማድረግ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በልዩ ልዩ ረቂቅ ስልት በሚበትኑት መረጃ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር እንዲጋጭ፤ ደም እንዲቃባ፤ ሰላም እንዲደፈርስ፤ ሕዝብ እንዲፈናቀል፤ ሕዝብ በመሪዎቹ ላይ እምነት እንዲያጣ በማድረግ “በአመራር ላይ ያለው ኃይል አገር ማስተዳደር አቅቶታል” በሚል በአገር ውስጥና በውጪ ተዓማኒነቱን ማሳጣት ነው።

ከዚህ ዓይነቱ እኩይ ተግባር ጋር በተያያዘ መገንኛዎች “መንግሥትን ከህዝብ የመነጠሉ ዘመቻ የተሳካ መሆኑ ተገመገመ፤ መንግሥት በሚስጢር የያዘው ኩዴታ የዚሁ አካል ነው” በሚል አንድ ዜና አስነብበዋል። ዜናው ከዚህ በታች እንደሚከተለው የቀረበ ሲሆን ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ከዚህ የዲጂታል ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ ጋር በተያያዘ ምን እየሆነ እንዳለ ሰሞኑን የሚያቀርበው ዘገባ ይኖራል፤ በቀጣይም አገር ለማፍረስ የተካሄደውን የግድያ ሤራ አስመልክቶ ከዚሁ የዲጂታል የፈጠራ ወሬ ወረርሽኝ ጋር ያለውን ተዛምዶ በተመለከተ የሚያቀርበው ዘገባ ይኖረዋል።

መንግሥት ለመግልበጥ ውስጥ ውስጡን የተዘረጋው መረብ መበጠሱን  የመረጃ ምንጮች አመለከቱ። ዕቅዱ የቆየ ቢሆንም ተግባራዊ ለማድረግ የተፈለገው የለውጡን መሪዎች ተቀባይነት ካመናመኑ በኋላ ሲሆን፣ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ የሕዝቡን ንቃተ ህሊናና ባህል ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በከፍተኛ በጀት፣ በባለሙያዎችና በማዕከላዊ ዕዝ ደረጃ የተደራጀ የማኅበራዊ ሚዲያ ሠራዊት (ዲጂታል “ወያኔ”) ትልቁን ሚና እንደተጫወተ ታውቋል።

የመረጃው ምንጮች እንዳሉት ከፌዴራል መንግሥት ቀጥሎ ከፍተኛ ሠራዊትና የትጥቅ አቅም ያደራጀው ቡድን፣ መንግሥት አመኔታ እንዳይኖረው ባሰማራው የማኅበራዊ ሚዲያ ሠራዊት አማካይነት ውጤታማ ሥራ መሥራቱን ግምግሟል። በግምገማውም ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይን ለይቶ መምታት የሚለው ስትራቴጂ ግቡን መትቷል። ለዚሁም በዋናነት የዜጎች መፈናቀል፣ በተለይም በሚፈለገው መልኩ የተጠለፈው የአዲስ አበባ የባለቤትነት አጀንዳ፣ የለገጣፎ ህገወጥ ግንባታ አፈራረስና “ኦሮሞ መምራት አይችልም” የሚለው ስልት ከሚፈለገው በላይ ሰርጿል። የለውጡ መሪዎች የገነቡት የሕዝብ ድጋፍ እንዲተን ተደርጓል።

ዳግም ወደ ሥልጣን ለመምጣት እየሠራ ያለው ቡድን ሃሳቡን እውን ለማድረግ ቢነሳ የሚገዳደረው ኃይል የመከላከያ ሠራዊት ብቻ እንደሆነ ገምግሞ የመከላከያው ሠራዊት ውስጥ ሰርጎ የመግባት ሰፊ ሥራ ሰርቷል። ወዳጅ አገራትና ታማኝ የሠራዊቱ አመራሮች ሤራውን እንዳከሸፉት የገለጹት የመረጃው ሰዎች “ውጥኑ ውስን የብሔር ድርጅቶችን እንዲያካትት ተደርጎ የተሠራ ነበር” ሲሉ ገልጸዋል። የብሄር ድርጅት ያሏቸውን ግን አልዘረዘሩም።

ከመከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰአረ ግድያ ጋር ጉዳይ ግንኙነት ይኖረው እንደሆነ ለተጠየቁት ዝምታን የመረጡት ምንጮች፣ ሰሞኑንን የመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ከፍተኛ መኮንኖች በውስጣቸው ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለና ለሕገመንግስቱ ታማኝ ሆነው እንደሚሠሩ በተደጋጋሚ ያስታውቁት በምክንያት መሆኑንን ግን አልሸሸጉም።

የአሜሪካ የጦር መኮንኖች በሥልጠና ስም ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ለዚሁ ዓላማ ይሁን አይሁን ምላሽ ያልሰጡት የዜናው ሰዎች፣ ሕዝብ “እረኛውን ግደል፣ መንጋው ይበተናል” የሚል መርህ ያዘለውን አገሪቱን የመበተን ሤራ በማስተዋል ቢመረምር እንደሚሻል ግን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባህር ዳር የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ ድንገተኛ መግለጫ ሲሠጡ አዲስ አበባ ዙሪያ ሁሉንም ተቆጣጥረናል፤ ችግር የለም ማለታቸው ይታወሳል። እርሳቸው ዝርዝሩን ባይናገሩም የድሮው አውሮፕላን ማረፊያ በሚገኘው የደኅንነት ቢሮ አዲስ አበባ ላይ የታቀደውን ሤራ ሲያቀነባበር ተደርሶበት እጃቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁ መታኮስ መርጠው መመታታቸውን ውስጥ አዋቂዎቹ እንደማሳያ ገልጸዋል።

በዚህ መልኩ ያቀረበውን ዘገባ በተለየም የጦር ኃይሎች አካባቢ ግድያና ተኩስ በተመለከተ በወቅቱ የአሶሼትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ ኤልያስ መሰረት ጦር ኃይሎች አካባቢ ሰኔ 15 ቀን ምን እንደተከሰተ በወቅቱ ያሰባሰበውን መረጃ እንደዚህ ዘግቦት ነበር።

ሰኔ 15 ቀን አመሻሽ ላይ በአማራ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ ውስጥ ቦሌ አካባቢ የተከሰተው ግርግር እና ግድያ ብዙ ትኩረት ቢስብም ጦር ኃይሎች በተለምዶ ሲግናል (በድሮ አጠራሩ መኮ) የተከሰተው ሁነት ግን እስካሁን ይፋ አልሆነም።

ጋዜጠኛ ኤልያስ ቢያንስ ሶስት ምንጮች አረጋገጡልኝ እንዳለው ጦር ኃይሎች አካባቢ በነበረው ግጭት ሁለት ወይም ሶስት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል። እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ገደማም የጥይት ተኩስ ይሰማ ነበር። ይህ ክስተት በዕለቱ ከነበሩት ሌሎች ግድያዎች ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ግልፅ አይደለም።

በቅርቡ ስለ ጉዳዩ ጋዜጠኛው የጠየቃቸው አንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊ “ስለ ጉዳዩ መረጃ የለኝም፤ አጣርቼ መልስ ልሰጥህ እሞክራለሁ” የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር።

በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ አለኝ ያለ አንድ ግለሰብ ለጋዜጠኛው ተከታዩን መረጃ አቀብሎ ነበር፦ “ስለ ሰኔ 15ቱ (የጦር ኃይሎች አካባቢ ጉዳይ) የተወሰነ መረጃ አለኝ። መረጃውን ላገኝ የቻልኩት ደግሞ በዛ ምሽት ከሞቱት ሶስት የፌዴራል ኮማንዶዎች አንዱ የአክስቴ ልጅ ስለነበር ሬሳ ለመቀበል ከቤተሰብ ጋር በሄድንበት ጊዜ የአሟሟቱ ጉዳይ ስለተነገረን ነው። እናም ጉዳዩ ከጄኔራሎቹ ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠረ አንድ ኮሎኔል ለመያዝ በሄዱበት ጊዜ በተፈጠረው የተኩስ ልውውጥ ምክንያት ነው። ግን እስካሁን አንድ የመንግሥት አካል ስለ ጉዳዩ ምንም ነገር አለማለታቸው እጅግ በጣም አሳዝኖኛል” በማለት የዓይን እማኝነቱን መስጠቱን ኤልያስ ዘግቧል።