የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የስነ ምግባር ደምብ እየተዘጋጀ ነው። የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ከሃላፊነታቸው እና ከመወሰን ስልጣናቸው ጋር የሚጋጭ ነገር ሲያጋጥማቸው የጥቅም ግጭት አጋጠማቸው ይባላል።

በስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የኮሚሽኑ አማካሪ አቶ እውነቴ አለነ ከፍተኛ ባልስልጣኑ ሊያጋጥሙት ከሚችሉ የጥቅም ግጭቶች መካከል፥ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎቹ በሚመሩት ተቋም ውስጥ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በሚመሩበት ጊዜ የጥቅም ግጭቶች ይከሰታሉ ተብሎ እንደሚታሰብ ይገልጻሉ።

አማካሪው እንደሚሉት ከሃብት ምዝገባ እና ማሳወቅ ጋር ተያይዞ መሰል ጉዳዮችን የሚያይ ድንጋጌ ቢኖርም፥ ድንጋጌው ግልጽነት የሚጎለው እና መሬት አውርዶ ለመተግበር አመቺነት የሌለው ነው።

እንደ ሀገር ባለስልጣኖቹ መሰል ጉዳዮችን የሚያስታርቁበት ወይም የሚከላከሉበት የራሱ የሆነ ወጥ ህግ የለም። ባለፉት አመታት ለመሰል ችግሮች መፍትሄ ሊሰጥ የሚችል ህግ ለማውጣት ሲሰራ ቢቆይም በተለያዩ ምክንያቶች እውን ሊሆን አለመቻሉንም ተናግረዋል።

አሁን ላይም ይህን ህግ አውጥቶ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።

አንድ ባለስልጣን ከቤተሰብ እና የቅርብ ከሚላቸው ዘመዶች ውጭ ሊቀበለው ስለማይገባው ስጦታ፣ ግብዣ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በግልፅ ገደብ የሚያስቀምጥ መሆኑንም አንስተዋል።

ባለስልጣኑም ከመሰል ችግሮች ራሱን መጠበቅ ካልቻለ ሊወሰዱ ስለሚችሉ እርምጃዎች የሚያስረዱ ይዘቶች የተካተቱበት መሆኑንም አስረድተዋል።

የስነ ምግባር ደምቡ ባለስልጣናትን ተጠያቂ ከማድረግ ባለፈ በህዝብ እና በከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች መካከል ያለውን ያለመተማመን ክፍተት ለመሙላት አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ታምኖበታል።

በትእግስት አብርሃም – FBC

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *