“Our true nationality is mankind.”H.G.

አብይ አሕመድ – ደህና ይሰንብቱ? ትህነግ ወደ መንበር?

ለትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር /ትህነግ፣ ኦዴፓ ተላላኪ በነበረበት ዘመን የአብራክ ልጅ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። ኦነግ ደግሞ በወቅቱ “ አልላላክም ” ብሎ ስለነበር አገር ጥሎ እንዲሰደድ የተፈረደበት እንግዴው ነበር። ዛሬ ዘመን ተቀይሮ ኦዴፓ በአዳዲስ ሃይሉና በቅንጅት በተደረገ ትግል “ አልላላክም” ሲል ጠላት ሆነ። እንግዴ ልጅ ሆነ። ውታፍ ነቃይ ተባለ። ባንዳ ተባለ። ከሃጂ ተባለ። እንደተፈጠረው እንዲጠፋ ተወሰነበት። ኦነግ በደጋፊዎቹና በመሪዎቹ ላይ የደረሰው አጸያፊ ተግባር ተዘንግቶ ኦዴፓን እንዲተካና በተራው የበኩር ልጅ እንዲሆን ደፋ ቀና ተይዟል።

ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ በትህነግ የደረሰበት የግፍ መአት እንዴት ይዘነጋል? መከረኛው የኦሮሞ ህዝብ በቶርቸር፣ በአልሞ ተኳሾች ግድያ፣ በእስር፣ በመሸማቀቅ፣ በስደት፣ ሃብቱን በመነጠቅ፣ ማቅ ለብሶ የቆዘመበት ዘመን ለትህነግ አይታየውም። ትህነግ ይህን ጸያፍ ተግባሩን የፈጸመው ይህ አሁን ያለው ትውልድ ፊት መሆኑንን፣ አንዳንዱም ሃዘን ገና ያልጠገገ መሆኑንን ረስቶ የኦሮሞን ሕዝብ በፈረቃ ሊነዳ እየዳከረ ነው።

የኦሮሞ ሕዝብ በውክልና እንደ ልማዱ አንጠልጥሎ ወደ አራት ኪሎ በውክልና ለመመለስ እንደ ቀድሞ በገሃድ ሳይሆን ህልሙን በውክልናና በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ “ቢሉሱማውን” አፋፍሟል። አሳዛኙ ጉዳይ ይህንኑ የትህነግ “ ሴራ” በመሸከም እንወክለዋለን በሚሉት ሕዝብ ላይ ለመጫን እዛና እዚህ የሚንከላወሱ ወገኖች ጉዳይ ሆኗል። እነዚሁ ክፍሎች በስፋት ተቃውሞ እየተሰነዘረባቸውና ጥያቄ ውስጥ እየገቡ መሆኑም እየተመለከተ ነው። የኦሮሚያን ጉዳይ ከላይ አነሳሁት እንጂ በአማራ ክልልም ትህነግን “ ወግድ” ያለውን አዴፓን ለማሰወገድ ተመሳሳይ ሩጫ አለ። ሴራና የውክልና ማተራመስ!!

ትህነግ ህልመኛ ወይስ ዳግም ነጋሽ

ገና በዳዴ ሳይሄድ በየስርቻው፣ በየመዋቅሩ፣ በየቢሮው፣ በተገኘበት ሁሉ ፈንጂ የተቀበረበት የዶክተር አብይ መንግስት መዛሉን አፍቃሪ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር / ትህነግ ደጋፊና ተከፋይ የዲጂታል ፊት አውራሪዎች እየገለጹ ነው። በተመሳሳይ ከኦሮሞና አማራ አብራክ የወጡ ወይም እንደወጡ የሚናገሩ ይህንኑ የዶከተር አብይን አስተዳደር የማዛል ዘመቻውን ዘይት እያርከፈከፉበት ይገኛሉ። አብዛኞች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በዘይቱ ላይ እየፈሰሱ ነው። እውን ዶክተር አብይ በትህነግ እቅድ መሰረት” ደህና ሰንብቱ” ይባሉ ይሆን?

ትህነግ እንደ ስትራቴጂ ለሚከተለው አብይን የመብላት መንገድ የአውራ ጣታቸውን እነሚቀስሩለት በይፋ የተናገሩት የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህር አስመላሽ ዮሀንስ (ዶ/ር) በአማራ ክልል አዴፓ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሕዝባዊ ድጋፍ ማጣቱን፣ በተመሳሳይ ኦዴፓም እንዲሁ ህዝብ እንደገፋው በጽሁፋቸው ያትታሉ። 

በምትካቸው በአማራ ክልል አብን፣ በኦሮሚያ ኦነግ ሙሉ የህዝብ ድጋፍ እንዳላቸው ያትቱና በትግራይ ትህነግ ያለተቀናቃኝ ዋንጫውን እንደሚያነሳ ያክላሉ። በውጤቱም ዶከተር አብይ ኦዴፓን ወክለው አገር መምራት የሚያስችል እድል ያጡና በዛው ያከትማልቸዋል ባይ ናቸው። 

ስለ ትህነግና ኦነግና፣ ትህነግና አብን ትሥሥር ወይም የመቆራኘት ጉዳይ ምንም ያላነሱት የህግ ምሁሩ አስመላሽ ዮሃንስ፣ ትህነግ ምርጫው እንዳይራዘም የሚወተውተው በዚህ ምክንያት መሆኑንን ያስረዳሉ። አያይዘውም በዚሁ ከላይ ባነሱት የራሳቸው ጭብጥ መነሻ ዶክተር አብይ ምርጫው እንዲራዘም ሊያደርጉ እነደሚችሉ ይሰጋሉ። እሳቸው ስጋት በገቡበት ጉዳይ ግን ዶከተር አብይም ሆነ ፓርቲያቸው ኢህአዴግ ምርጫው በታቀደለት የጊዜ ገደብ እንደሚካሄድ በተደጋጋሚ ይፋ አድርገዋል። አንዳንድ ፓርቲዎች ይራዘም የሚል ድምጽ ከማሰማታቸው በቀር። ምንም ይሁን ምን ግን እንደ እሳቸው ገለጻ ትህነግን ባይገልጹም ትንተናው ኦነግና አብን መጪውን ምርጫ ያሸንፋሉ።

ኦነግ ምርጫ ያሸንፋል ሲባል ምን ማለት ነው? የትኛው ኦነግ?

ኦነግ በኢትዮጵያ እድሜ ጠገብ የነጻ አውጪ ቡድን ነው። ሲቋቋም በሸዋ ልጆች የሚመራ የነበረ ቢሆንም ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ግን መሪነቱን የወለጋና አካባቢው ተወላጆች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተረክበው ቻርተሩን ካረቀቁ በሁዋላ አንዴ ፓርላማ፣ አንዴ ኤርትራ፣ አንዴ ጫካ እያለ እዚህ ደርሷል። ኦነግ ፖለቲካዊ ሸፍጥ ቢፈጸምበትም ጃዋርን ጨምሮ የተሳሳተ የትግል መስመር ይከተል የነበረና የከሸፈ ድርጅት እያሉ በይፋ ሲያወግዙት ነበር።

ከሽግግር መንግስቱ እንዲገፋ ተደርጎ ከአገር ከወጣ በሁዋላ ለአራትና ለአምስት ቦታ ሲከፋፈል የኖረው ኦነግ ብዙ ያልጠሩ ጉዳዮች እንዳሉበት ራሳቸውን የኦሮሞ ተቆርቋሪ አድርገው የሚጠሩ አካላት የሚናገሩት ጉዳይ ነው። እነዚህ ጉዶች ከምርጫ መቃረብ ጋር ይፋ እንደሚሆኑ ግምት አለ። ለሁሉም ግን አሁን የተፈጠረውን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ተከትሎ ወደ አገር ቤት የገቡት የኦነግ ክፍሎች አራት ናቸው።

ኦነግ የተባበረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን  /ኦነግ ዩኒት/ በአቶ ገላሳ ዲልቦ የሚመራ፣ የሽግግር ኦሮሞ ነፃነት ግንባርን / ኦነግ ትራንዚሽን/ አባነጋ ጃራ የሚመራ፣ ኦነግ ሸኔ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራና በብርጋዴል ጄነራል ከማል ገልቾ የሚመራው ኦሮሞ አንድነት ነፃነት ግንባር የሰላማዊ ትግል ጥሪውን አክብረው ወደ አገር ቤት ቢመለሱም፣ አቶ ዳውድ የሚመሩት ኦነግ ሸኔ ታቅዶ ይሁን አይሁን መረጃ ማቅረብ ባይቻልም ለሶስት መከፈሉ ይታወቃል። መሳሪያ ያነሱና ጫካ የገቡ፣ ከውጭ ሆነው ጫካ ያለውን ሃይል የሚደጉሙ አመራሮችና በዴሞክራሲያዊ መንገድ አገር ቤት ቁጭ ብሎ የሚንቀሳቀሰው ክፍል ናቸው ክፍልፋዮቹ። ይህንን ክፍልፋይ የታቀደና ማዕከላዊ መንግስቱን ከምርጫ በፊት አስገድዶ ስልጣን ለመቀማት የሚደረግ የትግል ስልት እንደሆነ የሚገልጹ ቢኖሩም፣ አቶ ዳውድ ” ጫካ ያለውን ቡድን አላውቀውም” ይሉታል።

ይህ በንዲህ እንዳለ በጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ የሚመራው ኦዴፓ  በአባ ነጋ ከሚመራው የሽግግር ኦሮሞ ነፃነት ግንባርን / ኦነግ ትራንዚሽን/ ጋር ወደ ውህደት የሚወስዳቸውን ስምምነት ከስምንት ወር በፊት መፈራረማቸው አይዘነጋም። ይህንን የሚያስታውሱና ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አካላት፣ የገላሳ ዲልቦና የአባ ነጋ ስምምነት ሲጠናቀቅ፣ ኦዴፓ ውህደት ለማድረግ እየተጠባበቀ መሆኑን ይናገራሉ። እንደተባለው አባ ነጋና ገላሳ ዲልቦ የሚመሩት ኦነግ ስምምነቱን ፈጽሞ፣ ጠቅላላ ጉባኤ አካሂዶ፣ ለምርጫ ቦርድ የኦነግ ስም እንደሚገባው አስታውቆ አመልክቷል። 

አቶ ዳውድ የሚመሩት ኦነግ ሸኔም በተመሳሳይ ኦነግ ስሙ መሆኑንን ጠቅሶ ለምርጫ ቦርድ አስገብቷል። ይህንኑ አስመክቶ ለቢቢሲ ሲናገሩ  “… የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አንድ ለመሆንና ለመዋሃድም እየሰራን ነው ኦነግን በተመለከተ ግን እኛም የኦሮሞ ሕዝብም የሚያውቀው አንድ ኦነግ ነው ያለው” ብለዋል። አባ ነጋ በበኩላቸው  “ምርጫ ቦርድ መመዝገብ ሕጋዊ ግዴታችን ነው። መመዝገብ ስላለብንም ነው ሂደቱን የጀመርነው። ኦነግን አንድ ድርጅት የማድረግ ሥራ ግን የፖለቲካ ሥራ ነው። እየተነጋገርንበት ነው። በቅርቡ ጨርሰን አንድ ንግግር እናደርገዋለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ሁለቱም እንደሚሉት አንድ የመሆን ንግግር አለ። ግን በየፊናቸው “ኦነግ” የሚለውን የመታገያ ስም የግላቸው ለማድረግ ማመልከቻ አስገብተዋል። በ1991 ኦነግ የሚለውን ስም አስመዝግበው ሲጠቀሙበት የነበሩት አቶ ገላሳ ዲልቦ እንደሆኑ የሰነድ ማስረጃዎች ያሳያሉ። በዚሁ የስም ጉዳይም በአሜሪካን አገር ፍርድ ቤት የደረሰ ክርክር ተደርጎ አቶ ገላሳ ዲልቦ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በተሰጣቸው ሰነድ አማካይነት አቶ ዳውድን በፍርድ ቤት መርታታቸውም የሚታወስ ነው።

እንግዲህ የኦነግን የባለቤትነት ጥያቄ የያዘው ምርጫ ቦርድ ጉዳዩን ይዞ እየመረመረው መሆኑንን አስታውቋል። ዛሬ ጥያቄ ያቀረበው የአባ ነጋ ጅራ ኦነግና የገላሳ ዲልቦ ኦነግ በኦፊሴል በመዋሃዳቸና አባ ነጋ ሊቀመንበር፣ የቄሮ መሪ የነበረው ወጣት ምክትል ሊቀመንበር መደረጋቸው ይፋ ሆኗል። በዚህ መነሻ ምርጫውን የትኛው ኦነግ በበላይነት ያጠናቅቀዋል? የሚለው ጉዳይ ከወዲሁ ፍንጭ እያሳየ መሆኑንን ስለ ጉዳይ ዝርዝር መረጃ ያላቸው ከወዲሁ እየገለጹ ነው።

እዚህ ላይ የሚነሳው ጠረጴዛ ላይ ቁጭ ያለው የኦዴፓና የአባ ነጋ ጅራ ኦነግ የውህደት ስምምነት ጉዳይ ነው። አባ ነጋ ጅራ በወለጋና አካባቢው፣ እንዲሁም በሃረርጌ ድጋፍ እንዳላቸው ከሚነገርላቸውን ገላሳ ዲልቦ ጋር ውል ፈጽመውና ጡንቻ ጨምረው ወደ ኦዴፓ ስምምነታቸው ፊታቸውን ካዞሩ፣ ምርጫ ቦርድ ቀድመው ለተመዘገቡትና በሰነድ ለሚታወቀው የገላሳ ዲልቦ አካል ለሆነው የአባ ነጋ ኦነግ ፈቃዱን ከሰጠ፣ ኦዴፓና ኦዴፓ ጠረጴዛ ላይ ያለውን ስምምነት ፈጻጽሞ በኦነግ ስም ወደ ምርጫ የሚገባበት እድሉ ከደጅ ነው።

በአባ ነጋ ጅራ የሚመራው ኦነግ አመራር የሆኑ እንዳጫወቱኝ ከሆነ በድፍን ሸዋ፣ በወለጋና አካባቢው፣ በኢሏባቦር፣ በሃረርጌ፣ በአርሲ፣ በጅማ፣ በባሌ አብዛኛው ክፍል ፓርቲያቸው አብላጫ በቂ ድምጽ እንደሚያገኝ ባይጠራጠሩም፣ ኦዴፓ ሸዋ፣ ጀማ፣ አርሲ፣ ምዕራብ ሃርርጌ እንዲሁም በበርካታ ቦታዎች እንደሚመረጥ ግምታቸው ሰፊ ነው። እናም የሁለቱ ጥምረት በኦሮሚያ በቀላሉ መንግስት መመስረት የሚያስችል ይሆናል። አሁንም ቢሆን እነ ጀነራል ሃይሉ ጎንፋን ጨምሮ ፓርቲያቸው ከኦዴፓ ጋር በሰላም እየሰሩ መሆናቸውን እንደ ማስረጃ አንስተውልኛል።

ስለ ትህነግ እምነትና ከላይ በመግቢያው ስለተገለጸው የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ምሁር ትንተና በድርጅታቸው ስም ሳይሆን በግል ” በአባ ነጋ ጅራና በገላሳ ዲልቦ የሚመሩት ድርጅቶች/ አሁን አንድ ሆነዋል/ ወደ ቀድሞው መንገድ አያዩም። እንይም ቢሉ ምክር ቤቱና አባላቱ አይፈቅዱም። ኦዴፓን ገፍቶ ከትህነግ ጋር የሚዶልቱበት ምድራዊ መሰረት የለም። ጉዳዩ በኦሮምኛ እንደሚባለው ዝንጀሮ ቁጫጭን ወሃ ቅጂልኝ ገላዬን ልታጠብ እንዳለችው ነው” ሲሉ አሰተያየታቸውን አካፍለውኛል። አያይዘውም ” የኢትዮጵያ እስር ቤቶች ቋንቋ ሙሉ በሙሉ ኦሮምኛ የሆነበትን ወቅት እንዲሁ በቀላሉ መርሳት የሚቻል አይሆንም ” ሲሉ ከትህነግ ጋር የጎን የሚያሴሩትን ወርፈዋል። እኚሁ ወዳጄ እንዳሉ አስተያየቱ የግላቸው ቢሆንም የፓርቲው አቋም እንደሆነ ጠቁመው ከምኞት ይልቅ በትግራይም በተመሳሳይ አማራጭ ሃሳቦች በነጻነት ለህዝብ እንዲቀርብ እንደ ምሁር ቢሰብኩ እንደሚሻል መክረዋቸዋል። 

ትህነግ በአማራ ክልል – የሴራ ፖለቲካ 

የአማራ ክልል ፖለቲካና ውስጣዊ ግጭት የሚያስፈራቸው ጥቂት አይደሉም። የአማራ ክልል መሪዎች ላይ እስካሁን በምርመራ ይፋ ያልሆነ ግድያ ሲፈጸም የአዴፓ ጉዳይ እንዳከተመ ተደርጎ መወሰዱ የሚታወስ ነው። ይህንኑ ግድያ አስመልክቶ በእሽቅድድም የተቃወመውና ኦዴፓን ተጠያቂ ያደረገው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር መሆኑ የበርካታ በሳል ፖለቲከኞችን ቀልብ መሳቡም የሚታወቅ ነው።

“እረኛውን ምታ በጎቹ ይበተናሉ” የሚል መርህ አንግቦ የሚንቀሳቀሰው ዲጂታል ወያኔ ያሰማራቸው የማህበራዊ ገጽ ሰራዊቶቹ በተለያየ ስም ይህንኑ ግድያ አስመልክቶ የሚያራቡት ዜናና ዓላማ ያለው ቅስቀሳ ያበሳጨው አዴፓ በታሪኩ ተሰምቶ የማያውቅ እንደ መብረቅ የታየ የምላሽ መግለጫ ሰጥቶ ነበር። በምላሹ “ ተገንጣይ” እያለ የከረመ የብሶት ስሜቱን ያወረደው አዴፓ የክልሉን ሰላም ማረጋጋቱን ቢያስታውቅም ዛሬም ድረስ ችግሩ እበራፍ ላይ መሆኑንን በርካቶች ይመሰክራሉ።

ዛሬ በአማራ ክልል ጎጃሜ፣ ጎንደሬ፣ ሸዌ፣ ወሎ፣ ወዘተ እየተባለ የሚሰራጨው የመከፋፈል ስልት ሰፊውን አማራ ለማዳከምና አሽመድምዶ ለመጣል ሲሆን፣ ዘመቻው በድርጅት ደረጃና በበጀት የሚደገፍ እንደሆነ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይናገራሉ። እንደውም በአማራ ክልል “ሴራችን ተሳክቷል” የሚል ድምዳሜ ላይ እንደተደረሰ መረጃ ያላቸው እየተነፈሱ ነው። እውነታው ይህ ቢሆንም በስመ አማራ ስም የሚንቀሳቀሱ ግን ሊሰሙና መጪውን ጊዜ ለመመልከት ሲታትሩ አይታዩም። የድርሻዬን በሚል አይነት ክልሉን ወደውም ይሁን ተገዝተው እየናጡት ነው። በዚህም ሳቢያ ሕዝቡ ማግነት የሚገባውን ከማግኘት ይልቅ ያለውን እያጣ ነው።

አማራን እንወዳለን የሚሉም ሆነ ለአማራ እንታገላለን የሚሉ ወገኖች “ ሴራውን” ማጤን አልቻሉም የሚሉ ወገኖች፣ የአማራ ክልል ነዋሪዎች፣ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች በአቡሸማኔ ላይ ተቀምጠው የሚጋልቡትን የፖለቲካ ግልቢያ ትተው በሰላማዊ መንገድ ከአዴፓ ጋር መምከሩ እንደሚሻላቸው ይመክራሉ። ለጊዜው ዝርዝር ውስጥ መግባት ባያስፈልግም አሁን አማራ ክልል ውስጥ እየጨሰ ያለው የቀውስ ረመጥ መላ ካልተባለ አድሮ ይህንን ትልቅ ሕዝብ ለውርደትና የሚዳርግ፣ እስከወዲያኛው ከማይወጣው ችግር ውስጥ የሚቀረቅር አደጋ እንደሚያስከትል ከግምት በላይ መናገር ይቻላል።

በኦሮሚያ ተቃዋሚዎችን ለማስማማት ሩጫ አለ። በአማራ ክልል ግን ሁለት ድርጅት ማስማማት ያልቻሉ የክልሉ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ሁሉን ትተው አቅማቸውን ሁሉ ተጠቅመው አዴፓንና አብን ወደ አንድ መድረክ የማምጣት ስራ እንዲያከናውኑ የሚመክሩ ጥቂት አይደሉም። አብንም ከምስረታው ጀምሮ የሚነሳበትን የንክኪ ጥያቄ ግልጥ በማድረግ፣ ችግር ያለባቸው አካላት ካሉ በመለየት ራሱ አጽድቶ ሊቀርብ እንደሚገባ የሚጠቁም በርካታ ናቸው።

በአማራ ክልል አዴፓ “ ሞቷል” በሚል ግምገማ በባዶ ቤት ለመፈንጨት ይቻል ዘንድ ሴራው ውስጥ ውስጡ እየጋመ እንደሆነና፣ ይህንኑ ሴራ ለመተግበር የሚልከሰከሱ መኖራቸውን የሚጠቁሙ “ የአማራን ሕዝብ እንወዳለን፣ ከክፉም እንታደጋለን የሚሉ ሁሉ ቸግሮች በሰላም ተፈተው በክልሉ አስተማማኝ ጸጥታ እንዲሰፍን ቅድሚያ እንዲሰጡ አብዝተው የሚወተውቱ “ ወንድማማቾች የውስጥን ችግራቸውን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ያልቻሉበት ምክንያት አይገባንም” ሲሉም ይደመጣሉ።

ትህነግ ዛሬ ላይ መገንጠልን እንደማስፈራሪያና እንደ አማራጭ አስቀምጦ፣ 300 ሺህ በላይ ሰራዊት ለክፉ ቀን አዘጋጅቶ፣ በበጀትና በመሳሪያ ራሱን አደራጅቶ፣ ጽንፈኞችን እየመራ ወደ አራት ኪሎ ለመጋለብ ያስቀመጠው አጭር ጊዜ አንድ ዓመት እንደሆነ በዲጂታል ሰራዊት አመራሮቻቸው ይፋ እየተናገሩ ነው። ለማንኛውም በሚል የአየር ትራንስፖርትም ለመጀመር ዝግጅታቸውን አተናቀዋል። አማራውን በተመሳሳይ በሴራ አባልተው ሽባ ለማድረግ ክንዳቸውን የሚችሉት ድረስ እየዘረጉ፣ እያስታጠቁና በማንነት ሰበብ እያሳመጹ እንደሆነ የክልሉ አመራሮች ይፋ ያደረጉት፣ ሕዝብም የሚያውቀው ሃቅ ነው። ግና አማራ ክልል ዛሬም እርስ በርሱ ይናከሳል።

መጨረሻው

ኢህአዴግ ወደ አንድ ፓርቲነት እንዲመጣ የተወሰነው ከዛሬ አስራ ሶስት ዓመት በፊት ቢሆንም በትህነግ ተንኮል ምክንያት እውን ሳይሆን ቀርቷል። ዛሬ ዶክተር አብይና መሰሎቻቸው አጋር ፓርቲዎችን ይዘው ኢህአዴግን ወደ አንድ ፓርቲነት ለማሸጋገር እየሰሩ ነው። ከአንድ አጋር ክልል ውጪ የተቀሩት ሃሳቡን ተቀብለውታል። እናም ትህነግ ከኢህአዴግ ህብረት መውጣት የራሱ ውሳኔ ይሆናል።

አሁን ባለው አካሄድ ኢህአዴግ በስም ደረጃ እንጂ በገቢር እንደሌለ የሚሰብኩት የትህነግ ሃላፊዎችና ደጋፊዎች መነሻ ፍርሃታቸው እነሱን ያገለለ አንድ ትልቅ አገራዊ ፓርቲ እንዳይቋቋም ነው። በዚም ምክንያት ኦሮሚያ የአቶ ዳውድ ኦነግ፣ በአማራ አብን፣ ሲዳማን ከደቡብ ወደ ስልጣን እንዲመጡ ስራውን እየሰራ ነው። ምርጫው እንዳይራዘምም ከዓመት በፊት በሚዲያና በተገኘው መድረክ ሁሉ ያለማቋረጥ እየወተወተ የቆየው ለዚሁ ህልሙ ነው።

እንደ ትህነግ ምኞት ኦዲፒንና አዴፓን ድሮ የሰራቸው እሱ ስለሆነና ዛሬ እነሱ ህብረት ፈጥረው መሪ ሲሆኑ በገዛ ፈቃዱ ካሰበው የጊዜ ቀመር ውጭ ወደ ትግራይ በማፈግፈጉ በእልህ ሊያጠፋቸው ወስኗል። በዚም መሰረት የሴራ ፖለቲካ በማምረትና ሴራ አስፈጻሚዎችን በማሰማራት መሪዎችን ከህዝብ መነጠል፣ ይጠቅሙናል ካላቸው ጋር በጎንና በገሃድ መሸረብ፣ ላይ ተጠምዶ እየታየ ነው።

ከዚህም በላይ በኢህአዴግ ደረጃ ስብሰባ ተቀምጦ የሚወስናቸውን ጉዳዮች ሲተገበሩ አደባባይ እየወጣ መኮነን፣ ማሳጣት፣ መስመር ማሳት ላይ የተጠመደው ከላይ ያቀደውን እቅዱን ለማስፈጸም ካለው ጉጉት የተነሳ ነው። የልዩነት ሃሳቦችን የሚያበዛው እንደ አማራጭ ያስቀመጠው የመገንጠል የቆየ እቅዱን ኢትዮጵያዊው የትግራይ ሕዝብ እንዳይቃወም ለማድረግ ሲል እንደሆነም በስፋት አስተያየት ይሰጣል።

እስከ ምርጫ ቀን የተቆረጠላቸው ዶከተር አብይ ትህነግን ወደ ስልጣን ያመጡት ታላላቆቹ አገራት ከጎናቸው ናቸው። አብረዋቸው እንደሆኑ በይፋ እየገለጹ ነው። አንዳንድ ትርጉማቸው የማይገባ ውልም እየተፈራረሙ ነው። ከሁሉም በላይ ግን በኦሮሚያ የአባነጋ ጅራና የገላሳ ዲልቦ ጥምረት ዝም ብሎ የተደረገ እንዳልሆነ የሚናገሩ ወገኖች “ ለትህነግ ህልም መፍትሄ ተበጅቷል” ሲሉ ይደመጣሉ።

የዳውድ ኢብሳ ሸኔ የተወሰነ ድምጽ ቢያገኝ ከሶስቱ የጥምረት ድምጽ ሊበልጥ ስለማይችል፣ በከፊል  ከአንድ አጋር ክልል በቀር ሁሉም የዶክተር አብይ ደጋፊ መሆናቸው አንድ ላይ ሲደመር መንግስት ለመመስረት እንደሚያስችላቸው በስሌት ደረጃ ያሰሉ ይመሰክራሉ። እናም ትህነግ ይህንን ስለሚረዳ የሴራ ፖለቲካው ላይ እስከ መጪው ምርጫ ድረስ ሙጭጭ ብሎ እንደሚቀጥል ይታመናል። ለክ አሁን ገዳዩ የትምህርት ፖሊሲ ሲቀየር “ አሃዳዊ “ ብሎ ስም ፈጥሮ እንደሚጮኸው!!

በነገራችን ላይ የትምህርት ፖሊሲው 6፤2፤4 ሆነ ተባለ እንጂ በክሎች መብት ጉዳይ የተቀየረ ህገ መንግስታዊ ለውጥ ሳይኖር “አሃዳዊ የትምህርት ፖሊሲ ” እንደተነደፈ አድርጎ መቀስቀስ የዚሁ የማተራመስ እቅድ አካል ካልሆነ በቀር ሌላ ምንም ስም ሊሰጠው አይችልም። መነሻው አማራንና አማርኛን ጥላቻ ብቻ ነው። ይህንን የሚረዱ ወገኖች በተለይም የአማራ ክልል ጉዳይ ያገባናል የሚሉ በዚህ የጥላቻ ጥግ መሰረት ራሳቸውን ፈትሸው ከትህነግ ጋር የሚዳሩትን ድሪያ በማቆም ለክልሉ ሰላም ቢሰሩ ደግ ይሆናል። ዛሬ አማራ ክልል ስልጣን ሳይሆን መረጋጋትና አስተማማኝ አንድነት ቅድሚያ ጉዳይ ነውና።

አዴፓም ቢሆን ያለበትን ችግር በመቅረፍ፣ አግባብነት ከጎደለው እስርና ማሳደድ ተቆጥቦ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ሊመጣና አብሮ ለመስራት ያለውን ፈቃደኛነት ሊያሳይ ይገባል። ይህ ሲባል ግን የተገደሉትን ምርጥ የአማራና የኢትዮጵያ ልጆች ደም ህግና ደንብ በሚፈቅደው መሰረት መርምሮ ከዳር ሊያደርስ ግድ ነው። የውክልና ዓላማ የሚያራምዱ ማናቸውም ቢሆኑ የሕዝብ ጠላቶች ናቸውና።

አሳዬ በላይ አዲስ አበባ ድርጅት ዘርፍ 

ዝግጅት ክፍሉ – ይህ ጽሁፍ የጸሃፊው እምነት ብቻ ነው

0Shares
0