ግለሰቧ በምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ ትምህርት ቤት ሊገነቡ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ ትናንት በኢንጅነር ጸደቀ ይሁኔ ደሴ ላይ አዳሪ ትምህርት ቤት ተገንብቶ ሥራ በመጀመሩ ባለብሩህ አዕምሮ የአማራ ክልል ልጆች እየተማሩበት ይገኛል፡፡

ቀጥሎም የዳስ ትምህርት ቤት መኖሩን የሰማው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ ስላሴ ‹‹ እንዴት!? ይህማ አይደረግም! ቦታውን ሄጄ ማየት አለብኝ!›› ብሎ ወሰነ እና ጉዞውን ወደ ዋጎች ምድር አደረገ፡፡ ዜናው እውነት ሆኖ አገኘው፡፡ ከዚያው እንዳለም ወሰነ፤ በሦስት ወራት ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ አድርጎ ለማስገንባትና ለ2012 የትምህርት ዘመን ዝግጁ ለማድረግ፡፡
ኃይሌ ቃሉን ተገበረና ብዙዎቹን አስደመመ፤ ወደ ስፍራው ተመልሶ ሄዶም አስመርቆ አስረከበ፡፡ ደብረ ብርሃን ላይም አንድ በጎ አድራጊ ኢትዮጵያዊት አዳሪ ትምህርት ቤት እያስገነቡ እንደሆነ ሰምተናል፤ ከስፍራው ሄደንም አረጋግጠናል፡፡

ዛሬ ደግሞ ሌላ ዜና! ሌላ የአዕምሮ ልማት፣ ሌላ የትውልድ ቀረጻ ጉዞ! ወሬው የተሰማው ከወደ ምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ ነው፡፡ ወይዘሮ አያልነሽ ባይሌ የተባሉት በጎ አድራጊ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ማስተማሪያ ትምህርት ቤት ነው የሚያስገነቡት፤ ለግንባታው ደግሞ 12 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያስፈልግ ታውቋል፡፡

በጎ አድራጊዋ በምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ ዘመናዊ የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት ለማስገንባት ቦታ ተረክበዋል፡፡ ‹‹የሕዝብን አዕምሮ መቀየር ለሁሉም ነገር ቁልፍ ነው›› በማለት በበጎ ተግባሩ ላይ ለመሰማራት እንደፈለጉ የማቻከል ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መላኩ ሙሉሀብት ለአብመድ ዛሬ ነሐሴ 22/2011 ዓ.ም በስልክ አስታውቀዋል፡፡

በበጎ አድራጊዋ ወይዘሮ አያልነሽ ባይሌ የተቋቋመው አያልነሽ የበጎ አድራጎት ድርጅት በወረዳው ኳሽባ በተባለ ቀበሌ ላይ ነው ትምህርት ቤቱን የሚገነባው፡፡ ትምህርት ቤቱ ሲገነባ ሩቅ ቦታ ተጉዘው መማር ላልቻሉ የአካባቢዉ ህጻናት እፎይታ የሚሰጥ እንደሆነ የገለጸው የማቻከል ወረዳ አስተዳደር ግለሰቧ ለምትገነባው ትምህርት ቤት 1 ነጥብ 8 ሄክታር መሬት ማስረከቡንም ነው ያስታወቀው፡፡

የትምህርት ቤቱ ግንባታ በቀጣዩ ዓመት እንደሚጀመር ታውቋል፡፡ ግንባታው ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የመማሪያ ክፍል፣ ቤተ መጽሀፍት እና ቤተ ሙከራ ተሟልቶለት በ 5 ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ማስታወቃቸውንም ዋና አስተዳዳሪው አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡ እስከዚያው ድረስ ደግሞ በአካባቢው ለሚገኝ ሌላ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ወንበር ድጋፍ እንዳደረጉ ዋና አስተዳዳሪው ነግረውናል፡፡ የግለሰቧን አርዓያነት ሌሎች እንዲከተሉም ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በጎ አድራጊ ግለሰቧን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፤ እንዳገኘናቸው የእርሳቸውን ሀሳብ አካትተን እናቀርባለን፡፡ በየአካባቢው የምትገኙ ባለሀብቶችስ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት የትውልድን አዕምሮ ለማልማት ምን እየሰራችሁ ነው?

በምስጋናው ብርሃኔ (አብመድ)

ፎቶ፡- ከማቻከል ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የቻይናው ሮኬት ስብርባሪ በኢትዮጵያ ቢወድቅ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *