Image may contain: Henok RG, smilingየወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን ፈርጥ የነበረችው ትንሿ ዜኒት ሙሐባ “ሖዴም ሽብር ሽብር…” አያለች ከጦሳ ተራራ ላይ እይተንደረደረ በሚወረወረው ሞገደኛ ድምጿ በአራቱም አቅጣጫ ታስተጋባለች። ይህንን ያልታሰበ የገበያ ስኬት አዝመራው እንዳሻተለት አርሶ አደር በየክፍለ-አገሩ ከሚቸበቸበው የካሴት ክር ሽያጭ ትርፉን የሚቃርመው የማራቶን ሙዚቃ ቤት አሳታሚ በጊዜው ይስተዋል በነበረው የአሳታሚዎች ፍክክር በለስ የቀናው ነጋዴ ሆኖ በመገኘት በሌሎቹ አሳታሚዎች ላይ ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ የሥራ ጫና አሳድሯል።
በአንድ በኩል ይችኑ ጉደኛ ልጅ በተሻለ ክፍያ ሁለተኛ ሥራ ማሰራት የሚሉት የዜኒትን ዱካ ሲያስሡ፤ የተቀሩት ደግሞ ተረኛዋን ዜኒት ሙሃባን አድኖ ለማግኘት ብርቱ ጥረት ላይ ይጠመዳሉ። “አያያዙን አይቶ ጭብጦውን ቀማው” በሚል የብልጣብልጥ ነጋዴነት መንገድ ተጉዘው የማራቶንን አዱኛ ለመንጠቅ ጥረት ያደረጉት፤ የማይበሉትን እንጀራ እንዳለሙ ህልማቸው ህልም ብቻ ሆኖ እንዲቀር የሚይስገድድ ዱብዳ ተፈጠረ፤ ሮጣ ያልጠገበቸው እና ብዙ ተስፋ የተጣለባት ወሎዬዋ ኮረዳ በሚያሳዝን መልኩ ካንዲት ታሪካዊ የካሴት ክር ውጪ ሌላ የምታስደምጠው ሥራ ሳይኖር በአጭር ተቀጨች። የሌላዋ ዜኒት ሙሃባ አሰሳ ከአምባሰል እስከ ራስ ደጀን ቀጥሎ ጣና ባሕር ዳር ቢደርሥም ለጊዜው ምንም ተስፋ የሚጣልበት ግኝት አልነበረም።
የአዲስ አበባ አድባር ምስጋና ይግባት እና ድንገት ተረኛዋን ዜኒት ሙሃባ ከጎንደር ክፍለ አገር ሊያስመጣ የሚችል አስደሳች ዜና ከማህሌታዊው ዜመኛ አበበ ብርሐኔ እጅ ላይ ተገኘ። “ዳሩ ምንዋጋ አለው አሺ አትልም !” ሲል ገራገሩ አበበ ብርሐኔ ተወልዶ ካደገባት የአዲስ ዘመን አውራጃ ቀዬ በአይናፋርነቷ እና በተስረቅራቂ ቅላጼዋ የሚያውቃትን አብሮ አደጉን አሰፉ ደባልቄን ለእድለኛው የናዲ ሙዚቃ ቤት አሳታሚ ጀባ አለ። የመጀመሪያውን የአዲስ አበባ የስልክ ጥሪ “እኔ ምንም አልፈልግም፤ አዲስ አበባም አልመጣም ትምህርቴን መማር ነው ምፈልገው፤ ድጋሚ እንዳይደውሉ!” ስትል የስልኩን ማናገሪያ በአቶ ሳህሉ ጆሮ ላይ የጠረቀመቸው ተሽኮርማሚዋ አሰፉ ደባልቄ፤ በገራገር የባላገርነት ሥነ-ልቦና እና ሐይማኖታዊ አስተዳደግ ተፅእኖ ስሟን እንኳን ደፈራ የማትጠራትን የእናት አገሯን መዲና አዲስ አበባ ከተማን እንኳን ለመርገጥ ብዙ ሌሊቶችን ያለ እንቅልፍ ማሳለፍ ነበረባት።
https://www.youtube.com/watch?v=WmR5HfQ7w1k
ዛሬ በሃያሏ አሜሪካ መዲና ውድ በሚባለው የንግድ ጎዳና በሥሟ በተመዘገበ ህንጻ ላይ ታዋቂ ምግብ ቤት ከፍታ እና ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ገንብታ በአገር አሜሪካ እጅግ ስኬታማ ከሚባሉ ጥቂት የአገሯ ልጆች ተርታ የምትመደብ ግለሰብ ለመሆን፤ አቶ ሳህሉ ተስፋ ባለመቁረጥ ደጋግመው የሞከሩትን የስልክ ጥሪ በስተመጨረሻ መመለስ ነበረባት።
አሰፉ ደባልቄ በአገሪቱ የገበያ ሙዚቃ (mainstreem music) ውስጥ እንደ ክስተት ከተገኙ እና እጅግ ማራኪ ድምጽ ካላቸው አንጎራጓሪዎች መካከል የምትመደብ ድምጻዊት ብትሆንም፤ በተፈጥሮዋ ባላት የበዛ ፍርሃት እና የባህል ተጽእኖ ምክንያት ድምጿ እንጂ ማንነቷ የማይታወቅ የኪነት ሰው ለመሆን ተገዳለች። በ1980 ዓ.ም ባሳተመቸው የመጀመሪያ የካሴት ክር ሥራዎ ወደ የገበያው ሙዚቃ በይፋ የተቀላቀለችው ድምጻዊት፤ በተፈጥሮ በተዳለችው አስደማሚ ድምጽ ምክንያት በዘመኑ ተወዳጅ የሚባሉት ዝነኛ እንስት ድምጻውያን ማግኘት ያልቻልሉትን ፈጣን ስኬት በተደጋጋሚ በማግኘት በተቃራኒ ጾታ ጥምረት ታላላቅ ከሚባሉ ድምጻውያን ጋራ ለመስራት ችላልች። አበበ ተሰማ፣ ኪሮስ ዓለማየሁ፣ አርጋው በዳሶ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ ጸጋዬ እሸቱ እና ኬኔዲ መንገሻ ወዘተ። “ኬኔዲን እኮ ያኔ አይደለም፤ ነገ የሚወለዱት ልጆች እንኳን ሊያውቁት የሚችሉት ድምጻዊ ነው።” ስትል እድለኛ ሆና አብራቸው እንድትሰራ የረዷትን ሰዎች ታመሰግናልች።
እስከ ዛሬ ድረሰ በተቃራኒ ጾታ የስንኝ ቅብብል የተሰሩ ጊዜ አይሽሬ ሙዚቃዎችን ስናዳምጥ በድምጿ ልዩነት የምናውቃት እና ላለፉት 30 ዓመታት ድምጿን ሳታሰማን አገሯን ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ ተመላልሳ የጎበኘችው አሰፉ ደባልቄ በጤና መኖሯን እንኳን የምንጠራጠር ብዙዎች ነበርን። “ለሁሉም ጊዜ አለው” እንዲል መጻፉ፤ ከብዙ የህይወት ውጣ ውረድ በኋላ በምድረ አሜሪካ የከበረች ነጋዴ ሆና ከርማ በናሆም አሳታሚ ያላሳለሰ ጥረት “አለሑኝ” ልትለን ችላለች። ለዚህም የአሣታሚው ናሆም ሬከርድስ ባለቤት አቶ ኤልያስ ፍቅሩ ምስጋና ይገባዋል።
የአሰፉ አዲስ አልበም የምትታወቅባቸውን ተወዳጅ ሥራዎቿን ቃናቸው እና ለዛቸው ሳይጓደል በሚገርም ሁኔታ በአዲስ መልክ የተጫወተቻቸውን ሙዚቃዎች ማካተቱ በጣም የሚደነቅ ሃሳብ እንደሆነ ብዙ አድናቂዎቿ ይስማሙበታል። ለዚህም ምክንያቱ ደገሞ አሰፉ ድሮም ቢሆን በሥራዎቹ እንጂ በሥሟ እምብዛም የማትታወቅ ድምጻዊ ባለመሆኑ ሰዎች ምርጥ አዳዲስ ሥራዎቿን ሰምተው፤ ቆየት ያሉትን ሲያደምጡ አሰፉ አውሎ ነፋስ አምጥቶ የጣላት የዘመኑ ዘፋኝ ሳትሆን ያቺ በጥቂት አስደማሚ ሥራዎቿ ምክንያት ለ30 ዓመታት በናፍቆት እና በጉጉት ስትጠበቅ የነበረችው አይናፋሯ አሰፉ (እማሆይ) እንደነበረች እንደሚያስረዳ ይናገራሉ። በአዲሱ አለበሟ ከቀድሞዎቹ የፋሲለደስ ባልደረቦቿ አበበ ብርሓኔ፣ ኢንጂነር ፋንታ ወጨፎ፣ አባይ መንግስት አንስቶ እስከ የቅርብ ጊዜዎቹ ባለንጀራዎቿ ሔኖክ ነጋሽ እና ይስማለም በርጋ ተሳትፈውበታል። አውዳመትን በድሮው የማይሰለች የሙዚቃ ቃና ለማክበር ጥሩ ጊዜ ላይ የተለቀቀ አዲስ ሥራ በመሆኑ የዘንድሮው እንቁጣጣሽ ልዩ ስጦታ (surprise) ልንለው እንችላልን።
https://youtu.be/Ma0Ono_nDFQ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *