ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

በህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ሊወያዩ ነው

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ግብፅና ሱዳን የፊታችን መስከረም ወር ላይ በካይሮ ሊወያዩ ነው።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የሶሰትዮች ውይይት ካደረጉ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል። ከዚህ ቀደም ሶስቱ ሀገራት የህዳሴው ግድብ ውሃ አያያዝና አለቃቀቅ እንዲሁም በናይል ተፋሰስ የታችኛው ሀገራት ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በሁለት አለማቀፍ ኩባንያዎች ሲያስጠኑት የነበረው ጥናት በሚፈለገው ደረጃ መጓዝ አልቻለም።

ይህ ጥናት በሚፈለገው ፍጥነት መሄድ ባለመቻሉም ሶስቱ ሀገራት አምስት አምስት ባለሙያዎችን አዋጥተው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ እንዴት ሊይዝ አንምደሚገባ ምክር ሀሳብ እንዲያቀርቡ የባለሙያዎች ቡድን አቋቁመው ነበር ።

የተቋቋመው የባለሙያዎች ቡድንም  የህዳሴው ግድብ በየዓመቱ  ምን ያህል መጠን ያለው ውሃን ይያዝ? በስንት ዓመትስ ይሙላ? የሚለውን አጥንቶ መጨረሱ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም ሶስቱ ሀገራት ለምክረ ሀሳቡ ተግባራዊነት መፈረም ሲጠበቅባቸው ግብጽ ባለመፈረሟ  ምክንያት  በጥናቱ ላይ አጠቃላይ ስምምነት ሳይደረስ ነገሮች ተጓተው ቆይተዋል።

በግድቡ አሞላል ላይ በሶስቱ ሀገራት የተቋቋመው የባለሙዎች ቡድን  ጥናት ግድቡ እስከ አምስት ዓመት ሊሞላ እንደሚችል እና በየዓመቱ ምን ያክል ውሃ እንደሚለቀቅ እንዲሁም እንደሚያዝ የሚያሳይ ነበር።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ  ከኤፍ ቢ ሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የግብጽ፣ የኢትዮጵያ አና የሱዳን መሪዎች በጥር ወር አዲስ አበባ ተገናኝተው የተጓተቱ ውይይቶች እንዲቀጥሉ ተስማምተው የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ከተወሰኑ ወራት ቆይቶ በኋላ ሱዳን  ባጋጠማት የፖለቲካ ችግር  ምክንያት ውይይቶች በታቀደላቸው ጊዜ ሊካሄዱ አልቻሉም ።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት  የግብጽ የውሃ ሚኒስትር መሃመድ አብደል አቲ ኢትዮጵያ መጥተው የነበረ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ፥ አመጣጡም ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ላይ ያደረገችውን የራሷን ጥናት ለማቅረብ መሆኑን  ተናግረዋል።

በግብጹ የውሃ ሚኒስትር በኩል በመጣው ጥናት መሰረትም የህዳሴ ግድብ ውሃ መሙላት ያለበት በሰባት ዓመታት ውስጥ ነው ። ሆኖም ሚኒሰትሩ ያቀረቡት ጥናት ከኢትዮጵያ ፍላጎት ጋር የተቃረነ መሆኑን የራሷ የግብጽ መገናኛ ብዙሀንም ሲዘግቡት የቆየ ነው።

ሃይል ማመንጨት ከጀመረ በኋላም አዲስ አበባ፣ ካይሮና ካርቱም ጽህፈት ቤቶች ተቋቁመው የሶስቱም ሀገራት ባለሙያዎች ቁጥጥር ያድርጉበት የሚል ሀሳብም አለበት።

እነዚህና ሌሎች በግብጽ በኩል የቀረቡት ፍላጎቶች ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ ካላት ፍላጎት የማይጣጣም መሆኑም የሚታወቅ ነው። የውሃ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ፤ የዚህ የግብጽ ሰነድ ምላሽ የሚሰጥ ደብዳቤ መጻፉን ተናግረዋል።

ሁሉንም ሀገራት የማይጎዳ ጥናት በኢትዮጵያ ሀሳብ አመንጭነት ተሰርቷል፤ የማይሆን ጥናት መውሰድ ለኢትዮጵያ የማያዋጣ መሆኑንም አክለዋል። በሌላ በኩል ግብጽ በራሷ አስጠንታ ባቀረበችው ሰነድ  ዙሪያ ለመወያየትም ሱዳን አስፈላጊ መሆኗን ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ገልጸዋል።

ሱዳን ባለችበት የፖሊቲካ ሁኔታ ምክንያት በውሃ ዘርፍ የሚደራደር ሚኒስትር አለመሰየሟን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ይህን ታሳቢ በማድረግም በመስከረም ወር የሶስትዮሹ ውይይት ይደረጋል ነው ያሉት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት አሁን ያለበትን  ሁኔታም በተመለከተም የሃይል ማመንጫ ተርባይኖች ተከላና የብረታ ብረት ስራዎች ከሜቴክ ተቀምተው ለሌሎች የውጭ ኩባንያዎች ከተሰጡ በኃላ በግንባታው ላይ ለውጦች እየታዩ መሆኑን አንስተዋል።

ከአንድ ዓመት ከሶስት ወራት በኋላም ሃይል ወደ ማመንጨት ይገባሉ ተብለው ለሚጠበቁት ሁለት የሃይል ማመንጫ ተርባይኖች የሚያስፈልጉ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።

የሃይል ማመንጫ ተርባይኖች የሚቀመጡባቸው ቦታዎች የብየዳ ስራ በመጠናቀቅ  ላይ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፥ በተለይም ክረምቱ ሲያልቅ ከዚህ በላይ የግንባታ ስራዎችን ለማከናወን ታቅዷል ነው ያሉት።

በግንባታው ላይ የሚከናወኑ የብረት ስራዎች እና እጅግ ተጓትው የቆዩት የጥቅጥቅ ኮንክሪት ስራዎችም ተዛምደው መቀጠል የሚችሉበት ሁኔታ ላይ መድረሳቸውን ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ጠቁመዋል።

በዙፋን ካሳሁን +FBC

Related stories   አውሮፓ ህብረት እየተሽኮረመመ ታዛቢ ሊልክ ነው