ብሪፖርተር በብሩክ አብዱ

ለሐጅ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ወደ መካ የተጓዙ ምዕመናንን ጨምሮ ለተጓዦች የምሥጋና አቀባበል ዝግጅት ያደረጉ 180 ኢትዮጵያውያን፣ ባለፈው ሳምንት በሳዑዲ ዓረቢያ ጂዳ ከተማ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

በእንዲህ ዓይነት ሃይማኖታዊ ጉዞዎች ላይ መሰባሰብና ማመስገን የተለመደ መሆኑን በመጠቆም ክስተቱን ለሪፖርተር ያስረዱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ዮሐንስ ሸዴ፣ በሥፍራው የተሰባሰቡ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸውን ሰዎች ጨምሮ ሁሉም በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በዕለቱ በጂዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን በመከታተል፣ 70 የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወዲያውኑ እንዲፈቱ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ አሥር ያህል ተጓዦችና ሌሎች ታሳሪዎችም በተከታታይ ቀናት እንዲፈቱ መደረጋቸውንም አክለዋል፡፡

‹‹እስከ 100 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን እስካሁን በቁጥጥር ሥር ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ፈቃድ የሌላቸው በመሆናቸው ከሳምንት በኋላ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል፤›› ሲሉ አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ውጪ ተጓዦችን ከነዋሪዎች ጋር ያገናኘው ስብሰባ ከማኅበራዊ ሚና የዘለለ ሌላ ዓላማ አልነበረውም ሲሉ አክለዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው የቆንስላ ጽሕፈት ቤቱ፣ ‹‹የቆንስላ ጽሕፈት ቤቱ ስለክስተቱ መረጃ ከደረሰው ወቅት አንስቶ የሃይማኖት አባቶች፣ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦችን ያካተተ አጣሪ ኮሚቴ እንዲዋቀር በማድረግ፣ ጉዳዩን የማጣራት ሥራ የጀመረ ከመሆኑም ባሻገር የኢፌዴሪ መንግሥትም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው እንደሆነ ለመግለጽ እንወዳለን፤›› ብሏል፡፡

የተዋቀረው የአጣሪ ኮሚቴም የጉዳዩን መነሻ ምክንያት ለማወቅ እየሠራ እንደሚገኝም ቆንስላ ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡

የዘንድሮ የሐጅ ጉዞ ሐምሌ 5 ቀን ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፣ 15 ሺሕ የሚጠጉ ተጓዦች ወደ ሥፍራው ማቅናታቸው አይዘነጋም፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ የሐጅ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ የሐጅ ጉዞ የሰጠው ኮታ 43,337 ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም ከአሥር ሺሕ በላይ ምዕመናን ተጉዘው እንደማያውቁ ይነገራል፡፡

Related stories   የአገራችን የፖለቲካ ቁማርና፣ 250ሺ ኢትዮጵያውያን ወደ የመን የሚሰደዱበት “ሚስጥር”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *