(ከ ደረጀ ተፈራ)

እንደሚታወቀው በጥንት ጊዜ የነበሩ በርካታ  ፀሃፍትና የታሪክ ተመራማሪዎች ኢትዮጵያን ከአባይ (ግዮን) ወንዝ፣ ከቀይ ባህር እና ከህንድ  ውቅያኖስ ጋር በማዛመድ የምትገኝበትን ቦታና  የህዝቧን አሰፋፈር በተመለከተ ፅፈዋል። ለምሳሌ ከክርስቶስ ልደት በፊት 8ኛው ክ/ዘ እና በ4ኛው ክ/ዘ ይኖሩ የነበሩ ሆሜር  እና ሄሮዱተስ የተባሉ የግሪክ ፀሃፍት በየዘመናቸው ፅፈው ባስቀመጡት ማስታወሻ ኢትዮጵያ ከግብፅ በስተ ደቡብ የምትገኝና የግዛት ክልሏም በአንድ በኩል ቀይ ባህር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ እንደሚደርስ ገልፀዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በ12ኛው ክ/ዘ ጥንታዊ የኦሮሞ አርብቶ አደር ነገዶች (Primitive Oromo pastoral tribes) አሁን ደቡብ ሶማሌና ሰሜን ኬንያ ተብሎ በሚጠራው የጁባና የዋቢ ሸበሌ ወንዞች በሚፈሱበት ሰፊ አካባቢ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ በጉርብትና ከሶማሌ አርብቶ አደር ጎሳዎች ጋር በከብት አርቢነት ይኖሩ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ።

ይልማ ደሬሳ የተባሉ በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመን የገንዘብ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነው ያገለገሉ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ፣ ከአባቶቼ በቃል ሲወርድ የሰማሁትና ከታማኝ  ምንጮች  ያነበብኩት ነው በማለት ሰለ “ኦሮሞዎች  ወደ ደጋ ኢትዮጵያ  መውጣት” በሚል ምዕራፍ  ስር  “የኢትዮጵያ ታሪክ፤ በአስራ ስድስተኛው  ክፍለ  ዘመን” በተባለ መጽሐፋቸው ላይ የኦሮሞ ነገዶች ከየት ተነስተው የት እንደደረሱና ለምን ቀድሞ ይኖሩበት ከነበረው አካባቢ እንደተሰደዱ የጻፉትን ማየት ይቻላል።

ቦረና እና ባሬንቱ የሚባሉ ጥንታዊ የኦሮሞ አርብቶ አደር ነገዶች (Primitive Oromo pastoral tribes) ቀድመው ይኖሩበት ከነበረው አካባቢ በሁለት አቅጣጫ ማለትም በሶማሌ እና በኬንያ በኩል ፈልሰው በመምጣት “በባሊ” (ባሌ) ተራራማ ቀበሌዎች እና ለአባያ የስምጥ ሸለቆ ሃይቅ ቅርብ በሆነ “መደ ወላቦ” በተባለ አካባቢ መጥተው እንደሰፈሩ የታሪክ መዛግብት ይነግሩናል። እነዚህ ቦረና እና ባሬንቱ የሚባሉ ጥንታዊ የኦሮሞ ነገዶች የሰፈሩበት የአካባቢው የተፈጥሮ ልምላሜ እየተስማማቸው ስለመጣ ከብቶቻቸው እጅግ እየረቡላቸው፣ የህዝቡም ብዛት እየጨመረ መጣ። በዚህ የተነሳ ለከብቶቻቸው የግጦሽ መሬት ጥበት አያጋጠማቸው መጣ። ያጋጠማቸውን ይህንን የመሬት ጥበት ችግር መጀመሪያ በተናጠልና በቤተሰብ ደረጃ በዙሪያቸው በመስፋፋት ለመቅረፍ ቢሞክሩም ችግሩን በበቂ ሁኔታ ሊቀርፈው አልቻለም። በመሆኑም እንደ ማንኛውም አርብቶ አደር ማህበረሰብ ወቅትንና ልምላሜን ተከትለው ከብቶቻቸውን ከቦታ ቦታ እየነዱ በህብረት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ እራሳቸውን ከሰውም ሆነ ከአውሬ ጥቃት ለመከላከል ይከተሉት የነበረውን በቤተዘመድ ወይም በጎሳ ተሰባስቦ በጋራ የመጓዝና የመኖርን የቆየ ባህል መሰረት ባደረገ መልኩ ከጎሳ እስከ ነገድ ድረስ ቅንጅት በመፍጥውር ገዳ የሚል ባህላዊ የውጊያ (የወረራ) አደረጃጀት ፈጠሩ። ገዳ ብለው በሰየሙት ማህበራዊ ትስስር በየጎሳ መሪዎቻቸው አማካኝነት ተዋጊ ወንዶችን በማዋጣት በህብረት (በመንጋ) እየተንቀሳቀሱ ጎረቤቶቻቸውን በድንገተኛ ወረራ በማጥቃት ከብቶች መዝረፍና ህዝቡን ከኖረበት ቀዬ ማፈናቀል ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ ነባር (Native) የኢትዮጵያ ማህበረሰቦችን በወረራ በማፈናቀል ሰፋፊ መሬቶችን በመንጠቅ መስፈር ጀመሩ። ይህ በወረራ መሬት የመንጠቅ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ አድማሱን እያሰፋና ይዘቱን እየቀየረ በመሄድ በጦርነት የተሸነፉ ጎሳዎችን በባርነት መግዛት፣ መሸጥ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ማንነታቸውን እያጠፉ ሞጋሳ በሚባል ባህላቸው ህዝቡን ኦሮሞ ወደ ማድረግን ተሸጋገሩ።

የገዳ ስርዓት አጀማመሩና እድገቱ ይህ ሆኖ ሳለ ኦነጋውያን የስርዓቱ ድክመቱንና ጥፋቱን በመሸፋፈን ከሰማይ የወረደ የፍፁማን ወይም የቅዱሳን ማህበር ይመስል በቃላት አሰማምረው፣ ያልሆነውን ባህሪ አላብሰው ከውልደቱ ጀምሮ ዲሞክራሲያዊነቱን የሚገልጽ ጥራዝ በማዘጋጀት በሃሰት ዓለምን አሳስተው በተባበሩት መንግስታት የቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ ተቋም የማይዳሰስ ረቂቅ ቅርስ (intangible cultural heritage) እንዲመዘገብ አደረጉ። የኦሮሞ ልሂቃንና ፅንፈኛ ብሔርተኞች የገዳን (የሞጋሳን) ሥርዓት በበርካታ የኢትዮጵያ ነባር ህዝቦች ላይ የፈፀመውን ድምሰሳ በመካድ አቃፊና ዲሞክራሲያዊ ነው ይላሉ። በተቃራኒው ደግሞ ለሺ አመታታ የኢትዮጵያ ሲያስተዳድር የነበረውን ዘውዳዊውን መንግስት ሲወቅሱ ይሰማል፣ በተለይም በዳግማዊ ምኒልክ ኢትዮጵያዊነት በኃይል ሳንወድ በግድ ተጫነብን፥ ባህላችንና ማንነታችን ተጨፈለቀ እያሉ ጣራ ድረስ ይጮሃሉ። ነገር ግን ሞጋሳ በሚባለው በኦሮሞ የገዳ ሥርዓት የወረራ ባህል ቋንቋና ማንነታቸው ተጨፍልቆ ያለ ፍቃዳቸው ተገደው ኦሮሞነት የተጫነባቸው፣ ከገፀ ምድር ስላጠፉት የኢትዮጵያ የጥንት ነባር ህዝቦች ሲናገሩ አይሰማም። በፅንፈኛ የኦሮሞ ብሔረተኞች ከአሶሳ በደኖ፣ በአርባ ገጉ፣ በቅርቡ ደግሞ በቡራዮና በኤፌሶን አጣዬ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ሲያወግዙም ሆነ ለተጎጂዎች የሰብአዊነ አዘኔታ ስሜት ሲያሳዩ አይታዩም። እንደ እውነቱ ከሆነ የኦሮሞ አባ ገዳዎች (አባ ሉባዎች) ሞጋሳ በሚባለው የወረራ (የጦርነት) ባህላቸው ለበርካታ ዘመናት በተከታታይ ኦሮሞ ባልሆኑ ነባር የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ወረራ ፈፅመዋል፣ ህዝቡንም  በመግደል፣ በማፈናቀል፣ ከጦርነቱ የተረፉትን ህፃናትን፣ ሴቶችን እና ምርኮኞችን ተወልደው ያደጉበትን የራሳቸውን ቋንቋ፣ ባህልና ማንነታቸውን በማጥፋት በሞጋሳ ኦሮሞ ያደርጋሉ። በህዝቡም መሬት ላይ ሰፍረው ባለቤት በመሆን በተወላጁ ላይ አዛዥ ናዛዥ፣ ሰጪና ከልካይ ይሆናሉ። በዚህ ሁኔታ ከባሌ፥ ከደዋሮ፣ ከፈጠጋር፣ ከወጅ፣ ከሸዋ፣ ከዳሞት፣ ከቢዛሞ፣ ከእናርያ፣ ከገኝና ከመሳሰሉት ጥንታዊ የኢትዮጵያ አውራጃዎች (ግዛቶች) ከምድረ ገፅ የጠፋ ወይም የተደመሰሱ ቁጥራቸው ከ20 በላይ የሆኑ የራሳቸው ቋንቋ፣ ባህልና ማንነት የነበራቸው ነባር ማህበረሰቦች ነበሩ።

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በጻፉት የዶክትሬት የመመረቂያ ጽሁፍ በሰዮ (በቄለም) ወለጋ አካባቢ ብዛታቸው ከአስር በላይ የሆኑ የተለያዩ ነባር (Native) ማህበረሰቦች በሞጋሳ ኦሮሞ እንደሆኑ እስከ ስማቸው ዘርዝረው ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ በኦሮሞ መስፋፋት ምክንያት በደረሰባቸው ወረራ ወለጋን ጨምሮ በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች ከዘር ማሳሳት እስከ ጨርሶ መጥፋት የደረሰባቸው፣ ከመሬታቸው የተነቀሉ፣ እጅግ ጠባብ በሆነች አነስተኛ አካባቢ ተጨናንቀው የሚገኙ፣ በየሸለቆውና በየተራራው አናት ላይ ተገፍተውና ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ አስከፊ ህይወት በመግፋት ላይ የሚገኙ ግፉአን ህዝቦች በርካቶች ናቸው። በግልፅና በቀጥተኛ መንገድ ሲገለፅ ሞጋሳ የገዳ ስርዓት አንዱ ክፍል ሲሆን በኦሮሞ ወረራ ወቅት በጦርነት የተማረኩ ሰዎች (ማህበረሰብ) ኦሮሞ (Oromization) የሚደረጉበት ባህል ነው። በጦርነት ተማርኮና ተሸንፎ በሞጋሳ ኦሮሞ የሚሆነው ሰው ወይም ህዝብ፣ ሞጋሳ የሚያነሳው የኦሮሞ የጎሳ መሪ (አባ ገዳ)፣ የወራሪው የኦሮሞ ጎሳ ተወላጆች በዛፍ ስር ይሰበሰባሉ። ከዛም በሬ ይታረዳል፤ በሬው የታረደበት ቢላዋን የበሬውን ደም ይቀቡና በዛፉ ዙርያ ከተሰበሰበው ሰው መሃል ከመሬት ላይ ይተክሉታል። አባ ገዳው ተነስቶ ከተናገረና ከመረቀ በኋላ በሞጋሳ ኦሮሞ የሆነው ሰው (ማህበረሰብ) ከመሬት የተሰካውን ደም የተለቀለቀውን ቢለዋ በእጃቸው እየነኩ “የእናንተ ጠላት የኛም ጠላት ነው፥ የእናንተ ወዳጅ የኛም ወዳጅ ነው፥ እናንተ የምታሳድዱትን እኛም እናሳድዳለን” ብለው ታማኝ፣ ለአባ ገዳዎች ታዛዥ ለመሆናቸው ቃል ኪዳን (ውል) ይገባሉ። በመቀጠል አባ ገዳው በሞጋሳ ኦሮሞ ለሆኑ ሰዎች ክንዳቸው ላይ ሜድቻ  (መዲቻ) ያስርላቸዋል። ሜድቻ ለሞጋሳው ሥነ ሥርዓት ከታረደው በሬ ቆዳ በቀጭኑ የተተለተለ ገመድ (ጥብጣብ) ሲሆን መዲቻው በሞጋሳ ኦሮሞ በሆኑ ሰዎች ክንድ ላይ ይታሰራል።  ሜድቻ በሞጋሳ ልጆችና በጦርነት በማረኳቸው ወላጆች መካከል የተፈፀመን ቃልኪዳንን ያመለክታል። በሌላ አነጋገር ሜድቻ ክንድ ላይ ማሰር የመሸነፍ ወይም በኦሮሞ የመማረክ ምልክት ነው። እነዚህ ተሸንፈው ሜድቻ ክንዳቸው ላይ የታሰረላቸው ሰዎች ተወልደው ያደጉበትን ያባቶቻቸውን ባህልና ቋንቋቸ ትተው በሞጋሳ የኦሮሞ ማንነት ይጫንባቸዋል። እነዚህ ሰዎች እንደየ አካባቢው ገርባ፣ ገባሮ ወይም ደለታ ተብለው ይጠራሉ፣ ትርጉሙም አገልጋይ፣ ባሪያ፣ ጭሰኛ እንደማለት ነው። ገርባ (ገባሮ ወይም ደለታ) የሚባሉት ሰዎች እውነተኛ ኦሮሞ ናቸው ከሚባሉት ጥንታዊ የኦሮሞ ነገዶች ከሆኑት ከቦረና እና ከባሬንቱ ያነሰና በገዳ ህግ የተገደበ መብት ነው ያላቸው። በገዳ ህግ የተገደበ መብት አላቸው ሲባል ለምሳሌ ተራ ተዋጊ እንጂ የጎሳ መሪ ወይም አባ ገዳ መሆን አይችሉም፣ ከአባ ገዳ የተለየ ዱለቻ የሚባል ሹመት ይሰጣቸዋል። ገርባዎች እንደ ቅጥረኛ ወታደር ዓይነት ሞጋሳ ላነሳው አባ ገዳው ሌሎች ማህበረሰቦችን በመውረር መሬታቸውን ለመቀማት፣ ከብቶቻቸውንና ሴቶቻቸውን ለመዝረፍ/ ለመቀማት በዘመተበት ቦታ ተከትለው በመሄድ ሜቲቻ ሲታሰርለት ጠላትህ ጠላቴ ነው ብሎ ለአባ ገዳው በገባለው ቃል ኪዳን መሰረት ይሞትለታል። ሌላው ገርባ የሆኑ ሰዎች የመሬት ባለቤት መሆን አይችሉም፣ ነገር ግን እውነተኛ  ኦሮሞ ናቸው ለሚባሉት ለቦረና እና ለባሬንቱ ኦሮሞዎች ጭሰኛ፣ አገልጋይ፣ ባሪያ ይሆናሉ። ሌላው የገዳ ስርዓትን ኢዲሞክራሲያዊና ጨቋኝ መሆኑን የሚያሳየው አባ ገዳው ገርባውን እንደ ግል ንብረቱ ስለሚያየው (የገዳ ህግም ስለሚፈቅድለት) በሞጋሳ ደም የራሰ ቢለዋ አስጨብጦ ኦሮሞ ሆነሃል ባለው ጊዜ “ጣላቴ ጠላትህ ነው” ብሎ ገርባው በገባው ውል (ቃል) መሰረት ለአባ ገዳው በጎረቤቶቹ ላይ ለሚያደርገው የወረራ ጦርነት ወታደር ሆኖ ይዋጋል፣ አባ ገዳው (ጌታው) ሲፈልግ ጭሰኛ አድርጎ ያሳርሰዋል፣ ካልፈለገ ደግሞ ገበያ ወስዶ በባሪያ ደንብ ይሸጠዋል። ለዚህ እንደ ጥሩ ምሳሌ የሚጠቀሱት የጅማው የኦሮሞ ባላባት አባ ጂፋርና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በመጸሃፋቸው የጠቀሷቸው የወለጋ የኦሮሞ ባላባቶች (አባ ገዳዎች) ናቸው። እነዚህን ግፈኛ የኦሮሞ ባላባቶች ክፉ ሰራቸውን በአዋጅ በማስቆም ፍጹም ባይሆንም ቢያንስ ህዝቡ አንጻራዊ እፎይታ እንዲያገኝ ያደረጉት ኦነጎች የሚወቅሷቸው ዳግማዊ ምኒልክ ናቸው።

ሌላው ደግሞ በሞጋሳ ገርባ (ገበሮ ወይም ደለታ) የሆነው ህዝብ፣ በገዳ ህግ መሰረት በወረራ ኦሮሞ ያደረጋቸው የጎሳው አንጋፋ የሆነ ሰው ወይም አባ ገዳ ወላጅ አባታቸውን ተክቶ አባት ይሆናቸዋል። በመሆኑም በሞጋሳ ኦሮሞ የሆኑ ሰዎች በእውነተኛ የስጋ ወላጅ አባቶቻቸው መጠራትን በመተው ሞጋሳ ባደረጋቸው በአንጋፋ ሰው ወይም አባ ገዳ ስም ይጠራሉ ማለት ነው። ለምሳሌ “ጋሻው መክት” እና “መክት ማንደፍሮ” የሚባሉ አባትና ልጅ “ጫላ መገርሣ” በሚባል  አባ ገዳ (አንጋፋ ሰው) መሪነት በመንደራቸው ላይ በተደረገ ወረራ (ጦርነት) በጫላ ተማርከው በሞጋሳ ስርዓት መሰረት ኦሮሞ ሲሆኑ፣ ይኸው ጫላ የሚባል  አባ ገዳ (አንጋፋ ሰው) ሜድቻ ካሰረላቸው ቀን ጀምሮ ያባታቸውን ስም በጫላ ይቀየራል ማለት ነው። በመሆኑም አባትና ልጅ ወግቶ በማረካቸው በጠላታቸው ሰው ስም ይጠራሉ። በዚሁ መሰረት ጋሻው ጫላ እና መክት ጫላ ተብለው አባትና ልጅ መጠራት ይጀምራሉ። ስለዚህ በሞጋሳ ኦሮሞ የሆኑ ሰዎች ሜትቻ በክንዳቸው ላይ ከታሰረላቸው ቀን ጀምሮ ብሔራቸውም ሆነ ያባታቸው መጠሪያ ስም በኦሮሞ በመቀየር አዲስ ማንነት ይጫንባቸዋል። ይህ ሁኔታ የኦሮሞን ህዝብ ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥሩ እንዲጨምር ምክኛት ሆኗል። በዚህ ሁኔታ ገርባ የሆኑ ሰዎች ከእውነተኛ ታሪካቸው ጋር እስከመጨረሻ ይለያያሉ። በመሆኑም ሞጋሳ ህዝብን በወረራ ከባህሉ፥ ከታሪኩና ከማንነቱ የሚያቆራርጥ ስርዓት ነው። ይህ የሚያሳየን የገዳ ሥርዓት ዲሞክራሲያዊ፣ አቃፊና የሌላውን ባህል ቋንቋና ማንነት የሚያከብር ሳይሆን በየ ስምንት አመቱ ጉልበቱ የደከመ ሽማግሌ አባ ገዳን በአዲስ ጉልበት ባለው ወጣት ተዋጊ አባ ገዳ እየቀየረ ህዝብን ሲገል፣ ሲያፈናቅልና መሬት ሲቀማ፣ የሌሎችን ቱባ ባህል ቋንቋና ማንነትን ሲደመስስ የኖረ የወረራ ባህል ወይም በፕሮፓጋንዳ በሃሰት እላይ የተቀመጠ ኋላ ቀር ስርዓት ነው።

ሞጋሳ የሚባለው የገዳ የጦርነት ወይም የወረራ ባህል ደግሞ የገዳ ስርዓትን ማስፈፀሚያ መሳሪያ ሆኖ ያገለገለ ነው። አንዳንድ ምሁራን የኦሮሞ ጎሳዎች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ሌላውን የኢትዮጵያ ህዝብ አፈናቅለው መሬቱን በመቀራመት ከመስፈራቸው (land grabbing and settlement) በተጨማሪ የባህል፣ የቋንቋና የማንነት ድምሰሳ ስለፈፀሙ በነባሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረጉት የሰፈራ ቅኝ ግዛት (settler colonialism) ነው ይላሉ። ያም ተባለ ይህ ጨፍላቂ ባህል፣ የሰው ልጅ መገኛ ከሆነችው ከኢትዮጵያ ምድር የተገኙ ለኢትዮጵያም ሆነ ለዓለም ቅርስ ሊሆኑ የሚችሉ ባህሎችንና ምንነቶችን ያጠፋ፣ የጥንታዊ የሰው ልጆችን ማህበራዊ እድገት፣ ለውጥና ለዘመናት ሲገነቡና ሲዳብሩ የመጡ ማንነቶችን ወዘተ  በሳይንሳዊ መንገድ ለማጥናት ግብአት ሊሰጡ የሚችሉ ነባር ህዝቦችን እስከ ባህላቸው፣ ቋንቋና ማንነታቸው ጭምር ጠራርጎ ያጠፋ ነው። እንደ ሞጋሳ (ገዳ ሥርዓት) ዘር አመንምኖና አሣሥቶ የሚያጠፋ፤ ባህልን፥ ቋንቋንና ማንነትን ጨፍልቆ ከምድረ ገፅ ያጠፋ ጨካኝ (inhuman) ስርዓት በዓለም ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ አይታወቅም። በኢትዮጵያ ውስጥ በ16ኛውና በ17ኛው ክ/ዘ በኦሮሞ ጎሳዎች የተፈጸሙ የባህልና የቋንቋ ድምሰሳ፣ የማንነት ጭፍለቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተወገዘ  የባህል ማሳሳትና ማጥፋት (Cultural Genocide or Indigenocide) ነው። በጥንት ዘመን የነበረው ጥንታዊ የኦሮሞ ማህበረሰብ (Primitive Oromo pastoral tribes) እና አሁን በዘመናችን በሚገኘው  የኦሮሞ ህዝብ (Contemporary Oromo)  መሃል ብዙ  ልዩነት እንዳለ መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። ጥንታዊ የኦሮሞ አርብቶ አደር ጎሳዎች ወደ መሃል ሃገር ሳይንቀሳቀሱ  በፊት የነበራቸው ባህል፣ አኗኗር፣ እምነት፣ አስተሳሰብ፣ የህዝቡ ስብጥር፣ ብዛት እና የመሳሰለው አሁኑ በዘመናችን ካለው በብዙ መልኩ ይለያል። እምነትን ብንመለከት ቀድሞ ይከተሉት የነበረውን ባህላዊ እምነት ወይም አምልኮት (Traditional belief) በጊዜ ሂደት በመተው እስልምናን፣ የኦርቶዶክስንና  የአውሮፓ ሚስዮናውያኑን የክርስትና እምነትን ተቀብለዋል። እንዳሚታወቀው ቀደም ባለው ጊዜ በተከታታይ ለረጅም ዘመናት ያለማቋረጥ በአባ ገዳዎች (በአባ ሉባዎች) መሪነት በተደረጉ ወረራዎችና መስፋፋቶች የኢትዮጵያ የተለያዩ ነባር/ Native ጎሳዎችና ነገዶች (ማህበረሰቦች) በሞጋሳ፣ በጉዲፈቻ እና በመሳሰለው ኦሮሞ ሆነዋል፣ በሂደቱም የህዝቦች መቀየጥ (assimilation) በመደረጉ አሁን ከሚገኘው የኦሮሞ ህዝብ ውስጥ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያልተቀላቀለ ፍጹም የጥንቱን ግንዱን ይዞ የመጣ ቅይጥ የሌለበት ቦረና እና ባሬንቱ ከሚባሉ ጥንታዊ የኦሮሞ አርብቶ አደር ነገዶች የሚወለድ እውነተኛ ንፁህ ኦሮሞ ነው ተብሎ የሚገመተው 20% በታች እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ። ለምሳሌ አሁን ያለው የኦሮሞ ህዝብ ቁጥር 40 ሚሊዮን ነው ብንል 8 ሚሊዮን ብቻ ነው በዘሩ (በደሙ) ኦሮሞ የሆነው። የቀረው 32 ሚሊዮን ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ እንጂ በደሙ ኦሮሞ ያልሆነ ከሌላ ብሔረሰብ በሞጋሳና በጉዲፈቻ ወደ ኦሮሞነት የተቀየረ ነው። –//–

ደረጀ ተፈራ

ምንጭ

  1. “የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ” በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
  2. “የኢትዮጵያታሪክ፤ በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን” በአቶ ይልማ ደሬሳ
  3. ፕሮፌሰር ሀብታሙ ተገኝ፡ (ርዕዮት ስርጭት)
  4. አቶ አአቻሜለህ ታምሩ

Subscribe to the  Zaggolenews online news magazine


 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *