“Our true nationality is mankind.”H.G.

ነገሮች እየከበዱ መምጣታቸዉ አይቀርም!የቹቹ አለባቸው ደወል!!

By – Chuchu Alebachew

አሁን ያለዉ የአገራችን ፖለቲካ ፤ መታመም ከጀመረ ረዘም ያሉ ወራትን አስቆጥሯል። እዉነት ነዉ በለዉጥ ወቅት ፖለቲካዊ ህመም የሚጠበቅ ነዉ። ነገር ግን ህመሙ ጤነኛና በወቅቱ የሚያገግም እንዲሆንም ይጠበቃል። ይሁን እንጅ የኛ የለዉጥ ህመም ጤነኛ አይመስልም። እንዴዉም አሁን ያለዉ እዉነታ እንደሚነግረን፣ ፖለቲካችን ከህመም አገግሞ ጤነኛ ለመሆንም ጊዜ የሚወስድበት መሆኑ አይቀርም።

የሰሞኑን በኢህአዴግ አባል ድርጅት በሆነዉ ህወሀት አስተባባሪነተ እንደተዘጋጀ የሚታመነዉና ፣ በመቀሌ ከተማ የተካሄደዉ የብሄርተኞችና፣ ሳይኖሩ አለን የሚሉ አንዳንድ የፖለቲካና ፖለቲካ መሰል ድርጅቶች በጋራ ለመስራት ያሳዩት አቋም፣ ነገሮችን ቆም ብለን እንድንመረምር ያስገድደናል። ሁኔታዉ ኢህአዴግ አፉ እንጅ ነብሱ እንደሌለ ያስረዳናል። ህገመንግስታችንን አትንኩብን የሚሉ ወገኖች፣ ህገ መንግስቱ በመርህ ደረጃ ያስቀመጠዉን፣ “አንድ ማህበራዊና ኢኮnoሚያዊ ማህበረሰብ መፍጠር” የሚለዉን ዋነኛ አገራዊ አጀንዳ እዉን ለማድረግ የሚያግዘዉን፣ አማርኛ ቋንቋን ልጆቻቸዉ ከህፃንነታቸዉ ጀምሮ እንዲማሩት የተያዘዉን እቅድ አለመፈለጋቸዉን ስናይ፣ የነዚህ ወገኖች ነገር ግራ ያጋባል።

እነዚህ ወገኖች በአሁኑ ወቅት፣ ምንም ጥሩ ነገር ቢሰራ የሚወዱ አይመስሉም። ብቻ ሁለመናቸዉ የዶ/ር አብይን ማናቸዉም እቅድ ማጣጣል ሆኗል። ይሄ የጽንፈኞች መልክ የለሽ ፀረ- አብይ እንቅስቃሴ፣ ዶ/ር አብይ እያጣ የመጣዉን ድጋፍ እንደገና እንዲያንሰራራ የሚያደርግለት መሆኑ አይቀርም። ደግሞ እኮ ተመሳሳይ መድረኮችን ለማስኬድ ኮሚቴ አቋቁመዋል። ሌላ የሰላም መንግስት መሆኑ ነዉ።

የአማራ ፖለቲካ!

የአማራ ፖለቲካ ህመም ደግሞ፣ ከህመሙ ከማገገም ይልቅ እየባሰበት ሂዷል። እንዴዉም ራሱ ባዘጋጀዉ ድግስ ጭምር የራሱን መሪወች ወደመቃወም አምርቷል። የሰሞኑ የአዲስ ነገር አሳዝኖኛል። መቃወም ወግ ነዉ፣ ግን ተቃዉሞ ሁኔታ፣ ወቅትና ጊዜ ያስፈልገዋል። በህዝባዊ በአል ላይ ፤ ያዉም ባለጉዳይ ሁነን ነገሩ በራሳችን ላይ ባይደረግ ጥሩ ነበር።

ሌላኛዉ የሰሞኑ የአማራ ፖለቲካ ህመም መገለጫ፣ በአብን አመራር ዙሪያ የሚሰሙት ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች ናቸዉ። የበለጠ ሞላን መልዕክት ካየሁ በሁዋላ፣ ነገሩ ቀላል አልመሰለኝም። ይሄ ሁኔታ ተሎ ካልተፈታ፣ ወደሁዋላ ለመመለስ ዳዴ እያለ ያለዉን የአማራ ፖለቲካ የባስ ወደ ሁዋላ ሽምጥ እንዲጋልብ ያደርገዋል። ህዝቡም ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል። ብቻ ብዙ ነገር መጉደሉ አይቀርም።

ሌላዉ የአማራ ፖለቲካ እንዲታመም፣ ከህመሙ በወቅቱ እንዳያገግም፣በህመም ዉስጥ ሆኖ እንዲቀጥል ዋነኛ ምክንያት የሆነዉ” አክቲቪስት” ነኝ ባይ፣ ዛሬም መግዛት በሚገባዉ ፍጥነትና ልክ ልብ አልገዛም።

ብቻ ነገሮች ተበላሽተዋል፣ በብልሽት ዉስጥም ሆነን መቆየታችንም አልቀረም። ሁኔታወች የሚነግሩን ይሄን ነዉ። ብልሽቱ ከነጭራሹ እንዳያጠፋን፣ ድፍረትና ሀላፊነት የተሞላበት መፍትሄ መፈለግ ይጠይቃል።

መፍትሄ:-

1. የዶ/ር አብይ መንግስት:- ነቃ ብሎ ህግ የማስከበር ስራን ማጠናከር አለበት። በሀገር ህልዉና የሚመጣን ማናቸዉንም ነገር አለመታገስ። ቀልድ ይበቃል። ቀልድም የሚያምረዉ አገር ሲኖር ነዉ። እንዲሁም ሰበብ ተፈልጎላቸዉ ያላግባብ የታሰሩ ሰወችን መፍታት። በተለይ አዲስ አበባ። ፖሊስ ተጠርጣሪወችን በሚመረምርበት ወቅት ህጋዊነትን ባረጋገጠ መልኩ መሆኑን መከታተልና ማረጋገጥ ።

2. አዴፓ:- አዴፓ የአማራ ፖለቲካ በጽኑ መታመሙን አዉቆ ተሎ መፍትሄ መፈለግ አለበት። ጊዜ የለም። አመራሩ በየመንደረ ሲዞር ከሚዉል፣ የታመመዉን ፖለቲካ ለማከም የሚያስችል ስልት መቀየስና ወደተግባር መግባት አለበት። መፋዘዝ አያለሁ። በተለይም ሁሉንም አማራዊ ድርጅቶችንና ሙህራንን በአጭር ቀን ጠርቶ፣ የታመመዉን ፖለቲካ ማከም ስለሚቻልበት ሁኔታ መምከር አለበት። አዴፓ ቢያንስ ይችን ነጥብ እንድትሰማኝ እማጸንሀለሁ። እርግጠኛ ነኝ አንተም ታተርፍበታለህ፣ የአማራን ፖለቲካም ትታደገዋለህ።

3. አብን:- ሰሞኑን በራሳችሁ አመራሮችና በአንዳንድ ወገኖች ጭምር የምንሰማዉ ነገር ደስ አይልም። ችግራችሁን ቁጭ ብላችሁ ፍቱ። ሀቅ ላይ ቁማችሁ ተነጋገሩ። ሀቅና ፍትህ ላይ ከቆማችሁ፣ ችግራችሁን ትፈታላችሁ፣ ለህዝባችሁም ተስፋ ሁናችሁ ትቀጥላላችሁ። የተበላሸ ነገር ካለ ተጋፈጡት፣ ችግሩ ግለሰባዊ ከሆነ ከድርጅት አይበልጥም። ችግርን ለመፍታት የሚከብደዉ ችግሩ ድርጅታዊ ሲሆን ነዉ። ይሄ ደግሞ አብንን የገጠመዉ አልመሰለኝም።

4.” አክቲቪስቱ” ያዉ የአማራ ህዝብ አክቲቪስት ሁኑ። የሆነ ግለሰብ፣ መንደር፣ቡድን፣ድርጅት አገልጋይ አትሁኑ። አከሸቲቪስትነት ከአገልጋይነት የተለየ ነዉ።

5. ወጣቱ:- ራስክንና የአማራን ህዝብ ብቻ ሁን። ማንም “ወፍ ዘራሽ” እንዳይጠቀምብህ በብስለት ጻፍ፣ ተናገር፣ ተወያይ።

ቸር ያሰማን!!!!

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የመ/ሰራዊትን መለያ ለብሶ ከሱዳን ወደ ወልቃይት ሊገባ የነበረ የትህነግ የሽብር ሃይል ተደመሰሰ፤
0Shares
0