ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የደቡብ ክልል ምክር ቤት አዲስ ፕሬዚዳንት ይሾማል

ሪፖርተር – በብሩክ አብዱ ከስምንት ወራት በኋላ የሚሰበሰበው የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዓርብ ነሐሴ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚያደርገው ስብሰባ፣ አዲስ ፕሬዚዳንት እንደሚሾም ታወቀ፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት አቶ ደሴ ዳልኬን በመተካት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ከርዕሰ መስተዳድርነታቸው ተነስተው፣ በሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ማዕከል ምክትል ዋና አስተባባሪ ሆነው እንደሚሾሙ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡  

ሰኔ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ባደረገው የአመራር ሽግሽግ፣ የቀድሞውን የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳን በመተካት ነበር አቶ ሚሊዮን የንቅናቄው ምክትል ሊቀ መንበር በመሆን የተመረጡት፡፡

በተመሳሳይ የደኢሕዴን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ አብርሃም ማርሻሎ፣ ጌታሁን ጋረደው (ዶ/ር) እና አቶ ክፍሌ ገብረ ማርያም ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን፣ አቶ ደሴ ዳልኬ ደግሞ ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዝቅ እንዲሉ በንቅናቄው መወሰኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከአሁን ቀደም የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉት አቶ መለስ ዓለሙ፣ ለክልሉ ምክር ቤት በፕሬዚዳንትነት ሊሾሙ እንደሚችሉ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ አቶ መለስ በአሁኑ ወቅት በሚኒስትር ማዕረግ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ማዕከል ምክትል ዋና አስተባባሪ በመሆን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡

የፌዴራሉን መንግሥት ጨምሮ ሁሉም ክልሎች ዓመታዊ በጀታቸውን በየምክር ቤቶቻቸው አፀድቀው ወደ ሥራ የገቡ ቢሆንም፣ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ግን ባለመሰብሰቡ ክልሉ በጀት ሳያፀድቅ አዲሱን የበጀት ዓመት መጀመሩ በርካቶችን ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡ በመሆኑም በዓርቡ ስብሰባ የክልሉን የ2012 በጀት ዓመት በጀት ማፅደቅ አንዱ አጀንዳ እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡

የፊታችን ዓርብ የምክር ቤቱ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት፣ የምክር ቤቱ አባላት በሐዋሳ ከተማ በክልሉና በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የምክክር ስብሰባ እያካሄዱ ነው፡፡

የምክክር ስብሰባውን በመምራት ላይ ያሉት አቶ መለስ ዓለሙ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Related stories   "የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎችን ላለመላክ የወሰነው የማይታዘዝና የማያጎበድድ መንግሥት ይመጣል የሚል ስጋት ነው"አንዳርጋቸው ፅጌ