ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

“… ከእንቅልፌ ስነቃ እዛው ነኝ ለካ… “

የትላንት ስብሰባ ላይ የተከበሩ ዶክተር አዲስ ዓለም ባሌማ ህወሃትን ወክለው ሲናገሩ በቀጥታ ቴዲ አፍሮ የዘፈናት ዘፈን ነበረች ያቃጨለችብኝ። ” … ከእንቅልፌ ስነቃ እዛው ነኝ ለካ ” ቴዲ ይደጋግማታል!!የተናጋሪውን ሃሳብ፣ እምነትና፣ የተሰጣቸው ተልዕኮ ልክ ሌሎችም በተመሳሳይ እንደሚያደርጉት ነውና አልገረመኝም። ከ”ባንዳነት” በቀር በፖለቲካው ዓለም መለዋወጥ/ መገለባበጥ የተለመደ በመሆኑ። ይህም የተለመደ የፖለቲካና የፖለቲከኞች አክሮባት ጊዜን፣ አካባቢያዊ ሁኔታን፣ ዓለም ላይ የሚከሰቱ ለውጦችን ወዘተ ተከትሎ ይሆናል። ሆኗል። ወደፊትም ይሆናል!! እድሜ የሰጠው ብዙ ያያል።እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ህወሃትን የወከሉት ዶር አዲስዓለም ስለ ግልጽነት፣ መተማመን፣ ፍትሃዊ ምርጫ … እጅግ አስፈላጊነት ሲናገሩ ስሰማ ” እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ? እኔ ያለፉት 28 ዓመታት ጡት እጠባ ነበር? በአፍዝ አደንግዝ መስማትና ማየቴ ተውስዶ ነበር? ጤነኛ አልንበሩክም? …” እያልኩ እጠይቅ ነበር። እዛው፣ እድሮው ሰፈር መሆናቸው አስዘነኝ። ከማዘንም ባለፈ አስደነገጠኝ!!ሁለት የምርጫ ዘመን ከሃያ ወረዳዎች በላይ ምርጫ ሲዘረፍ አይቻለሁ፤ መዘረፍ ብቻ ሳይሆን በብሄር እየተለዩ ሰዎች ካርዳቸውን እንዳሻቸው እንዳይጠቀሙ ሲደረግ የነበረውን ሰምቻለሁ። በሚስጢር የተነገረኝም ጉድ አለ። የቻልኩትን ሪፖርት አድርጊአያለሁ። አዲስ አበባ የተወለድኩብት ቀበሌ ኮሮጆ ሲሰረቅ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ በላንባዲና እያሰሰ ሲያስመልስ አይቻለሁ። እኚህ ሰው በአመራር ያሉበት ትህነግ መቶ በመቶ ምርጫ አሸነፍኩ ብሎ በአደባባይ የቃፊር ተስካር ደግሶ ራሱን ሲሞሽር አይቻለሁ። ይህንን ሁላችንም አይተናል። እናም ስለየትኛው የምርጫ ግልጽነት፣ ተአማኝነት፣ መተማመን ለማን እንደሚናገሩ ሳስብ ነው ወዲያው ዘፈኑ ያነቃኝ!! ” … ከእንቅልፌ ስነቃ እዛው ነኝ ለካ ” ከሁሉም በላይ ግን እኚህ ሰው ሰለ ግልጽነትና ስለመተማመን እየሰበኩን ባለበት ሰዓት የትህነግ ይፋዊ የፌስ ቡክ ገጽ ዲፋክቶ ስቴት ለማቋቋም እየሰራ መሆኑንን ይፋ አድርጎ ነበር። ከሁሉም በላይ ደግሞ ስለ አካታች፣ አሳታፊነትና መተማመንን የሚያሰርጽ ምርጫ አስፈላጊነት ሲናገሩ በአቋማቸው ሳቢያ አሸባሪ ተብለው ከኢትዮጵያ ፖለቲካ እድል ፈንታቸውን የተነፈጉ ፊት ለፊት ነበር። ይህ ብቻ አይደለም እሳቸው ያሉት ካልሆነ አገሪቱ ወደ እልቂት ታመራለችም ብለውናል። ይህን ስሰማ አንድ አፍቃሪያቸው “የስልክ እንጨት ዘመን” ብሎ ያስረዳኝ ታወሰኝ!!በዛ ስሜት ውስጥ ሆኜ ምላሹን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ” ዘመኑ ተቀይሯል፤ ብትፈልጉ በሚስጢር፣ ብትፈልጉ በቴሌቪዥን ህዝብ እየሰማ ችግር ካለ እንነጋገር” ብለው ሲጀመሩ፣ ቀሪውን ማዳመጥ አቃተኝ። እስኪ ህዝብ እየሰማ በቀጥታ ውይይት፣ ክርክር፣ ንትርክ ይካሄድ … ተመራቅዘን ከምንቀር፣ ምስኪን ሕዝብ በሴራ እየተዥጎረጎረ ከሚባትት መፍትሄ ቢሆን!! ሃምሳ ዓመት ሴራ ያማል!! ሃምሳ ዓመት መካካድ ያማል።ሰለ ” ባንዳነት” የተንሳው ጉዳይ የአገው ፖለቲከኛ አቤቱታ ጋር ተስታኮ ቢሆንም … መመራቀዙ የት እንደደረሰ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይና ጉዳይ ከአገው ብሄራዊ ሸንጎ ትከሻና እሳቤ ውጪ መሆኑንን የሚያመላክት ነው። ዛሬ ዓለም ላይ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ቁጥራቸው ከ3.2 ሚሊዮን ዘሏል። 227 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል። አፍሪካ ጎዳናዋ ሁሉ አስከሬን ይሆናል እየተባለ ነው። ለወሬ፣ ለነጋሪ፣ ለምሁራን፣ ለሳይንቲስቶች፣ ለባለጠጎቹ ግራ ያጋባ ወረርሺኝ ዓለም እያስደገደገ ባለበት በዚህ ጥቁር ዘመን ውሃ የማይዘልቃቸው ደረቅ አልጌዎችንና የስልጣን ጥመኞችን ማየት ያሳዝናል። ተስፋም ያስቆርጣል። ልዩነትን በባንዳነት መመንዘር ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላሉት ሳይሆን ቀድሞውንም የተደመጥ የአደባባይ ሚስጢር ነው። አገርን አጀንዳ እየቀያየሩ ማተራመስ ሆን ተብሎ በበጀት የሚሰራ የባንዳነቱ መተግበሪያ ቋት እንደሆነ ህዝብ ያውቃል። ለውጡ በእንጪጩ አጥመልምሎና አልፈስፍሶ ለመጣል ያልተማሰ ጉድጓድ የለም። ከግድያ ሙከራ ጀምሮ እስከ መፈንቅለ መንግስት ተሞክሯል። ሊፈርጥና ከሃድ ሊሆን በቋፍ ያለ የአማራ ክልል መሪዎችና ” ኢትዮጵያ” ሲል የሚያኮራው የጀነራል ሰዓረ ግድያም የዚሁ የባንዳነቱ ሌላው ማሳያ ነው።አማራ ክልልን ማፈራረስ፣ የመከለከያውን መሪ ገሎ ሰራዊቱን መበተን፣ የሶማሌ ክልልን ቀውስ ውስጥ መክተት፣ ዜጎችን ማፈናቀል፣ ማፈንና ዩኒቨርስቲዎችን ማተራመስ ሽፍታ ማምረት በባንዳነት ከሚገኝ ሂሳብ የሚወራረድ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን አይችልም። ሌላም ሌላም …ይህ ሁሉ ህዝን አይመለከትም። ይህ ሁሉ የህዝብ ጉዳይ ሆኖ አያውቅም። ሴረኞች ለስልጣን ጥም ሲሉ የሚጭኑበት በሽታ ነው። ኮሮናው ብዙም ያልጨከነብን ለዚህ ይሆናል። ብዙ ተጎድተናልና!! ስንቴ እንጎዳ? በስንቱስ እንጎዳ? ደረቅ አልጌዎች የጅምላ መቃብር ፓርካቸው ነው። እዛው ናቸው። አማራና ኦሮሚያ የተፈጠሩ ውስን ዘረኛ ድርጅቶችም መቃብር አቋፋሪ ናቸው። እጅግ ጥቂት ዘረኞች የሚጋልቧቸው ፈረሶች ናቸው። አደጋና ስጋት አይታያቸውም። ድርጎ ልቡናቸውን ስለቦታል። ድርጎ ” ሙክት ያኮላሸውን” እንዲሉ አድርጓቸዋል። ለሁሉም ግን የምስኪኖ ሕዝብ አምላክ አለ!! እነሱ ግን እዛው ናቸው ” … ከእንቅልፌ ስነቃ እዛው ነኝ ለካ ፣ እዛው ነኝ ለካ፣እዛው ነኝ ለካ . እዛው ነኝ ለካ ..…

Related stories   በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 110 ሺህ ዶላር ተያዘ