“Our true nationality is mankind.”H.G.

“ኮሮና” እና የሽግግር መንግስት !

ከሽግግር መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያተርፈው ምንድን ነው? እነማን ይሳተፋሉ? መመዘኛው ምንድን ነው ? የሕወሃት አጫዋች የነበሩና ለውጥ እንዳይመጣ ከሕወሃት ጎን ሆነው የታገሉትስ ይሳተፋሉን? ሕወሃትስ እንደ ደርግ/ኢሰፓ ይገለላል ? ወይንስ ይሳተፋል? ከ10 የማያንሱ የኦሮሞ ድርጅቶች እንዳሉ ይታውቃል። ለነዚህ የሚሰጠው ወንበር ከሕዝብ ቁጥር ፕሮፖርሽን አንጻር ይሆናል ወይንስ እንዴት ይደለደላል? ማን ምን ያህል ወንበር እንደሚያገኝ መመዘኛው ምንድን ነው?

ሲሳይ አጌና ————————-

በምርጫ 97 ወቅት ሰኔ 1 እንዲሁም ጥቅምት 23 እና 24 በዋናነት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተካሄደው ጭፍጨፋ ማን ምን ሚና ነበረው? የግንቦት 30ውን ወረቀትስ እንዴት ተቀነባበረ ? በማንስ ተበተነ ወዘተ የሚለው የማይታለፍ እንደሆነ ቢታወቅም ይህ ግን ለኔ ለግዜው ወቅታዊ አይደለም።

በተመሳሳይ ከ2010 ለውጥ ወዲህ ከተካሄዱ ፍጀቶች በስተጀርባ የማን ሚና ምን ነበር የሚለውን ጨምሮ የቅርቡ የ86ቱ ሟቾችም ጉዳይ በተመሳሳይ የማይታለፍ ቢሆንም ፥ አሁን ላይ ሰዎቹን ከሚጠረጠሩበት ጉዳይ ጋር እያይዞ ማንሳቱ ፋይዳ የለውም። ፋይዳ የማይኖረው የጥፋተኛነትም ሆነ የጸጸት ስሜት የሌለባቸውን ሰዎች በማያፍሩበት ምናልባትም በሚኮሩበት ጉዳይ ለመግጠም መሞከር የሚለውጠው ነገር ስለማይኖር ነው።

አንዳንዶች የሚገርማቸው ከዚያ ሁሉ ወንጀል እና ነውር በኋላ ግለሰቦች አደባባይ ሲወጡ በአደባባይ የሚደግፏቸው እና ፌስቡክ ላይ የሚያጨበጭቡላቸው ሰዎች መገኘታቸው ነው። መታወቅ ያለበት ለነዚህ ወገኖች ድጋፍ የሚሰጠው ጽንፈኛው ብሄርተኛ ሃይል መሆኑ ግልጽ ነው። ይህ ሃይል ደግሞ በጭፍን ብሄርተኝነት ድንዛዜ ውስጥ ያለ በመሆኑ መቃወሙን እንጂ ውጤቱ ምን እንደሚሆን አይረዳውም።

የሚገባው ወይንም የሚባንነው አዲስ አበባ አሌፖ፡ ኢትዮጵያም ሶርያ ሲሆኑ ነው። ይህ ሃይል በማናቸውም ሁኔታ ሥርዓት እንዲፈርስ የሚቋምጥ፥ በጥላቻም ሆነ በሌላ ተቃውሞ ለተባለ ነገር ሁሉ ድጋፍ የሚሰጥ በመሆኑ ይህን በድንዛዜ ውስጥ ያለ ሃይል በአምክንዮ ማንቃት አይቻልም።በዚህ ወይንም በዚያ ብሄር ሥር የተኮለኮለው ድንዛዜ ውስጥ ያለው ሃይል የጥላቻ ፡ የዘረፋ እና የሰቆቃ ፊታውራሪዎች የሆኑት ስብሃት ነጋ የአማራ ነጻ አውጪ ነኝ ብለው ቢመጡ የሚያጨበጭብ፡ አባይ ጸሃዬ ኦሮሞን ነጻ ላወጣ ነው ቢሉ የሚከተል ፥ ጌታቸው አሰፋ የደቡብ ብሄሮችን ልታድግ ነው ቢሉ ቀይ ምንጣፍ የሚዘረጋ ወዘተ መሆኑን የሚጠራጠር የድንዛዜያቸውን መጠን ያልተረዳ ብቻ ነው።

Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ

በመሆኑም ለማይሰሙ የሥልጣን ርሃብተኞች ሃጢያታቸውን ከማስታወስ፥ እንዲሁም በድንዛዜ ውስጥ ያሉ ተከታዮቻቸውን ለማንቃት ከመጨነቅ ግለሰቦቹ የትናንት ወንጀላቸውን እንዳይደግሙት መንግስት የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ሕጋዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ማሳሰቡ አስፈላጊ ይሆናል። እንደ ፓርቲ ለመመዝገብ አራት ሺህ ፊርማ ማሰባሰብ ያልቻሉ የት ይደርሳሉ የሚለው ንቀትም ተገቢ አይመስለኝም።

ግለሰቦቹ የራሳቸው ችግር ቢኖርባቸውም መንግስት በሕገወጥ መንገድ ሥልጣኑን የሚያራዝምበት ሁኔታ ውስጥ ከገባም በጉዳዩ ላይ መወያየቱ ክፋት የለውም። ለዚህ ምላሽ ለማግኘት ግን ሥልጣን ያለው መንግስት ምርጫውን ለማካሄድ ፍላጎት ነበረው ወይንስ አልነበረውም ? የሚለውን መጠየቅ ግድ ይላል። ቀን ተቆርጦ ዝርዝር መርሃ ግብር ወጥቶ ሂደቱ በቀጠለበት የኮሮና ቫይረስ መከሰቱ በፈጠረው ስጋት ምርጫው መስተጓጎሉ ግልጽ ሆኗል። በዚህ ሂደት ውስጥ መንግስት ምርጫው እንዲራዘም መፈለጉን የሚያሳይ ሁኔታ በግሌ አልታየኝም።

ይህ የመቶ ሺህዎችን ሕይወት የቀጠፈውና ሚሊዮኖችን የለከፈው ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) እንኳን ምርጫ አድርጋ የማታውቀውን ኢትዮጵያን በምርጫ ውስጥ ክፍለዘማናት ያስቆጠሩትን አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቷል። እንኳንስ ግለሰቦች እና ቡድኖች ሕግ ሆነው በኖሩባት ኢትዮጵያ ይቅር እና ሕግና ሥርዓት ለዘመናት በገነባቸው አሜሪካ ሕገ መንግስት ላይ ኮሮና ቫይረስ እያንዣበበ ይገኛል። International Institute for Democracy and Electoral Assistance (IDEA) የተባለ ተቋም ይፋ እንዳደረገው እ/አ/አ ከየካቲት 21 እስከ ሚያዚያ 29 2020 ባለው ግዜ ውስጥ 52 ሃገራት የምርጫ ግዚያቸውን አሸጋሽገዋል።

ከዚህ ውስጥ 17ቱ ያሸጋገሩት ዋና ምርጫ እና ሪፈረንደም ሲሆን፣አሜሪካውያንም ከ175 ዓመታት በኋላ የምርጫ ቀን ልንቀይር ይሆን ወይ ? የሚል ጥያቄ ማንሳታቸው ይፋ ሆኗል። የአሜሪካው ዕጩ ፕሬዚዳንት ዴሞክራቱ ጆ ባይደን በመጪው ህዳር 3/ 2020 GC የሚካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ውድድር ትራምፕ በኮሮና አሳበው ሊያሻግሩት ይሞክራሉ ሲሉ ከሰዋል።

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

ይህንን ተከትሎም በአሜሪካውያኑ ዘንድ የህግ ክርክር ተነስቷል።በርግጥ የምርጫ ቀኑን የመለወጥ ስልጣን የፕሬዚዳንቱ ሳይሆን የኮንግረሱ መሆኑን ዋሺንግተን ፖስት የህግ ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። ኮንግረሱም ቢሆን በየአራት ዓመቱ በህዳር ወር የመጀመሪያው ማክሰኞ ምርጫ ይካሄዳል የሚለውን ከ1845 ጀምሮ የተተከለውን የምርጫ ቀን ማሻሻል ቢችልም የምርጫ ቀኑን በሳምንታት መግፋት እንጂ ፥ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እ/አ/አ ከጥር 20 /2021 ዕኩለ ቀን በኋላ በኋይት ቤተመንግስት ውስጥ እንዲቆዩ የማድረግ ስልጣን የለውም።

ሁኔታው ወደዚያ ካመራ ሕገመንግስታዊ ማሻሻያ የግድ የሚል መሆኑን አሜሪካውያኑ የህግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ምርጫቸውን በፖስታ ቤት ጭምር መላክ በሚችሉት አሜሪካውያን ላይ የኮረና ቫይረስ ተጽዕኖ የጎላ እንደማይሆን ቢታመንም 2/3 ኛ የሚሆኑት አሜሪካውያን ኮረና ቫይረስ የአሜሪካንን ፕሬዚዳንታዊ ምርጭ ሊያስተጓጉል እንደሚችል ስጋታቸውን መግለጻቸውን የአሜሪካውያኑ የጥናት ትቋም ፒው ሪሰርች ከ10 ቀን በፊት ይፋ አድርጓል። ኮሮና ቫይረስ ለዓለም ሕዝብ ምን ያህል ፈተና እንደሆነ በዝርዝር ማየቱ ያስፈለገው የኢትዮጵያን ሁኔታ ከዚያ አንጻር ለመመዘንም ጭምር ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሕገመንግስት የፓርላማውም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ዘመን የሚያበቃው መስከረም 25 / 2013 ዓ.ም ነው። (እነ ጃዋር መስከረም 30ን ከየት እንዳመጡት አይገባኝም። ምክንያቱም ፓርላማው ስልጣኑ የሚያበቃው በ2013 ዓ.ም የመጨረሻው ሰኞ መስከረም 25 ነውና።) ፓርላማው የስልጣን ዘመኑ ከማብቃቱ በፊት ባለው አስገዳጅ ሁኔታ ስልጣኑን ለማራዘም ያለውን አማራጭ በተመለከተ መንግስት በባለሙያ ማስጠናቱን ይፋ አድርጓል።

ጥናቱን ያካሄዱት ባለሙያዎች መሆናቸው ከመነገሩ ባሻገር ያቀረቧቸው አማራጮች ሕገመንግስታዊ መሆናቸውን ሌሎች ገለልተኛ ባለሙያዎችም እየመሰከሩ ነው። የሽግግር መንግስት ብሎም ከዚያ አለፍ ያለ ጥሪ ለማድረግ በአንድ መድረክ በተገኙት ልደቱ እና ጃዋር መካከል እንኳን በዚህ ዙርይ አንድነት የለም። ልደቱ ሕገመንግስቱን በማሻሻል ማራዘም ሕጋዊ መሆኑን ተቀብሎ ግን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያስገምታል ሲል ጃዋር ደግሞ ምንም ሕጋዊ ምክንያት የለሚ ሲል ተደምጧል።

Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ

አውያዩ ግርማ ጉተማም ጉዳዩን ለማጥራት ያልፈለገው ለማስተተላለፍ በወሰኑት የጋራ መልዕክት ላይ ውዥንብር እንዳይፈጠር ይመሰለኛል።ህገ መንግስቱን ለማራዘም ህጋዊ መንገድ ካለ እና ይህም በአስገዳጅ ሁኔታ የተገባበት ከሆነ የሽግግር መንግስት ለምን ያስፈልጋል? ከሽግግር መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያተርፈው ምንድን ነው? እነማን ይሳተፋሉ? መመዘኛው ምንድን ነው ? የሕወሃት አጫዋች የነበሩና ለውጥ እንዳይመጣ ከሕወሃት ጎን ሆነው የታገሉትስ ይሳተፋሉን? ሕወሃትስ እንደ ደርግ/ኢሰፓ ይገለላል ? ወይንስ ይሳተፋል? ከ10 የማያንሱ የኦሮሞ ድርጅቶች እንዳሉ ይታውቃል። ለነዚህ የሚሰጠው ወንበር ከሕዝብ ቁጥር ፕሮፖርሽን አንጻር ይሆናል ወይንስ እንዴት ይደለደላል? ማን ምን ያህል ወንበር እንደሚያገኝ መመዘኛው ምንድን ነው? የካቢኔ ቦታ የሚሰጣቸው ድርጅቶች እንማን ይሆናሉ ? በምንስ መመዘኛ? አንዳንዶቹ ተጽዕኖ ፈጣሪ ድርጅቶች እና ግለሰቦች መለያቸው ይበልጥ ረብሻ ኣና በግርግር ከመሆኑ አንፃር የሽግግር መንግስቱ እነሱን ቀና በማድረግ ሁከት ማንገስ እንጂ መረጋጋት እንዲመጣ ያደርጋልን ? ሃገራዊ ራዕይ እና ኢትዮጵያዊነት እየለመለመ አክራሪነት እየከሰመ ባለበት ሁኔታ ውስጥ አክራሪዎች የበዙበት የሽግግር መንግስት የትናንት ጭለማን ከመጥራት ውጭ ምን መፍትሄ ያመጣል?ለኢትዮጵያ መድህን የሚሆናት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ነው። ለዲሞክራሲያው ምርጫ ደግሞ መረጋጋት ያስፈለጋል። ለመረጋጋት ደግሞ የተረጋጋ መንግስት ግድ ይላል። የተረጋጋ መንግስት እንዲቀጥል ደግሞ ሁላችንም ከሕግ በታች መሆናችንን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። በለውጡ ማግስት የተፈጠሩ ግርግሮች እንዳያገረሹ የሚያሳስበን ዜጎች ትግል እየሸጡ የከበሩ እና በብሄረሰብ ተሟጋችነት ሞት የሚነገዱትን የህወሓት ጉዳይ ፈጻሚዎችን እረፉ ልንላቸው ይገባል።

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0