በህገ መንግስቱ ምርጫው በየዓምስት አመቱ ይካሄድ ሲል አስቸጋሪ ሁኔታ ቢፈጠር ምን ይሁን የሚለውን ክፍተት የህገ መንግስት ትርጓሜ በመጠየቅ ምርጫውን በቀጣይ የሚካሄድበትን የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ እንደሚያስችል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ 6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ በተያዘለት ቀነ ገደብ ለማከናወን አለመቻሉን አስመልክቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በምክር ቤቱ ጸድቋል፡፡ የውሳኔ ሃሳቡን መርምሮ ቀጣይ ምርጫው በምን መልኩ መካሄድ አለበት የሚለው ላይ ህገ መንግስታዊ የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያቀርብ ለህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱም ይታወሳል።
ምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበውን ሕገ መንግስታዊ የመፍትሄ ሃሳብ መርምሮ፤ ምርጫን በተመለከተ የተቀመጡ ሶስት አንቀጾች ላይ የህገ መንግስት ትርጓሜ እንዲሰጥ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ትናንት በ 25 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
ምክር ቤቱ ያጸደቀው የውሳኔ ሃሳብ ምን ያህል ህጋዊና የተሻለ መንገድ ነው? ስንል የህግ ባለሙያውን አነጋግረናል።
የህግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ቁምላቸው ዳኜ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መካሄድ እንዳለበት ቢደነግግም ምርጫውን በተያዘለት ቀነ ገደብ ለማካሄድ የማያስችሉ አስገዳጅ ምክንያቶች ቢከሰቱ ምን መደረግ አለበት የሚለውን በግልጽ አያስቀምጥም።
በመሆኑም ህገ መንግስቱ ቀጣዩ ምርጫ እንዴትና በምን መልኩ ይካሄድ የሚለውን በግልጽ ባለማስቀመጡ ምርጫ ቦርድ ሕገ መንግስታዊ የመፍትሄ አማራጮችን ለምክር ቤቱ ሲያቀርብ ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፣ ህገ መንግሥት ማሻሻል፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅና የህገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ መሆናቸውን ይናገራሉ።
አቶ ቁምላቸው ከቀረቡት የመፍትሄ አማራጮች መካከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን የሚለው የመፍትሄ ሃሳብ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 60/1 ላይ የተቀመጠና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ በምክር ቤቱ ፈቃድ እንዲበተን ማድረግ ይችላል የሚለውን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።
በዚህ አንቀጽ እንደሰፈረው ምክር ቤቱ የተበተነ እንደሆነ ከስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ምርጫ መደረግ ስላለበት እስከ የካቲት ወር ድረስ ምርጫ ሳይካሄድ ለመቆየት ያስችላል። ነገር ግን ይሄ አንቀጽ ዓላማው ምርጫን ለማራዘም ሳይሆን ለአብነት ገዢው ፓርቲ የስልጣን ዘመኑ ሳያልቅ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ላይ ዕምነት ባይኖር ወይም በምክር ቤቱ አባላት መካከል ልዩነት ቢፈጠር፤ ፓርላማውን በትኖ በስድስት ወር ውስጥ ምርጫ በማካሄድ የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት የቀረበ መፍትሄ ነው። ስለዚህ ይሄንን አንቀጽ የምርጫውን ጊዜ ለማራዘም መጠቀም ከህግ አንጻር አግባብ እንዳልሆነ ያስገነዝባሉ።
እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማውን ነሃሴ ላይ ከበተኑት ምርጫውን በስድስት ወር ውስጥ ማድረግ የግድ የሚል ቢሆንም ፤ ኮሮና ቫይረስ በአገሪቱ በጤና ቀውስነቱ እስከ ታህሳስና ጥር ድረስ ከቀጠለ የዜጎች ጤና አጣብቂኝ ውስጥ ስለሚገባ ምርጫውን በስድስት ወር ውስጥ ለማካሄድ ያዳግት ይሆናል። ምርጫው ካልተካሄደ ደግሞ ህግ መንግስታዊ ቀውስ ይከተላል። ከስድስት ወር በኋላ አገሪቱም ወደ መንግስት አልባነት እንደምታመራ ያስረዳሉ።
ምርጫ ቦርድ የመራጮችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ሙሉ በሙሉ ሳያጠናቅቅ ኮቪድ 19 መከሰቱን ገልጸው፤ እስከ መስከረም ወር በቁጥጥር ስር ዋለ ቢባል እንኳን በስድስት ወር ውስጥ ቦርዱ ያላከናወናቸውን አያሌ ስራዎች አከናውኖ፤ ዜጎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን አንሸራሽረውና ተከራክረው ምርጫውን ማካሄድ ይቻላል ወይ? የሚለው እራሱ አጠያያቂ እንደሆነ አቶ ቁምላቸው ይናገራሉ።
በተጨማሪም በአንቀጽ 60/5 መሰረት ምክር ቤቱ ከተበተነ በኋላ አገሪቱን የሚመራው የፖለቲካ ድርጅት የባለ አደራ አስተዳደር ስለሚሆን የመንግሥትን የዕለት ተዕለት ሥራ ከማከናወን እና ምርጫን ከማካሄድ በስተቀር አዲስ አዋጆችን፣ ደንቦችንና ድንጋጌዎችን ማውጣት ወይም ነባር ህጎችን መሻርና ማሻሻል አይችልም።
አሁን ላይ አገሪቷ አያሌ ፈተናዎችና ችግሮች የተጋረጡባት ሆና እያለች በዚህ መልኩ መሄድ ለፈተናዎች በቂ ምላሽ ለመስጠት የሚችል ሙሉ መንግሥት እንዳይኖራት ያደርጋል። ከዚህ አንጻር የመጀመሪያው የመፍትሄ ሃሳብ ምርጫውን በቀጣይ ለማካሄድ አዋጭ መንገድ አለመሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ቁምላቸው ሌላው የቀረበው የመፍትሄ ሃሳብ ህገ መንግሥት ማሻሻል በህገ መንግሥቱ ግልጽ የሆነ መሰረት ያለው ሲሆን፤ ይህም በአንቀጽ 104 እና 105 ላይ በግልጽ ተቀምጧል። የህገ መንግሥት ማሻሻያ ሃሳብን ለማመንጨት ሶስት ምዕራፎች አሉት።
የህገ መንግሥት ማሻሻያ ሃሳብን ማመንጨት፤ የፌዴራል መንግሥት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2/3 ድምጽ ከደገፈው ወይም የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በ2/3 ድምጽ ሲያጸድቀው ነው። የፌዴሬሽኑ አባል ከሆኑ ክልሎች 1/3 ድምጽ (አሁን ባለው ሁኔታ) ከዘጠኙ ሶስቱ ክልሎች በምክር ቤቶቻቸው ከደገፉት የማሻሻያ ሃሳብ መንጭቷል ማለት ይቻላል።
የማሻሻያ ሃሳቡን ማጽደቅ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በ2/3 ድምጽ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት እና ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤቶች የ2/3ኛው በድምጽ ብልጫ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት ነው።
እንዲሁም ህገመንግስቱ የመንግስትና የዜጎች የጋራ ሰነድ በመሆኑ ህገመንግስቱን ለማሻሸል መላውን ህዝብ ያሳተፈ ውይይት ማድረግም የሚፈልግ በመሆኑ፤ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ህዝባዊ ውይይት ለማድረግ ኮቪድ 19 እንቅፋት ስለሚሆን ዜጎች ሃሳባቸውን ተለዋውጠው፣ ተከራክረውና ተወያይተው ድጋፍ ባላደረጉበት ሁኔታ ህገመንግስት ማሻሻያው እራሱ ኢ-ህገመንግስታዊ ይሆናል። በመርህ ደረጃ ጥሩ መንገድና ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ ቢሆንም፤ ኮቪድ 19 በአገሪቱ የጤና ቀውስ ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ ይሄንን የመፍትሄ ሃሳብ በተግባር ተፈጻሚ ማድረግ እንደማይቻል ገልጸዋል።
የህግ ባለሙያው ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዜጎች ሳይሳተፉበትና ውይይት ሳያደርጉበት የህገ መንግስት ማሻሻያው ቢደረግ፤ አምባገንን መሪዎች የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ለይስሙላ የህገ መንግስት ማሻሻያ እንደሚያደርጉት ሁሉ፤ መንግስትም የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ሲል የወሰደው የመፍትሄ ሃሳብ በሚል ከፍተኛ ውግዘትና ነቀፋ በኃያላን መንግስታትና በፖለቲከኞች ዘንድ ከፍተኛ ውግዘት እንደሚያስከትል ተናግረዋል።
በሶስተኛ ደረጃ የቀረበው አማራጭ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ሲሆን፤ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 93/1 መሰረት የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደ የህግ ማስከበር ሥርዓት መቋቋም የማይቻል ከሆነ፤ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የፌዴራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ስልጣን እንዳለው የህግ ባለሙያው ይናገራሉ።
አቶ ቁምላቸው በአንቀጽ 93 እንደሰፈረው ከህገ መንግሥቱ አንቀጽ 1፣ 18፣ 25 እና 39/1 እና 2 በስተቀር ያሉ መብቶች ላይ ገደብ ይጥላል። በዚህም የምርጫ ጊዜን ማራዘም የሚቻል መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ የመፍትሄ ሃሳብ ጠንካራ ጎኑ አስፈላጊውን ስልጣንና ኃላፊነት ያለው መንግሥት እንዲኖር ያስችላል። በአገር አቀፍ ደረጃም ተፈጻሚ መሆን ይችላል።
ነገር ግን የፓርላማውን የስልጣን ዘመን የሚመለከተው አንቀጽ 58 መብት ሳይሆን መደበኛ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ስለሆነ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይሄንን አንቀጽ መገደብ ይቻላል ወይም አይቻልም የሚለው ነጥብ እራሱ አከራካሪ መሆኑን ይገልጻሉ።
ሆኖም ይህ አማራጭ ተግባራዊ ቢደረግ እንኳን ምርጫው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማዕቀፍ ውስጥ ስለሚካሄድ፤ ተዓማኒነትና ነጻነቱንም ጥያቄ ውስጥ ይጥላል። እንዲሁም ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚያዳብር እንደማይሆን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ ከነሃሴ በፊት መፍትሄ ካገኘ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማራዘም ምንም ምክንያት ስለማይኖር፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማራዘም ምርጫውን ከነሃሴ በኋላ እንዲካሄድ ቢደረግ የመንግስትን ስልጣን ለማራዘም ነው ተብሎ ከፍተኛ ቅሬታ እንደሚያስነሳ ባለሙያው ያስረዳሉ።
በመሆኑም የቀረቡት አማራጮች የራሳቸው የሆነ ጠንካራና ደካማ ጎን ያላቸው ሲሆን፤ የተሻለ አማራጭ የሚሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀው የህገ መንግስት ትርጓሜ መጠየቅ የሚለው የመፍትሄ ሃሳብ ነው የሚሉት አቶ ቁምላቸው፤ የህገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 62/1 እና አንቀጽ 84/1 መሰረት በግልጽ ተቀምጧል ይላሉ።
ይህም ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ ህጎችን በማስታረቅ የህገ መንግሥት ክፍተቶችን ለመሙላት የተለመደ አሰራር በመሆኑ ህገ መንግስቱ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መካሄድ እንዳለበት ሲደነግግ፤ ነግር ግን ምርጫውን በተያዘለት ቀነ ገደብ ለማካሄድ የማያስችሉ አስገዳጅ ችግሮች ሲከሰቱ ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ ያስቀመጠው ድንጋጌ ወይም አንቀጽ የለም።
ስለዚህ በህገ መንግስቱ ምርጫው በየዓምስት አመቱ ይካሄድ ሲል አስቸጋሪ ሁኔታ ቢፈጠር ምን ይሁን የሚለውን ክፍተት የህገ መንግስት ትርጓሜ በመጠየቅ ምርጫውን በቀጣይ የሚካሄድበትን የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ እንደሚያስችል ያስገነዝባሉ።
በመሆኑም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የራሱን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ህገ መንግስታዊ ትርጓሜ ሰጠ የሚባል ትችት ቢያስነሳም፤ ካለው ነባራዊ ችግር አንጻር ህገ መንግስቱን ለመተርጎም ህጋዊ ስልጣን በተሰጠው አካል መታየቱ፣ ስነ ህጉን ለማሳደግና ለማዳበር ጠቃሚ በመሆኑ፣ የህግ አውጪውንና ተርጓሚውን አካል ያሳተፈ በመሆኑ የህገ መንግስት ትርጓሜ መስጠት ህገ መንግስታዊና ከቀረቡት የመፍትሄ አማራጮች የተሻለው መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ባለሙያው እምነት፤ አገሪቷ ሉአላዊነቷ ተከብሮ፣ ጸንታና ታፍራ፣ ብሄራዊ ጥቅሞቿ ተጠብቀው የሚቀጥለው ምርጫ ተካሂዶ ህግና ሥርዓት ተከብሮ አገር እንድትቀጥል ለማስቻል ከቀረቡት አማራጮች አንዱን የግድ መውሰድና ተግባራዊ ማድረግ ባይቻል ኖሮ፤ ህገመንግስታዊ ቀውስ ሊከሰት ይችል ነበር። ህገ መንግስታዊ ቀውሱ ደግሞ ወደ ፖለቲካ ቀውስ አምርቶ አገሪቷ መንግስት አልባ ሆና ወደማያባራ ትርምስ ውስጥ ልትገባ ትችል ነበር ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2012

ሶሎሞን በየነ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *