“Our true nationality is mankind.”H.G.

እንዳይሸጥ የተከለከለ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሲሸጡ የነበሩ በቁጥጥር ስር ዋሉ

 

ለገበያ እንዳይቀርብ የተከለከለ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት 15 ሺህ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሲሸጡ የነበሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መርማሪ ሳጅን ማናስበው አላምረው እንደገለፁት ተጠርጣሪዎቹ ለገበያ እንዳይቀርብ የተከለከለ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የንግድ ፍቃድም ሆነ ከምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ህጋዊ የፈቃድ ወረቀት ሳይኖራቸው በማህበራዊ ድረ ገፅ በማስተዋወቅ እና ለሽያጭ በማቅረብ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲጠቀሙ በመሸጥ ላይ እንዳሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ገልጸዋል።

ፖሊስ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተጨማሪ መረጃዎችን በማሰባሰብ እና አስፈላጊውን ህጋዊ ሂደት ተከትሎ በቤታቸው ባደረገው ፍተሻ ተጨማሪ ከ1 ሺህ 800 በላይ ፈቃድ የሌላቸው የአፍ መሸፈኛ ጭምብል እንዲሁም 15 የሙቀት መለኪያ መሳሪያ መያዙን ሳጅን ማናስበው ተናግረዋል።

በዚህ በህገ ወጥ ተግባር ላይ ተሳትፎ አላቸው ብሎ የጠረጠራቸውን 11 ግለሰቦች ፖሊስ ይዞ ምርመራ እያደረገ መሆኑም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ከተከሰተ ጀምሮ ከሌሎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ለሚያመርቱ አካላት ወይም ድርጅቶች የብቃት ማረጋገጫ እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ህብረተሰቡም የንፅህና መጠበቂያ ሲገዛ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን በማረጋገጥ እንዲገዛ ማሳሰባቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ኤፍ.ቢ.ሲ

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0