በነጭ ፖሊስ ቁጥጥር ስር በግፍ በሞተው ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ምክንያት በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች በተቃውሞዎች እየተናጡ ነው።

የአርባ ስድስት ዓመቱ ጆርጅ በሚኒያፖሊስ ከሚገኝ ሱቅ ውጭ ግንቦት 17/2012 ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ።

ብዙዎችን ያስደነገጠው ቪዲዮ እንደሚያሳየው ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ መሬት ላይ ተኝቶ ነጭ ፖሊስ አንገቱን ላይ በጉልበቱ ተንበርክኮበት ይታያል።

ጆርጅ ፍሎይድ ከመሞቱ ሰላሳ ደቂቃ በፊት ምን ተፈጠረ? በአካባቢው ከነበሩ የአይን እማኞች፣ ቪዲዮና መግለጫዎች የሚታወቁት ነገሮች የሚከተሉት ናቸው።

ካፕ ፉድስ ከተባለ አንድ መደብር ሲጋራ ገዛ። የመደብሩ ሠራተኛ ጆርጅ ፍሎይድ የሰጠኝ 20 ዶላር ሐሰተኛ ነው በማለት ፖሊስ ጋር ደወለ።

ቴክሳስ ተወልዶ ያደገው ጆርጅ ፍሎይድ በሚኒያፖሊስ መኖሪያውን ካደረገ ዓመታትን አስቆጥሯል።

በቅርቡም በአንድ ሬስቶራንት ውስጥ በጠባቂነት ተቀጥሮ እየሰራ የነበረ ቢሆንም፤ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እንደ በርካታ ሚሊዮን አሜሪካውያን ሥራ አልባ ሆኗል።

ጆርጅ ፍሎይድ የካፕ ፉድስ የተባለው መደብርም ደንበኛ ነበር።

በበርካታ ጊዜያትም እቃ እየመጣ እንደሚገዛ፣ ሁሉንም በትህትና ሰላም የሚል፣ በወዳጅነት የሚቀርብ ሰው እንደነበርም የመደብሩ ባለቤት ማይክ አቡማየለህ ለኤንቢሲ ተናግረዋል።

Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

በዚያች መጥፎ ቀን ግን የመደብሩ ባለቤቱ ማይክ አቡማየለህ በሥራው ቦታ ላይ አልነበሩም። በመደብሩ ተቀጥሮ የሚሰራው ታዳጊ የተጠራጠረውን ዶላር ሪፖርት አደረገ። ከ911 ጥሪ በተገኘው መረጃ መሰረት ታዳጊው ሲጋራውን መልስልኝ እንዳለውና ፍሎይድም አልመልስም እንዳለው ተናግሯል።

ሱቅ ሻጩ አስከትሎም ጆርጅ ፍሎይድ የጠጣ እንደሚመስልና ራሱንም መቆጣጠር አልቻለም ብሎ ተናግሯል።

ጥሪው ከተደረገ ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ፖሊሶች ደረሱ። በወቅቱም ጆርጅ ፍሎይድ ከሁለት ግለሰቦች ጋር በአካባቢው የቆመ መኪና ውስጥ ተቀምጦ ነበር።

ወደ መኪናዋ ከተጠጉ በኋላ ቶማስ ሌን የተባለው ፖሊስ ሽጉጡን በማውጣት ከመኪናው እንዲወርድ ትዕዛዝ ሰጠው። በወቅቱ ሽጉጡን መምዘዝ ለምን እንዳስፈለገውም አቃቤ ሕግ ያለው ነገር የለም።

ቶማስ ሌን ለአቃቤ ሕግ በሰጠው የምስክርነት ቃል “እጅህን ወደላይ አልኩት እናም ከመኪናው ጎትቼ አወረድኩት” ካለ በኋላ “ጆርጅ ፍሎይድ በእጅ ሰንሰለት ለመታሰር አንገራግሯል” ብሏል።

ከታሰረ በኋላ ግን ጆርጅ ፍሎይድ ታዛዥ መሆኑን የገለፀው ፖሊሱ ቶማስ ሌንም “ሐሰተኛ ገንዘብ በመያዝ” እንደታሰረ ለጆርጅ መናገሩን አስረድቷል። ከዚያም ወደመኪናቸው ሊያስገቡት ሲሉ ትግል እንደተፈጠረም ተገልጿል።

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

የስልክ ጥሪው ከተደረገ ከአስራ አራት ደቂቃ በኋላም ጆርጅ “ሰውነቱ ድርቅ ብሎ ተዝለፍልፎም መሬት ላይ ወደቀ። ለፖሊሶችም ጠባብ ቦታ እንደሚያፍነውና እንደሚያስጨንቀው መናገሩን” ሪፖርቱ ጠቅሷል።

የስልክ ጥሪው ከተደረገ አስራ አራት ደቂቃ በኋላ ነበር ዴሪክ ቾቪን ቦታው ላይ የደረሰው። እሱም ሆነ ሌሎች ፖሊሶች ከኋላ ሊጭኑትም እየሞከሩ ነበር። በዚህ ወቅት ነበር፣ በአስራ ዘጠነኛው ደቂቃ ቾቪን ጆርጅ ፍሎይድን መሬት ላይ የጣለው።

እጁን ታስሮ የነበረው ጆርጅ ፍሎይድም መሬት ላይ ከወደቀ በኋላ ነበር አንዲት ታዳጊ ሁኔታውን የቀረፀችው።

ጆርጅ ፊቱ ላይ መረበሽና መጨነቅም ይታይበት ነበር። የመጨረሻ እስትንፋሱም ሆነ ደቂቃዎች በቪዲዮ ተቀርፆም ለዓለም ሕዝብ ተጋርቷል።

በእጅ ሰንሰለት ታስሮ እንዲሁም በፖሊሶች ተይዞ የነበረ ሲሆን፤ አንደኛው ነጭ ፖሊስም በጭንቅላቱና በአንገቱ መካከል የግራ ጉልበቱን ጭኖበት ነበር።

“መተንፈስ አልቻልኩም” በማለት በተደጋጋሚ ሲለምን እንዲሁም እናቱ እንድትደርስለት ሲማፀን የነበረው ጆርጅ “እባክህ፣ እባክህ፣ እባክህ” ሲልም ተሰምቷል።

ለዘጠኝ ደቂቃ ያህል የሚጠጋ (8 ደቂቃ ከአርባ ስድስት ሰድስት ሰኮንዶችም) በጉልበቱ አንገቱን እንደተጫነው ከአቃቤ ሕግ የተገኘ ሪፖርት ያሳያል።

Related stories   ሀገሪቷን ከጥፋት ለመከላከል ፣ ህግን ለማስከበር ፌዴራል ፖሊስ ተግባሩን ያጠናክራል
ዴሪክ ቾቪን
አጭር የምስል መግለጫበግድያው የተከሰሰው ዴሪክ ቾቪን

ፖሊሱ አንገቱን ተጭኖት ስድስት ደቂቃ እንዳለፈው ነው ጆርጅ ፍሎይድ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማሳየት ያቆመው።

ጆርጅ መለመኑንም አቆመ፣ አንድ መንገደኛም ፖሊሶቹን የልብ ትርታውን እንዲያደምጡ ጠየቃቸው። አንደኛው ፖሊስ የቀኝ እጁ ላይ ትርታ መኖሩን ለማረጋገጥ ቢሞክርም ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማግኘት አልቻለም። ሆኖም ፖሊሶቹ ከጆርጅ ሰውነት ላይ አልተነሱም።

በሃያ ሰባተኛው ደቂቃ ነጩ ፖሊስ ምንም እንቅስቃሴ ከሌለው ሰውነቱ ላይ ጉልበቱን አነሳ። ጆርጅ ፍሎይድም በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ቢደርስም ከአንድ ሰዓት በኋላ መሞቱ ታውቋል። ከመሞቱ ከአንድ ቀን በፊትም ከጓደኛው ክርስቶፈር ሃሪስ ጋር በሚወያዩበት ወቅትም ጊዜያዊ ሥራ እየፈለገ መሆኑንም ነግሮት ነበር።

“አሟሟቱ ጭካኔ የተሞላበት ነው። ህይወቱን እንዲያተርፉለት ሲለምን፤ ሲማፀንም ቆይቷል። እምነትህን ላንተ በማይቆም ሥርዓት ላይ ስትጥል ይኸው ነው ውጤቱ። ፍትህንም ሕጋዊ በሆነ መንገድ ስትሻም ሆነ ሳታገኛት ስትቀር በራስህ መንገድ ለማግኘት ትሞክራለህ” ብሏል።

Read the original – BBC Amharic

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *