(ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ሁሉም ፓርቲዎች አንድ ዓይነት አቋም መያዛቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

የጋራ ምክር ቤቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለድርድር የሚቀርብ አለመሆኑንም ገልጿል። የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ያላትን አቋምና የግንባታ ሂደቱን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ላይ የሚያደርጉት ድርድር ላልተወሰ ጊዜ መቋረጡ ይታወቃል።

ኢትዮጵያም ግድቡን በተያዘለት ጊዜ ውኃ ለመሙላት የማንም ድጋፍና ዕርዳታ እንደማያስፈልጋት መግለጿ ይታወሳል።

በዚህም ግብፅ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የሀሰት መረጃዎችን ለዓለም በማስተጋባት በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

Related stories   በዓድዋ ከተማ የመብራት አገልግሎት ዛሬ ጀመረ

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሣ አደም እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ በምክንያታዊነትና ፍትሐዊነት ለመጠቀም የግብፅ ፈቃድ አያስፈልጋትም።

ግብፅ ባይሳካላትም የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት እንደ መልካም አጋጣሚ ስትጠቀምበት ቆይታለች ብለዋል።

የውኃ ሙሌቱን ለማደናቀፍ ግብፅ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚያወግዙ የገለጹት አቶ ሙሣ በግድቡ ግንባታ እንዲጠናቀቅ ተመሣሣይ አቋም መያዛቸውን ይፋ አድርገዋል።

ግብፅ የዓባይን ወንዝ በምክንያታዊና ፍትሐዊ መንገድ ለመጠቀም ከቅኝ ግዛት ሥምምነት ታሪክ ይልቅ ተፈጥሯዊ መብት እንደሚበልጥ ማወቅ አለባት ብለዋል።

የአፍሪካውያን ጉዳይ በአፍሪካውያን መፈታት እንዳለበት እናምናለን ያሉት አቶ ሙሣ፤ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን  በራሳቸው ተወያይተው ሥምምነት ላይ መድረስ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከ1 ሚሊዮን 485 ሺህ ብር በላይ በሥጦታና በቦንድ ግዥ ለግድቡ ግንባታ ማበርከቱን ገልጸዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ድጋፍ ቀጣይነት ይኖረዋልም ብለዋል።

Related stories   "ሬንጀርስ" የሚባል በመሳሪያ የተደገፈ ዝርፊያ የሚፈጽም የማፍያ ቅርጽ ያለው ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም የግድቡ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ 13 ቢሊዮን 54 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል ብለዋል።

በተያዘው የ2012 ዓ.ም 605 ሚሊዮን ብር በሥጦታና በቦንድ ግዥ መሰብሰቡን ገልጸዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በገቢ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የገለጹት አቶ ኃይሉ፤ ኅብረተሰቡ በዚህ ሳይዘናጋ በ8100A አጭር የጽሑፍ መልዕክትና ሌሎች አማራጮች ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *