“Our true nationality is mankind.”H.G.

“የሰውን” ዘር መሰረት አድርጊያለሁ የሚለው አምነስቲ!!

የአምንስቲ ኢንተርናሽናልን ሪፖርትር በጥሞና አነበብኩት። እጅግ ስሜት የሚነኩ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በሪፓርት ውስጥ ተካቷል። ግፍ ለተፈጸመባችሁ አይደለም፣ ለሰማነው እንኳን ከባድ ጸጸት ጥሎብናል። የኢትዮጵያውያን እናትና አባቶች ሆይ መጽናናቱን ይስጣችሁ እላለሁ!! የመረጃው ጥራትና ሚዛናዊነት እንደተጠበቀ ሆኖ የቀረበው ሪፓርት አሳሳቢ ስለሆነ መንግስት ተገቢውን ማጣራት አድርጎ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አበክሬ እጠይቃለሁ።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ሪፓርቱን ጠለቅ ብለን ስንፈትሽ ግን የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት አንድ ክልልን፣ ያውም አንድ የፖለቲካ መስመርን ብቻ ተከትሎ ለምን ተዘገበ የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል። ከታሪክና ከተሞክሮ እንደምንረዳው። አምንስቲ በአንግሎ ሳክሰን ነጮች የተሞላ፣ በግልጽ ከሚዘግበው ባልተናነሰ የሕቡዕ ዓላማና ግብ የተበጀለት ከምዕራብውያን ውጭ ሌላው የዓለም ፍጡር ሁላ ግፈኛና አረመኔ አስመስሎ ለማሳየት የተመሰረተ ተቋም ነው።

ለዚህም ነው በርካቶች አምንስቲን ቀለም አምላኪ ነጮች፣ የኒዎ ኮሎኒያል ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ያለ ክብሩና ያለ ንጽህናው በማወደስ፣ በማሞገስና ተደማጭነት እንዲኖረው በማድረግ፤ ዓላማቸውን እንዲያሳካ የሚያሰማሩት ለስላሳ ሃይል (Soft Power) ነው ። ይህ ብቻ አይደለም፣ አምንስቲ የገዢዎቹን ተልዕኮ ማስፈጸሙ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተረፈው ሰዓት፣ ጊዜና እግረ መንገዱን የራሱን “ጥሪ” እና “ተልዕኮ” አንግቦ፣ የበለጠ ለቀረበውና ለከፈለው የሚተጋ የመፈንቅለ መንግስትና የብሔር ግጭት ሴራ መጠንሰሻና መቀፍቀፊያ ተቋም እንደሆነ በርካቶች የሚያሰማሙበት ነው።

ወደ ሀገራችን ጉዳይ ስንመለስ፣ ባለፈው ሶስት ዓመት፣ በመንግስት ሃይልም ሆነ በታጣቂ ቡድን፣ በፓለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በጽንፈኛ ቡድኖች ቀጥተኛ ተሳትፎ በሺ የሚቆጠሩ ዜጎች በግፍና በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ እህቶቻችን፣ እናቶቻችን ተደፍረዋል። በፖለቲካ ሃይሎች የጥላቻ ፖለቲካ ምክንያት፣ ያለ ምክንያት በግፍ የፈሰሰው የሱማሌው፣ የጋሞው፣ የወላይታው፣ የኦሮሞው፣ የአማራው፣ የትግራዩና የጉራጌው ደም ከመቃብር በላይ እየጨሆ ነው።

በዩኒቨርስቲዎቻችን ውስጥ ሞታቸው ከንቱ ሆኖ የቀሩ ልጆቻችን፣ እምጥ ይግቡ እስምጥ መላቸው ሳይታወቅ ደብዛቸው የጠፋ እህቶቻችን ጉዳይስ የታለ!? አምንስቲ ሆይ ዛሬ ኢትዮጽያ ውስጥ ያንድ ወገን ዘገባ፣ ያንድ ቡድን ትርክት በቂ ተጫዋችና ተዋናኝ አለው።

ኢትዮጵያውያን የቸገረንና ዘመኑ የደቀነብን ፈተና ግን ዘር ለይቶና ብሔር ቆጥሮ የሚሰራጭን የጥላቻ ዘገባ ሰበብ እያደረገ የሚፈጸምው ፍጅትና እልቂት ነው። ይህ አልበቃ ብሎ ግን ሚዛናዊነትና ርትዕ የጎደለው፣ የአንድ ፓለቲካ መስመር ተከትሎ የሚቀነቀን ፣ አንዱን አቃፊ ሌላውን አግላይ ሪፖርት ማቅረብ “የሰውን” ዘር መሰረት አድርጊያለሁ ከሚል ተቋም ሲቀርብ ማየት ከአሳፋሪነትም በላይ ነውር ነው።

ስለሰው ዘር ፍትህና ርትዕ ከቆማችሁ፣ የሌሎቻችን ሞት፣ ስደት፣ እርዛትና ግድያ ለምን አልተሰማችሁም፤ ለምንስ አልቆጫችሁም?! ብትወዱትም ብትጠሉት፤ ሌሎቻችንም እንደ ሰው ልጅና እንደ ዜጋ የሚሳሳልን፣ የሚያለቅስልን በሕይወት እንድንኖርለት የሚፈልግና የምትፈልግ እናት፣ አባት፣ እህትና ዘመድ፤ ቢያንስ ደግሞ ወገን ያለን ፍጡሮች ነን። አምንስቲ ሆይ፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ፣ የሰውን ዘር በእኩል የሚያይ ግፍና ግፈኞችን የሚጸየፍና በስማቸው የሚጠራ ለፍትህ እንዲቀርቡ ጥሪ የሚያቀርብ ሪፓርት አሁኑኑ እንዲወጣ እንጠይቃለን።

Via Moshe Semu

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0