የጣና ሐይቅ የመኖር ዋስትና በእጅጉ እየፈተነ ያለውን የእምቦጭ አረም ለመከላከል እና ለማስወገድ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ምክክር ተደርጓል።
ጣናን የወረረውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ባለፉት ዓመታት ጥረት ቢደረግም መፍትሔ አልመጣም። ዛሬ የተደረገው ምክክርም ሁነኛ መፍትሔ ለማምጣት ያለመ ነው። በምክክሩ የተገኙ ተሳታፊዎች ጣና የማን ነው? የሚለው ጥያቄ መመለስ መቻል እንደሚገባ አንስተዋል። “ጣና አገራዊና ዓለማቀፋዊ ሀብት ሆኖ ሳለ ለአማራ ክልል ብቻ መሰጠቱ ተገቢ አይደለም። የፌዴራል መንግሥት ከጥቅሙ ብቻ ሳይሆን ከችግሩም መጋራት መቻል አለበት” ብለዋል ተወያዮቹ። ጣና ሐይቅን ከአረም ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችለውን አቅም በመለዬት የሚያንሰውን መጠዬቅ እንደሚገባ ያመለከቱት ተሳታፊዎቹ ዘላቂ መፍትሔ በባምጣት ረገድ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ አንስተዋል። እምቦጭን ለመከላከል እና ለማስወገድ በሚደረገው ሂደት የጋራ ስምምነት እንደሌለ የተናገሩት ተሳታፊዎቹ “በመጀመሪያ የጋራ ስምምነት ያስፈልጋል” ብለዋል። የቴክኒክና የማስተባበሪያ ኮሚቴው ትኩረት ማነስም እንዲስተካከል አሳስበዋል።
በክልሉ ያለው የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻና ነቀፌታ ሥራውን እንዳልተሠራ ከማድረጉም ባለፈ ጥሩ የሚሠሩ አካላት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑም ተነስቷል። ዘመቻው በዕውቀት እና በተግባር የተመሠረተ ሆኖ ለጣና መሥራት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ተሳታፊዎቹ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጠንካራ ጥናት መሠራት እንደሚኖርበትም አመልክተዋል።
ችግሩን ለመፍታት ከጫጫታ ባለፈ በብልሃት የተሞላ አሠራር እንደሚያስፈልገውም ተናግረዋል። “በእምቦጭ አረም የመጀመሪያው ተጎጂ የአካባቢ ማኅበረሰብ ነው” ያሉት ተሳታፊዎቹ የእንቦጩን ባሕሪ መለዬትና ማወቅ እንደሚገባም ተናግረዋል። ችግሩን ለመፍታት ለአርሶ አደሩ የሚሰጠው ትምህርት በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል። የሐይቁን በአረሙ የተያዘውን ክፍል ብቻ ሳይሆን ያልተያዘውንም አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል።
ጣና ላይ መዘናጋት ከተፈጠረ ከእጅ እንደሚያመልጥ በማመላከት ወደሐይቁ መዳረሻ ያሉ የመንገድ ሥራዎች በአስቸኳይ መሠራት እንዳለባቸውም ተመላክቷል። በየዩኒቨርሲቲዎች ገንዘብና ጉልበት ፈስሶባቸው የተሠሩ የምርምር ውጤቶች ወደተግባር እየገቡ አለመሆኑም ተነስቷል። ጣናን ለመታደግና ወደትግበራ ለመግባት ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እንደሚያስልጉም ተነግሯል። የቁርጠኝነት ችግር ከሌለ በስተቀር ያን ያክል ሊያጠፋ የሚችል ችግር እንደሌለም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል። “ከተቋቋመው ኤጄንሲ ባለፈ ምርምር የሚያደርጉ ባለሙያዎች ተመርጠዋል፤ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው እንዲሠሩ መደረግ አለበት” ተብሏል በምክክሩ።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወርቀሰሙ ማሞ “በጣና ሐይቅ ላይ ይህን ያክል ዓመት ሠርተን ውጤት ካላመጣን አካሄዳችን ልክ አልነበረም ማለት ነው፣ በመሆኑም አካሄዳችንን አስተካክለን መሄድ አለብንም” ብለዋል። በሚሠራው ሥራ ዕውቀት እና ተነሳሽነት ሊኖር እንደሚገባም ተናግረዋል። “ወደትግበራ ለመግባት ያለንን ከሌለን መለዬት መቻል አለብን” ሲሉም አሳስበዋል። የክልሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የየራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። የጣና ዙሪያ አርሶ አደሮች ብቻ ሳይሆን ሌላው አርሶ አደርም ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ያመለከቱት አፈ ጉባኤዋ “ካልሆነ ግን ለአካባቢው አርሶ አደሮች የተለዬ ድጋፍ ሊደግላቸው ይገባል” ብለዋል። እምቦጭ በሰው ኃይል፣ በማሽን፣ በኬሚካል እና በተለያዩ የመከላከያና የማስወገጃ ዘዴዎች ሊወገድ የሚችልበት ዝርዝር ጥናት ለክልሉ መንግሥት መቅረብ እንዳለበትም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) “ችግሮቹ ሳይንሳዊ ምላሽ ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል። እስካሁን የነበሩ የመፍትሔ ሐሳቦች ለምን አልተሳኩም የሚለው ጉዳይ የሁሉም የቤት ሥራ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል። በጣና ዳርቻ በእምቦጭ አረም የተያዘውን 900 ሄክታር መሬት በቶሎ ካልተወገደ በቀጣይ ከፍ ያለ ችግር እንደሚያጋጥምም ገልጸዋል። “ሥራችን ጣናን የማዳን ጉዳይ ሳይሆን እኛን የማዳን ጉዳይ መሆን መቻል አለበት፣ ጣና የያዘው እኛን ነው፤ ጣናን ስናስብ እኛን ማሰብ፣ እኛን ስናስብም ጣናን ማሰብ መቻል አለብን” ብለዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተደድር ተመሥገን ጥሩነህ “ጣና አይነጥፍም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፤ ጣናን ለመታደግ በተባባሪነት ከልባችን መሥራት አለብን” ብለዋል። የጣናን ዙሪያ ማልማትም ዋናው ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል። ሥራዎችን በዕውቀትና በሰከነ መንገድ መምራት እንደሚገባ አሳስበዋል። ሐሳብ ያለቸው ሰዎች ሐሳብ ማዋጣት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። ተባብሮ ከተሠራ የጣና ሐይቅ ጉዳይ ከእጅ እንደማይወጣም ተናግረዋል። “የጣና ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳደር ተመሥገን ጥሩነህ ለጣና ከፍተኛው ስጋት እምቦጭ ብቻ ሳይሆን የባሕር ሸሽ እርሻም እንደሆነ አመልክተዋል። “ለዚህም ዘላቂ መፍትሔ መስጠት አለብን” ብለዋል። በጣና ሐይቅ ዙሪያ ያለው የመረጃ አያያዝም ጠንካራና የተደራጀ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
በምክክሩ ጣና ሐይቅ ላይ ጠንካራ እና ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚሻ ስምምነት ላይ ተደርሷል። የተሠሩ ሥራዎችንና ሂደቶቹን በየወሩ እየተገናኙ ለመገምገምና ለመምከርም ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
(አብመድ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሲሲሊ፥ ለወሲብ በባርነት የሚሸጡ ሴት ናይጄሪያውያን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *