“Our true nationality is mankind.”H.G.

ሰረባር ባለእግዚአብሔር – ከላልይበላ ቀደምት የሆነው ፍልፍል ቤተክርስቲያን

ከላልይበላ በፊት ፍልፍል ቤ/ክ
በንጉሥ ላልይበላ ከላልይበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት በፊት እንደተሠራ የሚነገርለት ወጥ አለት ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን፡- ሰረባር ባለእግዚአብሔር።ሰሜን ጎንደር ዞን በርካታ ዕድሜ ጠገብ ሰው ሰራሽ እና ለዕይታ ማራኪ የሆኑ የተፈጥሮ ቅርሶችን የያዘ ነው።
በዞኑ በርካታ ቅርሶችን ከያዙት ወረዳዎች መካከል የጃናሞራ ወረዳ ተጠቃሽ ነው። በወረዳው ከሚገኙት ሰው ሰራሽ ቅርሶች መካከል በ11ኛው ክፍለ ዘመን በንጉሥ ላልይበላ እንደተሠራ የሚነገርለት የሰረባር ባለእግዚአብሔር ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን ይገኝበታል።
ይህ ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን ከወረዳው መዲና መካነ ብርሃን በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ደቡብ አቅጣጫ ሰረባር በተሰኘው ቀበሌ የሚገኝ ነው፡፡
የሰረባር ባለእግዚአብሔር ቄሰ ገበዝ ዓለማየሁ መንግሥቱ ቤተ ክርስቲያኑ ከላልይበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ቀድሞ በንጉሥ ላሊበላ የተሠራ መሆኑን ነግረውናል፡፡ ‘ሰረባር’ ‘ቀይ አፈር’ ማለት እንደሆነና አካባቢው ቀይ አፈር የሚበዛበት እንደሆነም ገልጸውልናል። ከወጥ አለት የተፈለፈው ቤተ ክርስቲያኑ በጠቅላላ 32 ምሰሶዎች፣ ስድስት መስኮተ ብርሃኖች፣ ሦስት መንበሮች እና ሰፋፊ መቅደስ፣ ቅድስት እና ቅኔ ማኅሌትን የያዘ ነው።
በፍልፍል ቤተ ክርስቲያኑ የአለት ጣሪያና ግድግዳ ላይ የጨረቃ፣ ከዋክብት፣ ፀሐይ እና ሌሎች ምልክቶች ተቀምጠውባቸዋል። በቅርስነት የሚታወቁ ልዩ ልዩ ንዋዬ ቅድሳትም በቤተ ክርስቲያኑ እንደሚገኙ ቄስ ዓለማየሁ ነግረውናል።
ይሁን እንጂ ቅርሱ ለረዥም ጊዜ ጥገና ስላልተደረገለት በዝናብና በፀሐይ ምክንያት የመሰንጠቅ እና የመፈራረስ አደጋ አጋጥሞታል። በክረምት ወቅትም በተሰነጠቀው በኩል በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ውኃ ስለሚገባ በውስጥ በሚገኙ ቅርሶች ላይ ጭምር ጉዳት መድረሱን ቄስ ዓለማየሁ አስረድተዋል። በቅርሱ ላይ የከፋ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ጥገና እንዲደረግለት ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን የገለጹ የቤተ ክርስቲያኑ ቄሰ ገበዝ በዚህ ዓመት በመንግሥትና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ መጠለያ ተሰርቷል።
የቅርሱ አካባቢ ከንክኪ ነፃ ሆኖ እንዲጠበቅም ጠይቀዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ጃናሞራ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አማረ ታደሰ እንደገለጹት ደግሞ ሰረባር ባለእግዚአብሔር መቼ እንደተሠራ የተፃፈ መረጃ ባይኖርም ንጉሥ ላልይበላ አስራ አንዱን የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከመሥራታቸው በፊት በ11ኛ መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ እንደሠሩት በአፈታሪክ ይነገራል። ሰረባር ማለት በአገውኛ ቋንቋ ቀይ አፈር የሚል ስያሜ እንዳለውም አቶ አማረ ገልጸዋል።
የምሕንድስና ዕውቀት ባልተስፋፋበት እና ዘመናዊ መሣሪያ ባልነበረበት ወቅት ከአንድ አለት በእጅ ተፈልፍሎ የተሠራው ቅርስ ትኩረት ባለመሰጠቱ በፀሐይና ዝናብ ምክንያ ጉዳት ደርሶበታል።
ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ለክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጥገና እንዲደረግለት ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቶ በ2012 ዓ.ም በ780 ሺህ ብር ከብረት፣ እንጨት እና ቆርቆሮ መጠለያ ተሠርቶለታል። ከዚህም ውስጥ 550 ሺህ ብር ከክልሉ መንግሥት፣ 230 ሺህ ብር ደግሞ ከአካባቢው ነዋሪዎች መሸፈኑንም አቶ አማረ አስታውቀዋል።
አቶ አማረ እንደገለጹት የጃናሞራ ወረዳ ከሰረባር ባለእግዚአብሔር በተጨማሪ 40 በመቶ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ፣ የዘመነ መሣፍንት መቋጫና የአጼ ቴዎድሮስ የንግሥ ቦታ ደረስጌ ማሪያም፣ በደን የተሸፈኑ ልዩ ልዩ አርኪዮሎጅካል ጥናቶችን የሚጠይቁ 99 ዓመታትን ያስቆጠሩና ያልፈረሱ አጽሞች እና ሌሎችን በርካታ ማራኪ ተፈጥሮሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን የያዘ አካባቢ ነው።
አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በመገናኛ ብዙኃን የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ አማረ በመንገድ ችግር እነዚህ ቅርሶች ለመንከባከብ እና ለጉብኝት ክፍት ለማድረግ ፈተና መሆኑን ገልጸዋል፤ ይህም ከቱሪዝም ዘርፉ መገኘት የሚገባውን ገቢ እና በዘርፉ የሚፈጠረውን የሥራ ዕድል አሳጥቷል።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ – አብመድ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   መሠረታዊ የኮምፒውተር ደህንነት መጠበቂያ መንገዶች
0Shares
0