በተለምዶ አውቶቡስ ተራ አካባቢ ነዋሪ እንደሆነች የገለጸች አንዲት የ29 ዓመት ወጣት ” እናቴን ቀብሬ ብቻዬን ቁጭ አልኩ ” ስትል የኮሮና ቫይረስ ማህበራዊ ወጋችንን ገና ከአሁኑ እንደገደለው ትናገራለች። ይህንን ያለችው ወዳጆቿና ጎረቤቶቿ ድንኳን ሞልተው ስላላስተዛዘንዋት ቅር በመሰኘትዋ ሳይሆን ሊመጣ ያለውን አደጋ ስታስበው የሚሰማትን ስሜት ለማጋራት ነው።

በጣሊያን ሲጀመር ልክ አሁን በኢትዮጵያ እንደታየው እንደነበር የሚገልጸው የሚላን ነዋሪ፣ ኮቪድ ቀስ ብሎ ጣሊያንን በሃዘን መታት። ቤተሰብ፣ ጎረቤት፣ የአካባቢ አስተዳደር፣ የጤና ተቋማት፣ የጤና ባለምያዎች፣ መንግስት… እጃቸውን ሰጡ። ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ማወቅ ተሳናቸው። የመከላከል ስራ ካቅም በላይ ሆነ። ሬሳ በወጉ ሳይሆን የቆሻሻ ያህል እንኳን መሰብሰብ አሳር ሆነ። ቃል የማይገልጸው፣ በታሪክ የሚዘገንን መከራ!!

የኒው ዮርክ ሲቲ ነዋሪ ሰለሞን ” በህይወት ብኖርም አእምሮዬ ተጠብሷል” ይላል። በኒውዮርክ ያየውን የመናገርና የማስረዳት አቅም የለውም። እሱ እንደሚለው ኒውዮርክ ላይ የሆነው ” ገሃነም ” እንደሚባለው አይነት ነው። አሁን ጭንቀቱና ለቅሶው ምንም ዓይነት አቅም ለሌላት አገሩና አፍሪቃ ነው። ይህ ክፉ ቀን ሳይመርጥ ጨቅላ አዋቂውን ሊጠራርግ በደጅ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲከኞች በእልህና በስልጣን ጥማት ሲወዛገቡ መስማቱ ያሸማቅቀዋል።

አምሳል ሰይፉ ” እገሌ ከገሌ ሳይባል በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ፖለቲከኞች እድሜ ልኬን አፍራለሁ” ስትል የሰለሞንን ሃሳብ ትጋራለች። የኢትዮጵያ ጤና ሳይንስ ኢንስቲቲዩት ባወጣው ጥናት መሰረት 8.5 ሚሊዮን ሕዝብ በቫይረሱ እንደሚጠቃ የሚሰማ አንድ ጤነኛ ሰው ማገዝ ቢያቅተው ቢያንስ አርፎ ሊቀመጥ በተገባ ነበር ስትል የሃረታችንን መጠን ታሳያለች።

እንደ ጥናቱ ኢትዮጵያ እድለኛ ከሆነች በህዳር ወር እስከ 26 ሺህ ልጆቿን ከቻለች በግል፣ ካልቻለችም ልክ ሌሎች እንዳደረጉት በጅምላ ትቀብራለች። አሁን አሳሳቢ የሆነው 8.5 የሚጠጉ ወገኖች የትና እንዲት? እንዲሁም በምን አቅም ህክምና ያገኛሉ? የሚለው ነው። ቀና ወገኖች እንደሚያደርጉት አደጋውን ለመቀነስ ከመረዳዳት ውጪ በየጥጉ ” ጊዜው አሁን ነው?” በሚል በወገን ሃዘን፣ በህጻናት እንባና ሕይወት ቁማር መጫወት ቅድሚያ ማግነቱ ከሰውነት ተርታ የመውጣታችን ምልክት ካልሆነ ምን ይባል ይሆን?

ዶክተር ሊያ ከባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ትናንት ይፋ እንዳደረጉት ዘጠና ሰባት የህክምና ዘርፍ ሰራተኞች በስፋት በቫይረሱ ተጠቅተዋል። ሰማኒያ አንዱ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተጠቁ ሲሆን ከአጠቃላዩ ተጠቂዎች  ዘጠና አንዱ በአዲስ አበባ የሚገኙ ናቸው። እጅግ አሳሳቢ የሆነውና አስደንጋጩ ጉዳይ እስካሁን ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ንክኪ ነበራቸው ተብለው የተለዩ እና እራሳቸውን አግልለው የነበሩ የጤና ባለሙያውች ቁጥር 2340 መድረሱ ነው። 1721 የሚሆኑት ተጋላጭ የነበሩት በመጋቢት ወር ነው። እናም ገና ከአሁኑ አደጋው የማይቻል መሆኑንን እያመላከተ ነው። ይህ ሁሉ እየሆነ ነው እንግዲህ “ከመስከረም ሰላሳ በሁውላ መንግስት ይገለበጣል” የሚባለው። በዚህ ሁሉ ችግር አገር ቢተራመስ ምን እንደሚሆን ማሰብ የማይችሉ እንዴት አገርስ ይመራሉ?

ዛሬ ዓመት ያልሞላቸው ህጻናት እየተቀጠፉ ነው። እናት ዘጠኝ ወር ልጇን በሆዷ ተሸክማ ፍሬዋን መሳም የማይቻልበት ደረጃም እየተደረሰ ነው። እናት ልጅን፣ ልጅ እናትን፣ ባል ሚስትን፣ ሚስት ባልን በሞት ስትነጠቅ ቀልድ ሆኗል። በቃ ልክ እንደቆሻሻ ሰው እየተለቀመ ግፍ ነው በሚባለው የጅምላ መቃብር እየተዘጋበት ነው።

ከ26ሺ በላይ ሰዎች በበሽታው እንደሚሞቱ ተገምቷል አዲስ አድማስ ሙሉ ዘገባ ከታች ያንብቡ

በአገራችን የኮቪድ – 19 ወረርሺኝ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቀው በመጪው ህዳር ወር ላይ እንደሚሆን የተጠቆመ ሲሆን ከ8.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው እንደሚያዙና ከ26ሺ በላይ የሚሆኑ በቫይረሱ ህይወታቸውን እንደሚያጡ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው፤ የኮቪድ 19 ጥናቱ ያመለክታል፡፡ ወረርሽኝ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርስበት ጊዜ ሰኔ ወር መጀመሪያ ገደማ መሆኑ ቀርቶ  ወደ መጪው ህዳር ወር 2012 ዓ.ም መገፋቱ ተጠቁሟል፡፡ በዚሁ መሠረትም ህዳር ወር 2013 መጀመሪያ አካባቢ 8 ሚሊዮን አምስት መቶ አስራ አንድ ሺ አስራ አንድ ሰዎች በቫይረሱ የሚያዙ ሲሆን፤ በዚሁ ወር አጋማሽ ላይ የሟቾች ቁጥር 26ሺ አምስት መቶ አርባ አራት እንደሚደርስ ጠቁሟል፡፡
የቫይረሱ ስርጭትና የሞት መጠን በምስራቅ አፍሪካ አገራት በፍጥነት እየጨመረ፣ ያመላከተው መረጃው፤ በኢትዮጵያ በሳምንቱ የበሽታው የስርጭት መጠን በ78% የሞት ምጣኔው ደግሞ በ61% ጨምሯል ብሏል፡፡ ከበሽታው የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መሄዱንም ከጥናቱ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡
የበሽታው የስርጭት መጠን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያደርሳል ተብሎ በሚጠበቅበት የህዳር ወር ላይ 392ሺ767 የሆስፒታል አልጋዎችና 21ሺ038 የጽኑ ህመምተኛ አልጋዎች እንደሚያስፈልጉ የተነበየው የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ጥናት፤ በሽታው እስከ ፈረንጆቹ አዲስ አመት ድረስ እንደሚቆይና እስከዚያው ጊዜ ድረስም በአጠቃላይ ከ50ሺ በላይ ሰዎች በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ አመልክቷል፡፡

 

 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *