ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኮሮና የምርመራ አቅምን በቀን 14 ሺህ ለማድረስ እየተሰራ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ

በኢትዮጵያ የኮሮና የምርመራ አቅምን በቀን 14 ሺህ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት 5ኛ ልዩ ስብሰባውን አካሂዷል።
በስብሰባው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሃገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከሃገራዊ ለውጡ፣ በድንበር አካባቢ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ዙሪያ፣ ከሃገራዊ ምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እንዲሁም ከግብርና እና ከግብአት አቅርቦት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
በምላሻቸውም ሃገራዊ የምርመራ አቅምን በቀን 14 ሺህ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሮና ቫይረስ አደገኛ እና ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ጠቅሰው፥ ቫይረሱ በመላው ዓለም ከፍተኛ ቀውስ ማስከተሉን አንስተዋል።
እስካሁን ባለው ሁኔታም በአፍሪካ ከ185 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ገልጸው፥ በኢትዮጵያም የቫይረሱ ስርጭት ከእለት ወደእለት እየጨመረ ይገኛል ብለዋል።
እስካሁንም 2 ሺህ 20 ሰዎች መያዛቸውን ጠቁመው፥ 27 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
ወረርሽኙ በመላ ሃገሪቱ የተዳረሰ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ አዲስ አበባ ከፍተኛውን ቁጥርር ይይዛል ነው ያሉት።
ቫይረሱ በዓለም ላይ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና የጤናው ዘርፍ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግር አስከትሏል።
ከኮቪድ ጋር በተያያዘ የምርመራና የለይቶ ማቆያ ጋር በተያያዘ አቅም መፈጠሩን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር፥ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ከ31 በላይ ላቦራቶሪ ተቋቁሟል ብለዋል።
ይህ ቁጥር በሰኔ እና ሐምሌ ወር የሚጨምር ሲሆን፥ ሐምሌ ወር ላይ በቀን ከ14 ሺህ በላይ ሰዎችን የመመርመር አቅም ላይ እንደሚደረስም አውስተዋል።
54 የህክምና ማዕከላት ተዘጋጅተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ምልክት ላሳዩ 30 ሺህ ሰዎች፣ ከውጭ የሚመጡ 45 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ማቆያ እንዲሁም ቫይረሱ ያለባቸውን 17 ሺህ 500 ሰዎች ማቆያ መዕከላት መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
ከኮቪድ19 ጋር ተያይዞ ባለፉት ሶስት ወራት የተፈጠረው አቅም ወባን በመሳሰሉ ሌሎች ዘርፎች መድገም ቢቻል ኖሮ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻል እንደነበርም አስታውሰዋል።
ከባህል መድሃኒት ጋር በተያያዘ በሰጡት ምላሽም የባህል መድሃኒት አለን የሚሉን ሰዎችን በማበረታታት ምርምር መቀጠኩንም ነው ያነሱት።
ከቫይረሱ ጋር ተያይዞም ለሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ከ400 ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉንም ገልጸዋል፤ መንግስት በኮሮና ዙሪያ ያለውን መረጃ ሳይደብቅ ይፋ እያደረገ መሆኑን በመጥቀስ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ከኮቪድ19 ጋር በተያያዘ የመከላከል አቅምን (በባለሙያዎች የተነገሩ ምክረ ሃሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ) ማሳደግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ኢኮኖሚን በማሳደግ ሊደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ መቀነስ ይገባልም ነው ያሉት።/ ፋና /
Related stories   የቻይናው ሮኬት ስብርባሪ በኢትዮጵያ ቢወድቅ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል?