“Our true nationality is mankind.”H.G.

የትግራይ ክልል ከመቼውም ጊዜ የተሻለ በጀትና ድጋፍ እንደተደረገለት ጠ/ሚ አብይ ይፋ ገለጹ፤ አቧራ ሳይሆን አሻራ እንትከል ሲሉም ጥሪ አቀረቡ

– ክልሉ የማዳበሪያ እዳውን አልከፈለም

ትግራይ ክልል ከተመሰረተበተ ጊዜ አንስቶ እስከ ቅርብ ጊዜ የሚመደብለት ዓመታዊ በጀት 7 ቢሊዮን ብር እንደነበረና አሁን ከለውጡ በሁዋላ ግን  ወደ 10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ማደጉን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስታወቁ። መንግስት የትግራይን ሕዝብ መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት አሁንም ትኩረት ስጥቶ እንደሚሰራ አመልክተዋል። ክልሉ ያለበትን የማዳበሪያ እዳ ባይከፍልም መንግስት ከፍተኛ እገዛ አድርጎ ማቅረቡን ጠቅሰዋል።

5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ ልዩ ስብሰባ  ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ በተካሄደበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ከምክር ቤቱ አባላት ከቀረቡላቸውና ምላሽ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል የትግራይ ክልል ጉዳይ ይገኝበታል።

ከትግራይ ክልል ልማትና የሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲሁም በፌዴራሉ መንግስትና ክልሉን በሚመራው ፓርቲ መካከል ያሉ አለመግባባቶችን መሰረት ያደረጉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም “የትግራይን ሕዝብ የምናውቀው በቴሌቪዥን ሳይሆን በእጁ በልተን አብረነው ኖረን ነው” ካሉ በኋላ “ሕዝቡ የተከበረና ጀግና ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

Related stories   “ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በአንድነት በመከባበር፤ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት ሊያከብር ይገባል”

የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ለአገር አንድነት የተዋደቀና ዋጋ የከፈለ መሆኑን አንስተው የማንም የበላይም ሆነ የበታች የመሆን ፍላጎት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን የሚስተዋለው ችግር ሕዝቡንና ፓርቲዎችን ቀላቅሎ መመልከት መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደርግን ለመገርሰስ ተደርጎ በነበረው ትግል የተለያየ አመለካከት ያላቸው ፓርቲዎች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

ከዛሬ 40 ዓመታት በፊት አንድ ፓርቲም ሆነ አንድ አመለካከት ያልነበረ መሆኑን በማንሳት አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታም በርካታ ፓርቲዎች በክልሉ እንዳሉና የትግራይን ሕዝብ በአንድ ሀሳብና እይታ መመልከት ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል መንግስትም ሆነ ክልሉን የሚመራው ፓርቲ ሁሉንም አባላት ጨፍልቆ ምንም እንደማይሰሩ መመልከት ተገቢ አለመሆኑንና ከጫፍ ያሉ ጥቂት አመራሮች ብቻ ችግር ያለባቸው መሆኑን ነው የተናገሩት።

በዚህም አንድ ሰው ሲወቀስ የትግራይ ሕዝብ ተወቀሰ የሚለው አካሄድ ትክክል አለመሆኑን፤ በክልሉ የተለያየ አይነት አመለካከትና አስተሳሰብ ያላቸው ፓርቲዎችና ግለሰቦች መኖራቸውን መረዳት ተገቢ ነው ብለዋል።

Related stories   የኢትዮዽያ የቁርጥ ቀን ልጅ "ስለአባይ እውነቱን እንካችሁ" – መካ አደም አሊ

መገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመሳደብ በባለሀብቶች ጭምር የሚደገፉ ሚዲያዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ይህ አካሄድም ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በሚዲያ በብሄር መባላት የኖርንበትና ትርፍ ያልተገኘበት በመሆኑ ይሄ ሁኔታ ከሁለቱም ጫፍ መታረም እንዳለበትና ምክር ቤቱም የሚቆጣጠራቸውን ሚዲያዎች የመጠየቅ ሃላፊነት እንዳለበት ነው የተናገሩት።

የፌዴራል መንግስት ለትግራይ ክልል ልማት እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ እንደሚነዛው ውሸት ሳይሆን ለውጡ ለትግራይ ክልል ጭምር የመጣ መሆኑን አስምረውበታል።

ለአብነትም ከለውጡ ወዲህ ትግራይ ክልል ከተመሰረተበተ ጊዜ አንስቶ እስከ ቅርብ ጊዜ የሚመደብለት ዓመታዊ በጀት 7 ቢሊዮን ብር እንደነበረና አሁን ወደ 10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ማደጉን አስታውሰዋል።

ይህም 42 በመቶ የትግራይ ክልል በጀት እንዲያድግ ማድረጉን፣ በኮቪድ ወረርሽኝ ሳቢያም ተጨማሪ 46 ሚሊዮን ብር በቁሳቁስና በጥሬ ገንዘብ ከበጀቱ ውጭ ድጋፍ መደረጉን አብራርተዋል።

Related stories   አገርን የከዱ ተደመሰሱ፤ የሳተላይት መገናኛና መድሃኒት " ጁንታው" እጅ ሳይገባ ተያዘ

ለአርሶ አደሮች ከሚቀርብ ማዳበሪያ ጋር ተያይዞም ክልሉ ያለፈውን ዓመት ዕዳ ባይከፍልም የፌዴራል መንግስት ተበድሮ 445 ሚሊዮን ብር የሚገመት ማዳበሪያ ለትግራይና ለደቡብ መደገፉን ገልፀዋል።

የመቀሌን የውሃ ፕሮጀክት በተመለከተ የፌዴራል መንግስት ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጎ ያስጀመረው መሆኑንና ወደፊትም አቅም በፈቀደ መጠን የትግራይን ሕዝብ መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እንደሚሰራ ነው ዶክተር አብይ ያስረዱት።

እነዚህ ሁሉ ስራዎች እየተሰሩ ምንም አልተሰራም ማለት ተገቢ አለመሆኑን ትግራይ አካባቢ ያሉትም ሆኑ ሌሎች ሚዲያዎች ስድብና ብሽሽቅ ረብ የለሽ መሆኑን እንዲገነዘቡ አሳስበዋል።

የሚደረጉ ብሽሽቅና ስድቦች አቧራ እንጂ አሻራ የሚሆኑ ባለመሆናቸው ፊትን ወደ ልማት ማዞር እንደሚገባም ጭምር አስገንዝበዋል።

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0