ታላቁ የህዳሴ ግድብ  ግንባታው ለስድስት ዓመታት በመጓተቱ ምክንያት ብቻ ኢትዮጵያ ማግነት የነበረባትን ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንዳጣች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ተናገሩ። አሃዙ ገቢውን እንጂ ግንባታው በመጓተቱ አገሪቱ የከሰረችውን ሃብት አያካትትም።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተያዘለት የጊዜ መርሃ ግብር መከናወን ባለመቻሉ ምክንያት ኢትዮጵያ ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንዳጣች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ተናገሩ ፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያለበትን አፈጻጸምና የዲፕሎማሲ ስራዎች አስመልክቶ ከምክር ቤት አባላት ጥያቄ ቀርቦላቸዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ብረታ-ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን / ሜቴክ / ግድቡን ለመስራት ከገባበት በኋላ ብልሽቶችና መጓተቶች እንዳጋጠሙ ዶክተር ዐብይ ገልጸዋል ፡፡
በተለይም የግድቡ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራ ሁሉም ከዜሮ የተጀመረ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ባለፈው አንድ አመት ተኩል በዲፕሎማሲውና በፕሮጀክቱ ክንውን አመርቂ ስራ መስራቱን ለአባላቱ ገልጸውላቸዋል ፡፡
በዚህ አመት ግድቡ 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚይዝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል ፡፡
ግድቡ የትኛውን ሃገር ለመጉዳት ተብሎ የሚሰራ እንዳይደለ ግንዛቤ እንዲያዝ የገለጹት ዶክተር ዐብይ ፣ 50 ሚሊዮን በላዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃና መብራት እንደማያገኝ አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል 98 በመቶ የሚሆነው የግብጽ ሕዝብ ግን ንጹሕ የመጠጥ ውሃና መብራት አንደሚያገኝ ነው ዶክተር ዐብይ የተናገሩት ፡፡
እናቶቻችን የማገዶ እንጨት በጀርባቸው እየተሸከሙ ባሉበትና ይሄ ሁሉ የከፋ ችግር በገሃድ በሚታይበት ሃገር መብራትና ንጹህ የመጠጥ ውሃ አያስፈልጋቸውም የሚልን ሃይል ለመቀበል እንደሚቸገሩ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት ፡፡
በሌላ ዜና “በለውጥ ሃይሉ የትግራይ ሕዝብ የተለያዩ በደሎችና ግፎች ለምን ይፈጸምበታል ? ፕሮጀክቶችስ ለምን እንዲጓተቱ ይደረጋል ? የወልዲያ – ሃራ ገበያ ባቡር ግንባታ ለምን መቀሌ አልገባም ? “ ሚሉ ጥያቄዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርበውላቸዋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ ሃገሩን የሚወድ ፤ ለሃገሩ አንድነት የተዋደቀ እና የሚያኮራ ሕብ እንደሆነ ዶክተር ዐብይ ጠቅሰዋል ፡፡
ይሁን እንጂ ጥያቆዎች ሲቀርቡ ፓርቲንና ሕዝብን በለየ መንገድ መሆን እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረው ፣ ከሌሎች ክልሎች በተለዬ ሁኔታ ለትግራይ ሕዝብ 445 ሚሊዮን ብር በመመደብ የማዳበሪያ አቅርቦት እንዲያገኝ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ለአምስትና ስድስት ከተማ የሚሆን የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ትግራይ ክልል ላይ እየተከወነ እንዳለና በርካታ መንገዶችም እየተገነቡ እንደሚገኙ ነው ዶክተር ዐብይ የገለጹት ፡፡
በተለያዩ ሚዲያዎች ጭምር የሚባለው ነገር “አባራ እንጂ አሻራ“ ስላልሆነ በጊዜ በሂደት ሁሉም ነገር እንደሚታወቅ ነው ያብራሩላቸው ፡፡
የባቡር ግንባታን በተመለከተ ከአዲስ አበባ – ጂቡቲ በኪሎ ሜትር 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚያስወጣ ሲሆን ከ ወልዲያ – መቀሌ ግን በኪሎ ሜትር 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ዶክተር ዐብይ አስረድተዋል ፡፡
ስራውን ለመስራት ከተለያዩ ባንኮች ብድር ቢጠየቅም ስራው አዋጭ ባለመሆኑ ምክንያት ብድር ሊገኝ እንዳልተቻለ ገልጸው፤ በሂደት መቀሌ በባቡር ግንባታ እንደምትተሳሰር ገልጸዋል ፡፡
በመጨረሻም ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የ 5 ቢሊዮኑ የአረንገዴ አሻራ አካል እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ከአቀረቡ በኋላ ከምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ እና ከምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ጋር በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ግቢ ውስጥ ችግኝ ተክለዋል።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *