“Our true nationality is mankind.”H.G.

ባለፉት 10 ወራት ከወጪ ንግዱ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል

(ኢዜአ) ባለፉት አሥር ወራት ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ቡና፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የቅባት እህልና የጥራጥሬ ሰብሎች እንዲሁም ሥጋ፣ ወርቅ፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ለውጪ ገበያ ከምታቀርባቸው ምርቶች መካከል ይገኙበታል።

ከነዚህ ውስጥም በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያ አሥር ወራት ከአጠቃላይ የወጪ ንግዱ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር።

ከዚህ ውስጥም 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ721 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ማሳየቱን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት የወጪ ምርቶች ኮንትራት አስተዳደር ሥራ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን ይህም ላኪዎች ወደ ውጪ የሚልኩበትን ጊዜ፣ የምርት መጠን እንዲሁም የሚያስገኘውን ገቢ ክትትል ለማድረግ የሚያስችል ነው።

እንዲሁም ላኪዎች ምርቶችን ኤክስፖርት ሲያደርጉ ዋጋውን ባነሰ ዋጋ እንደሸጡ ሪፖርት ማድረግና መንግሥት ማግኘት የሚገባውን የውጭ ምንዛሬ ማሳጣት ያሉ ተግባራትን ጭምር እንደሚያስቀር አመልክተዋል።

አቶ ወንድሙ እንዳሉት የኮሮናቫይረስ እየተስፋፋ መምጣት በዓለም ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ ትልቅ የንግድ እንቅፋት ሆኗል።

በዚህ ምክንያት አንዳንድ ላኪዎች ምርታቸውን ወደ ውጪ ለመላክ የገቡትን ውል ተቀባይ አገሮች ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ በመግባታቸው ምክንያት ለመሰረዝ መገደዳቸውን ነው ያስረዱት።

ይህን ችግር ለመፍታት በተደረገው ጥረት በቆንጽላዎችና በኤምባሲዎች አማካኝነት በመነጋገር ውሉ እንዳይቋረጥና የተቋረጡትም ዳግም እንዲታደሱ መደረጉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

“በዚህም ወደ 980 ቶን ሰሊጥ፣ 616 ሺህ ቶን አኩሪ አተርና 120 ሺህ ቶን ነጭ ቦሎቄ የዋጋ ማሻሻያና ኮንትራት እድሳት ተካሂዶ ወደ ውጭ አገር እንዲላኩ ተደርጓል” ብለዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት የወጪ ንግድን ማሳለጥ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግና የንግድ ሚዛንን ለመጠበቅ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ይነገራል።

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን፣ ማዕድናትንና የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን ወደ ውጪ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘትና ወደአገር ውስጥ በሚገቡ ዕቃዎች የንግድ ሚዛኑን ለመጠበቅ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

ENA

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0