ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የአማራ ሐኪሞች ማኅበር ሪፖርት በማይደረግባቸው አካባቢዎች የኮሮናቫይረስ ስርጭት ይኖራል ሲል ኅብረተሰቡን አስጠነቀቀ፡፡

በኮሮናቫይረስ ላይ እየታዬ ያለው መዘናጋት ዋጋ እያስከፈለ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የአማራ ሐኪሞች ማኅበር አሳስቧል፡፡ በኢትዮጵያ በቅርቡ እየወጣ ያለው የኮሮናቫይረስ አሐዛዊ መረጃ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡ በበሽታው የሚያዙ፣ በጽኑ የሕክምና ክፍል ውስጥ የሚገቡ እና በበሽታው አማካኝነት ሕይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥርም እያሻቀበ ነው፡፡
ቫይረሱ በብዛት እየተገኘ ያለው የውጪ ሀገር የጉዞ ታሪክ በሌላቸው እና በቫይረሱ መያዙ በሕምና አስቀድሞ ከተረጋገጠ ሰው ጋር ንክኪ በሌላቸው ሰዎች ላይ ነው፡፡ ይህም ወረርሽኙ በማኅበረሰቡ ውስጥ በአሳሳቢ ደረጃ እየተሠራጨ መሆኑን እንደሚያሳይ የአማራ ሐኪሞች ማኅበር አስታውቋል፡፡
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አብራራው ታደሰ (ዶክተር) እንዳሉት ማኅበረሰቡ ስለወረርሽኙ ዕውቀት ቢኖረውም የባሕሪ ለውጥ አለማምጣቱ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን እንደማይዝ እና እንደማይገድል ተወርቶ ነገሮች በተቃራኒው ሆነው ታይተዋል፡፡ ማኅበረሰቡ በመዘናጋቱ ምክንያት ወረርሽኙ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለገደብ እየተሠራጨ መሆኑ ይበልጥ ሊያሳስብ እንደሚገባም መክረዋል፡፡
ቸልተኝነቱ በዚህ ከቀጠለ በወረርሽኙ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል፤ የሚያደርሰው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የጤና ቀውስ መጨመሩ እንደማይቀርም ዶክተር አብራራው አስጠንቅቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ባሕር ዳር፣ ደባርቅ፣ ደብረብርሃን ወይም ሌላ ቦታ በሽታው እንደተገኘ ሪፖርት አለመደረጉ የሀገሪቱ የመመርመር አቅም ዝቅተኛ መሆን እንጂ የቫይረሱ ስርጭት የለም ማለት እንይደለም፡፡
ዶክተር አብራራው እንዳሳሰቡት ማንኛውም ሰው በበሽታው እንደተያዘ በማሰብ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በእነርሱ ምክንያት የሚወድዷቸው ሰዎች ለጤና ችግርና ለሞት እንዳይጋለጡም የጥንቃቄ ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ ‘‘ጭንብል የምንጠቀመው፣ እጃችንን ቶሎ ቶሎ የምንታጠበው እና አካላዊ ርቀታችንን የምንጠብቀው በሽታው እንዳይዘን ብቻ ሳይሆን እኛም ለሌሎች እንዳናስተላልፍ ነው’’ ያሉት ፕሬዝዳንቱ በተለይ ከመተማ እና ከአዲስ አበባ መነሻቸውን የደረጉ ሰዎች ብቻ በበሽታው እንደሚጠቁ አድርጎ ማሰብ ፍጹም የተሳሳት እና መስተካከል ያለበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
እያንዳንዱ ሰው ለሌሎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ሳይዘነጋ የሚወዳቸውን ሰዎች ለመታደግ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡ ባለሙያዎች እና ብዙኃን መገናኛ ድርጅቶችም የግንዛቤ ፈጠራው የባሕሪ ለውጥ ማምጣት በሚችልበት መልኩ ማስተማርን መቀጠል እንደሚገባቸው አመላክተዋል፡፡ መንግሥትም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን መፈተሸ ይጠበቅበታል፡፡
ወደ ሆስፒታል የሚሄዱ ወላዶች፣ ቀዶ ሕክምና የሚደረግላቸው፣ የመተንፈሻ አካል ታካሚዎችና የጤና ባለሙያዎች እንዲመረመሩ ቢወሰንም ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑንም አንስተዋል፡፡ ‘‘ብዙ መመርመር እና በደንብ መለየት እስካልተቻለ ድረስ በሽታው በማኅበረሰቡ ውስጥ እየተዛመተ ይቀጥላል’’ በማለትም የመመርመር አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
 (አብመድ)
Related stories   የዓለም ጤና ድርጅት ለቻይናው ክትባት ይሁንታውን ሰጠ