ብልጽግና ፓርቲ እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በፈረሰው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ንብረቶች ክፍፍል ጉዳይ መስማማት እንደተሳናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ግንባሩ ባለፈው ጥር እንዲፈርስ ከተወሰነ በኋላ ብልጽግና ፓርቲ እና ህወሓት “የሚስማሙበት አንድ የጋራ አጣሪ እንዲመርጡ ለማስቻል የተደረገው ጥረት” አለመሳካቱን ቦርዱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በዚህም ምክንያት የኢሕአዴግ ንብረቶችን የሚያጣሩ ሁለት ኦዲተሮች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሾሙን የዛሬው መግለጫ ይጠቁማል። “ብልጽግና ፓርቲ እና ህወሓት በየበኩላቸው የመረጧቸው አንድ አንድ የሂሳብ አጣሪዎች” ሥራውን ያከናውናሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “የንብረት ማጣራቱን እንዲያደርጉ የተመረጡት ድርጅቶች የጋራ የስራ እቅድ፤ የጊዜ ሰሌዳ፤ ስራውን የሚያከናውኑበት ቦታ፤ ሁኔታ እና የስራ ህግጋት” አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ አዟል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሾማቸው የሒሳብ አጣሪዎችን ወጪ ኢሕአዴግ ከፈረሰ በኋላ መስማማት የራቃቸው ብልፅግና ፓርቲ እና ህወሓት ይሸፍናሉ።

ቦርዱ ከግንባሩ ንብረቶች ብልፅግና ሶስት እጁን ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ቀሪውን አንድ እጅ እንዲወስዱ ቢወስንም የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፓርቲ ተቃውሞ ማቅረቡን አስታውቋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “ብልጽግና ፓርቲ የንብረት ክፍፍሉ እያንዳንዱ ፓርቲ በተናጠል በነበረው የአባላት ብዛት ላይ የተመሰረተ እንጂ በእኩልነት ሊሆን አይገባም የሚል አቤቱታ” ማቅረቡን አረጋግጧል።
“ሁሉም ፓርቲዎች በግንባሩ የጋራ ንብረት እኩል የመጠቀም መብት አላቸው” የሚለውን የቀድሞው ኢሕአዴግ መተዳደሪያ ሕገ-ደንብ መሠረት በማድረግ የንብረት ክፍፍል ስሌቱን መወሰኑን ያስታወሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “ብልጽግና ከዚህ የተለየ ውጤት ሊያስከትል የሚችል ማስረጃ ወይም ሰነድ ካለው ለአጣሪው ማቅረብ እንደሚችል” እንደተገለጸለት አስታውቋል።

የቀድሞው ኢሕአዴግ ጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲፈርስ ሲወሰን የንብረት ክፍፍሉ በስድስት ወራት እንዲጠናቀቅ ተወስኖ ነበር። ሶስት የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች እና አምስቱ የግንባሩ አጋር ድርጅቶች የብልፅግና ፓርቲን ሲመሰርቱ ህወሓት ተነጥሎ ቀርቷል።
ለሶስት አስርት አመታት ገደማ የኢትዮጵያን መንበረ-ሥልጣን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ የቆየው ኢሕአዴግ፦ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፤ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ)፤ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) በአባልነት ያቀፈ ነበር። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ከኢሰፖ ቀጥሎ የመንግሥት ሥልጣን በመያዝ ኢሕአዴግ ሁለተኛው ነበር።

DW

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *