ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

«ኢትዮጵያን 360 ዲግሪ ቀለበት ውስጥ አስገብቶ መክበብ የሚችል ኃይል የለም» – ጀነራል ብርሀኑ ጁላ

የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጀነራል ብርሀኑ ጁላ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ አድርገዋል። ይከታተሉት።

አዲስ ዘመን፦በመከላከያ ያለው ሪፎርም ከምን ደረሰ ?

ጀነራል ብርሀኑ፦ ሪፎርም የጀመርነው ከለውጡ ጋር ተያይዞ ነው። ለውጡ ከተጀመረ ወደ ሁለት አመት እየተጠጋ ነው። ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ ሊሰራ የሚችለውን የሪፎርም ስራ ሁሉ እየሰራን ነው ። ሪፎርም የአንድ ወቅት ስራ አይደለም። ረዥም ግዜ ይጠይቃል። ደረጃ በደረጃ የሚሰራ ስራ ነው። እስከአሁን የሰራናቸው ትላልቅ ስራዎች አሉ። አንደኛው የሠራዊቱን ኑሮ ማሻሻል ነው። ብዙ ሄደንበታል። የሠራዊቱን ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የሠራዊቱን መተዳደሪያ ደንብ፣ የሠራዊቱን ደመወዝ፣ አመጋገብ ፣ ከሠራዊቱ ኑሮ ጋር በማሻሻል ሰርተናል። ሌላው አንድን ሠራዊት ሠራዊት የሚያደርገው አለባበሱና ቁመናው ነው። እሱን ቀይረናል። በፊት ሠራዊታችን ዩኒፎርም ገዝቶ ነበር የሚለብሰው። አሁን መንግሥት እንዲያቀርብ ሠራዊቱ የተሻለ ዩኒፎርም እንዲለብስ አድርገናል።

ከዩኒፎርሙ ጋር ተያይዞ መልክ ያለው ቁመና እንዲኖረው ተደርጓል። አደረጃጀት ሙሉ በሙሉ ቀይረናል። የምድር ኃይል (የምድር ጦር) ፣ የባሕር ኃይል፣ የሳይበር፣ ልዩ ኃይል፣ የሚባሉ አደረጃጀቶች አልነበሩም። እነዚህ ተፈጥረዋል። ተገቢውን መልክና ቁመና ይዘዋል። እዞች፣ ክፍለጦሮች፣ ብርጌዶች፣ ሻለቃዎችን በተመለከተ ሊኖር የሚገባው አደረጃጀት ተወስኗል። ሁሉም ተስተካክሎ ቦታ ቦታውን ይዟል። ሌሎች ከረዥም ግዜ አንጻር የታቀዱ አሉ። ደረጃ በደረጃ እየሄድንባቸው ነው። አቅም ፈጣሪ አቅሞች የምንላቸው አሉ። ከዚህ ቀደም የነበሩትን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማት የማሳደግ የጎደሉትን የማሟላትና የማጠናከር ሰፊ ስራ እየሰራን ነው። የጎደሉትን በማሟላቱ ሂደት ለምሳሌ ጁኒየር ስታፍ ኮሌጅ አልነበረንም። ለማቋቋም ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ነው።በሀገራችን የጦር ኮሌጅ (ዋር ኮሌጅ) አልነበረንም።ተቋቁሞ አንደኛ ዙር ስልጠና ጀምሯል። የጦር ኮሌጁ (ዋር ኮሌጁ) ጀነራሎችና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የውጭ ሀገር ሰዎች ገብተው የሚማሩበት ነው። ከሀገራችን አልፎ በአፍሪካ ስም ያለው ምርጥ የጦር ኮሌጅ እንዲሆን እንሰራለን። በሪፎርሙ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የሠራዊቱ መዋቅርና አደረጃጀት አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ቀድሞ ከነበረበትም ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰራን ነው።

በተለየያ ሙያ አስተምረው አሰልጥነው የሚያስመርቁ በርካታ ወታደራዊ ኮሌጆችና ማሰልጠኛዎች አሉን። እነዚህን በትምህርት ስርአት ፣ በአሰልጣኝ ፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት የማጠናከር ደረጃቸው ከሌላው አለም ጋር እንዲመጣጠን የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው። ሪፎርሙ በአጠቃላይ 22 ግብ 6 ፕሮግራሞች አሉት። በሁሉም መስክ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

ግብጾች ኢትዮጵያን 360 ዲግሪ እንከባታለን ከበን አስፈራርተን እጇን ጠምዝዘን አባይን ለብቻችን እንጠቀማለን ብለው እንደዚህ አይነት ፕሮፓጋንዳ መልቀቃቸውን አልተከታተልኩም። እንደዛ የሚያስቡ አይመስለኝም።

አዲስ ዘመን፡- ከሕዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ ግብጾች በቅርቡ የኃይል ማሳያ ወታደራዊ ሰልፍ አድርገዋል። በአቅራቢያችን ባሉ ዙሪያ ሀገሮች ጦር ሰፈር ለመገንባት መጠየቃቸውን የዘገቡ አሉ። እንዴት ይመለከቱታል ?

ጀነራል ብርሀኑ፦ ይሄ ትንሽ ወጣ ያለ ነገር ነው። ግብጾች ኢትዮጵያን 360 ዲግሪ እንከባታለን ከበን አስፈራርተን እጇን ጠምዝዘን አባይን ለብቻችን እንጠቀማለን ብለው እንደዚህ አይነት ፕሮፓጋንዳ መልቀቃቸውን አልተከታተልኩም። እንደዛ የሚያስቡ አይመስለኝም።

በሳል ሰዎች በደምብ ተሰብስበው እንደ ግብጽ መንግሥት ተወያይተው የለቀቁት ፕሮፓጋንዳ አይመስለኝም። ለግዜው ማለት የምችለው ይሄንን ነው። ሁለተኛው ነጥብ ምንም አሰቡ ምን ኢትዮጵያን 360 ዲግሪ ቀለበት ውስጥ አስገብቶ መክበብ የሚችል ኃይል የለም። አይኖርምም። የሚያስቡም ካሉ የለየለት የእብደት አስተሳሰብ ነው ። 360 ዲግሪ ማለት ዙሪያችንን ያሉ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገሮች በሙሉ ከግብጽ ጋር ወግነው ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ይዘው ይቆማሉ ይሰለፋሉ እንደ ማለት ነው። ይሄ ጎረቤት ሀገሮቻችንን የመናቅ አመለካከት ነው። ተንቀዋል። ለግብጽ ብሔራዊ ጥቅም ሲባል ደቡብ ሱዳን፣ኬንያ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ በጸረ ኢትዮጵያ አቋም ይሰራሉ እንደ ማለት ነው። ይሄ በፍጹም የሚታሰብ የሚሳካም አይደለም። ቢሞክሩትም ይመክናል። የመከላከያ ሠራዊታችን የሀገሩን ዳር ድንበርና የአየር ክልል ሁልጊዜም በተጠንቀቅ ዘብ ቆሞ ይጠብቃል።

አዲስ ዘመን፦ እንደተባለው ሞክረውስ ቢሆን ?

ጀነራል ብርሀኑ፦ በእኛ አጎራባች ሀገራት የጦር ሰፈር ለማግኘት ሊሞክሩ ይችላሉ። ከሰሜን አፍሪካ ተነስተው ምስራቅ አፍሪካ ድረስ ያውም በእኛ አጎራባች በሆኑ ሀገራት በድንበሮቻችን ቅርብ በሆኑ አካባቢዎች ጦር ሰፈር ለመገንባት አቅደው ሲመጡ የመጀመሪያው ጥያቄ ሀገራቱ ይቀበሏቸዋል ወይ የሚለው ነው። ደቡብ ሱዳን ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር እንድትችል የጦር ሰፈር ትሰጣለች የሚል እምነት የለኝም። ግብጽ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ሆና ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖና ጥቃት ለመፍጠር የተለያየ ስራ ለመስራት ብታስብ ደቡብ ሱዳን ይሄን ተቀብላ የምታደርግ ሀገር ናት ብዬ አልወስድም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ለዛሬዋ ደቡብ ሱዳን ሀገር ሆና መፈጠር በክፉው ቀን የነጻነት ታጋዮቿ ቤት እንደነበረች ይረሱታል ብዬ አላስብም። በኮሎኔል ጆን ጋራንግ የሚመራውን በተለያየ አመታት ወደ 40‚000 የሚጠጋውን የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ተዋጊ ሠራዊት ያሠለጠነው የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ወለድ መሆኑን ዛሬ ደቡብ ሱዳንን የሚመሩት እነ ፕሬዚዳንት ሳልባኬርና ምክትላቸው ማቻር የሚዘነጉት አይመስለኝም። ኢትዮጵያ ትልቅ ባለውለታቸው ነች። ደቡብ ሱዳኖች ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነገር ውስጥ አይገቡም የሚል እምነት አለኝ። ጥያቄው ከተነሳ የሀገራቱን ክብር የሚነካ ነው የሚሆነው። ደቡብ ሱዳን ለግብጽ ወታደራዊ ጦር ሰፈር አልሰጠችም። ግብጾች ለደቡብ ሱዳን የሠጡት የኮቪድ መከላከያ እርዳታ ማስክና ሳኒታይዘር ነው። ደቡብ ሱዳን ከግብጽ ጋር ተሰልፋ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ትቃረናለች የሚል እምነት የለንም።

አዲስ ዘመን፦ ግብጾች ለሱዳኖችና ለሌሎችም የጎረቤት ሀገሮች ወታደራዊ ጦር መሳሪያ በስውር እንደሚያስታጥቁ የሚገልጹ አሉ።ይሄን እንዴት ያዩታል ?

ጀነራል ብርሀኑ፦ በየሚዲያው የሚነገረው ሁሉ እውነት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። እስከዛሬ ግብጽ በሚስጥርም ቢሆን ለደቡብ ሱዳን የሠጠችው የሚታወቅ ጦርመሳሪያ የለም። የኢትዮጵያ መንግስት በዙሪያው ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ አጥብቆ ይከታተላል። ጠንካራ የመከላከያና የደህንነት ተቋም ያለው መንግሥት ነው። ከእይታ ውጪ የሚሆን ምንም ነገር የለም።

ከክፍለ ጦር በላይ ባሉ የሀላፊነት ቦታዎች “የብሔር ...

አዲስ ዘመን፦ግብጾች ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ግዙፍ የሚዲያ ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተዋል። እንዴት ያዩታል ?

ጀነራል ብርሀኑ፦ ግብጾች በሚዲያ ለከፈቱት ጦርነት የሚዲያ ሰዎች፣ ምሁራን፣ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ከዚህ ጥቃት በመከላከልና እውነቱን ለአለም ማሕበረሰብ በማሳወቅ ረገድ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ የሚል እምነት አለኝ። በዚህ ረገድ የእኛ ዋነኛው የስራ ድርሻና ኃላፊነት የሀገርን ሉአላዊነትና ዳር ድንበር ነቅቶ መጠበቅ ከየትኛውም አይነት የውጭ ጥቃት መከላከል ነው ።ይህ ማለት መከላከያ ምንም አይናገርም ማለት አይደለም። የራሳችን የሚዲያ ተቋም ሬድዮ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም፣ ጋዜጦችና መጽሔት እንዲሁም ኦን ላይን ሚዲያ አለን። ለሠራዊታችን ብቻ ሳይሆን ለሕዝባችንም ተደራሽ ናቸው። ሠራዊታችንም ሆነ ሕብረተሰቡ እውነቱን እንዲያውቅ የማድረግ የሚዲያ ስራዎችን እንሰራለን። ግብጽ ሰፊ ሚዲያ እንዳላት እናውቃለን። የእኛ ሀገር ሚዲያ በዛ ደረጃ አላደገም። በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የግብጾች የሚዲያ ጦርነት በሚያመክን መልኩ የእኛ የሚዲያ ኃላፊዎች ስትራቴጂያቸውን ነድፈው መስራት ይገባቸዋል ብዬ አስባለሁ።

ለኢትዮጵያ ሕዝብ እውነቱን በትክክል ማስረዳት፤ የግብጽ ሕዝብም እንዲያውቀው ተደራሽ በሚሆኑ የተለያዩ ቋንቋዎች መግለጽ አስፈላጊ ነው።

አንዱ በቅርቡ የሰማሁት ነገር ግብጾች ኢትዮጵያ የአባይን ውሀ ሙሉ በሙሉ ገድባ የግብጽን ሕዝብ በውሀ ጥም ልትጨርስ ነው የሚል የሕጻናት ማስፈራሪያ አይነት ፕሮፓጋንዳ ያካሂዳሉ ።

የግብጽ ሚዲያዎች በሀሰትና በፈጠራ ተሞልተው የሚነዙት ይህን የመሰለ ፕሮፓጋንዳ የግብጽን ሕዝብ ሊያስፈራራው ይችላል። እንዲህ አይነቱን የሀሰት ወሬ በተጨባጭ አጋልጦ ለግብጽ ሕዝብ፣ ለግብጽ ወዳጆች፣ ለአለም አቀፉ ሕብረተሰብ ሁሉም እንዲያውቀው ማድረግ ይገባል።

ግብጾች በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን የገዘፈ የሚዲያ ጦርነት ለመመከትና ለማጋለጥ የሚዲያ እውቀት፣ የውሀ እውቀትና ድንበር ተሻጋሪ ታላላቅ ወንዞች ላይ ሰፊ ግንዛቤና አለም አቀፍ ተሞክሮ ያላቸውን ምሁራን እንዲናገሩ መድረክ መፍጠር በዚህም የሕዝባችንን ግንዛቤ ያለማቋረጥ መገንባት ያስፈልጋል። የሚዲያ ጦርነት ሚዲያው ካለው ከፍተኛ ተደራሽነት አንጻር የተዛቡና ሆን ተብለው የተፈበረኩ አሳሳች መረጃዎችን ስለሚያሰራጭ አደጋ ከማድረሱ በፊት የመከላከል ስራ ግድ ይላል። የሚዲያ ጦርነት በባሕርይው ከዋናው የጦር ግንባር ያልተናነሰ መሆኑን እንረዳለን።

አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያዊ ሆነው በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ የሚዘምቱ፤ ለግብጾች በመሣሪያነት የሚያገለግሉትን በተመለከተ የሚነግሩን ሃሳብ ካለ ?

ጀነራል ብርሀኑ፦ በሀገራችን ውስጥ ድሮ በንጉሡም ዘመን ይሁን በደርግ በኋላም በኢህአዴግ ግዜ ያልነበረ በባሕላችን በአስተዳደጋችን በሕይወታችን ውስጥ በፍጹም አይተን የማናውቃቸው ነውር ተደርገው የሚወሰዱ አዳዲስ ነገሮች ተከስተዋል።

ለምንድነው እንደዚህ የሆነው ብለን ስንጠይቅ ለውጥና የለውጥ እንቅስቃሴ በተፈጠረባቸውና በሚካሄድባቸው ቦታዎች ሁሉ ስርአተ አልበኝነትና እብደት ይነግሳል። ስርአተ አልበኝነቱ መልክ እስኪይዝ፣ እስኪሰክን ድረስ ከመንገድ የወጡ ያልተለመዱ ነገሮች ይበራከታሉ። ወደእኛ ስንመለስ የለውጡ መጀመሪያ አካባቢ ሲጻፉ የነበሩ የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት የሚነኩ፤ መረጃን አሳልፈው ለጠላቶቻችን ሲሰጡ የነበሩትን በምሳሌነት ማንሳት እችላለሁ። የኢትዮጵያ ሠራዊት ሞራል ደካማ ነው ፤ ሠራዊቱ በጎሣ የተከፋፈለ ነው ብሎ መጻፍና መናገር ትልቅ ወንጀል ነው። ሠራዊቱና አመራሩ እንዲጋጭ እንዳይግባባ መተማመን እንዳይኖረው ለሀገር ጠላት በር ለመክፈት ሆን ተብሎ ሲሰራ የነበረ ምናልባትም ከጀርባ በጠላቶቻችን ፋይናንስ የተደረገ በሀገር ክህደት ወንጀል የሚያስጠይቅ ስራ ነበር።

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

ከሠራዊቱ ውስጥ መረጃ አግኝቻለሁ በሚል የራሳቸውን መረጃ ፈጥረውና ፈብርከው ወይም ከሠራዊቱ የለቀቁና ቅሬታ የነበራቸው ሰዎች የሚሰጡትን የጥላቻ መረጃ ያለአንዳች የጎንዮሽ ማረጋገጥ እውነት አስመስለው በመጻፍ ለገንዘብ ማግኛ ሲጠቀሙበት የነበረ የሚዲያ እንቅስቃሴ አይተናል። የሕግ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ተወስኖ አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር። በዚሁ መንገድ እየተሄደበት ሳለ አንዳንድ ሰዎች የሠሩት ወንጀል ለሕግ ቀርቦ መልሰው እንዳይደግሙት መደረግ አለበት የሚለውን ሁኔታ በስፋት አጢነን ማሳሰቢያ እንስጣቸው፤ ስህተት ሳይመስላቸው ሰርተውትም ሊሆን ይችላል ብለን ያለፍናቸው አሉ።

ክሳቸው ተጠናቆ ቁጭ ብሎ እያለ የሽግግር ወቅት ስለሆነ ግዴለም እንለፋቸው ፤ ስርአተ አልበኝነት የወለደው ሁኔታ ነው። መከላከያ ትልቅ ሀገራዊ ተቋም ነው። የሀገርን ሉአላዊነት ዳር ድንበር የማስከበር ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ስራዎችን የሚሰራ ግዙፍ ብሔራዊ ተቋም ስለሆነ ከግለሰቦች ጋር ሲካሰስ አይውልም። ለተቋሙ ክብር ሲባል ለአሁኑ እንተዋቸው ለውጡ እየሠከነ ሲሄድ ከዚህ ውስጥ ይወጣሉ ብለን የተውናቸው ያለፍናቸው አሉ። እነሱም ጉዳዩን ተረድተውት ሊሆን ይችላል ይህን አይነቱን ነገር ትተዋል።

በተለይ በዚህ ወሳኝ ወቅት መከላከያን አንስቶ ማብጠልጠል፣ ጠንካራና ደካማ ጎን እያሉ በጽሁፍ ማሰራጨት፣ ስለመከላከያ ሠራዊት አደረጃጀት፣ ሞራል፣ ትጥቅና እንቅስቃሴ መናገር የለየለት የሀገር ክህደት ወንጀልና ባንዳነት ነው። በአሁኑ ሰአት ከውሀ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ ሀገራችን ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ ነው ያለችው። ሌሎች ችግሮችም አሉ። ከምርጫ ጋር ተያይዞ በዚህ አጋጣሚ ወደስልጣን ለመውጣት የሚያስችል እድል እናገኛለን ብለው እራሳቸውን አሳምነው የተቀመጡ አሉ።

ሀገሪቷን ቀውስና ችግር ውስጥ ለመክተት ያለእረፍት እየተንቀሳቀሱ ስለሆነ መንግስት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው ይገኛል። ከዚህ አንጻር አሁን ያለንበት ጊዜ ሚዲያውና ጋዜጠኛው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚወስድበት ነው። የራሱን ሀገር ለጠላት አሳልፎ የሚሰጥ ጋዜጠኛ አለ ብዬ አላምንም። ሀገር ሀገር ነች። አልፎ አልፎ ግን የጋዜጠኝነትን ስራ የሠራ እየመሰለው ሀገሪቱን ለአደጋ አጋልጦ የሚሰጥ ስለሚኖር ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል።

አዲስ ዘመን፦ የመንግሥት ሕጋዊነት መስከረም 30/2013 ዓ.ም ላይ ያበቃል።ከዚያ በኋላ መንግሥት የለም፤ ሁከት ይፈጠራል የሚሉ ድምጾች ይሰማሉ። መከላከያ የሀገርና የሕዝቡ ሰላም ጉዳይ ስለሚመለከተው ይሄን እንዴት ያየዋል?

ጀነራል ብርሀኑ፦ ከመጪው መስከረም 30/2013 ዓ.ም በኋላ መንግስት፣ ሕግ፣ መከላከያም የለም የሚለው የተዛባ እሳቤ ከመንገድ የወጣ ነው። ኢትዮጵያ ከምርጫ ታሪክ በፊት ጥንትም ነበረች። ዛሬም አለች። ወደፊትም ትኖራለች።ትቀጥላለች። ከመስከረም በኋላ ሕግና መንግሥት የለም፤ ሀገሪቷ የትርምስ አረንቋ ውስጥ ትገባለች ብሎ ማወጅ ኢትዮጵያ ሀገሬ ነች ከሚሉ ዜጎች አይጠበቅም ። ትክክል አይደለም ። በሕግም ያስጠይቃል።

የፖለቲካ ትግል አድርገህ ሕዝቡን ከጎንህ አሰልፈህ ስልጣን ላይ ያለውን ኃይል በሰላማዊ መንገድ አሸንፈህ ወደ ስልጣን መምጣትን ሕገመንግስቱ ይፈቅዳል። ከዚህ ውጪ በሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር ውስጥ አልፈን ስልጣን ለማግኘት አንችልም ብለው ራሳቸውን ያሳመኑ ክፍሎች ሀገር ትጥፋ፤ሕግ ስርአትና መንግሥት የለም አይኖርም ቢሉ ተገቢነት የለውም።

አሁን ያለው መንግስት በህጋዊ መንገድ ስልጣን ላይ ቆይቷል። ሕዝቡን እያስተዳደረ ባለበት ሁኔታና ምርጫ ሊያደርግ ሲዘጋጅ አለምን የከፋ አደጋ ውስጥ የከተተው የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገራችንም ተከስቷል። ከዚህ በመነሳት በአምስት አመት አንድ ግዜ የሚደረገው ብሔራዊ ምርጫ በተፈጠረው ከባድ ችግር ተራዝሟል። ኢትዮጵያ ለብቻዋ የፈጠረችው ያመጣቸው ነገር የለም።

ምርጫ ሲራዘም በመምራትና በማስተዳደር ላይ ያለው መንግሥት ምን ይሆናል የሚለውን ሕገ መንግሥቱ ይመልሰዋል ። መከላከያ ሠራዊት የሕገ መንግሥቱ የበላይነት አስጠባቂ ነው። መከላከያ ሁሉም ነገር ሕገመንግስቱ በደነገገው መሰረት ብቻ እንዲተገበር የመጠበቅ የማስከበር ግዴታ አለበት። ይህን ችግር ለመፍታት መንግሥት ያደረገውን ስናይ ምርጫ ከተራዘመ የመንግሥት ስልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር ሕገመንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ሕገ መንግስቱ ይተርጎምና መፍትሄ ይበጅለት ነው ያለው። ይሄ እርምጃ ሕገ መንግስታዊ ነው ብለን እናምናለን። ሠራዊታችን ሕገ መንግስታዊ ሠራዊት ነው የምንለው ለዚህ ነው።

ከሕገመንግስቱ ውጪ ስልጣን የማራዘም ነገር መንግስት ቢያመጣ እኛም ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን። ስልጣኔን ለአመት ለሁለት አመት አራዝማለሁ በሚል ሕገመንግስቱ ከሚፈቅደው ውጪ የመጣ የታየ ነገር የለም። የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በሕዝብና በሀገር ላይ ግልጽ ተጨባጭ የሚታይ አደጋ ደቅኗል። የሚጠቁት ዜጎች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ ነው። ከሚያደርሰው ጥፋትና አደጋ በመነሳት ወደ 58 የሚጠጉ የአለም ሀገራት ምርጫቸውን አራዝመዋል። የእኛም የተለየ አይደለም።

አዲስ ዘመን፦ ምርጫው ካልተደረገ ሁከትና አመጽ እንፈጥራለን የሚሉትስ ?

ጀነራል ብርሀኑ፦ አይችሉም። ሕገመንግስቱ የሚፈጠሩ ችግሮችን በሕግና በስርአት በሰላማዊ መንገድ በውይይት ይፈታል እንጂ ሁከት፣ ብጥብጥ፣ ትርምስ ፍጠሩ የሀገር ሰላምና ጸጥታ አደፍርሱ አይልም። መከላከያ መሰረታዊ ተልእኮው የሀገርን ዳር ድንበርና ሉአላዊነት መጠበቅ በመሆኑ ሠራዊቱ በፖለቲካ ጉዳይ አይገባም፤ ገለልተኛ ሆኖ ይሰራል ተባለ እንጂ ሠራዊቱ ወታደሩ መኮንኖቹም ሆኑ ጀነራሎቹ ስለፖለቲካ አያውቁም ማለት አይደለም።

መናገር ካስፈለገ እንዲያውም የሰከነና የሰፋ እውቀት አላቸው። ሠራዊቱ ገለልተኛ ሆኖ የሀገሩን ሰላምና ጸጥታ

ይጠብቅ ያስከብር ሲባል ፖለቲከኞች በሚፈጥሩት ሀገር የማተራመስ ዘመቻ ውስጥ ሕዝብ ሰላም ሲያጣ፣ ወጥቶ መግባት ሲያቅተው፣ ስርአተ አልበኝነት ሲሰፍን፣ ሀገር የዋልጌዎች መፈንጫ ስትሆን፣ ሕግና ስርአት ሲጣስ ዳር ቆሞ ይመለከታል ማለት አይደለም።ይሄ አይታሰብም። ይህች ሀገር ለሲቪሉም ለወታደሩም የጋራ ሀገራችን የሁላችንም ቤት ነች።

አንደኛውና ዋነኛው ጉዳይ ሠራዊታችን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የማስከበር ግዴታ አለበት። ሁለተኛው ሀገራዊ ሉአላዊነትን ከማስከበር ጋር የሀገሪቱ ሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕግ ሕገመንግስቱ መከበር አለበት። ዜጎች ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅድላቸው መሰረት ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ፣ ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ፣ መደራጀት፣ በምርጫ መወዳደር፣ መምረጥ፣ መመረጥ ይችላሉ። ይሄ ሁሉ የሚሆነው በሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ ብቻ ነው።

አይ በሰላማዊ መንገድ ሳይሆን በመበጥበጥ፣ ነውጥ በመፍጠር፣ ፋብሪካ በማቃጠል፣ ጎማ በማንደድ፣ ድንጋይና ግንድ ኮልኩሎ መንገድ በመዝጋት፣ ዜጎች ለፍተው ያፈሩትን ንብረትና ቤት እሳት ለኩሶ በማጋየት፣ የመንግስትን ንብረት በማውደም፣ ንጹሀን ዜጎችን በመግደል የሕዝብን ሰላምና ደህንነት የማወክ የአመጽ ስራና እንቅስቃሴ እናካሂዳለን የሚሉ ካሉ በሕግ ይጠየቃሉ። ይሄ በግልጽ መታወቅ አለበት።

መጪው መስከረም 30/2013 ዓ.ም ብቻ አይደለም የወደፊቶቹም መስከረሞች በሰላም ይቀጥላሉ። የሚያስቆመው የሚገታው ኃይል የለም። ኢትዮጵያም ሰላሟ ተጠብቆ ብዙ መስከረሞችን ታልፋለች ። መከላከያ ሠራዊቱ፣ ሕዝቡም፣ ሀገራችንም ትቀጥላለች። በሕዝብ ተመርጦ ስልጣን የያዘ መንግስት መከላከያን የመምራት ኃላፊነት አለበት። በዚህ መልኩ ብንረዳው ይሻላል። አንዳንድ ሰዎች ያልሆነ መልእክት አስተላልፈዋል በሚል ሰው መረበሽ የለበትም።ምንም የሚፈጠር ረብሻ ሁከት አይኖርም። ሕግና ስርአት ተከብሮ ይቀጥላል።

አዲስ ዘመን፦ በሱዳንና በእኛ ድንበር ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ቢገልጹልኝ ?

ጀነራል ብርሀኑ ጁላ፦ በኢትዮጵያና በሱዳን ወሰን አካባቢ ያለውን ነገር በተመለከተ ብዙ የተጋነኑ የሚዲያ ውጤቶችን እያየን ነው። ሚዲያዎች፣ ማህበራዊ ድረ ገጾች፣ ኦን ላይን ሚዲያዎች ከሱዳን ጋር በተያያዘ ብዙ የተጋነነ ነገር ነው የሚጽፉት። ለምሳሌ ብጠቅስ አንዳንድ ጊዜ የሱዳን ሠራዊት የኢትዮጵያን ገበሬ እንደወጋ፣ የሁለቱ ሀገር ሠራዊቶች እንደተዋጉ፣ የኢትዮጵያ መሬት እንደተወሰደ ተደርጎ ይጻፋል። ይነገራል። የእኛ ሠራዊት በቦታው ላይ አለ ። ሁሉንም ነገር እናውቃለን። የተጋነነውም ሆነ የፈጠራው ወሬ ለሀገር ለሕዝብ አይጠቅምም።

ይሄን በቅብብሎሽ የሚያሰራጩት የተለያዩ ሚዲያዎች ቦታውን ያለውንም ሁኔታ አያውቁትም።ሄደው ያረጋገጡት ነገር የለም ።ትክክለኛ መረጃ የላቸውም።በስማ በለው የሰሙትን ያስተጋባሉ።ይጽፋሉ። ይሄ ሚዲያውን ተአማኒነት ያሳጣዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገሩን ዳር ድንበር ለማንም አሳልፎ አይሠጥም። እውነቱ ይሄ ነው።

ሌሎች ደግሞ በእዛ አካባቢ ሰላም እንደሌለ ለማስመሰል የሚፈልጉ ኃይሎች የሚለቁት መረጃ አለ። ከሱዳን ጋር መልካም ጉርብትና አለን። ሱዳንና ኢትዮጵያ ጥሩ ወዳጅ ሀገሮች ናቸው። በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ አብረውን እየሠሩ ያሉ ናቸው። ሱዳኖች ሕዳሴ ግድቡ ይጠቅመናል ብለው ያምናሉ። ሕዳሴ ግድቡን ለመደገፍ ብዙ ጥረት አድርገዋል። ግንባታው ከተጀመረ ጀምሮ እስከዛሬ አልተለዩንም። አሁንም ግብጾች የሚያነሱትን ጥያቄ በተመለከተ ሱዳኖች አለም አቀፍ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት በእኩልነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ችግሩ እንዲፈታ ይፈልጋሉ። በመርህ ደረጃ ሱዳንና ኢትዮጵያ ምንም ግጭት የላቸውም የሚለው ነጥብ መሰመር አለበት።

ወደ ድንበሩ ጉዳይ ስንመለስ ከጥንት ጀምሮ ድንበርና ወሰን ላይ ሁልግዜ ግጭት አይጠፋም። በሱዳን ብቻ ሳይሆን ደቡብ ሱዳን፣ በኬንያ ፣ በሶማሌ ከወሰን ጋር በተያያዘ ግጭት ይከሰታል። ይሄንን ፈታ አድርገን ስንገልጸው ሰው ድንበር ተሻግሮ ወደእኛ መሬት ይመጣል። የእኛም ድንበር ተሻግረው ወደዛ ይሄዳል። ያርሳሉ። ይወስዳሉ። ይሸጣሉ። የጋራ ገበያ ይውላሉ። የእኛ ምርትና ሸቀጥ ተሻግሮ ወደዛ ይሄዳል። የእነሱም ተሻግሮ ወደ እኛ ድንበርና ግዛት ይገባል። ኮንትሮባንድ ንግዱ በጥቅም መተሳሰሩ አለ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ግጭት ነበረ። አለ። ይኖራል።

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

ከገበሬው ከኮንትሮባንዲስቶችም ጋር መጋጨቱ አይጠፋም ። አልፎ አልፎ በስህተት ወታደርም ከወታደር ይጋጫል። ወሰኑ ላይም ይሄ የኔ ነው ፤ ይሄ የአንተ ነው በሚል ግጭት ይፈጠራል። ይሄ ጉዳይ ድሮም የነበረ ነው።

በዚህ ምክንያት ትኩስ አጀንዳ እንደተገኘ ተደርጎ የሚነገረው ሁሉ ስህተት ነው። አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች መጠቀሚያ ሊያደርጉት ሲሞክሩ ይታያል። ተገቢ አይደለም።

እዛ ቦታ ላይ እርሻ ያለው ባለሀብት ለሀገር በመቆርቆርና በማሰብ ሳይሆን ለግል ጥቅሙ ሲል የተለያዩ ሚዲያዎችን ስፖንሰር እያደረገ ሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል ቀውጢ እንደተፈጠረ፤ ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት ወሮ እንደያዘ እንደወሰደ እያስመሰለ የሚያሰራጨው ወሬና የሚናገረው ነገር ሕዝቡን ሊያደናግር አይገባም።

በዚህ መንገድ ሁለቱን ሀገሮችና ሕዝቦች አጋጭቶ ሰላም ከደፈረሰ በኋላ እዛ ቦታ ላይ እርሻ ሊያርስ ምርቱን ሊሰበስብ ለገበያ አውጥቶ ሊሸጥ አይችልም። ሰላም ከሌለ ምንም የለም ። ይሄን ማወቅ አለበት። ጦርነት ከተፈጠረ ባለሀብቱም ሰርቶ ማግኘት ማትረፍ መጠቀም አይችልም። ይነቀላል። ሀብቱ ይወድማል። ሰላም ከሌለ የሚሆነው ይሄ ነው። ስለዚህ ሁለቱን ሕዝቦችና ጎረቤት የሆኑትን ገበሬዎች በማስማማት በመተባበር ሰላም በማስፈን ነው መስራት ያለባቸው።

የግል ጥቅምን ከወሰንና ከሀገር ጉዳይ ጋር ማያያዝ ተገቢ አይደለም።ሀገራዊ ድንበርና ወሰንን የሚመለከተው ጉዳይ የግለሰቦች ጥያቄ አይደለም። የመንግስት ጉዳይ ነው። የተዛባ የወሰን ጉዳይ ችግሮችን በተመለከተ ሁለቱ መንግስታት ተነጋግረው መፍትሄ ያበጁለታል። የአንድ ሀገር ወሰን እንዴት እንደሚከበር የሚገልጽ ሕግ አለ። እኛን ወደ ትርምስ ወደ ክተት አዋጅ የሚያስገባን ነገር የለም።

ቦታው ላይ እርሻ አለን የሚሉ ባለሀብቶች እርሻቸውን ከአጎራባች ወሰንተኞች ጋር ተግባብተው ተስማምተው ማረስ ነው ያለባቸው። በመገፋፋት ብጥብጥ እንፈጥራለን፤ ሁለቱ ሀገሮች እንዲዋጉ እናደርጋለን ካሉ ሁሉም የእኛም ሰዎች ሆኑ እነዛ እርሻቸውን ማረስ አይችሉም። ስለዚህ ዘላቂ ጥቅማቸውን በእርጋታ ማየት አለባቸው። እንደውም ለመጋጨት የሚሞክር የታጠቀ ኃይል ካለ እነሱ አስታራቂ መሆን ነው ያለባቸው። አሁን ግን አዝማች ሁነው ለኦን ላይን ሚዲያ መረጃ የሚያቀብሉት እነሱው ናቸው። ለሀገር ለድንበር ተቆርቁረው አይደለም። ለግል ጥቅማቸው ብለው ነው ። ይሄ ትክክል አይደለም። መስተካከል አለበት።

ሱዳን ከእኛ ጋር ጦርነት ለማድረግ እቅድ፣ አላማ፣ ፍላጎት የላትም። እኛም የለንም። ይሄ ሴራ ሙሉ በሙሉ መቆም አለበት። አንዳንዶቹ ባለሀብቶች የታጠቀ ኃይል እየገዙ ትንኮሳ እየፈጸሙ ኢትዮጵያና ሱዳን እንዲጋጩ የሚጥሩ ናቸው። ይሄን ድርጊት ግብጾች ይፈልጉታል። እዚህ ላይ ሁለት ነገር ነው ያለው። አንደኛው ግልጽ ተልእኮ የተሰጣቸው ሊኖሩ ይችላሉ። ይሄ እየተጣራ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሳያውቁት ለግብጽ የሚያግዝ ነገር እየሠሩ መሳሪያ ሆነዋል ማለት ነው። ኢትዮጵያዊ ነኝ ሀገሬን እወዳለሁ የሚል ይሄን ማድረግ የለበትም።

አዲስ ዘመን፦ ወታደሩ ፖለቲካ ውስጥ አይገባም ገለልተኛ ሆኖ ይሰራል የሚለውን አባባል መንዝረው ወታደር ደግሞ ስለፖለቲካ ምን ያውቃል የሚሉ ሰዎችን ፈጥሯል። እንዴት ያዩታል ?

ጀነራል ብርሀኑ፦ በነገራችን ላይ ወታደር ፖለቲካ አያውቅም፤ ፖለቲካ ውስጥ አይገባም የሚለው አባባል ትልቅ ስህተት ነው። መታረም መስተካከል አለበት። ወታደር የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይሆንም ሲባል ፖለቲካዊ አቋም ይዞ ለአንዱ ወግኖ ሌላውን አያጠቃም ማለት ነው። ይህ ደግሞ ወታደር የሀገሩን ታሪክ ጂኦግራፊ የሀገሩን ፖለቲካ አያውቅም ማለት አይደለም።

ሠራዊቱ ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ በተለያዩ የሙያ መስኮች ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ላይ የደረሱ ምሁራን እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል። ውትድርና የነጠረ ሳይንስ ነው። ውትድርና ማቴማቲክስ ነው። ታንኮች፣ መድፎች፣ ሞርታሮች፣ ሚሳይሎች በሂሳብ ስሌትና ቀመር ነው የሚተኮሱት።የሚወነጨፉት። ውትድርና ጂኦግራፊም ጂኦ ፖለቲክስም ነው። ስለማንኛውም የመሬት ገጽ (ተራራውን፣ ሸለቆውን፣ ሸጡን፣ ሜዳውን፣ ተዳፋቱን፣ ኮረብታና ጋራውን) የአየር ጸባዩን ለይቶ አውቆ ለውጊያ ያመቸኛል አያመቸኝም፤ ያስጠጋኛል አያስጠጋኝም ብሎ አጥንቶ ጥቅምና ጉዳቱን መዝኖ የሚንቀሳቀስ ነው። ከጂኦ ፖለቲክሱም አንጻር የአጎራባች ሀገራትን ወታደራዊ አቅም አቋም መንግስታዊ አስተዳደርንም አካቶ ለግዳጁ በሚመጥን መልኩ ያጠናል። ይፈትሻል። ውትድርና የአየር ንብረት ሳይንስ አዋቂም ነው። ለግዳጅ ከመሰማራቱ በፊት የአየር ንብረቱ ጸሀያማ፣ደመናማ፣ ጭጋጋማ፣ ዝናባማ፣ ካፊያ ያለው፣ ወይስ በረዶአማ ነው ብሎ አጥንቶ የሚሰራበት ሙያ ነው። ውትድርና ፊዚክስም ነው (አውሮፕላኖች፣ ሄሊኮፕተሮች፣ ጀቶች፣ መርከቦች፣ተመሪ ሚሳይሎች ወዘተ) በናቪጌሽን ሳይንስ በፊዚክስ ስሌትና ቀመር ነው የሚመሩት። የሚበሩት። ውትድርና ኬሚስትሪም ነው። ከትንሽ እስከ ትልቁ ጦር መሳሪያ ድረስ የሚጠቀምባቸው አረሮች ሙሌት ተመጥኖ የሚሰራው በኬሚስትሪ ነው። ውትድርና ኮሚዩኒኬሽንም ነው። የቅርብና የሩቅ፤ የአየር ለአየርና የአየር ለምድርና የባህር ወታደራዊ የሬድዮ ግንኙነቶች ሁሉ የተመሰጠሩ ኮዶችን የሚጠቀሙ ኮሚዩኒኬሽንስ ናቸው። ውትድርና ኢኒጂነሪነግም ነው።( ምሽጎቹ፣ ጦር ካምፖቹና ወንዝ መሻገሪያ ድልድዮቹ የተለያዩ መሳሪያዎች ምርቶች፣ ኮንስትራክሽኖች ሁሉ የሲቪል የመካኒካል የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪነግ ውጤቶች ናቸው። ይሄ ብቻም አይደለም። የዘመኑ ምጥቀት ውትድርናን ወደ ኬሚካል ዋርፌር እና ባዮሎጂካል ዋርፌር፤ ወደ ሳይበር ዋር (ጦርነት) አስፈንጥሮታል። ውትድርና የአመራር ጥበብና ክህሎትን ( ዘ አርት ኦፍ ሊደርሽፕ ) የሚጠይቅ የአስተዳደርና የአመራር የጥብቅ ዲስፕሊን ሙያም ነው። ውትድርና ከታሪክ፣ ከፖለቲካ ትምህርትና እውቀት ጋርም የተቆራኘ ነው። የውስጥም ሆነ የውጭ ጦርነቶች መነሻ ገፊ ምክንያቶች የተካሄዱበት ዘመን፣ የነበረው መንግስታዊ ስርአት፣ የተሰለፈው ኃይል፣ በተቃራኒው የነበረው አሰላለፍ፣ የመጨረሻው ውጤት ሁሉ በታሪክ ተመዝግቦ የሚሰፍር የታሪክም አካል ነው ውትድርና።

ከዘመነው ሳይንስና ቴክኒዮሎጂ ጋር እየመጠቀ የሚሄድ ሙያም ነው። ብዙ ማለት ይቻላል። በአጭሩ የውትድርና ሙያ የነጠረ ሳይንስና ሁሉንም ሳይንሶች አጠቃሎ የያዘ ነው። ውትድርናን ጠመንጃ ከመያዝ ጋር ብቻ አያይዘው ወታደር ስለፖለቲካም ስለሌላውም ምንም አያውቅም፤ የእሱ ስራ ጠመንጃ ይዞ ሰላም ማስከበር ብቻ ነው የሚሉ ሰዎች በእጅጉ የተሳሳቱ የሙያውን ምንነት የማያውቁ ናቸው።

ሌላው በትልቁ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ምሁራን ለሀገራቸው የሚሰጡት ትልቁ ስጦታ እውቀታቸውን ነው። ያስተምራሉ። ትውልድ ይቀርጻሉ። ሠራዊቱ ደግሞ ከተራ ወታደር፣የበታች ሹም፣ መስመራዊ መኮንን፣ ከፍተኛ መኮንን እስከ ጀነራል መኮንኖች ድረስ በተሰለፉበት ሀገራዊ ወታደራዊ ግዳጅ ሁሉ የሚሰጡት መተኪያ የሌላትን ሕይወታቸውን ነው። ለሀገር ከዚህ በላይ ታላቅ ስጦታ የለም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ሀገሬን ወገኔን እወዳለሁ የሚል ማንኛውም ዜጋ የሀገሩን ሰላም ጸጥታና ደህንነት ለመጠበቅና ለማስከበር ሁልግዜም ከሠራዊቱ ጎን መቆም መሰለፍ ይገባዋል ብለን እናምናለን።

አዲስ ዘመን፦ በተለያየ ሙያ ሀገራቸውን ያገለገሉና በጡረታ የተገለሉ ከፍተኛ ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ መኮንኖች፣ ሰፊ እውቀትና ልምዳቸውን ለመንግስት ምክረ ሀሳብ በመስጠት የሚያካፍሉበት ወታደራዊ ምክር ቤት (ሚሊተሪ ካውንስል) በርካታ ሀገራት አላቸው። እኛስ አለን ?

ጀነራል ብርሀኑ፦ ሀገራችን ከፍተኛ ወታደራዊ ምክር ቤት አላት። (ሚሊተሪ ካውንስል) ማለት ነው። የሚመራው በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥና በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆን በመደበኛው የውትድርና አገልግሎት ውስጥ ያሉትን ያቀፈ ነው።

በጡረታ ላይ የሚገኙ እድሜያቸውን ሙሉ ለሀገር ያገለገሉ የደከሙ ወታደሮች መኮንኖች ጀነራሎች ያካበቱት ልምድና እውቀት የሀገር ሀብት ነው። እንደዚህ አይነት ስብስብ መኖሩ ይደገፋል። ለሀገር ይጠቅማል። ሀሳብ ያመነጫሉ። ከተለያዩ ልምድና ተሞክሯቸው በመነሳት ሰፈ ሀሳብ የማመንጨት አቅም አላቸው። ያ ሀሳብ ተጠቃሎ በአንድ ሲዋሀድና ሲጨመቅ ተጨባጭ ውጤት ያስገኛል ። ለሀገር ለተቋማትም ይጠቅማል። ከሀገራዊ ተቋማት አንዱና ግዙፉ መከላከያ ነው። መከላከያ እንዲህ አይነቱ እድል ተገኝቶ ምክረ ሀሳብ የሚሰጡ ሀገር ሲከላከሉ ሕይወታቸውን ያሳለፉ ወታደሮች፣ መኮንኖች፣ ከፍተኛ መኮንኖች ጀነራሎች የሚያመጡት ሀሳብ ለሠራዊቱ እጅግ በጣም እንደሚጠቅም ያምናል። እንደሚታወቀው ውጥረት በተሞላበትና ፋታ በማይሰጡ የጸጥታ ማስከበር ስራዎችና ከለውጡ ጋር ተያይዞ በአራቱም ማእዘናት የገጠሙን በርካታ ችግሮች ነበሩ። የሪፎርሙ ስራም አለ። በእነዚህ አጣዳፊ ሀገራዊ ምክንያቶች የተነሳ ሰከን ብሎ ለማሰብ ግዜ አልነበረንም። ሀሳቡ መሰረታዊና ጠቃሚ ነው። ወደፊት እንዴት አድርገን እንደምንሄድበት እናየዋለን ብዬ አስባለሁ።

አዲስ ዘመን፦ ዛሬ ላይ በተለያዩ አቅጣጫዎች ያለው ሀገራዊ ሰላምና ጸጥታ ምን ይመስላል ?

ጀነራል ብርሀኑ፦ እኔ እስከማውቀው ድረስ ከዚህ በፊት ከነበረው የጸጥታ ሁኔታ ጋር ሳነጻጽረው አሁን ያለው ሰላም በጣም የተሻለ ነው። የተሻለበት ምክንያት ይሄ ለውጥ ሲመጣ በየቦታው እየፈላ ሲንተከተክ ሲገነፍል የነበረ ግርግርና ሁከት ነበር። ዛሬ አንዱ ሲፈታ ነገ ደግሞ ሌላው ጋ እየተነሳ ያስቸግር የነበረው ግጭት መገፋፋቱ፣ አንዱን በሌላው ላይ እያነሳሱ ጥፋት የማድረሱና እርስ በእርስ ማናቆሩ አሁን የለም።

Related stories   የአውሮፓ ህብረት የይስሙላ ምርጫዎች ሲታዘብ ቆይቶ አሁን አልታዘብም ያለበትን ምክንያት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሳውቅ ተጠየቀ

እስከአሁን ባለው ሁኔታ የሀገራችን ሰላምና ጸጥታ ከመቼውም ግዜ የበለጠና የተሻለ ሰላማዊ ነው ማለት እችላለሁ። ከለውጡ ጋር ተያይዞ የተነሱት አይነት የጸጥታ ችግሮች አሁን የሉም። ችግሮቹ እየተፈቱ እያደር መስከንና ማስተዋል እየሰፈነ መጥቷል። በቂ ልምድና ተሞክሮ ተወስዶበታል። ለምሳሌ ደቡብ ክልል አስቸጋሪ የጸጥታ ሁኔታ ነበር። አሁን በጣም ጥሩ ሁኔታ ነው ያለው። ሁለተኛው ጉዳይ ክልል ከክልል በወሰን ላይ አለመግባባት ነበረ። በመጣው ለውጥ ምክንያት ያኮረፉ ሰዎች የሚፈጥሩት ግጭት ነበረ። እሱም ተዳክሟል ። ጉጂ፣ጌዶ፣ ቦረና አሁን ሰላም ነው። በአማራ ክልል አሁን ያለው ሰላም ከበፊቱ በእጅጉ ተሻሽሏል። የእስከ አሁኑ ይህንን ይመስላል። ይሄ ማለት ሰላም ለማደፍረስ እያደቡ ያሉት ኃይሎች ተኝተዋል ማለት አይደለም። ለዚህም ሠራዊቱም ሆነ መላው የሀገሪቱ የጸጥታና ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ነቅተው ይጠብቃሉ።

አዲስ ዘመን፦ ኮረና ቫይረስ ወደ ሠራዊቱ እንዳይገባ ለመከላከል መከላከያ የሠራውን ስራ ቢገልጹልኝ ?

ጀነራል ብርሀኑ፦ ኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ የአለምም የኢትዮጵያም እጅግ አደገኛ ጠላት ነው። ሠራዊታችን ውስጥ እንዳይገባ ለማድረግ ከፍተኛ ስራዎችን ሰርተናል። እየሠራንም ነው። ብዙዎቹ የጥንቃቄ እርምጃዎች በመከላከያ ኦን ላይን ሚዲያ ላይ ይወጣሉ። በራሳችን የጤና ባለሙያዎች ስለኮረና ቫይረስ ምንነትና የስርጭት መንገድ የማስተማሩና የማሳወቁ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ርቀትን የመጠበቁ፣ እጅን መታጠቡ ልምድ እንዲሆን ተደርጓል። የእያንዳንዱን ሰው ሙቀት በጦር ሰፈሮች የመለካት ስራ ይካሄዳል። ለግዜው ሠራዊቱ ከካምፑ ውጪ ያለው እንቅስቃሴ እንዲገታ ተደርጓል።

ይህም ንክኪ እንዳይፈጠርና ቫይረሱ ከውጭ ወደውስጥ እንዳይገባ እንዳይስፋፋ ለማድረግ ነው። ሲንቀሳቀሱ ማስክ የመጠቀም ግዴታም አለ። የግልና የጋራ ንጽህናን፣ መኖሪያ ቤታቸውንና የጦር ካምፑን ንጽህና በየእለቱ ይጠብቃሉ። ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች፣ የነፍስ ወከፍና የቡድን ጦር መሳሪያዎችን የማጽዳቱ ስራ ያለማቋረጥ ይካሄዳል። ዲስ-ኢንፌክታንት (ጸረ ቫይረስ) ርጭት ይካሄዳል። ምክንያቱም ኮረና ቫይረስ ብረት ነክ ቁሶች ላይ ብዙ ስለሚቆይ ሲነካ ለቫይረሱ ተጋላጭ ስለሚያደርግ መከላከያ ለዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። በሠራዊቱ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ውስጥ የሚሰሩ ዶክተሮቻችን፣ ነርሶቻችን ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ምስጋናም ይገባቸዋል።

በመጀመሪያ ትኩረት በመስጠት ያቀድነው በጭራሽ ኮረና ቫይረስ (ኮቪድ) ሠራዊቱ ውስጥ እንዳይገባ ማድረግ አለብን ብለን ነው። ኮረና ለመግባት የሚችልባቸው በሮች ሁሉ ተጠርቅመው መዘጋት አለባቸው በሚል ያካሄድነው ጠንካራ ስራ ለመከላከል የሚሰጡ መመሪያዎችን ደንቦችን ሁሉ ለመተግበር በቀላሉ ስላስቻለን ጠቅሞናል። ኮቪድ ወደ ሠራዊቱ ገባ ማለት የሀገሪቱን የመከላከያ አቅም አደጋ ላይ ጣለ ማለት ነው። ይህ እንዳይሆን ሰፊ ስራዎችን ሰርተናል። እየሠራንም ነው። እንቅስቃሴያችን በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሠራዊታችን ራሱን ከኮረና ቫይረስ ጠብቋል ብለን ነው የምንወስደው። ቫይረሱ አስከፊ ጥፋት ባደረሰባቸው ሀገሮች እንዳየነው ሠራዊቱ እራሱን አድኖ ተከላክሎ ለሕዝቡም አስቸኳይ እርዳታ ለመስጠት ተሰማርቷል። የከፋ ነገር ቢከሰት በሚል እኛም ሙሉ ዝግጅት አድርገናል።

አዲስ ዘመን፦ ግብጽን በተመለከተ የመጨረሻ ሀሳብ ቢሰጡን ?

ጀነራል ብርሀኑ፦ ግብጾች የሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ እያራመዱ ያሉት አቋም ፍትሀዊ አይደለም። ለግብጽ ትልቅ አደጋ ይፈጥራል። ግብጽ በከፋ ደረጃ ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ጠላትነት ገፍታ ውሀውን ሳይቀንስ እጠቀማለሁ ብላ የምታስብ ከሆነ በጣም ተሳስታለች። ግብጾች ማወቅ ያለባቸው ዋናው ጉዳይ የአባይ ወንዝ ውሀ ምንጭ ኢትዮጵያ መሆኗን ነው። ውሀውም የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ተራሮች ነው ። የራሳችን የሆኑ 90 ገባር ወንዞች ናቸው ወደ አባይ ወንዝ የሚፈሱት። እያንዳንዱ ወንዝ ለመጠጥ ውሀ፣ ለመስኖ ለተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ከተገደበና ስራ ላይ ከዋለ አባይ የሚባል ወንዝም ውሀም አይኖርም። ይደርቃል። ግብጾች አባይ ውሀ ከምንጩ እንዳይቋረጥ ፍሰቱ እንዳይቀንስ ውሀውን በቀጣይነት ለመጠቀም ኢትዮጵያን አግዘው ነው መቆም ያለባቸው።

ኢትዮጵያ የራሷ የሆነውን የአባይ ውሀ ተጠቅማ አንድም ነገር አልምታ ተጠቅማ አታውቅም። ግብጾች የሕዳሴ ግድቡን ተርባይን መትቶ ፍሰቱን ለሚቀጥል ውሀ ይሄን ያህል ያዙኝ ልቀቁኝ ማለታቸው ትክክል አይደለም። በያዙኝ ልቀቁኝ ደግሞ የሚገኝ የብቻ ጥቅም የለም። የሁሉም ነገር አማራጮች (ጦርነትን ጨምሮ) ጠረጴዛ ላይ ነው የሚሉት አባባላቸው ድሮ ልጆች እያለን አንዱ ሌላውን የሚያስፈራራበት ጨዋታ አይነት ነው። ግብጾች የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሰው ጦርነት ሲመጣ እንዴት ጦርነት መስራት እንደሚችል በሚገባ የሚያውቁ ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሩ ሕልውናና ክብር ከመጡበት ሞት የማይፈራ ጀግና ሕዝብ መሆኑን አይደለችም ግብጽ አለም ያውቃል። በሀገሩ ጥቅምና ሕልውና የሚደራደር ኢትዮጵያዊ የለም።

የጦር መሳሪያ በገፍ መሰብሰብ ብቻ በጦርነት ውስጥ ለድል አያበቃም። በጦርነት ውስጥ ለድል የሚያበቁ ሳይንሳዊ የሆኑ የጦርነት መሰረታውያን የሚባሉ ሕጎች አሉ። ለድል የሚያበቁት የመሰረታውያኑ ቁልፎች በሙሉ በኢትዮጵያ እጅ ናቸው። ግብጾች ጋ አይደለም ያሉት። ግብጾች 30 እና 40 አመት ሙሉ ሲሰበስቡት የኖሩት አይነት ብዙ የጦር መሳሪያ ክምችት አላቸው። በዚህ አስፈራርተው የጋራ የሆነውን ውሀ እንዳትነኩ ለማለት አይችሉም። መሪዎቹ እንደዛ ማሰብ አልነበረባቸውም።

ከኢትዮጵያ ጋር በጭራሽ መጣላት የለባቸውም። ኢትዮጵያን ተንከባክበው መያዝ ውሀውን እንዴት አድርገን በጋራ እንጠቀም ነበር ማለት የነበረባቸው። ፈጣሪ ውሀውን ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጠረው ወደ ሱዳንና ግብጽ እንዲፈስ አደረገው። የወንዙ ውሀ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ግብጽም ላይ ጥቅም ላይ ይውላል። ከታች ያለው ሀገር እንጂ ከላይ ያለው ሀገር ውሀውን መጠቀም አይችልም የሚል የአለም ሕግ የለም። ይሄ የተሳሳተ የመሪዎቿ አስተሳሰብ ግብጽን በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳታል። ብዙ ጠላት ታፈራለች። ጠላትነት በጨመረ ቁጥር ጭራሹንም ውሀው ሙሉ በሙሉ የእኔ ነው ወደሚል ነገርም ይወስዳል ። መቼም ቢሆን የግብጽ ሠራዊት ኢትዮጵያ ገብቶ ምሽግ ሰርቶ የአባይን ገባር ወንዞች አይጠብቅም ። የኢትዮጵያን ምድርም አይረግጥም። እነዚህ ወንዞቻችን ከጦርነትም በላይ ታላቅ አቅምና ጉልበት አላቸው።

የግብጽ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች ሚዲያቸውና ምሁራኑ የግብጽ ሕዝብ እንዲደነግጥ እንዲፈራ ውሀ የሚያጣ እንዲመስለው አድርገው ውሀ የምትለቅለትን ኢትዮጵያን በጠላትነት እንዲመለከት የረዥም ዘመን ስራ ሰርተዋል። ዛሬ ችግር ያመጣባቸው ይሄ ይመስለኛል። የፖለቲካ አመራር ማለት የግብጽን ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም አይቶ የግብጽን ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመከባበር በፍቅር በወንድማማችነት አስተሳስሮ ያለጦርነት ያለጠላትነት በጋራ እንዲጠቀም ማድረግ ነው። ብልህና አርቆ አሳቢ ለሀገሩና ለህዝቡ የሚጨነቅ የፖለቲካ መሪ ይሄን ነው የሚያደርገው።

ጠላትን መቀነስ ወዳጅን ማብዛት የሚባል ስሌት አለ።መፎከር ሁሉም አማራጭ ጦርነትን ጨምሮ ጠረጴዛ ላይ ነው ያለው ማለት የሀሰት ሪፖርት ጽፎ መበተን፤ ግዙፍ የሚዲያ ዘመቻ ከፍቶ ኢትዮጵያን ማጥላላት በጠላትነት መፈረጅ ትርጉም የለሽ ነገር ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ብዙ አልተናገረችም። እኔ እንደሚመስለኝ ድሮ ጀምሮ ከዛሬ 2000 እና 3000 አመት ጀምሮ የግብጽ መሪዎች ለሕዝቡ ሲያወሩት የኖሩት የአባይ ውሀ የእኛ ነው፤ የእኛ ስጦታ ነው፤ እግዚአብሄር ለእኛ ነው የሰጠን ሲሉት የነበረው ተረት ተረት ከፍተኛ ችግር ፈጥሮባቸዋል።

ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ነች የአባይን ውሀ የምታመነጨው። ለሱዳንና ለእኛ ደግሞ ከኢትዮጵያ የሚመጣውን ውሀ እግዚአብሄር ሰጥቶናል ብለው ለግብጽ ሕዝብ ነግረውት አያውቁም። ለታዳጊ ሕጻናት ሁሉ ያንኑ ተረት ነው ሲያስተምሩ የኖሩት። ይሄ ነው ትልቅ ችግር የፈጠረባቸው። የእኛ ብቻ ነው ብለውት ኖሩ። ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ ስትገነባ ማጣፊያው ሲያጥር ተቸገሩ። አሁን ማስተካከል ያለባቸው የድሮውን የፈጠራ ወሬአቸውን ነው። በተረፈ ኢትዮጵያ ግብጽ ላይ የተለየ የጣለችው ምንም ነገር የለም። የአባይን ውሀ እኛ ለእርሻ እንጠቀምበት ብንል እንኳን ለእሱ የሚሆን መሬት የለንም። ምክንያቱም መሬታችን ተራራማ ነው ። ግብጾች የራሳችንን የአባይ ወንዝ ውሀውንም ኤሌክትሪኩንም አትጠቀሙ ከሆነ የሚሉት ወደፊት ሌላም ብዙ ነገር እንጠቀማለን። የሚከለክለን የሚገታን ማንም የለም። ስለ ውሀ ድርሻና ክፍፍል ገና አልተነሳም። ወደፊት ነው የሚነሳው። ስለ ግድቡ ብቻ ነው ንግግር እየተደረገበት ያለው። ግድቡ ተገድቦ ፣ ውሀ ይዞ፣ ኤሌክትሪክ አመንጭቶ እንዲሄድ ነው እየተነጋገርን ያለነው። የአባይ ውሀ 85 ከመቶ የእኛ ነው ብንል 40 ፐርሰንቱ የእኛ ነው 70 ፐርሰንቱ የእኛ ነው ብንል ማነው የሚያቆመን ማንም አያቆመንም። ግብጸች ተሳስተዋል። መሪ የላቸውም። አልሲሲ በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል የአባይን ወንዝ ውሀና ግድቡን የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ አድርጎ እየተጠቀመበት ያለ ይመስለኛል። የአባይን ውሀ እኔ ነኝ የማስከብርላችሁ፤ እኔ ከሌለሁ ማንም አያስከብርላችሁም የሚል አይነት ጨዋታ እየተጫወተ ይመስለኛል። ይሄ ደግሞ አያዋጣም። የትም አያደርሳቸውም።

አዲስ ዘመን፦ ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ እናመሰግናለን።

ጀነራል ብርሀኑ ጁላ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2012

ወንድወሰን መኮንን