” አንድን ድርጅት  ወደ ስልጣን በመጣበት መንገድ ተኪዶ ማጥፋት አይቻልም” ሲል የትግራይ ተወላጅ የሆነና ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ አስተያተቱን ይጀምራል። ይህንን ከጅምሩ ለማለት ያስቻለውን ጉዳይ ሲያብራራ ” ወደ ስልጣን የመጣበትን መንገድ ማስተር አድርጎታል፤ በዚያ መልኩ ልግጠምህ ብትለው ይበልጥሃል። በቃ ለምዱ ስላለው። ብዙ ወድቆ ስለተነሳና ስለተማረበት እንጂ ልዩ ተዓምር የለውም”

“ለግዜው አሌክስ በለኝ” የሚለው ሌላው የትግራይ ተወላጅ ” ትግራይ በቅርቡ አገር ትሆናለች፤ ይህ መንግስት እድሜ የለውም” በማለት የቀደመውን አስተያየት ይሰጣል። ትግራይ አሁን እያደረገች ያለው ሁሉ የመንግስት ምስረታ ምልክቶች መሆናቸውን የሚጠቁመው አሌክስ ” በኢትዮጵያ አገር መሆን የሚችሉት የሶማሌ፣ የትግራይ ክልል ብቻ ስለሆኑ ሌሎች በተለይም አማራና ኦሮሞ ከወዲሁ ቢስማሙና ሃይላቸውን ቢያሰባስቡ አገሪቱ ላይ የሚፈጠረውን ኪሳራ ሊቀንሱ ይችላሉ ባይ ነው።

ስለ ትግራይ አገር መሆን ሲታሰብ ዋናው ችግሩ ኢኮኖሚ ብቻ እንደሚሆን አሌክስ ያምናል። ይሁን እንጂ ከኤርትራ ጋር የመቀላቀሉ ጉዳይ የቀን ካልሆነ የሞተ አጀንዳ መሆኑንን በፍጹም እርግጠኛ ሆኖ ይናገራል። ኤርትራን ተቀላቅሎ በቀይባህር ላይ ሃያል በመሆኑ የኢኮኖሚውን ችግር መቅረፍ እንደሚቻል ሲያልም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በህይወት እያሉ ግን ይህ ሊሳካ እንደማይችል አይክድም።

የኢሳያስን ሞት የሚመኘው የትግራይ አገር መሆን ጉዳይ አከራካሪ ቢሆንም ጉዳዩን ለማመጣጠን በሲውዲን የሚኖረውን ኤርትራዊ የአሌክስ ባልደረባ አስተያየቱን እንዲያጋራ ተጋብዞ ነበር። ወደ አገር ቤት በቅርቡ ስለሚመለስ ስሙን ደብቁልኝ በማለት ” እኔ እስከሚገባኝ በፈቃደኛነት የኤርትራ ህዝብ ከትግራይ ጋር ውህደት ሊፈጥር ይችላል የሚል እምነት የለኝም። ምናልባት ወደፊት ከረዥም ጊዜ በሁዋላ ሊሆን ይችላል” ብሏል።

Related stories   አስከሬን እንዲለቀም ታዘዘ - ትህነግ የአጽም ፖለትካ ድራማ ይፋ ሆነ

እሱ እንደሚገባው ዛሬ ላይ ህወሃት እያራመደ ያለው የፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ የደጋውን የኤርትራ ክፍል የመወስወስና መሰረታቸው ትግራይ እንደሆነ ለማሳየት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ቅስቀሳ አብዛኞች ኤርትራዊያንን ቅር የሚያሰኝ፣ ” በአካባቢያዊ ስሜት ሊከፋፍሉንና አገራችንን ሊያፈራርሱ ነው” የሚል ምላሽ እያገኘ መሆኑንን ነው።

የትግራይን አገር የመሆን እርምጃና እንቅስቃሴ መረዳት ለማይፈልጉ ብቻ እንጂ ለሁሉም ግልጽ ጉዳይ እንደሆነ የሚናገረው የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ እንደሚያስረዳው የትግራይ አዲሱ ትውልድ የትግራይን አገር የመሆን ውሳኔ ይደገፋል። አልፎ አልፎ  ህወሃት ላይ የሚሰሙ ተቃውሞዎች እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። ተቃውሞዎቹ የሚደገፉት በማዕከላዊ መንግስት በመሆኑ ይበልጥ ሃይል የሚሰጥና የአገር ግንባታውን የሚያጣድፍ ይሆናል።

“ይልቁኑ ” አለ ይህ አስተያየት ሰጪ ” ይልቁኑ ይህ አብይ የሚመራው መንግስት እድሜ እንደሌለው አስቀድሞ መረዳት ያስፈልጋል” ሲል ፖለቲካዊ ሟርቱን ያሰማል። ህወሃት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን መንግስት ሳታጠፋ እንቅልፍ እንደማትተኛ፣ ዛሬ ላይ ያለው የፖለቲካ አየርም ህወሃት ባቀደቺው መሰረት አብይን የማስወገድ ጫፍ ላይ መዳረስዋን ያሳያል። አክሎም ” በኦሮሚያ በቅርቡ ነገሮች መላክቸውን ይቀይራሉ” ሲል በኦሮሚያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችና የህወሃትን ጥምረት በገደምዳሜ ያሳብቃል።

የቀድሞ የሻዕቢያ ተዋጊ የነበረውና ዛሬ ነዋሪነቱን በአሜሪካ ያደረገው ዘሮም ” እመነኝ ህወሃት ታማለች፣ ሞተን ካልሆነ በስተቀር ወደ ኤርትራ አይታሰብም። ይልቁኑ የወልቃይት ጥያቄ በቅርቡ ይቀጣጠላል” ሲል አዲስ መረጃ ያነሳል። ” ቦታውን አልነግርህም፤ እኔ የወልቃይት ተጋዮችን አሰለጥን ነበር። ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። እነሱ ወደ ሃይል ርምጃ ከሄዱ ኢሳያስም ሊያግዛቸው ይችላል… ከዚህ በላይ ሌሎች የሚከተሉትን ጉዳዮች አንተው ሙላበት ” በማለት ከላይ ባሉት አስተያየት ሰጪዎች ሃሳብ ላይ ውሃ ይደፋበታል።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

አሌክስ አማራና ኦሮሞ ህብረት ቢፈጥሩ በአፍሪካ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደሚሆኑ፣ ሁለቱ ህዝቦች በብዙ ምክንያት የሚገናኙና ሊለያዩ የማይችሉ በመሆናቸው እድል ፈንታቸው ህብረት ብቻ መሆኑንን እንደ አንድ ቀና ዜጋና ባለሙያ ያመለክታል። አሌክስ አያይዞም ህወሃት የሚመች የፖለቲካ መድረክ ቢመቻችላት ይህንን ህብረት እውን ማድረግ አያቅታትም። ግን አሁን አይሆንም። እንዲያውም ችግሩን ማስፋት ነው የሚፈለገው።

አቶ ጃዋር በቅርቡ ” የትግራይ አገር መሆን ጉዳይ በቅርቡ ተግባራዊ የሚሆን ይመስለኛል” ሲል መናገሩና በተደጋጋሚ በኦሮሞ ጉዳይ ጽንፍ ረግጦ ያሻውን ቢልም ” ለኦሮሞ መገንጠል አይጠቅመውም” የሚለው አቋሙ ከላይ የተነሳውን ሃሳብ ያጠናክረዋል። ጃዋር ይህንን ቢልም ከአማራ ልሂቃን ጋር ህብረት ፈጥሮ ለመስራት ሲሞክር አይታይም። ይልቁኑም አማራ ክልል ውስጥ በመግባት የቅማንትና የአገው እንዲሁም የክልልነት ጥያቄ ለሚያነሱ ወይም ከክልል ለመውጣት የሚጠይቁ ሃይሎችን ማበረታታት ላይ ያተኩራል። ሰፊ የሚዲያ ሽፋን እንዲሰጥ ያደርጋል። በግልጽ ይደግፋል። ይህ አቋሙ በውልቃይት ጠግዴና በራያ፣ እንዲሁም ኦሮሚያ ክልል ለሚኖሩ አማሮች የተለየ ነው። አሌክስ ይህንን አስመልክቶ ጃዋርና ህወሃት ዛሬ ላይ ስትራቴጂ ነድፈው በሚሰሩት ስራ የሚናገሩት ተመሳሳይ ነው፤ ይወልቃይትና የራያ ጉዳይ ህወሃትን ስለሚያስከፋ ጃዋር አይደፍረውም። ምክንያቱም የሚበላሽበት ጉዳይ ይበዛል።

የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት፣ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ጨምሮ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ አስተማማኝ ሃልና አቅም አንዳለው፤ ኮሽ ባለ ቁጥር የሚበረግግ እንዳልሆነ ሲናገሩ ይደመጣል። አሁን ያለውን አካሄድ የሚገመግሙ እንደሚሉት ” ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰማው የሚዲያ ተኩስ እንጂ መሬት ላይ ያለው ጉዳይ ሌላ ነው”

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

ሁሉም አስተያት ሰጪዎች ዝምታን የመረጡበት ጉዳይ ግን የኢትዮጵያንና የኤርትራን የመከላከያና የደህንነት ስምምነት ነው። ከዚህም በላይ ኤርትራዊያን ወደ ኢትዮጵያ እንጂ ወደ ክልል ግንኙነት የማያስቡ መሆናቸው ላይና የሁለቱ አገራት ጥብቅ ሚስጢራዊ ግንኙነትና በምስራቅ አፍሪቃ የተያዘው አዲሱ የባለጠጋዎቹ እቅድ በህወሃት አማካይነት ይከሽፋል ወይ? ለሚለው ጥያቄ ነው።

የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ” ልምከራችሁ” ሲል አንድ ሃሳብ ያነሳል። መንግስት በትግራይ ክልል ሃላፊዎች ላይ የከፈተውን የሚዲያ ዘመቻ ያቁም። ይፈለጋሉ የሚላቸውን ክፍሎች ስም እያነሳ የሚወተውተውን ውትወታ ይግታ። አሁን ህወሃትን ከምንም በላይ የሚያበሳጫት ያለውና ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ገመድ ለመበይጠስ የሚጣደፉት በዚሁ ምክንያት ነውና። ይህ ከሆነ ነገሮች ይረግባሉ። ከትግራይ ወገንም ስድቡና ማጠልሸቱ ይቆማል።

አብዛኞች ” እረኛውን ምታ በጎቹ ይበተናሉ” በሚለው እቀድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ ያነጣጠረ የማጠልሸትና ከሕዝብ የመለየት ስራ በድል መጠናቀቁን ህወሃት ገምግማ ወደ ቀጣዩ የትግል ስልት ለመዘዋወር መወሰኗን ጎልጉል ጋዜጣ አትሞ ነበር።

ጎልጉል ” ይህ በዕዝና ቁጥጥር የሚመራ ኃይል ዋና ትኩረት የሚያደርገው በለውጡ ዙሪያ ያሉትን አመራሮች ማጠልሸት፤ የሕዝብ ድጋፋቸውን ማምከን፤ ከተቻለም ሕዝብ እንዲነሳባቸው ማድረግ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በልዩ ልዩ ረቂቅ ስልት በሚበትኑት መረጃ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር እንዲጋጭ፤ ደም እንዲቃባ፤ ሰላም እንዲደፈርስ፤ ሕዝብ እንዲፈናቀል፤ ሕዝብ በመሪዎቹ ላይ እምነት እንዲያጣ በማድረግ “በአመራር ላይ ያለው ኃይል አገር ማስተዳደር አቅቶታል” በሚል በአገር ውስጥና በውጪ ተዓማኒነቱን ማሳጣት ነው። ሲል ነበር የዘገበው

 

 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *