መግቢያ፤

ለረዥም ዓመታት የአማራ ብሔርተኝነትን በማቀንቀን ኅብረተሰቡን በአንድ ለማስተባበር የሚጥሩ ወገኖች የመኖራቸውን ያክል ከወያኔዎች በበለጠ የገንዛ ወገናቸው ላይ በደል ያደረሱ አማሮች ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡ ቅድመ 2010 ዓ.ም የአማራውን ብሔርተኝነት ሲቃወሙ የነበሩ ሁሉ ለውጡን ተከትለው ‹‹ከእኛ በላይ አማራ ላሳር›› በሚል ከፊት ቀድመው ተሰልፈው አገኘናቸው፡፡ የብሔርተኝነቱ ዋናው ዓላማ ሕዝቡን በአንድ ማሰለፍ በመሆኑ በአስተሳሰብ ወይም በጥቅም ተማርከው የገቡትን ሁሉ ያለ ምንም ንስሃ ተቀበልናቸው፡፡

የአማራ ብሔርተኝነት ትልቅ ችግር የገጠመው እዚህ ላይ ነበር፡፡ ምርኮኞች ከዚህ በፊት የሠሩትን ስህተት እንዳይደግሙ ሕዝቡን በአደባባይ ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባ ነበር፤ ያ ባለመደረጉ ማን በትክክል የሕዝቡ ትግል ገብቶት ወይም የትኛው ደግሞ ለጥፋት የተጠጋ መሆኑ የሚታወቅበት መንገድ አልነበረም፡፡

በምርኮ የተቀላቀሉ አዲሶቹ ብሔርተኞች ‹‹አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ›› እንዲሉ የአማራነት ውኃ ልክ እኛ ነን በማለት በየመድረኩና በየማኅበራዊ ሚዲያው ሽለላቸው የሚቻል አልሆነም ነበር፡፡ የመፈናቀል፣ የግድያና የሕዝብ እሮሮዎች በዚህ ቡድን በእጅጉ የሚፈለጉ አማራነትን ለማስመስከርም ጥሩ አጋጣሚዎች ተደርገው ተወሰዱ፡፡ የአማራን ምድር ከአማራ ውጭ ማንም አይረግጣትም የሚለው ፉከራ ያደነቁር ነበር፡፡ ደሴ ላይ የፈላ ጀበና በሰዎች ላይ መወርወር፣ እስቴና ሞጣ ላይ መስጊድ ማቃጠል፣ ጎንጅ ቆለላ ለምርምር የሔዱ ምሁራንን ቀጥቅጦ መግደል ማውገዝ የማይቻልበት ደረጃ ደረሰ፡፡ ይህ የአማራ ሕዝብ ዕሴት ያልሆነ ከምክንያት ጋር የተፋታ ከሌሎች ጽንፈኛ ብሔርተኞች የተኮረጀ የማይጠቅም አካሔድ ነው በማለት የሚቃወሙ አማሮች በምርኮኞቹ የዐቢይ አህመድ ተላላኪ አሊያ በድፍረት እነርሱ በነበሩበት ድርጅት ተላላኪነት ይፈርጁ ጀመር፡፡ የፈላ ውኃ መድፋት፣ የማንፈልገውን ወደ አካባቢያችን እንዳይመጣ ማድረግ የተዋደቅንለት የሞትንለት ትግል ነው ብለው በአደባባይ ሲጽፉ ሀፍረት እንኳ አልነበራቸውም፡፡

ይህ ቡድን የፖለቲካ ልምድ አለው፤ ሚዲያውን በሚገባ ተቆጣጠረ፡፡ በወጣት ማኅበራት፣ በፋኖ፣ በአብን፣ በአዴፓ በሁሉም ቦታ ያልገባበት የለም፡፡ ሰዎችን በሀሰት መክሰስ፣ መወንጀል፣ መጮኽ ዋና መታወቂያው ሆነ፡፡ በሁሉም ተቋማት አደረጃጀቱን በመዘርጋቱ ምክንያት በተቃዋሚም በገዥውም ፓርቲዎች፣ በማኅበራትና በፋኖዎች ወዘተ የሚፈልጉትን ማውገዝ የሚወዱትን ማጀገን ምንም ሳይሰሩ የአማራ ሕዝብ ባለውለታ ወዘተ የሚሉ ጽንፍ አካሔዶች ባህል ሆኑ፡፡ ለስብሰባ ገንዘብ ያላዋጣ ባለሀብት ወይም ተቋም ፀረ አማራ ነው በሚል ይፈረጅ ጀመር፡፡ በዚህም ሕብረተሰቡ ከሕወሓት የበላይነት ወደ ምርኮኞች የበላይነት ተሸጋገረ፡፡ ፓርቲዎችም ይህን ግሪሳ በመፍራት የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ድፍረቱን አጡ፡፡ ደረቅ ወንጀል የፈፀሙ ሁሉ ሳይቀር ሕግ የመጠየቅ ድፍረት አጣ፡፡ ከተያዘ አማራ በመሆኑ ታሰረ የሚል ፋሽን ደራ፡፡

ቅድመ ሰኔ 15፣ 2011 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባና የኦሮሞ ልዩ ጥቅም

ዶ/ር አምባቸው መኮንን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሆኖ እንደተመረጠ የቀደመው አመራር ባስቀመጠው መሠረት የኦሮሞ አማራ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማሻሻል በሚል ወደ አምቦ ሒደው በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱለት ጥያቄዎች መልስ ሲሰጥ ‹‹በአዲስ አበባ የኦሮሞ ልዩ ጥቅም እንዲከበር አብረን እንታገላለን›› ብሎ መናገሩን ተከትሎ ከፍተኛ ትችት ደረሰበት፡፡ በሁለት ቀን ልዩነት ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል ከምንፈልግበት አንደኛው ምክንያት የልዩ ጥቅም ጉዳይ ነው፤ እስከሚሻሻለል ግን የአገሪቱን ሕግ አክብረን እንሠራለን የሚል ይዘት ያለው መግለጫ ወጣ፡፡

በመሠረቱ በአዲስ አበባ የኦሮሞ ልዩ ጥቅምን በተመለከተ መጀመሪያ የተናገረው ዶ/ር አምባቸው አልነበረም፡፡ በወቅቱ የአብን ምክትል ሊቀመንበር የኦሮሞ በአዲስ አበባ ያለውን ልዩ ጥቅም እንደሚያከብሩ ከኤልቲቪ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ገልጧል። ስለሆነም የተለየ መለኪያ ከሌለን በስተቀር አንደኛው በተለየ መልኩ ዐይንህን ላፈር የሚባልበት መንገድ አይኖርም፡፡

ከላይ የጠቀስናቸው ኃይሎች አምባቸውን ከሥልጣን ለማውረድ በሚል ሰላማዊ ሰልፍ በባሕር ዳር አዘጋጁ፤ የአንድን የክልል አመራር ከሥልጣን ማውረድ የሚፈጥረው ለውጥ እንደማይኖር የታወቀ ቢሆንም ያ ወቅት የአማራው ብሔርተኝነት አደገኛ ቅርቃር ውስጥ መግባቱን አመላካች ነበር፡፡ ያ ክስተት አዴፓን እንደ ድርጅት ከመታገል ይልቅ ከውስጡ ያሉ አንዳንድ አመራሮችን የአማራ የቁርጥ ቀን ልጅ ሌሎችን ደግሞ ጥፋተኛ በማድረግ ብሔርተኝነቱ የእውር ድምብስ እንደሚጓዝ ያሳየ ክስተት ነበር፡፡ ከባሕርዳር በተጨማሪ እንደ ደብረ ታቦር ያሉ ከተሞች የአምባቸውን ምስል ለመዘቅዘቅም ሲሞትም ነጠላ ዘቅዝቆ ለማልቀስም የቀደማቸው አልነበረም።

አምባቸውና አሳምነው፤

አምባቸውና አሳምነው ኢሕዲንን ከ1983 ዓ.ም. በፊት የተቀላቀሉ አመራሮች ነበሩ፡፡ አምባቸው በካቢኔነት አሳምነው ደግሞ በወታደርነት ሁለቱም ከኢሕአዴግ ጋር እሰከሞቱበት ዕለት ድረስ ነበሩ፡፡ በውስጥ ሆነው የታገሉትን ከማንም በላይ የሚያውቁት እነርሱው ሆነው ለአማራ ሕዝብ ያስባሉ ከሚባሉ ሰዎች መካከል ግን ሁለቱም ነበሩበት፡፡ አሳምነው ከግንቦት 7 ጋር በተያያዘ በመፈንቅለ መንግሥት ታስሮ ቆይቷል፤ አምባቸው እስር አልገጠመውም፡፡ ሁለቱም ለጠሚ ዐቢይ ደኅና የሚባል አመለካከት ነበራቸው፡፡ ጄ/ል አሳምነው በባህር ዳር ስታዲዮም ጠሚ ዐቢይን የኢትዮጰያ ሙሴ በማለት ማንቆለጳጰሱ የሚታወስ ነው፡፡

ሰኔ 15 ቀን፤

የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ሀዘንሽ ቅጣ አጣ ከቤትሽ አልወጣ እንዲሉ በጎራ ከፋፍለው ግፋ በለው ሲሉ የነበሩ ምርኮኞች በስብሰባ ላይ የነበሩ አመራሮችን አስጨረሷቸው፡፡ በዋናነት በአሳምነው መሪነት ግድያው ይፈፀም እንጅ አሳምነውን ገፋፍተው ወደ እሳት የጨመሩት፣ ወንድሞቹን ገድሎ እርሱንም ብቻውን ያስገደሉት ወንጀለኞች አንዳንዶቹ ተደብቀው ሌሎቹ ደግሞ በሥራቸው ሳይሸማቀቁ ይኖራሉ፤ ፍትሕ ተቀብሮ፡፡

ድኅረ ሰኔ 15 የተፈጠረው ሁለት ብሎክ

ከሰኔ 15 ቀን በኋላ በዋናነት በአማራው ብሔርተኛ ሁለት ብሎክ ተፈጠረ፡፡ አንደኛው መግደልን እንደ ጀግንነት የሚቆጥር ከሰው ልጅ በተለይም ከአማራው ባሕልና ዕምነት የሚፃረር ዕውነትን የቀበረ አመክንዮ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አስቀድሞ አምባቸው ይገደል ይወገር ሲል የነበረው ነጠላ ዘቅዝቆ የሚያለቅስ ሆነ፡፡

ከሁሉም የበለጠ ሕዝቡን ክፍፍል ውስጥ የጨመረው ደግሞ መግደል ጀግንነት መሆኑን አብን በይፋ መደገፉ ነበር፡፡ የድርጅቱ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አዲስ ጊዜ ከሚባል ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ እርስ በእርሳቸው መገዳደላቸውን ገልፆ ጄ/ል አሳምነው የምንጊዜም ጀግናችን ነው በማለት ተናገረ፡፡ ይህ ቃለ ምልልስ በድርጅቱ ቃለ አቀባይ በኩል በመሆኑ አብንም ባለመቃወሙ ግድያውን ደግፎ መግለጡ ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ሆኖ አልፏል፡፡ አብን የአሳምነውን ግድያ ደጋፊና በአሳምነው ሀሳብም የሚያምን ከሆነ እንደተቃዋሚ ፓርቲ ሆኖ የመመዝገቡ ምክንያት ጥያቄ ውስጥ የጣለም ክስተት ነበር፡፡ አሳምነው አዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበር፤ በአዴፓ እምነት አብን የሚመለከት ከሆነ በተቃዋሚ ስም ለምን ተመዘገበ የሚል ጥያቄ ለሚያነሳ መልስ አይኖርም፡፡ በተጨማሪም ግድያውን አምኖ ማድነቅ ከግድያው ጋር በግልጽ ተባብረናል የሚል ትርጉም መስጠት እንደሆነም መተርጎም ይቻላል፡፡

በዓለም ላይ በርካታ መሪዎች በሰዎች ተገድለዋል፤ በአፍሪካም በምዕራቡ ዓለምም የመሪዎች መገደል አዲስ ክስተት በአማራና በኢትዮጵያ ብቻ ላይ የወደቀ መርገምትም አይደለም፡፡ የደቡብ ሱዳን አማፂያን መሪና የሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ጆን ጋራንግ፣ የቡርኪናፋሶው ቶማስ ሳንካራ፣ የኮሞሮሱ አህመድ አብደላህ፣ የግብፁ አንዋር ሳዳት፣ የላይቤሪያው ሳሙኤል ዶይ…. በአፍሪካ ሕይወታቸውን ካጡ መሪዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ አብርሃም ሊንከን፣ ጆን ኤፍ ኬኔዲ፣ ጀምስ ጋርፊልድ፣ ዊሊያም ማክኒለይ በሰው ከተገደሉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች መካከል ይገኙበታል፡፡ ሆኖም እንደ ሰኔ 15ቱ ዕውነትና ግብረ ገብነት አብሮ አልተገደለም፡፡

በየካቲት 28፣ 1986 እ.ኤ.አ. ኦሎፍ ፓልሜ የሚባል የስዊድን ጠቅላይ ሚንስትር በስቶክሆልም ከተማ በሰው ተገድሎ ነበር፡፡ ስዊድኖች የመሪያቸውን ገዳይ ለዓመታት ጠይቀዋል፤ የኦሎፍ ፓልሜ ግድያ ፋይል በስዊድን ከ34 ዓመታት በኋላ በዚህ ዓመት ገዳዩ ታውቆ ነው ፖሊስ ፋይሉን የዘጋው፡፡ ምንም እንኳ ረዥም ጊዜ ቢወስድም ፍትኅ ግን ተቀብሮ እንደማይቀር የስዊድን ትምህርት ሊሆን ይችላል፡፡

በእኛ አገርም ብዙ መሪዎች ተገድለዋል። የሕወሓቱ ጄ/ል ሀየሎም አርአያ የተገደለው በሰው ነው፤ ትግሬዎቹ ግን ሁሉም ከተገዳይ ወገን ነው የቆሙት። ለእምነት፣ ለሞራልና ሕግ መቆማቸውን አሳይተዋል።

መውጫ፤

ከላይ ከጠቀስናቸው ምክንያቶች በተጨማሪ ሕዝቡን ለመክፈል አብን እንደ ፓርቲ ስህተት ፈፅሟል፡፡ ምንም እንኳ ወንጀለኞችን በመደበቅ ሒደት ሚናው የጎላ ቢሆንም አዴፓ እንደ ፓርቲ ሕዝቡን አንድ አድርጎ ለመሔድ አወንታዊ ሚና ተጫውቷል ማለት ይቻላል፡፡ ከግድያው ማግስት በቴሌቪዥን የቀረቡት የአዴፓ አመራሮች “ለሟቾች ነብስ ይማር፤ በአፋቸው አማራ እያሉ አማራን መጨፍጨፋቸው እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነው” በማለት ከሞራልና ሕግ ጋር ቆመዋል። ነገር ግን አብን በጊዜው በተፈጠረው መጥፎ ክስተት አዝኖ ጉዳዩን ለሕግ መተው ሲገባው አቋም መያዙ ትክክል አልነበረም፡፡

ስለሆነም መፍትሔው አብን ስሕተቱን አምኖ ሕዝቡን ይቅርታ ሲጠይቅ እንዲሁም አዴፓ ደግሞ ወንጀለኞችን በየአሉበት መንጥሮ ለሕግ ሲያቀርብ ብቻ ነው፡፡ የፍትኅ ዋናው ዓላማ ማስተማር ነው፡፡ በወንጀል የገቡ ሰዎች በሙሉ ፍርድ ቤት አጣርቶ ከወሰነባቸው በኋላ እንደየጥፋታቸው በይቅርታ እንዲወጡ ማድረግም የሚቻልበት መንገድ አለ፡፡ በዚህ ረገድ ጥፋተኞችም መስሎን ተሳስተናል በማለት ራሳቸውን ለፍትህ ቢያቀርቡ ትልቅ ውለታ ይሆናል፡፡

ከዚያ በዘለለ ግን ወንጀለኞቸ በመንደራቸው ለመደበቅ የሚያደርጉት ሩጫ ማንንም የሚጠቅም አይሆንም፡፡

By Muluken Tesfaw

 

 

 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *