የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፤ የመግለጫው ሙሉቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከቅኝ ግዛት በባሰ የጭቆና ቀንበር ውስጥ ያለ ሕዝብ የይስሙላህ ምርጫ አያስፈልገውም!

ከወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ፡፡

የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር (ትህነግ/ሕወሓት) ጫካ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ዘግናኝ ግፍ ሲፈፅም እንደኖረ በርካታ ማስረጃዎች አሉን። ይህ ከጫካ ጀምሮ በአማራ ሕዝብ ጥላቻ ጥርሱን ሰብሮ የመጣ የማፍያ ቡድን ወልቃይት ጠገዴ ውስጥ አምባገነኑን ደርግን በመታገል ሰበብ ከገባ በኋላ በርካታ የአካባቢውን ባለሀብቶች ‘አድሃሪ’ እና ‘ፋሽስት’ የሚል ስም እየለጠፈ በአደባባይ በመግደል፣ ከሕዝብ ዕይታ ሰውሮ በማሰቃየት … በሕዝብ ላይ በርካታ በደሎችንና ወንጀሎችን ፈፅሟል።
ወልቃይት ጠገዴ አማራን ከኤርትራ የሚያዋስን በመሆኑ ግንኙነቱን ለማቋረጥ እንዲሁም በሕልም ሲያስቧት የነበረችውን ትግራይን ከሱዳን ጋር ለማገናኘት በኃይል ይዞ፣ የአካባቢውን ያልተነካና እምቅ ሀብት ለመጠቀም ሲል የመጀመርያውን ርምጃውን ያደረገው የወልቃይት ጠገዴ አማራ ላይ በዓለም የተወገዘውን የዘር ማጥፋትና ሌሎች ኢሰብዓዊ ደርጊቶችን መፈፀምን ነው። በወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ላይ የጅምላ ግድያ፣ እስርና ማፈናቀል በመፈፀም አካባቢውን በዘመናዊ ቅኝ ግዛት ይዞ የዘለቀው ጨካኙ ትህነግ (ሕወሓት) የአማራ ማንነትን ለማጥፋት ያልሞከረው ስልት የለም።

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ በምንም ሕግ የማይገሰሰውን በሕይወት መኖርና የአካል ደኅንነት መብቱን አጥቷል። በአማርኛ ‘‘ምግብ አለ ወይ?’’ ብሎ የጠየቀ ወጣት በእብሪተኛው የትግራይ ልዩ ኃይል ተገድሏል። መንገድ ላይ የተገኘ ወጣት በትግራይ ልዩ ኃይል ተገድሎ አስከሬኑ ወደ ገደል ተጥሏል። አማርኛ ሙዚቃ በማዳመጣቸው፣ በአማርኛ ተሳፋሪዎችን የጠሩ የሾፌር ረዳቶች፣ ሙዚቃ ቤታቸው ውስጥ ተከፍቷል የተባሉ ነጋዴዎች፣ አማርኛ ተናገሩ የተባሉ ንጹሐን በጭካኔ እየተደበደቡ አካላቸው ጎድሏል። ርስታቸውን ተነጥቀው ተሳድደዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በቋንቋና ባህሉ የመማር፣ የሐሳብ ነፃነት መብቱን ከተገፈፈ በትንሹ ድፍን 30 ዓመታት አልፈዋል። ሕጻናት በቤተሰቦቻቸው ቋንቋ እንዳይማሩ ይደረጋል። የትም ዓለም የማይከለከለው አማርኛ፣ የአማራ ባህል እና የአማራ ክለቦች ማሊያ ወልቃይት ጠገዴ ውስጥ እንደ ሽብር ወንጀል የሚታይና ያለ ሕግ በተገኘበት የሚያስቀጣ ሆኗል። በማንነታቸው ምክንያት በርካታ ወጣቶች በእስር ላይ ይገኛሉ። በተለይ ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ በማነታቸው የታፈኑ ዜጎች አሁንም ድረስ የት እንዳሉ አልታወቁም።

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

ወልቃይት ጠገዴን የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር በግድ ክልል አንድ ጋር በመከለል ከቅኝ ግዛት ባልተናነሰ አንዳንዴም በባሰ ሁኔታ የሚገዛው አካባቢ ነው። በቅኝ ግዛት ዘመን ዜጎች የራሳቸውን ቋንቋ እንዳይናገሩ የተከለከሉበት ታሪክ እምብዛም ነው። የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር ከአፓርታይድም ከሌሎች ቅኝ ገዥዎችም በባሰና በተለየ መልኩ የአካባቢውን ሕዝብ በጅምላ ማንነቱን በመደፍጠጥና የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈፀም ከምድረ ገፅ የማጥፋት ሥራ እየሠራ ይገኛል። ወልቃይት ጠገዴ ላይ ሲያስገድል፣ የክልሉ ዋና ከተማ ከሆነው መቀሌና ሌሎች ከተሞች በአንፃራዊነት አማርኛ መናገርና ሙዚቃ ማዳመጥ እንደሚቻል ስናስብ ወልቃይት ጠገዴን የትግራይ ገዥዎች በልዩ ሁኔታ እየጨቆኑት ያለ መሆኑን ቀላል ማሳያ ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር በየቀኑ መግለጫ የሚያወጣበት አማርኛ ወልቃይት ጠገዴ ላይ የሚያስገድል፣ የሚያስደበድብና ከቀየ የሚያፈናቅል፣ አገዛዙ ለራሱ ፕሮፖጋንዳ የሚጠቀምበት ነገር ግን አማራዎች የራሳቸውን ቋንቋ እንዳይጠቀሙ የተከለከሉበት መሆኑ አካባቢው ምዕራባውያን ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት ካደረጉት ቅኝ ግዛትም በከፋ ሁኔታ እንደሚገኝ የሚያሳይ እውነት ነው።

የራሱ ማንነት ያለው የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ አሁን ባለበት ከቅኝ ግዛት የባሰ የግፍ ቀንበር ዲሞክራሲያዊም ይሁን አይሁን ምርጫ የሚባል ለማድረግ ቀርቶ በኅልውና የሚያስችሉና በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መሠረታዊ የሰው ልጅ መብት የተባሉትን በሕይወት የመኖርና የአካል ደኅንነት መብትም በኃይል ተገፍፎ ኖሯል። እጅግ በርካታ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው፣ ርስታቸው ከትግራይ ለመጡ እንዲከፋፈል ሆኗል። አሁንም ድረስ ዜጎች በማንነታቸው እየተፈናቀሉ፣ በርስታቸው ሠርተው የመኖር መብታቸውን በማንነታቸው ምክንያት ተነጥቀዋል።
ባለፉር ዓመታትም ትህነግ (ሕወሓት) ሕዝብን በዚህ አስከፊ አገዛዝ ስር ይዞ በሌላው የሀገራችን ክፍል በማስመሰል ‘‘ምርጫ አደረኩ’’ ሲል ኖሯል። ከቀደመው አባዜ ያልወጣውና የአማራ ሕዝብ የወልቃይት ጠገዴን ጥያቄ በማንገብ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በመሆን ገፍትሮ ያባረረው የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር አሁንም ወልቃይት ጠገዴ ላይ የሚያደርሰው በደልና ጭካኔ እልባት ሳያገኝ፣ ለትግል አንድ መነሻ የሆነው ወልቃይት ጠገዴ ከአገዛዝ ቀንበር ሳይላቀቅ በግድ የተከለለውን አካባቢ ጨምሮ ምርጫ እንደሚያደርግ እየተናገረ ይገኛል። ሆኖም በዚህ የከፋ አገዛዝ ስር የሚገኝ ሕዝብ በኮሮጆ ገዥዎችን የመቀየር መብት ቀርቶ መሠረታዊና ተፈጥሯዊ መብቶቹን እንደተነፈገ ነው።

Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

ይህ መሠረታዊና ተፈጥሯዊ መብቱን ተነፍጎ በከፋ አገዛዝና ጭካኔ ውስጥ ያለ ሕዝብ ደግሞ ትግል እንጅ በግል ሕይወቱ እንኳ ምንም ዓይነት ምርጫ የማድረግ መብት እንደሌለው ግልፅ ከሆነ ቆይቷል። በእርግጥም ለዚህ ከዋናው አፋኝና የጭካኔ አገዛዝ በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥቱን ጨምሮ የሌሎች ኃይሎች ቸልታም እንዳለበት የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ይገነዘባል።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብን የሚበድለው ትህነግ (ሕወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑ ግለሰብ የሕዝብን የማንነት ጉዳይ የሚወስን ተቋም መሪ ተደርገው ቆይተዋል። ከረፈደም ቢሆን እኝህ ግለሰብ ቢነሱም የፌዴራል መንግሥትና ሚዲያዎች የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብን ጉዳይ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ተባብረን ከማዕከላዊ መንግሥት በማሸሽ ሕዝብ እፎይታ እንዲያገኝ ቢደረግም ወልቃይት ጠገዴ ላይ ግን የቆየ የቅኝ ግዛት ተግባር እንዲቀጥል ዝም ተብሏል።

በመሆኑም የፌዴራል መንግሥትና ሌሎች አካላት ትግራይ ውስጥ ትህነግ (ሕወሓት) የሚፈፅመውን በመጠኑ ሲያጋልጡ ወልቃይት ጠገዴ ውስጥ ያለውን ከመጠን ያለፈ ግፍ ሲያወግዙና ሕግ ሲያስከብሩ አይታዩም። በመሆኑም በዚህ የከፋ አገዛዝ ስር ያለ ሕዝብ ምርጫ ማድረግ እንደማይችል ታውቆ በተለየ ሁኔታ ትኩረት እንዲሰጠው፣ የተገፈፈውን መሠረታዊ መብት እንዲከበርለት ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ሁሉ የበኩላቸውን እንዲወጡ ስንል እንጠይቃለን።
ሌሎች አካባቢዎች ላይ በዚህ አረመኔ አገዛዝ የሚፈፀሙ በደሎችን በማጋለጥ ሕዝብን ለማታገል ፍንጭ ያሳየው የፌዴራል መንግሥት ወልቃይት ጠገዴ ላይ ያለው ሁኔታ ትግል እንጅ ምርጫ ለማካሄድ የማያስችል መሆኑን በመገንዘብ ከወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጎን በመቆም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ጥሪያችን እናቀርባለን። በተመሳሳይ ስለአማራ ሕዝብ የቆሙ ድርጅቶች፣ ስለዜጎች መብት ግድ የሚላቸው አካላት በዚህ ወቅት ወልቃይት ጠገዴንም በኃይል ይዞ ምርጫ አደርጋለሁ የሚል እልህ ውስጥ የገባውን የትህነግ (ሕወሓት) የጭካኔ ሥርዓት በወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ላይ የሚያደርገውን የዘር ማጥፋት ዘመቻና አገዛዝ እንዲቃወሙ፣ ለዜጎች መብቶች ለሚቆሙ አካላት በማሳወቅ ሰብዓዊ ግዴያቸውን እንዲወጡ አበክረን እንጠይቃለን።

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማትና አካላት ርስቱን ተነጥቆ ለይምሰል ‘‘ምርጫ ያደርጋል’’ በሚል በትግራይ ገዥ ኃይል የሚደረገውን ጫና በተለየ ሁኔታ በሕግ እንዲያስቆሙ ጥሪያችን እናቀርባለን።

ይህ ሳይሆን ቢቀር በትህነግ (ሕወሓት) ተደጋጋሚ በደልና ትንኮሳ ያለ ሕዝብ ላይ የሚገባቸውን ኃላፊነት ሳይወጡ የቆዩ አካላት ከታሪክ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ ሊታወቅ ይገባል። ከምንም በላይ ትህነግ (ሕወሓት) በሕዝብ ላይ በሚፈፅመው ተደጋጋሚ በደልና ትንኮሳ ሕዝብ ከብሶት ወዳልሆነ የትግል አቅጣጫ ውስጥ እንዳይገባ ቀድሞ በደሉን ማስቆም ያለበት አካል ከቅኝ ግዛትም በባሰ ሁኔታ የሚገኘው ሕዝብ ላይ የይስሙላ ምርጫ አደርጋለሁ የሚለውን ጨቋኝ ኃይል እንዲያስቆም እንጠይቃለን።

ሰኔ 11/2012 ዓ/ም
ጎንደር

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *