የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ሰኔ 10፣ 12 ፣ 13 እና 14/2012 ዓ.ም መቀመጫቸዉን ግብፅ ያደረጉ የሳይበር ወንጀለኞች በኢትዮጵያ የኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፉን አስታውቋል።

የሳይበር ጥቃት ሙከራው የተቃጣው ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ፣ አኑቢስ ዶት ሃከር እና ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስ በተባሉ የሳይበር አጥቂዎች አማካይነት መሆኑን ኤጀንሲው ገልጿል።

ወንጀለኞቹ ለረጅም ጊዜ ሲዘጋጁ የቆዩ እና ኤጀንሲው ሲከታተላችው የነበሩ ሲሆን፥ በይበልጥ አርብ ሰኔ 12/2012 እና ቅዳሜ ሰኔ 13/2012 ከፍተኛ የሚባል የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ማድረጋቸውን ኤጀንሲው ገልጿል።

በዚህ ጊዜ ዉስጥ የ13 የመንግስት፣ 4 መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን የድረ-ገጽን የማስተጓጎል ሙከራ ማድረጋቸውን አስታውቋል።

የሳይበር ጥቃት ሙከራው በሀገሪቱ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የደህንነት መስሪያ ቤቶች እና የግል ድርጅቶች ድረ-ገጽ ላይ ያነጣጠረ ነበር።

ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ፣ አኑቢስ ዶት ሃከር እና ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስ የሳይበር ጥቃት አድራሽ ቡድኖች ሃላፊነቱን የወሰዱ ሲሆን፥ ዋና አላማቸዉም ከህዳሴው ግድብ ዙሪያ በተለይ በውሃ አሞላል ጋር በተያያዘ ሁሉን አቀፍ ተጽእኖ በሀገሪቱ ላይ ለመፍጠር በማሰብ እንደፈጸሙት ገልጸዋል።

የሳይበር ጥቃት የተሰነዘረባቸው ተቋማት አብዛኛዎቹ በድረ-ገጽ ግንባታ ሂደት ደህንነታችው ታሳቢ ያላደረጉ ተቋማት፤ በቀጣይነት የደህንነት ፍተሻ ያላደረጉ እና ከፍተኛ የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት የነበረባቸው መሆኑንም ኤጀንሲው አረጋግጧል።

ኤጀንሲው አስቀድሞ ቅድመ ዝግጅት በማድረጉ ምክንያት እና ይህን መጠነ ሰፊ የሳይበር ጥቃት መከላከል ባይችል ኖሮ ጥቃቱ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖሊቲካዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችል እንደነበርም ገልጿል።

በመከላከሉም ሊደርሱ የሚችሉ ከፍተኛ አደጋዎችን ማስወገድ መቻሉን እና ይህንንም ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ማሳወቁንም ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በቀጣይም መሰል ጥቃቶች በስፋት፣ በረቀቀ መንገድ እና ከተለያዩ ስፍራ ሊሰነዘር እንደሚችል ግምት ውስጥ በማስገባት ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት .et domain ከመጠቀማቸው በፊት የድረ-ገጻቸውን ደህንነት አረጋግጠው እንዲጠቀሙ፤ ራሳቸውን ከሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት ለመከላከል እና አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚኖርባቸው አሳስቧል።

ተቋማት ከኤጀንሲው ጋር በመተባበር ያለባቸውን የደህንነት ተጋላጭነት መድፈን እንዳለባችው እና የተለያዩ የሳይበር ደህንነት ጥቃት ሙከራ ሲያጋጥማቸውም ሆነ ሙያዊ ድጋፍ ሲያሻቸው ለኤጀንሲው በማሳወቅ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉ አስታወቋል።

ባለፉት ሁለት ቀናት ትብብር ላደረጉልን ተቋማት እና ግለሰቦች በተለይ ለኢትዮ ቴሌኮምና ለኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኤጀንሲው ምሰጋና አቅርቧል።

#FBC

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *